ንኮሳዛና ድላማኒ ዙማ | አፍሪቃ | DW | 17.07.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ንኮሳዛና ድላማኒ ዙማ

አዲሷ የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ደቡብ አፍሪቃዊቷ ኒኮሳዛና ድላማኒ ዙማ የአፍሪቃ ክፍለ ዓለምን ህብረት ለማጠናከር ቃል ገቡ ። ከአወዛጋቢ ድምፅ አሰጣጥ በኋላ በጠባብ ልዩነት ለዚህ ሃላፊነት የበቁት ድላማኒ ዙማ አፍሪቃውያንን

አዲሷ የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ደቡብ አፍሪቃዊቷ ኒኮሳዛና ድላማኒ ዙማ የአፍሪቃ ክፍለ ዓለምን ህብረት ለማጠናከር ቃል ገቡ ። ከአወዛጋቢ ድምፅ አሰጣጥ በኋላ በጠባብ ልዩነት ለዚህ ሃላፊነት የበቁት ድላማኒ ዙማ አፍሪቃውያንን ይበልጥ ለማግባባት በተያዘው ጎዳና ስራቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል ። ለህብረቱ ኮሚሽን ፕሬዝዳንትነት ያበቃቸው ድልም የግላቸው ሳይሆን በአጠቃላይ የአፍሪቃ ድል ተደርጎ መታየት እንደሚገባውም ተናግረዋል ። ደቡብ አፍሪቃዊቷ ኒኮሳዛና ድላማኒ ዙማ ለትላልቅ ተግዳሮቶችና ለአዲስ ሥር ጅምር እንግዳ አይደሉም ። በፀረ አፓርታይድ ዘመን የነፃነት ታጋይ ነበሩ ። ሁሉንም ዘር ባሳተፈ የመጀመሪያው ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሥልጣን በያዙት በኔልሰን ማንዴላ አስተዳደር ካቢኔ ውስጥ የመጀመሪያዋ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ነበሩ ። ማንዴላን በተኩት በታቦ ኤምቢኪ ካቢኔም በ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ለ 10 ዓመታት ያገለገሉ የመጀመሪያዋ ሴት ሚኒስትርም ናቸው አሁንም በአዲሱ ሃላፊነታቸው የመጀመሪያዋ ሴት የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር በመሆን ሥራቸውን በልበ ሙሉነት ነው የሚያያዙት ።

« በማንኛውም የስራ ደረጃ እንዳገለገልኩት ነው አሁንም የማገለግለው ። ሆኖም ግልፅ ነው በክፍለ ዓለማችን ሴቶች አሁንም ቢሆን ነፃ እንዳልሆኑ አልረሳም »

ለብዙ አፍሪቃውያት አርአያ የሆኑት የ63 ዓመቷ ድላማኒ ዙማ በተፎካካሪዎቻቸውም ዘንድ አልፎ አልፎ ንቅንቅ የማይል ፅኑ አቋም እንዳላቸው ዓላማቸውን ለማራመድ ወሳኝ እርምጃ በመወስድ ነው የሚታወቁት ። በተፈጥሮአቸውው ታጋይ ናቸው ። አስቀድሞም የፖለቲካ ዝንባሌ የነበራቸው ድላማኒ በለጋ እድሚያቸው የደቡብ አፍሪቃው ብሔራዊ ምክር ቤት አባል ሆኑ ። በሃያ ዎቹ አጋማሽ እድሜያቸው ላይም የትውልድ አካባቢያቸውን የክዋዙሉ ናታልን ክፍለ ግዛት ለቀው ወደ ብሪታኒያ ተሰደዱ ። በብሪታኒያም ህክምና እየተማሩ ከትምህርቱ ጎን ለጎን በፀረ አፓርታይድ እንቅሳቃሴ ይሳተፉ ነበር ። እጎአ በ1982 ከአሁኑ የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝዳንት ጄኮብ ዙማ ጋር ትዳር መስርተው 4 ልጆች አፍርተዋል ። ከ 16 ዓመታት በኋላ ፣ በ 1998 ከጄኮብ ዙማ ጋር ተለያዩ ። በማንዴላ ካቢኔ በጤና ሚኒስትርነት ጥሩ ስም ያተረፉት ድላማኒ ዙማ ከባለቤታቸው ጋር በተለያዩ በዓመቱ የመጀመሪያዋ ሴት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ ።

በዚሁ ሃላፊነታቸው በኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፕብሊክ የሰላም ድርድር በሸምጋይነት ባደረጉት አስተዋጽኦ ይወደሳሉ ። ይሁንና የዚምባብዌ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ተግባራዊ ባደረጉትና በሺህዎች የሚቆጠሩ ነጭ ገበሬዎችን በኃይል ባፈናቀለው የመሬት ይዞታ ማሻሻያ ላይ አንዳችም ወቀሳ ባለመሰንዘር ይተቻሉ ። እጎአ በ2009 ጄኮብ ዙማ የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝዳንት ሲሆኑ የቀድሞ ባለቤታቸው ድላማኒ ዙማ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኑ ። በአዲሱ ሃላፊነታቸውም ከከፍተኛ ሥልጣን ዝቅ እንደተደረጉ ነበር የፖለቲካ ታዛቢዎች አስተያየታቸውን የሰጡት ። ድላማኒ ዙማ ግን ሃላፊነቱን እንደወሰዱ የመስሪያ ቤቱን ያልጸዳ አሰራር ማስተካከል ላይ ነበር ያተኮሩት ። « ሙሰኛ ባለሥልጣናት ከክፍሉ መሰናበት አለባቸው ። በማንኛውም ደረጃ ቢሆን ሙሰኛ ባለሥልጣንን ቸል ልንል አይገባም ። ሁላችንም ታማኝ መሆን አለብን ፤ ሥራችንንም በታማኝነት ማከናወን ይገባናል ።»

Bundesaußenminister Frank-Walter Steinmeier (SPD) und seine südafrikanische Amtskollegin Nkosazana Dlamini-Zuma geben sich am Montag (09.03.2009) nach einem Kurzstatement im Auswärtigen Amt in Berlin die Hand. Zuvor führten sie ein Gespräch zu aktuellen internationalen und afrikapolitischen Themen, wie die Lage in Simbabwe. Foto: Arno Burgi dpa +++(c) dpa - Report+++

ድላማኒ ዙማ ከቀድሞው የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሽታይንማየር ጋር

ድላማኒ ዙማ ያሉትን በተግባር የሚተረጉሙ መሆናቸውን በተለያዩ ጊዜያት አስመስክረዋል ። የሃገር አስተዳደር ሚኒስቴር በታሪኩ የሂሳብ መርማሪዎች ጥፋት ያላገኙበት በርሳቸው የሥልጣን ዘመን ነው ። ለአዲሱ ሃላፊነታቸውም የፖለቲካ ተሞክሮአቸው ፣ የማያወላውል አቋማቸውን ፣ ዲፕሎማሲ ክህሎታቸው ጠቃሚ ነው ። እንደ አፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርነታቸው የተሰነጣጠረውን የአባል መንግሥታቱ አቋም አሰተባብረው ድርጅቱ አንድ አቋም እንዲይዝና በዛ ያሉት የክፍለ ዓለሙን አንገብጋቢ ችግሮች መፍትሄ ያገኙ ዘንድ የተላለፉ ውሳኔዎች ተገባራዊ እንዲሆኑ ማብቃት ይጠበቅባቸዋል ። ለእነዚህ ተግዳሮቶች መፍትሄ ለመሻት ወይዘሮ ድላማኒ ዙማ ብቃቱ እንዳላቸው ደቡብ አፍሪቃውያን ይተማመኑባቸዋል ።

ሂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 17.07.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15Z8p
 • ቀን 17.07.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15Z8p