ንቅሳትና መዘዙ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 01.03.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ንቅሳትና መዘዙ

«የጥርሷ ንቅሳት ያንገቷ ሙስና ረቡዕ ያስገድፋል እንኳን ሐሙስና!» ቆንጆ ወጣት ፤ በመነቀስ ፣ በውበት ላይ ውበት ጨምራ ፣ እጅግ ታማልላለች እንደማለት ነው ፣ የእነዚህ ሁለት ስንኞች ፍሬ ሐሳብ!፤ የአንገት ፤ የእጅ ንቅሳት ፣የጥርስ፤ ውቅራትና

የመሳሰለው ራስን ይበልጥ ለማስጌጥ፤  ለማስዋብ በአጋም እሾህም ሆነ መርፌ የሚጠቀሙበት  ሰው ሠራሽ ዘዴ፣ በዓለም ውስጥ በተለያዩ አገሮችና ነገዶች፣ የአያሌ ሺ ዓመታት ታሪክ ያለው ልማድ ሲሆን ፣ ባለንበት ዘመንም ይኸው ራስን ማስጌጫም ሆነ ገላ ላይ የተለያዩ ምልክቶች የሚቀረጹበት  አሠራር ፣ እንደየግለሰቡ ፍላጎት ፣ በተለይ በታላላቅ ከተሞች በዘመናዊ መሣሪያ  ማከናወን ይቻላል። ግን ዘመናዊውም  ሆነ ባህላዊው  መሣሪያ ፣ አያሳምም ፣ አይሰቀጥጥም ማለት አይደለም።  «ሲያጌጡ ይመለጡ!» የተባለው ምሳሌም አለምክንያት የተነገረ አይደለም።

82 ሚሊዮን ገደማ ኑዋሪዎች ባሏት ጀርመን 12 ሚሊዮን ያህሉ የተነቀሱ ናቸው። ከእግር ጥፍራቸው እስከ ራስ ቅላቸው በተለያዩ ቀለማት፤ ገላቸው በኅብረ ቀለማት ያሸበረቀም ሆነ የተለቀለቀ ወረቀት፤ የሚመስሉ ሰዎችን በተለይ ቀለል ያለ ልብስ በሚዘወተርበት ሞቃት ወራት ይበልጥ ማየት ይቻላል።

የቢራቢሮ፣ የሸረሪት፤ የጊንጥ፤ የኮከብና የመሳሰለውን  ምስል በክንዳቸው በደረታቸው ፤ በጀርባቸውና በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች የሚያስቀርጹም አሉ። የአንዳንዶቹ በታዋቂ ሰዓሊ ወይም ነቃሽ የተሠራ ነው የሚመስለው።  እ ጎ አ እስከ 2009 ዓ ም ድረስ ፣ ቀለም፣ እስከዚህም አይመረጥም ነበር። አደገኛው የመኪና ቀለም መቀቢያ ጭምር ሥራ ላይ ይውል ነበረና!  በስንቶች ላይ የጤንነት እክል እንዳጋጠመ በትክክል አይታወቅም።  አሁን ፤ አሁን ግን፣ ጉዳት አያስከትሉም የተባሉ  ቀለሞች ናቸው ለዚሁ ዓላማ እንዲውሉ የሚደረገው። ጉዳት አያስከትሉም የተባሉት፤ በእርግጥ እስከምን ድረስ ከጠንቀኝነት ነጻ ናቸው?! ተጣርቶ የታወቀ ጉዳይ የለም።ጀርመን ውስጥ፤ ሰዎች የሚነቀሱባቸው በአጠቃላይ 7,000 እስቱዲዮዎች መኖራቸው ይነገራል። በሙያው የሠለጠኑ ጥንቃቄም የሚያደርጉ ናቸው በሚባሉት  ነቃሾች እንኳ ምንጊዜም አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችል ተደርሶበታል። የአካል ቆዳ ሳንክ ያጋጥመዋል። ውደውስጥ ዘልቆ የሚገባው ቀለም ባዕድ ነገር ነው። በመርፌ መጨቅጨቁም ራሱ እንደሚያቆስልና  ጠባሳም ትቶ እንደሚያልፍ ፣ በቦን ከተማ የቆዳ ህክምና ባለሙያ MARINA SCHELER ይገልጻሉ።

ንቅሳት፣ እንደ እንሶስላ መሞቅ ፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድም  የቆየ ልማድ  መሆኑ ይታወቃል። በለጋ ወጣትነት ዕድሜ ጥርሳቸውን ማለትም ድዳቸውን ከተነቀሱት መካከል የሥራ ባልደረባዬ አዜብ ታደሰ   ተመክሮዋን እንዲህ ነበረ ያካፈለችን። 

ከተነቀስሽ በኋላ የድድ ወይም የጥርስ ህመም አላጋጠመሽም ማለት ነው?!

ጀርመናውያንስ ስለ ንቅሳት  ምን ይላሉ? በጎዳና መጠይቅ ከተደረገላቸው መካከል አንዳንዶቹ የሚሉትን እስቲ እናዳምጥ።----

« እርግጥ ንቅሣት፤ የተለያዩ ነገዶች መለያ ወይም መታወቂያ እንደነበረ አይታበልም ፤ በዚህ በኛ ግን ፤ አሁን የሚታወቀውና የምንፈልገውም፤ ራስን ለማስጌጥ ብቻ ነው። »

«የአካል ቆዳ ህይወት አለው። ያድጋል፤ እንዲሁም ይለወጣል። ከዚሁ ለውጥ ጋር ያለው ገጽም ይለወጣል። ንዑሱ ለውጥ፣ በአፋጣኝ ፣ አስቀያሚ ገጽ ይኖረዋል። »

«ተስማሚ ሆኖ ሲታይ ቆንጆ ነው፤ እንደነቃሹ ችሎታና ንቅሳቱን እንደሚያሳየው ተነቃሽ ማለት ነው። ታዲያ ኅብረተሰባችን፣ በተቻለ መጠን ላቅ ያለ መቻቻል ቢያሳይ መልካም ነው። »

«ፖለቲከኞች፤ ንቅሳታቸውን ቢያሳዩ ማለፊያ ነው። እርግጥ በአዶልፍ ሒትለር የሥልጣን ዘመን፣ ንቅሣት የተከለከለ ነበረ። ስለሆነም፤ ያ ክልከላ፤ ከአኛ ከጀርመናውያን አእምሮ አልጠፋም።  ወደ  እንግሊዝ አገር ብቅ ብንል፣ የፓርላማ አባላትየሆኑ ሰዎች፤ ተነቅሰው ማየት እንችላለን። አሜሪካ ደግሞ፣ በ«ኋይት ሐውስ» ቤተ-መንግሥት፣ የተነቀሱ ሰዎችን  ማየት አያዳግትም።»

የንቅሣት ጉዳይ በአውሮፓው ኅብረት አባላት ዘንድ ፣ ከጤንነት ጋር  በተያያዘ ተነስቶ ሳይመከርበት አልቀረም። የንቅሳት እስቱዲዮ ካላቸው መካከል አንዱ እንዲህ ነበረ ያሉት።

 «ሥራችን፤ በተንቀሳቃሽ ሥዕል መቆጣጠሪያ ኮምፒዩተር በኩል ይታያል፤ የምንጠቀምባቸውን መሣሪያዎች ንጽህና መቆጣጠር ይቻላል። ከጤና ጥበቃ በኩል ተቆጣጣሪ መጥቶ መመርመር ቢሻ ፣ በዚህ ረገድ አያስቸግረውም። ዕቃዎቹም ከማንኛውም በዓይን ከማይታዩ ተውሳክ አስተላላፊ አደገኛ ነፍሳት ነጻ እንዲሆኑ በሚያደርግ ዘዴም ነው የምንጠቀመው። »

«ይህን መሣሪያና ንጥር ለእንዲህ ዓይነት ተግባር ማዋልባለፉት ዐሥርተ-ዓመታት የታዬ፣ የዘለቀ ጉዳይ ነው። እንዴት እንደሚሠራበትም፤ የታወቀ ነው። ስለዚህ፤ ብርቱ ችግር ከፊት ቢደቀን ማንም ሊገርመው አይገባም። ይህ ዐቢይ ችግር ከዛሬ ነገ የሚወገድ አይደለም፤ የማይቻል ነውና!»

«በትክክል ፤ በዚህ ተግባር የተሠማራውን የንግድ ዘርፍ የሚጎዳ ሁኔታ ነው። እርግጥ ገሐዳዊውን  ይዞታ ተመልክቶ መሥራት ነው የሚሻለው። ማንኛውንም ተግባር በዚህ ረገድ ፤ አይሆንም ብሎ መከልከሉ የሚያዋጣ አይደለም ስለሆነም፣ አጠቃላዩን ችግር እንዴት ማስወገድ  እንደሚቻል መላ-መምታቱ ይበጃል።»

«አዎ፣ የንቅሳት ጉዳይ ሲነሳ ትንሽም ቢሆን ፍርሃት አድሮብኝ ነበር እንዳስብበትም አድርጎኛል።ነገር ግን፣ ያለኝ ትንሽ ጥቁር ንቅሳት ነው። በቀለማት ያሸበረቀ አይደለም ። እንደሚመስለኝ ፣ ችግር የሚያመጣ አይደለም። ወደፊትም ቢሆን፤ ለማስለቀቅ አላስብም፣ ፍርሃትን ወደ ጎን ገፋ አድርጌዋለሁ።»

የንቅሳት ዋናው ዓላማ ራስን ለማስጌጥ ካለ ፍላጎት የመነጨ ነው ከተባለ፤ ይህ ፍላጎት በተለያዩ አገሮች ህዝብ ልማድም እንደሚንጸባረቅ መገንዘብ እንችላለን። በዚህ በጀርመን ሀገር ብዙዎች ሴቶች፤ ወንዶችም ድዳቸውን  ሳይሆን በተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻቸው ይነቀሳሉ። የኮከብ፤ የመስቀል፤ የጽጌረዳ አበባ፤  የቢራቢሮ ፣ የሸረሪት፤ የጊንጥ ፣ የዘንዶ፤ የእባብ፣ የብዙ ነፍሳት ምስል በገላቸው ላይ ተስሎም ሆነ ተነቅሶ  ይታያል። ስለጀርመናውያቱ ንቅሳት አዜብ እንዲህ ትላለች።----

በአሁኑ ጊዜ በጀርመን  ሀገር፤ ንቅሳትን የማስወገዱ ተነሳሽነት 40 ከመቶ ከፍ ማለቱ እየተነገረ ነው። በመነቀሳቸው ይበልጥ የሚጸጸቱት በአመዛኙ ፣   በ 25 እና 50 የእድሜ እርከን ላይ የሚገኙት ሴቶች ናቸው። ዕድሜም ጨምሮ  ሳለ፣ ገላ ላይ ንቅሳት  መኖሩ የሚረብሻቸው ጥቂቶች አይደሉም። በመጥፎ  ንቅሳት ሳቢያ እየታመሙ፤ ማስወገድ የሚሹም ብዙዎች ናቸው። በጨረር የማስለቀቁ ዘዴ፤ ከሞላ ጎደል አንድ ወር የሚወስድና ሰፊ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑም የሚያስበረግጋቸው አሉ። በአማካዩ ለአንድ ጊዜ 200 ዩውሮ ስለሚከፈል ፤ በአጠቃላይ ዋጋው ከሺ ዩውሮ በላይ ሊያስገፈግፍ እንደሚችልም ነው የሚነገረው።  ይኸው አድካሚው ንቅሳት የማስለቀቁ ህክምና ፣ የማስለቀቂያ  መድኅኒቶችም ፤ ነቀርሳ ሊያስከትሉ ስለሚችሉ አደገኝነታቸው የሚያጠራጥር አይደለም። አንዳንድ የቀለም ዓይነቶች በቀላሉ አይወገዱም። ቢጫ እጅግ አስቸጋሪ ነው። ሰማያዊ ፣ አንዳንዴም አረንጓዴ ቀለምን ማስለቀቁ በጣም ከባድ ነው።

አንዳንድ ረቂቅ ወይን ጠጅ ዓይነት ቀለሞችን ፤ ቀን ልይቶ ማየቱ ያስቸግራል። ሲጨልም በዳንኪራ መርገጫ አዳራሾች ወይም  ክፍሎች ነው ደመቅ ባለ ሁኔታ ሲያንጸባርቁ ማየት የሚቻለው። ማሪና ሼለር እንደሚሉት፤ በጨረር ይህን ፈጽሞ ማስወገድ አዳጋች በመሆኑ፤ ቀዶ ጥገና ያሻል። ሁኔታው አስከፊ መልክ ከያዘ፤ ሌላ ቆዳ ቆርጦ መቀጠል ግድ ነው። ታዲያ ጠባሳ አይቀሬ ይሆናል።

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic