ኔፓል-መሬት መንቀጥቀጥ | ዓለም | DW | 27.04.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ኔፓል-መሬት መንቀጥቀጥ

ሳይንቲስቱን አያርካ እንጂ መሳሪያዉ አለ።ያለዉ ግን ላላቸዉ ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስና ጃፓን በብዛት፤ ሜክሲኮ በትንሹ ይጠቀሙበታል። ዩናይትድ ስቴትስ የምዕራባዊ የባሕር ዳርቻ ግዛቶቾዋ የሚከሰት የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋን የሚጠቁሙ መሳሪዎች ለመትከል ከ38 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ጠይቋታል።ለጥገና ፤በየዓመቱ 16 ሚሊዮን ዶላር ትከሰክሳለች።

አምገነናዊ አገዛዝ፤ የሐብታሞች የእብሪት እርምጃ፤ በሽታ፤ ጦርነት፤ ሰበብ ምክንያት ሆነዉ ብዙ ሺ ወገኖቹ በመሰቃየት፤ መንገላታት፤ መገደል መሞታቸዉ እንዳዘነ የኖረዉ ደኻ ዓለም፤በአረመኔዎች -በግፍ የተገደሉ፤ ባሕር ላይ ያለቁወገኖቹን ዘክሮ ሳያበቃ-ሌላ ሐዘን ታከለበት።ከኔፓል።ኔፓላዊዉ ጋዜጠኛዉ ወደ ራምኮት የሔደዉ ቅዳሜ እና ዕሁድን ከዘመዶቹ ጋር ለማሳለፍ ነበር።«አጎቴ ቤት ነበርን» አለ-ትናንት «መሬቱ ሲናጋ ከጠንካራዉ ወለል ሥር ተሰብስበን እንፀልይ ጀመር» ቀጠለ።«ሌለኛዉ ክፍል የነበረዉ አያቴ ግን ከለላ ከመፈለግ ይልቅ በመስኮት ዘሎ ወጣ»-የፀለዩቱም፤የሸሹትም እኩል ዳኑ።ሌሎች ግን ለመፀለይ-ለመሸሽ፤ ለርዳታም ጊዜ አላገኙም።ወይም ፀሎት፤ሽሽት፤ ጩኸታቸዉ ከንቱ ነበር።ሳይንስም ተፈጥሮም፤ ሼቫም፤ ቡዳሐም ጨከኑባቸዉ።አለቁ።ከ3 ሺሕ ሰባት መቶ በላይ።ለዓለም ሌላ መርዶ።

ሚያዚያ 6 2009 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ላ አኩዊላ የተባለችዉን የኢጣሊያ ከተማ እና አካባቢዋን የመታዉ የመሬት መንቀጥቀጥ ከሰወስት መቶ በላይ ሰዎችን ገድሎ ነበር።ፖለቲከኞች፤ የርዳታ ሠራተኞችና ሳይንቲስቶች የአደጋዉን መንስኤ፤የጥፋቱን ደረጃ፤ እና የርዳታዉን መጠን ሲያስተነትኑ-የከተማይቱ ፍርድ ቤት ዳኞች ግን ብዙ ጊዜ በማይደረገዉ፤ ብዙ በማይነኩ ወገኖች ላይ ነበር ያተኮሩት።ሳይቲስቶች ላይ።

ዳኞቹ ምርመራቸዉን በ2012 ሲያጠናቅቁ አደጋዉ እንደሚደርስ አስቀድመዉ ማስጠንቀቅ ነበረባቸዉ ያሏቸዉን ስድስት የከርሰ-ምድር እንቅስቃሴ አጥኚ ሳይንቲስቶችን፤ ሰዎችን በመግደል ወንጀል በየነቡቸዉ።ብይኑ ከብዙ ዉጣ ዉረድ በኋላ በ2014 ተሽሯል።መልዕክቱ ግን በ2004 የተከሰተዉ ሱናሚ ከሁለት መቶ 30 ሺሕ በላይ ሕዝብ መፍጀቱ ሥለ ሳይንስና ሳይቲስቶች ሐላፊነት የቀሰቀሰዉን ክርክር ያሟሟቀ ነበር።

ከሱማትራ እስከ ዲጎ ጋርሺያ፤ ከሺራልንካ እስከ ኬንያ ሁለት መቶ ሰላሳ ሺዎችን የፈጀዉ ሱናሚ፤ የኢጣሊያዉን ፍርድ ቤት አይነቱ ብይን-እና ትችት፤ የፎኪሺማዉ መቅሰፍት የተጠያቂነት ስሜት የፈጠረባቸዉ ወይም እልሕ ያጋባቸዉ የከርሰ ምድር እንቅስቃሴ አጥኚዎች፤ በየጊዜዉ አዳዲስ የሚሉትን ግኝት፤ መረጃና መላምት ይፋ ማድረጋቸዉን፤ እርስበርስ መነጋገር መወያየታቸዉንም አላቋረጡም።

የዓለም የመሬት መንቀጥቀጥና የከርስ ምድር አጥኚዎች በየጊዜዉ እንደሚያደርጉት ሁሉ ከሁለት ሳምንት በፊት ተሰብስበዉ ነበር።የሥብሰባዉ ሥፍራ ካታማንዱ-ኔፓል።የመነጋገሪያ ርዕስ፤ እና ጥናታዊ ፁሁፎች ይዘት፤- «የመሬት መንቀጥቀጥ፤ ሱናሚ፤ የባሕርና ከርሠ-ምድር እንቅስቃሴ---» እያለ ይቀጥላል።

ሳይንቲስቶቹ ለጉባኤቸዉ ኔፓልን የመረጡት፤ የሒማሊያዋ ተራራማ ሐገር በመሬት መንቀጥቀጥ በተደጋጋሚ ከሚመቱ እንደ ጃፓን፤ ሕንድ፤ ኢራን፤ ኢንዶኔዢያ፤ ሜክሲኮ፤ የዩናይትድ ስቴትስ ምዕራባዊ ዳርቻን ከመሳሰሉ አካባቢዎች አንዷበመሆኗ ነበር።በ1934 ኔፓልን እና የሕንድን የጠረፍ ግዛቶች የመታዉ የመሬት መንቀጥቀጥ በኔፓል ዘመናዊ ታሪክ ከፍተኛ ጥፋት ያደረሰ አደጋ ነበር።የቢሐር-ኔፓል መሬት መንቀጥቀጥ ተብሎ የሚጠራዉ አደጋ ከ10 ሺሕ 600 በላይ ሕዝብ ፈጅቷል።

በ1988 የደረሰዉ ተመሳሳይ አደጋ ደግሞ የቅርቡና ከፍተኛዉ አደጋ ነዉ።አንድ ሺሕ አራቶ መቶ ሰዉ ገድሏል።ሳይቲስቶቹ በብዙ ርዕሶቻቸዉ መሐል ኔፓልን የመቱትን በተለይ የሁለቱን የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች መንስኤ፤ የመጠንና የዘመን ልዩነታቸዉን፤አንስተዉ በሳይንሳዊ ቋንቋቸዉ ተነጋግሩ፤ እና -አጠቃለሉ-እንዲሕ ብለዉ፤-« የሚቀጥለዉ የመሬት መንቀጥቀጥ ነፓልን የሚመታዉ ምናልባት በሚቀጥሉት ጥቂት አስርታት ቢሆን ነዉ።»

ጋዜጠኛዉ ዘመዶቹን ጥየቃ ወደ ራምኮት የሔደዉ የሳይንቲስቶቹን መላምት ካታማንዱ ላይ በሰማ-በሳምንቱ ነበር-ባለፈዉ አርብ።ቅዳሜ ረፋድ።«ድንገት እንደ ሰደቻ ነዘረኝ።ከራሴዉ ሰዉነት የመጣ ነበር-የመሰለኝ።ብድግ ሥል ሙሉ በሙሉ ይንጠኝ ጀመር፤ ቤቱም ይርገፈገፋል።ወደ ዉጪ ወጣሁ ያዉ ነዉ-ሁሉም ይንቀጠቀጣል።»ይላል እሱ። የሚርገፈገፍ፤የሚንቀጠቀጥ፤ የሚርገበገበዉ ቤት፤ሕንፃ፤ ተራራ፤ መሬት በሴኮንዶች እድሜ በየሰዉ፤ እንሰሳ፤ ቁሳቁስ ላይ ተደረመሰ።ኔፓል-ምፀዓት።

የኔፓሉ ማስታወቂያ ሚንስትር ሚናንድራ ሪጃል-የአደጋዉን መጠን- ሲገልፁ ሥጋታቸዉን አልሸሸጉም ነበር።«ሁሉም እንደሚያዉቀዉ ዛሬ ሚያዚያ 25 በኔፓል ሠዓት አቆጣጠር አምስት ሰዓት ከ56 ደቂቃ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ደርሷል።ዋና ማዕከሉን ጎርኻ እና ላምጁንግ ካደረገዉ የመሬት መንቀጥቀጥ በኋላ ራስዋና ሲንዱሊ በተደጋጋሚ በድሕረ-መንቀጥቀጥ ተመተዋል።አሁን በደረሰኝ ዘገባ መሠረት 597 ሰዎች ሞተዋል።ቁጥሩ መጨመሩ አይቀርም።»

ሚንስትሩ የፈሩት አልቀረም።ቅዳሜ ቀትር ስድስት መቶ ያልሞላዉ የሟች ቁጥር እየጨመረ በሰወስተኛ ቀኑ ዛሬ ቀትር ላይ 3700 ደረሰ።የቆሰለዉ-ሰባት ሺሕ።የተረፈዉ፤ ፍርስራሽ፤ ጭቃና-ድንጋይ ከተከመረበት-ሜዳ ወይም ተራራ ፈሰሰ።ለሟች ተወዳጆቹ ማልቀስ-ማንባቱ፤ ለራሱ ርዳታ ፍለጋ መጮሕ መማጸኑን ዛሬም አላቋረጠም።ደኸይቱ ተራራማ ሐገር የመገናኛ አዉታሮችዋ ዉስን ናቸዉ።በቂ ሐኪም የላትም።ዝናቡም አላባራም።ነፋሱም ያፏጫል።ከሁሉም የከፋዉ የድሕረ-መሬት መንቀጥቀጡ ንዝረት ነዉ።በርካታ ሐገራት በቂ ባይባልም የርዳታ ሠራተኞችንና ቁሳቁሶችን ወደ ኔፓል አዝምተዋል።

ይሁንና የቆሰሉ፤ ፍርስራሽ የተጫናቸዉን፤ በየሥፍራዉ የተበተኑትን ሰዎች ለመርዳት የሚደረገዉ ጥረት በሐገሪቱ መልካዓ ምድራዊ አቀማመጥ፤ መንገድ፤ ሥልክ፤ የኤሌክትሪክ ሐይል በመሳሰሉ የመሠረተ-ልማት አዉታሮች፤ እጥረት፤ በተደጋጋሚዉ የድሕረ-ንዝረት ምክንያት እየተደናቀፈ ነዉ።

የኔፓል የሥራ ሚንስትር ባሕዱር ጉሩንግ እንደሚሉት ደግሞ እስከ ዛሬ ኔፓል የደረሰዉ የርዳት መሳሪያ፤ ቁሳቁስና ሠራተኛም በቂ አይደለም።«እንደ ቡልዶዞር እና ክሬን የመሳሰሉ ተጨማሪ መሳሪዎች ያስፈልገናል።በየሕንፃዉ ፍርስራሽና በተናዱ ተራሮች ሥር የሚገኙ ሰዎችን ማዳን አልቻልንም።በየቤቱ ፍርስራሽ ሥር ብዙ ሰዎች ና አስከሬኖች አሉ።»

ይሕን መሠሉ አደጋ ለኔፓል በርግጥ እንግዳ አይደለም።ከአሥራ-ሰወስተኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በየጊዜዉ በመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ትመታለች።የሒንዱ እና የቡድሐ አማኙ ሕዝብ በየጊዜዉ ዘመዶቹን የሚነጥቀዉ አደጋ የየአምላኮቹ ቁጣ እንደሆነ ከማሰብ መፀለይ ባለፍ ሌላ ለማድረግ እቅሙም እዉቀቱም የለዉም።

እንደ ኔፓል ሁሉ ከኢራን እስከ ሕንድ፤ ከፓኪስታን እስከ ሜክሲኮ፤ ከኢንዶኔዢያ እስከ ዩንይትድ ስቴትስ የሚገኙ ሐገራት በየዘመኑ የሚነሳዉን መቅሰፍት ማስተናገድ ግዳቸዉ ነዉ።

ባለፉት አስር ዓመታት ዉስጥ ብቻ ኢራን፤ኢንዶኔዢያ፤ ፓኪስታን በምትቆጣጠረዉ የካሽሚር ግዛት ቻይና እና ሐይቲ በደረሱ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ አልቋል።በየሥፍራዉ፤ አደጋዉ በደረሰ ቁጥር የሚነሳ አንድ ጥያቄ አለ።«ሰዉን ለማጥፊያ-ሰዉ አዉልባ በራሪ መሥራት የቻለ፤ ሰዉን ለመጨረስ-ኒኩሌር ቦምምብ ለማምረት የሚሽቀዳደመዉ ሰዉ፤ ሰዉን ለማዳን አደጋ ጠቋሚ መሳሪያ እንኳ መስራት እንዴት አቃተዉ?» የሚል-የየዋሆች ጥያቄ።

ዛሬም ተጠየቀ።«ምን እናድርግ» አሉ በዓለም የታወቀዉ የካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ የመሬት መንቀጥቀጥ ጥናት ተቋም ባልደረባ ፔጊይ ሔልዌግ፤ «ለብዙ አስርታት በርካታ ጥናትና ምርምር ብናደርግም፤ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋን የመተንበይ አቅማችን ከሌለ እኩል ነዉ።» አከሉ ሳይንቲስቱ።

ሳይንቲስቱን አያርካ እንጂ መሳሪያዉ በርግጥ አለ።ያለዉ ግን ላላቸዉ ብቻ ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስና ጃፓን በብዛት፤ ሜክሲኮ በትንሹ ይጠቀሙበታል። ዩናይትድ ስቴትስ በምዕራባዊ የባሕር ዳርቻ ግዛቶቾዋ የሚከሰት የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋን የሚጠቁሙ መሳሪዎች ለመትከል ከ38 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ጠይቋታል።ለጥገና ደግሞ በየዓመቱ 16 ሚሊዮን ዶላር ትከሰክሳለች።

እና ሳይንቲስት ሔልዌግ እንዳሉት የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋን አስቀድሞ በመጠቆም ሰዉን ከቅፅበታዊ እልቂት ለማዳን የሚችል እዉቀት፤ መሳሪና አቅም ላሁኑ «የለም ማለቱ» ለእዉነት ቀራቢ ነዉ።ደግሞ ሌላ እልቂት፤ መልስ የሌለዉ የየዋሆች ጥያቄም ይቀጥል ይሆናል።ብቻ መጥፎ እየሰማን ደጉን እንመኝ ነጋሽ መሐመድ ነኝ እስኪ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic