ኔቶ፣ የአውሮፓው ኅብረትና ሩሲያ | ዓለም | DW | 05.03.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ኔቶ፣ የአውሮፓው ኅብረትና ሩሲያ

የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት(ኔቶ) እና የአውሮፓው ሕብረት ፣ ሩሲያ በዩክሬይን ላይ ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ እርምጃ ወሰደች ሲሉ ነቀፉ። የሩሲያው ፕሬዚዳንት ብላዲሚር ፑቲን፣ በክሪሚያ ተጨማሪ ጦር አልተሰማራም፤ በዩክሬይን

በአሁኑ ጊዜ ወታደራዊ እርምጃ የመወሰድ ሐሳብም እቅድም የለም ሲሉ ትናንት ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠታቸው የሚታወስ ነው። ኔቶ ግን ፣ መግለጫው የሚታመን አይደለም ነው ያለው።

የኔቶ ዋና ጸሐፊ አንደርስ ፎግ ራስሙሰን፤ « ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ቢሰጥም፤ ሩሲያ የዩክሬይንን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በመጣስ፣ ዓለም አቀፍ ግዴታዋን ሳትወጣ ቀርታለች በማለት ለአምባሳደሮች ም/ቤት የምዕራቡን ነቀፌታ ብራሰልስ ውስጥ ትናንት ነበረ ያሰሙት። የአውሮፓው ሕብረት የውጭ ፖለቲካ ጉዳይ ኀላፊ ካትሪን ኤሽተንና የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ፤ ከሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላባሮቭና ከአዲሱ የዩክሬይን የሽግግር መንግሥት ተወካዮች ጋር ለመነጋገር በዝግጅት ላይ ናቸው። የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር

ትናንት እስዊትስዘርላንድ ውስጥ ፣ ከሩሲያው አቻቸውና ከወቅቱ የአውሮፓ የፀጥታና ትብብር ድርጅት ሊቀመንበር ፤ ከእስዊሱ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዲድዬ ቡርክሃልተር ጋር የተነጋገሩ ሲሆን፤ የጀርመኑ ው ጉ ሚ፤ የክሪሚያ ይዞታ መረጋጋት ስለማይታይበት ጊዜው ሳያልፍ በተቻለ ፍጥነት ሊመከርበት እንደሚገባ ጠቁመው፤ በውዝግቡ ሳቢያ ስለተደቀነው ሥጋት እንዲህ ብለዋል።

«ከፍተኛ ሥጋት የሚፈጥረው ስሜቱን መቆጣጠር የሚያቅተው ወገን የፖለቲካው ውዝግብ ሌላ ደም መፋሰስ እንዲከተል እንዳያደርግ ነው። ስለሆነም፤ ሁላችንም፤ እስከመጨረሻው ያለውን አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀም ሁኔታው ወደ ኃይል እርምጃ እንዳያመራ መግታት ይቻል ዘንድ መጣር ይበልጥ ተፈላጊ ነው።»

ኔቶ፣ ዩክሬይንን አስመልክቶ እንዲመክር በሩሲያም ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ እንዲወሰድ ያሳሰበች ፖላንድ ስትሆን፤ የቼክ ሪፓብሊክ የኔቶ አምባሳደር ዪሪ ሴዲሪም ከዩክሬይንም ሆነ ከሩሲያ ጋር የሚዋሰኑ ጎረቤት ሃገራትም ሥጋት ላይ ወድቀዋል ማለታቸው ተጠቅሷል። ይሁንና በኔቶም በአውሮፓው ሕብረት የፖላንድ ውትወታ ተቀባይነት አላገኘም። በክሪሚያ የተፈጠረው ውዝግብ በአውሮፓው የሰሜን አታላንቲክ ቀጣና የሚያስከትለው ተጽእኖ ይኖራል ፣ በመሆኑም ፣ የኔቶ ተጓዳኞች፤ በዚህ ብርቱ የውዝግብ ወቅት ሕብረታቸውን አጥብቀው ይገኛሉ ከማለት በስተቀር፣ የመከላከያው ጉድኝት ዋና ጸሐፊ ራስሙሰን፣ ተጨባጭነት አለው ስለሚባል እርምጃ ያስታወቁት ነገር የለም።

የአውሮፓ የውጭ ጉዳይ ም/ቤት የተሰኘው የምርምር ቡድን ባልደረባና የሩሲያ ጉዳይ ዐዋቂ የተባሉት እሽቴፋን ማይስተር በበኩላቸው፣ምዕራባውያን አሁን የቀራቸው አማራጭ የለም፤ ቭላዲሚር ፑቲን ማሰብ ማሰላሰሉን ትተው የበለጠ የከረረ እርምጃ እንዳይወስዱ መጠንቀቅ ያሻል፤ የሚመረጠው በማለት ምክራቸውን ለግሠዋል።

«እንደሚመስለኝ ፣ የአውሮፓው ሕብረት፣ እዚህ ላይ ጉዳዮችን ለመለወጥ በጣም ከባድ ነው። ከአውሮፓውያን አመለካከት ማድረግ የሚቻለው፣ ውዝግቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታይ ማብቃት ነው። ዩክሬይንን ችላ ሳይሉ፤ በተቻለ ፍጥነት፤ ወደ ክሪሚያ (ክራይሚያ)ዓለም አቀፍ ታዛቢዎችን በመላክ በዚያ ምን እንደተከናወነ ማወቅና ሩሲያ ልሣነ ምድሩን በኃይል እንዳትይዘው አስቸጋሪ ማድረግ ተፈላጊ ነው።»

የሩሲያ ው ጉ ሚ ሰርጌይ ላቭሮቭ፣ አገራቸው አቋሟን የማትለውጥ መሆኗን በመግለጽ፣ የአውሮፓው ሕብረትና ዩናይትድ ስቴትስ ማዕቀብ እንጥላለን ቢሉ ዋጋቸውን ያገኛሉ ብለዋል። ዛሬ ኔቶ ከሩሲያ ጋር ይነጋገራል፤ ነገ የአውሮፓው ሕብረት ርእሳነ- ብሔርና መራኅያነ-መንግሥት ውዝግቡ የሚበርድበትን እርምጃ ፣ ሩሲያ ያንቀሳቀሰችበት ሁኔታ ስለመኖር አለመኖሩ ይመክራሉ። ማዕቀብ ማድረግ ያስፈልጋል አያስፈልግም፣ ከውሳኔ ላይ እንደሚደርሱም ይጠበቃል። ዩናይትድ ስቴትስ፤ ከሩሲያ ጋር የነበራትን ወታደራዊ ትብብር አቁማለች። ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ፤ በሩሲያ ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ መውሰድ ተፋላጊ ነው ይላሉ። የአውሮፓው ኅብረት ኮሚሽን፤ ከሞላ ጎደል ግምጃ ቤቱ የተራቆተበትን አዲሱን የዩክሬይን የሽግግር መንግሥት፣ በገንዘብ ለመርዳት ዛሬ ከውሳኔ ላይ መድረሱ እንደማይቀር ነው የተገለጠው። በባራሴል ጉብኝት ያደረጉት የጀርመን የኤኮኖሚ ሚንስትር ዚግማር ገብርኤል---

«እኛ አሁን ዩክሬይን አስተማማኝ የኃይል ምንጭና የጋዝ አቅርቦት እንድታገኝና፤ ከሩሲያ በኩል የሚያስጨንቅ ሁኔታ እንዳያጋጥማት ማገዝ ይጠበቅብናል። ይህ ልንሸከመውና ልናበረክተው የሚገባ ጠቀሚ ድርሻ ነው። እኛ አውሮፓውያን መጨነቅ አይኖርብንም ትልቅ ጭንቀት ያለባት ዩክሬይን ናት። አውሮፓ በእርግጥ ዩክሬይንን የሚረዳ ከሆነ፣ ማድረግ የሚገባን፤ የኃይል ምንጭ አቅርቦት ችግሯን ማስወገድ ነው።»

ተክሌ የኋላ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች