«ኔብራ ስካይ ዲሽ» እና እሳተ ገሞራዎች፣ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 01.09.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

«ኔብራ ስካይ ዲሽ» እና እሳተ ገሞራዎች፣

«ሜራፒ» ከፈነዳ፤ በረጅሙ ታሪክ እጅግ በዛ ያሉ የአሳተ ገሞራ ፍንዳታዎች አጋጥመዋል፣ የነፋሱ አቅጣጫ ትክክል ነው፤ እናም፤ በኢንዶኔሺያም ሆነ እስያ ውስጥ በእሳተ ገሞራ አካባቢዎች፤ እዚህ መሃል አውሮፓ የታየው ዓይነት መዘዝ ነው የሚኖረው።»

«ኔብራ ስካይ ዲሽ» እና እሳተ ገሞራዎች፣

«ኔብራ ስካይ ዲሽ»

ባለፈው ሚያዝያ፤ በአይስላንድ የፈነዳው እሳተ-ገሞራ የአየር በረራን ባስጨነቀበት ወቅት ይህን ያሉት ለብዙ ዓመታት በኢንዶኔሺያ ደሴት በጃቫ፤ስለሜራፒ እሳተ-ገሞራ ሰፊ ምርምር ያደረጉት በፖትስዳም የሥነ-ምድር ምርምር ባልደረባ የሆኑት ማርቲን ትሲመርማን የተባሉት የዚሁ ዘርፍ ባለሙያ ናቸው።

ባለፈው እሁድ ኢንዶኔሺያ ውስጥ ሱማትራ በተሰኘችው ደሴት፤ 400 ዓመት አንቀላፍቶ የቆየ የእሳተ ገሞራ ተራራ፤ በመፈንዳት ከሚትጎለጎል ጢስ ጋር የጋለ ዓመድ በመበተን 30 ሺ የሚሆኑ የአካባቢው ኑዋሪዎች ወደ አስተማማኝ ቦታ እንዲሸሹ አስግድዶ እንደነበረ የሚታወስ ነው። አሁን አደጋው ጋብ በማለቱ ሰዎቹ ወደቀየአቸው በመመለስ ላይ ናቸው። በዓለም ውስጥ «የእሳት ሰቅ» በተሰኘው መስመር የምትገኘው ኢንዶኔሺያ 500 ያህል እሳተ-ገሞራ የሚፈነዳባቸው ተራሮችና ከረብታዎች ያሏት ስትሆን፤ 130 ገደማው ፍጹም ያልበረዱ፤ 69ኙ ደግሞ ይበልጥ አደገኞች መሆናቸው የተመሠከረላቸው ናቸው። ላይዋ የብሱ ፤ የቀዘቀዘ ፤ በረዶ በተሸፈኑት ክፍሎችም እጅግ የራዳ፤ ቢሆንም ፕላኔታችን ውስጥዋ ከውቅያኖስ ወለል በታችም ቢሆን እጅግ ሞቃትና እንደጋለች የምትገኝ ስለመሆንዋ በዓለም ዙሪያ የሚገኑት እሳተ-ገሞራዎች ምልክቶች ናቸው።

በተለይ፤ የሃዋዩ ሞና ሎዋ፤ ፊሊፒንስ ውስጥ በሉዞን ደሴት ፣ ከመዲናይቱ ከማኒላ 50 ኪሎሜትር ራቅ ብሎ የሚገኘው «ታል» የተሰኘው፣ የፓፑዋ ኒው ጊኒው «ዑላውን»፣

የኮንጎው «ኒራጎንጎ»፣ ሜራፒ(ከኢንዶኔሺያ)፣ የኮሎምቢያው «ጋሌራስ»፣ የጃፓኑ «ሳኩራጂማ»፣ የሜክሲኮው «ፖፖ ካቴ ፔትል»፤ የኢጣልያው ቬሱቪዬስ እና የዩናይትድ እስቴትሱ «የለውስቶን« ዋንኞቹ ምልክቶች ናቸው።

በሌላ በኩል ወደ አፍሪቃ ክፍለ ዓለም በሚጠጉት የእስፓኝ ግዛቶች በሆኑት የካናሪ ደሴቶች፤ በተለይም «ላ ፓልማ» በተሰኘችው ደሴት የሚገኘው የ «ሳን አንቶኒዮ» እሳተ-ገሞራ አንድ ቀን መፈንዳቱ እንደማይቀር ከ 9 ዓመት በፊት ሁለት ጠበብት ያካሄዱት ጥናት የሚጠቁም ሲሆን፤ እሳተ ገሞራው ከፈነዳ፤ በዓለም ውስጥ ከዚህ ቀደም ታይቶ ያልታወቀ እጅግ አደገኛ ማዕበል «ሱናሚ» 300 ሜትር ያህል ከፍታ ያለው ማዕበል በማስነሣት፤ የካናሪን ደሴቶች በ 15 ደቂቃ ውስጥ ያጠፋቸዋል። የምዕራብ አፍሪቃን ጠረፍ በ አንድ ሰዓት ውስጥ፤ የደቡብ አውሮፓን በ 3 ሰዓት፤ የዩናይትድ እስቴትስን ደግሞ በ 6 ሰዓት ውስጥ በማጥለቅለቅ እጅግ ብርቱ አደጋ ይሆናል የሚያስከትለው።

በዓለም ታሪክ ፤ እሳተ ገሞራ ያስከተለው ከባድ ጥፋት ሲወሳ፤ በተለይ ከ 3,600 ዓመት በፊት በሜድትራንያን ባህር ፣ ከቀርጤስ በስተሰሜን በምትገኘው ደሴት «ቴራ» ወይም «ሳንቶሪኒ» ላይ የፈነዳው እሳተ ገሞራ ለአትላንቲስ ውድመት መንስዔ ሳይሆን እንዳልቀረ ከሚወሳበት ሁኔታ ሌላ በመሃል አውሮፓ በዚሁ ፍንዳታ ሳቢያ የአየር ንብረት ለውጥም እንዲከሠት ማድረጉ ጭምር ነው የሚነገረው።

በምሥራቅ ጀርመን ፤ ዛኽሰን አንሃልት በተባለችው ፌደራል ክፍለ ሀገር ፤ ኔብራ በተሰኘችው ከተማ እ ጎ አ በ 1999 ዓ ም፣ የከዋክብትን አቀማመጥ የሚያሳይ ምስል በላዩ ላይ የተቀርጸበት፣ Nebra Sky Disk የሚሰኝ 32 ሴንቲሜትር ወርድ ያለው ከነሐስ የተሠራ እንቅብ መሰል መሣሪያ፤ ተቀብሮ መገኘቱ ይታወሳል። ይህ መሣሪያ ተግባሩ የተቋረጠው፤ከ 3,600 ዓመት በፊት ከቴራ የተትጎለጎለው የአሳተ ገሞራ ጢስ ፣ በመሃል አውሮፓ ሰማዩን ከ 20 -25 ዓመት ሸፍኖት በቆየበት ዘመን ነው የሚል መላ-ምት አለ። በዚያ ዘመን የአየሩ ሙቀት መጠን በአማካዩ፤ አንድ ወይም ሁለት ዲግሪ ሳይቀንስ እንዳልቀረ፤ በጋው ቀዝቃዛና ርጥበት ያልተለየው ፣ ሰብልን ያወደመ፤ ክረምቱም እጅግ ቀዝቃዛ እንደነበረ የተማራማሪዎች ጥናት ይጠቁማል።

ወርዱ 32 ሴንቲሜትር የሆነው ከነሐስ የተሠራው እንቅብ መሰል መሣሪያ፤ በላዩ ላይ የፀሐይ፤ ጨረቃና ከዋክብት ምስል የተቀረጸበት ሲሆን ፤ የተገኘው ሚትልበርግ በተሰኘው ከረብታ ከወርቅ ከተሠሩ 2 ጎራዴዎችና ከነሐስ ከተሠሩ አንባሮችና መጥረቢያዎች ጋር ነው። በሃለ-ቪተንበርግ፣ የአውሮፓ የኪነ ጥበብ ታሪክና ሥነ-ቅርስ ተቋም ፕሮፌሰር ፍራንሷ ቤርቴሜስ እንዳሉት እንዚህ ቅርሶች የተገኙት ለአንድ ጣዖት ተበርክተው ነው። በሃለ፤ የጥንታዊ ታሪክ ቤተመዘክር የተቀመጠው« ኔብራ እስካይ ዲስክ» ፣ እ ጎ አ ከ 2008 ዓ ም አንስቶ ለህዝብ እይታ ክፍት ሆኗል።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ