ናኖ ቴክኖሎጂ የኢትዮጵያ ቅርሶችን ይታደግ ይሆን?  | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 10.04.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ናኖ ቴክኖሎጂ የኢትዮጵያ ቅርሶችን ይታደግ ይሆን? 

በመንግስታዊው የኢትዮጵያ ባዩ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ያሉ ተመራማሪዎች ቅርሶችን ከውሃ ከጸሀይ ብርሃን መከላከል የሚያስችል ኬሚካል በቅርቡ ፈብርከዋል። ኬሚካሉን በድንጋይም ላይም ሆነ እንደ ወረቀት ባሉ ቁሶች ላይ በመቀባት ቅርሶቹን ከመበላሸት መጠበቅ እንደሚቻል ተመራማሪዎቹ ይገልጻሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:29

ናኖ ቴክኖሎጂ ላሊበላ እና የብራና ቅርሶችን ይታደግ ይሆን? 

ባለፈው መጋቢት ወር መጀመሪያ ኢትዮጵያን የጎበኙት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ለጋዜጠኞች መግለጫ የመስጠት ዕድል ሲያገኙ በቅድሚያ ያነሱት የኢትዮጵያን ጥንታዊ ስልጣኔ እና ታሪካዊ ሀገርነት ነው። የኢትዮጵያን ፊደል እና በቅኝ አለመገዛቷን በተጨማሪነት ያነሱት ፕሬዝዳንቱ “ከአፍሪካ ምርጥ እና ልዩ የሆነች ሀገር” ሲሉ አሞካሽተዋታል። ፕሬዝዳንቱ ይህን ምስክርነት የሰጡት ስለ ኢትዮጵያ የተነገራቸው ወይንም በዘገባ መልክ የቀረበላቸውን ይዘው ብቻ አይደለም። ይልቁንም ኢትዮጵያ በቅርስነት ከምትኮራባቸው መካከል አንዱ በሆኑት በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት በአካል ተገኝተው ተመልክተው ነው። 

“ላሊበላን እናዳየነው ከቦታው ውበት በላይ እነዚህ በጣም ድንቅ ውቅር ቤተክርስትያናት ልዩ የሆኑ ስራዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ምልክት ናቸው። ላሊበላ እስካሁን በጥንት ታሪክ ብቻ ሳይሆን ዛሬም የሚቀጥል፣ ነዋሪዎቹ ዕለታዊ መንፈሳዊ ኑሯቸውን የሚከታተሉበት ነው” ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል። 

የላሊበላ ነዋሪዎች “አማኝ እና በጣሙኑ መንፈሳዊ መሆናቸውን” የጠቀሱት ፕሬዝዳንት ማክሮን ይህ ግንዛቤም ሀገራቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የቀረበላትን የቅርስ ጥበቃ እና እንክብካቤ ትብብር እንድትቀበል እንዳደረጋት ተናግረዋል። ፈረንሳይ በተለይ በምርምር እና በአርኪዮሎጂ ዘርፍ 20 ዓመታትን ያስቆጠረ ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷን ያስታወሱት ፕሬዝዳንት ማክሮን አሁንም ለላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጥበቃ የሚውል የገንዘብ እና የቴክኒክ ትብብር እንደምትለግስ አስታውቀዋል። ይህ ትብብር ባለሙያዎችን መላክ ጭምር እንደሚያካትት በወቅቱ ይፋ አድርገዋል።

ይህን ስምምነት ከመፈጸሙ ወራት አስቀድሞ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የመፍረስ አደጋ ለተጋረጠበት ለላሊበላ ውቅር አብያተ ቤተክርስቲያን መፍትሔ ለማበጀት በቤተሙከራ ምርምር ተጠምደው ሰንብተዋል። ባለሙያዎቹ “የመጪው ጊዜ ሁነኛ የሳይንስ በረከት” የሚባልለትን የናኖ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ነው ምርምራቸውን ሲያካሄዱ የቆዩት። አቶ ከበደ ጋሞ በመንግስታዊው የኢትዮጵያ የባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የናኖ ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው። በናኖ ቴክኖሎጂ አንድ የምርምር ውጤት እንዴት እንደሚፈበረክ ለመረዳት በመጀመሪያ ስለ ናኖ ሳይንስ ማወቅ ያስፈልጋል ይላሉ። 

የኢትዮጵያ የባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተመራማሪዎች የናኖ ቴክኖሎጂ የምርምር ውጤት ውሃ እና ጸሀይ ወደ ቁሶች ውስጥ እንዳይሰርግ የሚከላከል ኬሚካል ነው። ኬሚካሉ በድንጋይም ሆነ በብረት፣ በወረቀትም ሆነ በጨርቅ ላይ ከተቀባ አንድን ቁስ በውሃ እና በጸሀይ ብርሃን ከመበላሸት እንደሚታደግ ተመራማሪዎቹ ይናገራሉ። የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን እንደ ምሳሌ ያነሱት አቶ ከበደ ኬሚካሉ እንዴት ቅርሱን ከጉዳት ሊከላከል እንደሚችል ያስረዳሉ።

 

“የተለያዩ በድንጋይ ላይ የሚበቅሉ ማይክሮ ኦርጋኒዝሞች እንደ አልጌ፣ ፈንገስ የመሳሰሉ ባህሪዎች ድንጋዩ ላይ እንደ ሻጋታ ይበቅላሉ። ያም ደግሞ ለላሊበላ ቤተክርስቲያን ወይም ለላሊበላ ቅርስ ራሱን የቻለ ጉዳት እያስከተለበት እንደሆነ ብዙ ጥናቶች  አመልክተዋል። ስለዚህ ምንድነው የምናደርገው የተለያዩ ናኖ ማቴሪያሎች የተለያዩ ባህሪያት ነው ያሏቸው። ያ ማለት ደግሞ አንዳንዱ ውሃ ጠል እንዲሆን ያደርገዋል። አንዳንዱ ደግሞ ጸረ- ባክቴሪያ ፣ ጸረ-ፈንገስ ባህሪ (anti bacterial, anti microbial activitiy) ያላቸው ናኖ ማቴሪያሎችን አብሮ አንድ ላይ እንዲሆኑ በማድረግ እና በመቀባት ነው ማለት ነው ያንን የምንከላከለው ማለት ነው። 

ስንቀባው አንደኛ ዝናብ እንዳይጎዳው ያደርገዋል። ያ ማለት ውሃ ጠል ባህሪ እንዳለው፣ ዝናብ እንዳያጎረጉደው፣ እንዳይሰረጉደው ያደርጋል ማለት ነው።  ሁለተኛ ደግሞ ባክቴሪያዎችም ሆነ ፈንገሶች እዚያ ላይ ተጣብቀው እንዳይጎዱት ቅርሱን ያ ጸረ ባክቴሪያ (anti bacterial) ባህሪ ስላለው ይገለዋል ማለት ነው። እዚያ ላይ እንዳይራባ ያደርጋል። በጸሀይ ደግሞ እንዳይጎዳ ሙሉ ለሙሉ የጸሀይ ብርሃኑ ሰርጎ እንዳይገባ እንዲያንጸባርቅ ያደርገዋል ማለት ነው” ሲሉ ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ።  

ኬሚካሉ በተለያዩ ቁሶች ላይ ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑን ተመራማሪዎቹ ይናገራሉ። በኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምርምሩን በዋነኛነት እያካሄደች ያለችው የ30 ዓመቷ ዊንታና ካሳሁን ናት። በኢንዱስትሪያል ኬሚስትሪ የመጀመሪያ ዲግሪዋን የያዘችው ዊንታና ለስድስት ዓመታት ያህል በቆዳ ኢንዱስትሪ ኢንስቲትዩት በተመራማሪነት ስትሰራ ቆይታለች። በኬሚካል ኢንጂነሪንግ ሁለተኛ ዲግሪዋን የሰራችው ተመራማሪዋ ካለፈው ሁለት ዓመት ወዲህ መስራት የጀመረችበትን የናኖ ቴክኖሎጂን ተጠቅማ ኬሚካሉን ለመፍብረክ ወደ ስድስት ወራት ያህል እንደወሰደባት ትናገራለች። የተፈበረከው ኬሚካል በቤተ-ሙከራ ውስጥ ተሞክሮ ያስገኘውን ውጤት ታብራራለች።   

በሙከራ ደረጃ ያለውን ይህን ኬሚካል ይበልጥ ለማሻሻል እና ውጤታማ የማድረግ ስራ እያከናወኑ እንደሚገኙ የምትገልጸው ወጣቷ ተመራማሪ ቀጣይ አላማቸው ይህንኑ አሳድጎ ለቅርሶች ጥበቃ እንዲውል ማብቃት መሆኑን ትናገራለች። ኬሚካሎቹን በቅርሶች ላይ በቀጥታ መጠቀም ከመጀመራቸው በፊት ግን በቤተ ሙከራ ደረጃ ተጨማሪ ሙከራዎች እንደሚያደርጉ ታስረዳለች። የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት የተሰሩት ባዛልት በተሰኘ የድንጋይ አይነት መሆኑን የምታብራራው ዊንታና በዚህ የድንጋይ አይነት ላይ ገና ሙከራ ማድረግ ይቀረናል ትላለች። 

የባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የናኖ ቴክኖሎጂ ዳይሬክተሩ አቶ ከበደም በመስሪያ ቤታቸው የተፈበረከው ኬሚካል እንደ ላሊበላ ያለ ቅርስ ላይ ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት በቤተ ሙከራ ተደጋጋሚ ሙከራዎች እንደሚደረጉ ይገልጻሉ። እነዊንታና በድንጋይ ላይ ሊያደርጉት ያሰቡት ሙከራ በሂደት ላይ ቢሆንም ኬሚካሉን በወረቀት ላይ ሞክረው ያዩት ውጤት በብራናዎች ላይ እንዲሞክሩ አደፋፍሯቸዋል። ኢትዮጵያውያኑ ተመራማሪዎች የፈበረኩት ኬሚካል ከተወሰኑ ሙከራዎች በኋላ ለብራና ጭምር ሊውል እንደሚችል ይናገራሉ። አቶ ከበደ ግን ኬሚካሉ በቀጥታ በብራና ቅርሶች ላይ ከመሞከሩ በፊት “መቅደም የሚገባቸው ነገሮች አሉ” ይላሉ።  

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic