ናሚቢያዊው ሽምቅ ተዋጊ ሔንድሪክ ዊትቦይ | አፍሪቃ | DW | 12.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ናሚቢያዊው ሽምቅ ተዋጊ ሔንድሪክ ዊትቦይ

አብዛናዎቹ የናሚቢያ ገንዘቦች የተዘረጋ ባርኔጣ ራሳቸው ላይ የደፉ የሔንድሪክ ዊትቦይ ፎቶግራፎች አሏቸው። ሔንድሪክ የጀርመን ቅኝ ገዢዎችን ለመፋለም የናማ ጦረኞችን በማደራጀት ይታወቃሉ። ሔንድሪክ በብዙዎች ዘንድ እናንሴባ ጋይብ ጋቤማብ በመባልም ይታወቃሉ፤ እባብ በሳሩ ውስጥ እንደማለ ነው።#ARAMH

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:57

ሔንድሪክ ዊትቦይ የጀርመን ቅኝ ገዢዎችን ተፋልመዋል

ናሚቢያ በአፍሪቃ ከቅኝ አገዛዝ ነጻ በመውጣት የመጨረሻዋ ሃገር ናት። ይኽች በአኅጉሪቱ ደቡባዊ ክፍል የምትገኝ አነስተኛ ሀገር እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1990 የናሚቢያ ሪፐብሊክ ተብላ ነጻ ሀገርነቷ ሲታወጅ በዐሥራ ዘጠነኛው እና ሃያኛው ክፍለ -ዘመን መጀመሪያ ከጀርመን ቅኝ አገዛዝ ሥርዓት ለመላቀቅ የተደረገው የዓመታት ትንቅንቅ ማሳረጊያ ኾኗል። በዚያ መራር ጸረ-ቅኝ -አገዛዝ ተጋድሎ ስማቸው በጉልኅ ከሚጠቀሱ ጀግኖች መካከል ሔንድሪክ ዊትቡይ አንዱ ናቸው።

የናሚቢያ የመገበያያ ገንዘብ የሀገሪቱን የታሪክ ክፍል ለማስታወስ ጥሩ መንደርደሪያ ይኾናል። አብዛናዎቹ የናሚቢያ ገንዘቦች የተዘረጋ ባርኔጣ ራሳቸው ላይ የደፉ የሔንድሪክ ዊትቦይ ፎቶግራፎች አሏቸው። ሔንድሪክ የጀርመን ቅኝ ገዢዎችን ለመፋለም የናማ ጦረኞችን በማደራጀት ይታወቃሉ። ሔንድሪክ  በብዙዎች ዘንድ እናንሴባ ጋይብ ጋቤማብ በመባልም ይታወቃሉ፤ እባብ በሳሩ ውስጥ እንደማለ ነው።  የናሚቢያ ገንዘቦች ላይ የታተሙ ፎቶግራፎች ታዲያ ድንገት ሠርገው እየገቡ ጥቃት በማድረስ ይሰወሩ የነበሩት የያኔው ሽምቅ ተዋጊ ሔንድሪክ ዊትቦይ እለት በእለት እንዲታወሱ የሚያደርጉ ናቸው። ወጣቷ የናማ ሴት ሞቭሊን ናታሻ ስለ ሸማቂው ጀግና እንዲህ ታስታውሳለች።    

"ልጅ ሳለሁ አያቴ ገንዘቧን እንዳመጣላት ያበደረቻቸው ጓደኞቿ ወይንም ሌሎች ሰዎች ጋር ትልከኝ ነበር።  እናም ሁል ጊዜ 'ሂጂና እናንሴቤን አምጪ' ትለን ነበር። እናም እኔ በመደነቅ 'አያቴ ምን?!' እላት ነበር።"

Deutsch-Südwestafrika Zeichnung Hererokrieg Hereroaufstand

የሔሬሮ ጦርነት፤ የሔሬሮ ተፋላሚዎች ከጀርመን ቅኝ ገዢ ጦር ጋር ሲዋጉ

ሔንድሪክ ዊትቦይ የተወለዱት በአንድ ወቅት በደቡብ ምዕራብ አፍሪቃ በአርብቶ አደርነት ይተዳደሩ ከነበሩት፤ እጅግ ከሚከበሩት የናማ ሰዎች ቤተሰብ ሲኾን ዘመኑም እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1830 ነበር። ናማዎች በኋላ ላይ ቋሚ መኖሪያቸውን ደቡብ ናሚቢያ ላይ አድርገዋል። እናም እዚያ ሔንድሪክ ዊትቦይ ከተጎራባቾቹ የሔሬሮ ሕዝቦች ጋር ባደረጉት ተደጋጋሚ ጦርነት ዝናን አትርፈዋል።  ኾኖም በ1890ዎቹ  የጀርመን ቅኝ ገዢዎች በናማ እና ሔሬሮ ግዛቶች ላይ ሲስፋፉ ሔንድሪክ በአፋጣኝ ነበር ስልታቸውን የቀየሩት። የሔሬሮ ጠላቶቻቸውም ከጀርመኖች ጋር በሚደረገው ፍልሚያ እንዲተባበሩ ጥሪ አስተላልፈዋል። የአካባቢው ነዋሪ ጡረተኛው ፖለቲከኛ እና ገበሬ አንቶን ቫን ቪተርሻይም ያብራራሉ።   

"ሔንድሪክ ዊትቦይ ሰዉ የጋራ ጠላቶቹን ለመፋለም በአንድነት እንዲቆም በተደጋጋሚ ይጥሩ ነበር። በጎጠኝነት አለያም በዘረኝነት ስር የጋራ ጠላት እንዳደፈጠ እኔም  እንደሚታየኝ መግለጥ አለብኝ። የጀርመን ቅኝ ገዢዎች ጎሣዎቹን ከፋፍለው በማናቆር የተጠመዱበት የከፋፍለህ ግዛ ስልት ሔንድሪክ በደንብ አጢነዋል። ጎጠኝት ሁሌም እንዲህ  ነው።"

ሔንድሪክ ዊትቦይ  ከጃኮብ ሞሬንጋ ጋር በመኾን ሕዝቡን እየመሩ ከጀርመኖች ጋር መራር ተጋድሎ ፈጽመዋል። በ1893 ጀርመኖች በሔንድሪክ ዊትቦይ መንደር ላይ ጥቃት አድርሰው በዐሥራዎቹ የሚቆጠሩ ሰዎችን ገደሉ። ይኽም ሔንድሪክ ዊትቦይ ስልታቸውን ዳግም እንዲቀይሩ አድርጓል። ከጀርመኖች ጋር ሥምምነት በመፈራረም የናማ አርበኞች ከሌሎች ጎሣዎች ጋር እንዲዋጉ መሣሪያ ያቀብሉ ነበር። ከዐሥር ዓመት ግድም በኃላ ግን ሔንድሪክ ዊትቦይ በቃቸው።  በ1904 አዛውንቱ አርበኛ ናማዎችን እየመሩ ጀርመኖች ላይ አመፁ። እናም ከዓመት በኋላ በጦር አውድማ ወደቁ። ጀርመኖችም በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ከተፈጸሙ የጅምላ ጭፍጨፋዎች ቀዳሚ በሚባለው በዚህ ግድያ የናማ እና ሔሬሮ ሰዎችን በአሰቃቂ መልኩ ጨረሱ።  

የሔሬሮ እና የናማ ዓመጽ ከሽፎ ሊኾን ይችላል። የሔንድሪክ ዊትቦይ በጋራ የመታገል ጥሪ ግን እንደ ታላቅ መሪ ስማቸው ምንጊዜም በመልካም እንዲነሳ ጽኑ መሠረት አስይዟል። እናም ይኽ ለዛሬዩቱ ናሚቢያ ጠቃሚ ትምህርት ነው ይላሉ የቀድሞው ፖለቲከኛ አንቶን ቮን ቪተርሻይም።  

Überlebende Herero nach der Flucht durch die Wüste

ከጀርመን ጭፍጨፋ የተረፉ የሔሬሮ ሰዎች በበረሃ ብዙ ከተጓዙ በኋላ

 

"ሔንድሪክ ዊትቦይ ትተውልን ስላለፉት ቅርስ ስንዘክር ሕዝቦችን ስለማዋሃዳቸው፤ የተለያዩ ጎሣዎች ከውጭ በሚመጣ ማናቸውም ጠላት ላይ አብረው እንዲነሱ በማስተባበር የነበራቸው ርእይንም ማሰብ ያለብን ይመስለኛል። ጎጠንነት እና ዘረኝነት ለእኛ ለናሚቢያውያን የወደፊት እጣ አደገኛ ጋሬጣዎች ናቸው።"

ከናሚቢያ የመገበያያ ገንዘቦች እና የጎዳና ስሞች ባሻገር ሔንድሪክ ዊትቦይ ትውስታቸውን በማስታወሻ ጽሑፋቸው ትተውልን አልፈዋል። ከዕለታዊ መዘክር ግለ-ታሪክ ሠነዳቸው በአንዱ ስለ ሐሳቦቻቸው፤ ስለተለዋወጧቸው ጦማሮች እና ስላገኟቸው ሰዎች ከትበዋል። ጽሑፎቹ ሔንድሪክ ዊትቦይ ስለ ቅኝ አገዛዝ አደጋ ይታያቸው የነበረውን በትንቢት መልክ ያመላክታሉ።  

ሔንድሪክ ዊትቦይ በናሚቢያ ጸረ-ቅኝ-አገዛዝ ተጋድሎ ያበረከቱት አስተዋጽዖ ዓለም-አቀፍ ዕውቅናን አጎናጽፏቸዋል።የተለዋወጧቸው ደብዳቤዎቻቸው እና ግለ-ታሪክ ጽሑፋቸው በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ድርጅት በምህጻሩ (UNESCO)  ተመዝግበዋል። ጽሑፎቹ «የዓለም ትውስታ» በሚለው የዓለም አቀፉ ተቋም ሠነድ ውስጥም በቅርስነት ተመዝግበው ይገኛሉ። 

 

ቪክቶሪያ አቬሪል/ ማንተጋፍቶት ስለሺ 

ኂሩት መለሰ

ቪክቶሪያ አቨሪል/ማንተጋፍቶት ስለሺ

 ይህ ዘገባ አፍሪቃዊ ሥረ መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ልዩ ዝግጅት አካል ነው።

 This report is part of African Roots, a project realized in cooperation with the Gerda Henkel foundation.

Audios and videos on the topic