ኒዠር እና የመለያው ምርጫ | አፍሪቃ | DW | 12.03.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ኒዠር እና የመለያው ምርጫ

የኒዠር ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ማወዛገቡን ቀጥሎዋል። የሀገሪቱ ተቃዋሚ ቡድኖች ህብረት ከመለያው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ለመራቅ ቢወስንም ፣ የተቃዋሚው እጩ በተወዳዳሪነት እንደሚቀርቡ ተሰምቶዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 07:01
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
07:01 ደቂቃ

ኒዠር

በኒዠር ባለፈው የካቲት 21፣ 2016 ዓም በተካሄደው የመጀመሪያ ዙር ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የሁለተኝነቱን ቦታ የያዙት የተቃዋሚው ቡድን እጩ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ሃማ አማዱ የፊታችን መጋቢት 20፣ 2016 ዓም ከሚካሄደው ሁለተኛው ዙር ፕሬዚደንታዊ ምርጫ እንደሚሳተፉ አስታውቋል፣ ምንም እንኳን የተለዪዩ የተቃዋሚ ቡድኖች በምሕፃሩ «ኮፓ» በሚል ያቋቋሙት ለስልጣን ለውጥ የቆመ ህብረታቸው ከምርጫው ለመራቅ ቢወስንም። ይኸው የህብረቱ ውሳኔ ብዙዎችን ማስገረሙን የስነ ማህበራዊ ጥናት ተመራማሪ ሳኒ ያህያ ዣንዡና ገልጸዋል።

« የኒዠር ተቃዋሚዎች ህብረት ሁለተኛው ዙር ምርጫ ሊደረግ ጥቂት ጊዜ በቀረው ባሁኑ ጊዜ ይህንን ርምጃ መውሰዱ አስገራሚ ነው። ምክንያቱም፣ ማንም ያልጠበቀው ነበርና። የተቃውሞው ወገን ፣ በመጀመሪያው ዙር ምርጫ 49% የመራጭ ድምፅ ባገኙት የሀገሪቱ ፕሬዚደንት አንፃር የሚወዳደረው እጩው ሊያሸንፍ እንደማይችል እና አቋሙንም እንዳዳከመው በሚገባ አውቆታል። በመሆኑም፣ በምርጫው ላለመሳተፍ ሌላ ምክንያት ማቅረብ ይኖርበታል።»

እርግጥ፣ የ«ኮፓ» በምርጫው ያለመሳተፍ ውሳኔ የምርጫ ዘመቻቸውን ከእስር ቤት ያካሄዱትን አማዱንም እንደሚጨምር ነበር የታሰበው። ግን፣ ጠበቃቸው አማዱ ከምርጫው አለመራቃቸውን አስታውቀዋል። የኒዠር አስመራጭ ኮሚሽን እንዳስታወቀው፣ በፕሬዚደንት ማሀማዱ ኢሱፉ አንፃር 14 የተቃዋሚ እጩዋች በተወዳደሩበት ምርጫ ካለፈው ህዳር ወዲህ በሕፃናት ሕገ ወጥ ንግድ፣ ብሎም፣ ከትውልድ መንደራቸው ጨቅላ ሕፃናትን ለናይጀሪያ ቱጃሮች አቅርበዋል በሚል ወንጀል ተከሰው በእስር የሚገኙት ሃማ አማዱ 18% የመራጩን ድምፅ በማግኘት ለመለያው ምርጫ ደርሰዋል። የተቃዋሚው ወገን ክሱን ፖለቲካዊ ምክንያት ያለው ሲል አጣጥሎታል።

Niger Niamey Präsidentschaftswahl Anhänger von Hama Amadou

የሃማ አማዱ ደጋፊዎች

የሶስተኛነቱን ቦታ ያገኙት የተቃዋሚው ወገን ፖለቲከኛ ሴይኒ ኡማሩ «ኮፓ» ከምርጫው ሂደት ለራቀበት እና ከስምንት ቀናት በኋላ ከሚደረገው የመለያ ምርጫም ለማይሳተፍበት ውሳኔው፣ የምርጫው ሂደት ትክክለኛ አልነበረም፣ የኒዠር ሕገ መንግሥታዊው ፍርድ ቤትም የመጀመሪያውን ዙር ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ውጤት ገና በይፋ አላወጣም፣ እንዲሁም፣ መንግሥት በእስር የሚገኙትን ሃማ አማዱን በሰብዓዊ መንገድ አልያዘም ያሉበትን ድርጊት እንደ ምክንያት ጠቅሰዋል።
እንደ አማዱ ጠበቃ ሜይትር ቡባካር ሞሲ አስተያየት፣ መንግሥት የምርጫውን ሂደት ለራሱ እንደሚመቸው አድርጎ መቀየሩ ግልጽ ነው።

«ሕገ መንግሥታዊው ፍርድ ቤት ከመሰብሰቡ እና የምርጫውን ውጤት ይፋ ከማድረጉ በፊት የካቢኔ ስብሰባ ያካሄዱት ፕሬዚደንት ኢሱፉ አስመራጩን ኮሚሽን በመጥራት በውጤቱ ላይ ተፅዕኖ ለማሰረፍ ያደረጉትን ሙከራ ተመልክተናል። ደደብ ያልሆነው የኒዠር ሕዝብም ሂደቱን ተከታትሎታል፣ ፕሬዚደንቱ አሁን ችግር ገጥሟቸዋል። እኛም ኢሱፉ በምርጫ ሳይሆን በስልጣናቸው እና በኃይል ተግባር በመጠቀም በስልጣን ለመቆየት እንደሚፈልጉ በሀገር አቀፍ ደረጃ እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እናጋልጣለን፣ በዚሁ ርምጃቸውም ላይ የርሳቸው ተባባሪዎች መሆን አንፈልግም።»

የምርጫው ሂደት ግልጽ እና ሁሉን ያሳተፈ መሆን እንደሚገባው ከማሳሰብ ወደኋላ ብሎ የማያውቀው የኒዠር ሲቭል ማህበረሰብ እና የኢሱፉ ተቃዋሚ ቡድን ተወካይ ሙዋሳ ቻንጋሪም ኒዠር ወደ ፖለቲካዊው ቀውስ እያመራች ናት ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

Niger Wahlzentrale Niamey

አስመራጩ ኮሚሽን

የኒዠር ሀገር አስተዳደር ሚንስትር ሀሱሚ ማሳውዱ እንዳስታወቁት፣ የመለያው ምርጫ ዕለት እንደፀና ይቆያል፣ በመጀመሪያው ዙር ምርጫም ፍፁሙን የድምፅ ብልጫ ለጥቂት ያጡት የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ኢሱፉም በመጋቢት 20 ው ምርጫ ላይ ይቀርባሉ።

የኒዠር በጎረቤቶችዋ ሊቢያ፣ በናይጀሪያ እና ማሊ የሚታየው አለመረጋጋት እና በዚያ የቀጠሉት ውዝግቦች አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል፣ በተመድ ዘገባ መሰረት፣ እጅግ ድሆች ከሚባሉት ሀገራት መካከል አንዷ ከሆነችው የዚችው የሳህል አካባቢ ሀገር ሕዝብ መካከል ሶስት አራተኛው በቀን ከሁለት ዩሮ ባነሰ ገቢ ነው የሚኖረው። የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን እጎአ በ1990 ዓም ባስተዋወቀችው ኒዠር የጦር ኃይሉ ተደጋጋሚ የመፈንቅለ መንግሥት ማካሄዱ የሚታወስ ሲሆን፣ የመጨረሻው መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደው የካቲት 18፣ 2010 ዓም ነበር፣ ይህን ተከትሎ በሀገሪቱ ዴሞክራሲ እና ሕገ መንግሥታዊው ስርዓት እንደገና እስኪተከል ድረስ ተቋቁሞ የነበረው የሽግግሩ መንግሥት ዘመን ያበቃው ፕሬዚደንት ማሀማዱ ኢሱፉ በ2011 ዓም ስልጣኑን በተረከቡበት ጊዜ ነበር።

ቴሬዛ ክሪኒንገር/አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic