ኑ ታሪካችንን እንይ «ዝክረ ዓድዋ » | ባህል | DW | 26.02.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

ኑ ታሪካችንን እንይ «ዝክረ ዓድዋ »

የጥበብ ስራዎቼ ማንነት ይሰኛል። በስዕሎቹ ላይ አፄ ምኒሊክ የተዋጉበት ጎራዴ ፤ ጠላት ይዞ የመጣዉ ዘመናዊ መሳርያ ሁሉ ይታያል። እኛ ኢትዮጵያዉያን ጋሻና ጦር ይዘን ነዉ ተዋግተን ነዉ ጠላትን እግሩ ላይ ያለን አፈር አራግፈን ያባረርነዉ። ሥራዎቻችን አባቶቻችን ሃገራችን እንዳትከፋፈል በጋሻና ጦር ጠላትን መክተዉ ማቆየታቸዉን አጉልቶ ያሳያል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:20

አባቶቻችን ጥለዉ ያለፉትን የታሪክ አሻራ እኛ ልጆቻቸዉ በሞያችን እናስተላፍ ብለን ነዉ።

 

« እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ፣ አገር አስፍቶ አኖረኝ። እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ። እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለኔ ሞት አላዝንም። ደግሞም እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም። እንግዲህም ያሳፍረኛል ብየ አልጠራጠርም።  አሁንም አገርን የሚያጠፋ፥ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል። እኔም ያገሬን ከብት ማለቅ የሰውንም መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር።

  አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም። ያገሬ ሰው! ካሁን ቀደም የበደልኩህ አይመስለኝም። አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም። ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለሚሽትህ፥ ለሃይማኖትህ፥ ለሀገርህ ስትል በሐዘን እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጠላኛለህ ፣ አልተውህም! ማርያምን! ለዚህ አማላጅ የለኝም!  ዘመቻዬም በጥቅምት ነውና እስከ ጥቅምት እኩሌታ የሸዋ ሰው ወረኢሉ ከተህ ላግኝህ።» ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ

ታላቁ የጥቁር ህዝብ ድል ዓድዋ የጀመረው ከጦርነቱ በፊት ህዝቡ የንጉሠ ነገስቱን ጥሪ ሰምቶ ከጫፍ ጫፍ የተመመ ዕለት ነው። መነሻው ላይም ድል አድራጊነት መንፈስ ነበር።  አድዋ ጉዞ 6 በገፃቸዉ ላይ ያስቀመጡት ጽሑፍ ነዉ።

የካቲት ታላላቅ ገድሎች የተፈጸሙበትና አንፀባራቂ ድሎች የተመዘገቡበት ወር ነዉ።የካቲት ወር ለኢትዮጵያዉያን፣ ለመላዉ አፍሪቃ ብሎም ለመላዉ ጥቁር ሕዝቦች ድል በደማቁ የታተመበት የዓድዋ ድል የተበሰረበት ወር ነዉ። በተለያዩ ሞያ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን  በሞያዎቻቸዉ የዓድዋን በተለያዩ ክንዉኖች በድምቀት ያከብራሉ፤ ያስባሉ። የዓድዋ ተጓዦች አድዋ ጉዞ ስድስት እያገባደዱ ነዉ። አዲስ አበባ የሚገኙ ወደ 14 የሚሆኑ ሰዓልያን በበኩላቸዉ «ዝክረ ዓድዋ» በሚል በተለይ ታሪክን አጉልተዉ የሚሳዩበትን የሥነ-ጥበብ ሥራዎች ለተመልካች ለእይታ ለማቅረብ ዝግጅታቸዉን አጠናቀዋል።

ከየካቲት 19 ጀምሮ በአዲስ አበባ ሙዚየም ለሕዝብ ለእይታ ስለሚቀርበዉ የጥበብ ሥራና ሰዓልያኑን አነጋግረናል ዝግጅት ይዘናል።  

“ዝክረ አድዋ” በሚል መጠርያ በአዲስ አበባ ሙዚየም ከየካቲት 19 ጀምሮ ለአስር ተከታታይ ቀናት 14 ሰዓሊያን ሥራቸውን ለእይታ የሚቀረቡበት ዓውደ ርዕይ፤ የአድዋን ጦርነትና ድል አጠቃላይ ታሪክ የሚያሳዩ ስራዎች ለእይታ የሚቀርቡበት እንደሆን ሰዓሊያኑ ተናግረዋል።  ከሰዓልያኑ መካከል ሰዓሊ ብርቱካን ደጀኔ እንዳለችዉ አባቶች አያቶቻችን ጥለዉልን የሄዱትን ታሪክ በሞያችን በብሩሻችን ለትዉልድ አስተላልፈን ለመሄድ ነዉ። 

«የኤግዚቢሽኑ ርዕስ « ዝክረ ዓድዋ » ብለነዋል። ይህ ዓዉደ ርዕይ ለአንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ለተከታታይ ዓመታት አባቶቻችን ጥለዉልን ያለፉትን ታሪክ እኛ ደግሞ ልጆቻቸዉ በሞያችን በቡሩሻችን አሻራ ጥለን ታሪኩን በቀጣይ እናስተላፍ ብለን ነዉ። የተባሰብንበት ምክንያት ለምን የራሳችን ጋለሪ አይኖረንም ብለን ይህን ጥያቄ ለመመለስ ስንል ነዉ። በዚህም የራሳችን የሆነ በቡድን ዓዉደርዕይ አናወጣም የሚል ነገር ነበር። መነሻችን ግን ሥራዎቻችንን ማሳያ የምናስቀምጥበት ቦታ ስለሌለን ጋለሪ ለማግኘት ነዉ። ሕጋዊ እዉቅናም አግኝተን እንቀሳቀስ የሚለዉን ጥያቄም ለመመለስ ነበር የተሰባሰብነዉ። መንግሥት ለምን ጥንታዊ ወይም ታሪካዊ ቤትን ሰጥቶን ስዕሎቻንንን እዝያ እያሳየን የቤቱንም በቅርስነት እየተንከባከብን ታሪክ አብረን ለምን አንተርክም የሚልም ሃሳብ ነበረን። መጭዉም የዓድዋ በዓል ስለሆነ ሁላችንም የጥበብ ሞያችን በእጃችን ነዉና ለምን የመጀመርያ የጋራ ዓዉደርዕያችንን ለምን በአድዋ ታሪክ ላይ አንሰራም በሚል ሃሳብ አመጣንና ተስማማን። በስምምነታችን ይህ ኤግዚቢሽንን በየዓመቱ ለመክፈትና በዓድዋ ታሪክ ላይ ሥራዎችን እየሰራን ታሪክን ለተተኪዉ ትዉልድ ማስተላለፍ አለብን ፤ ተተኪዉ ትዉልድም በእና እጅ ዉስጥ ነዉ ያለዉ መለወጥ የምንችለዉ ታሪክን የምንሰጠዉ እኛ ነን ስላሰብን ይህን ስራ ለመስራት በሙሉ ድምጽ ተስማማን።» 

በአብዛኛዉ ወጣቶችን ያካተተዉና ለጥበቡ ሞያቸዉን አሳልፈዉ የሰጡ ሰዓልያን የሚሳተፉበት ዓዉደ ርዕይ እንደሆነ የገለጸችልን ሰዓሊ ብርቱካን ደጀኔ በዓዉደርዕዩ ላይ የሚቀርቡት ስዕሎች የዓድዋን ድል በተለያየ ገፅታዉ የሚያሳዩ ናቸዉ ተናግራለች። 

  

«ሁሉም የየራሱ ፈጠራ ይኖረዋል ። ሰዓሊዉ በጥበቡ ማሳየት የሚፈልገዉ ምናልባት ከዓድዋ ጦርነት ቀደም ሲል ይሆናል አልያም በጠላት ወረራ ጊዜ በጦርነት ጊዜ ሊሆን ይችላል ። ካልሆነ ደግሞ ከድል በኃላ ሊሆን ይችላል።  እንደኔ ግን በጥበብ ስራዎቼ ማስቀመጥ የፈለኩት ማንነትን ነዉ የሥዕሎቼ ርዕስም ማንነት ይሰኛል። በስዕሉ ላይ የአፄ ምኒሊክ የተዋጉበት ጎራዴ አለ። ጠላት ይዞ የመጣዉ ዘመናዊ መሳርያም በስዕሎቼ ላይ ይታያሉ። እኛ ኢትዮጵያዉያንግን ጋሻና ጦርን ይዘን ነዉ ተዋግተን ያሸነፍናቸዉ። ይህ በስዕሌ ላይ ይታያል። የጥበብ ሥራዉ አባቶቻችን ሃገራችን የተከፋፈለች እንዳትሆን በጋሻና ጦር ጠላትን መክተዉ፤ የጥቁር ሰዉ ነጻነት ብለዉ ተዋግተዉ ማቆየታቸዉን አጉልቶ ያሳያል።  ከዚህ ሌላ በዉግያዉ ማለትም ኢትዮጵያዊዉ ጠላትን ሲመክት በዓድዋ ጦርነት አዉድማ ላይ በብሔር ተከፋፍሎ አማራ፤ ኦሮሞ ሳይል በሕብረት ሃገሪቱን ማቆየቱን ያሳያል። ስዕሉ ላይ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ጥንታዊ ቅርሶች ፤ የፋሲል የጎንደር ሃዉልቶች ደቡብ ዉስጥ የሚገኙት ተክል ድንጋዮች ይታያሉ። ይህ አንድነታችንን ያንፀባርቃል።  ጥበቡ የሚያሳየዉ በዓድዋ ጦርነት የሃገሪቱ ሕዝብ ሁሉ ማለትም ከሰሜን ከደቡብ ከምዕራብ ከምስራቅ ከመሃል ያለዉ ነዋሪ ሙስሊሙ ክርስትያኑ ሁሉ ደሙን አፍስሶ ፤ የዓድዋን ድል ለአንዲት ኢትዮጵያ መጎናፀፉን ያመለክታል።» 

የጋለሪ ችግችግር አለብን ብለሽ ነበር ፤ ይህን ስትይ ምናልባት ስዕልን የምትስሉበት ቦታ ነዉ ወይስ ለተመልካች የምታቀርቡበት ቦታ ነዉ?

«የቦታ ጉዳይ በሃገሪቱ ያለ ችግር ሊሆን ይችላል። የሚመለከታቸዉ ሰዎች የተመለከቱበት ጉዳይ ይወስነዋል። የመቀበል ያለመቀበል ጉዳይ ነዉ። ምክንያቱም በኢትዮጵያ የነበሩት ያለፉት መንግሥታት ሁሉ በሥነ-ጥበብ ጉዳይ ላይ ምንም ትኩረት አልሰጡም። ጥበብ ማለት ራሱ የሰዉን ልጅ አዕምሮ መለወጥ የሚችል ትልቅ አቅም ያለዉ ሞያ ነዉ። ያንን ጉዳይ አልተገነዘቡትም። አሁን ያለዉን ታሪክ ለቀሪዉ ትዉልድ ለማስተላለፍ ፤ ዋና መነሻችን ጥበብ ነች። ጥበብ አሁን ያለዉን ትዉልድ አሁን ያለዉን ታሪክ ለሚቀጥሉት አስር እና ሃያ ዓመታት መቶ አመታትም ሊሆን ይችላል፤ ቀርጾ የማቆየት አቅም አለዉ። ያንን ነገር አልተገነዘቡትም ነበር። እግዚአብሔር ይመስገን አሁን ወደ ሥልጣን የመጡት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዐቢይ አሕመድ ይህን ጉዳይ ትኩረት ሰጥተዉታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጥበብ ዉስጥ የነበሩም ሰዉ ናቸዉ። ለጥበብ ትልቅ ሞያ ትልቅ ፍቅር ያላቸዉ ናቸዉ። ሃገርን የመለወጥ አቅም አለዉ ብለዉ ያመኑ ሰዉ ናቸዉ። አሁን የተሻለ ሥራ እንሰራለን የተሻለ ሥራን እንደርሳለን ፤ አገራችንም ጋለሪ ማለትም የስዕል ማሳያ ቦታ ይኖራታል ብለን እናስባለን።»     

በግራፊክ አርት ተመርቆ ከ 15 ዓመት በላይ በሥነ- ጥበብ ስራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘዉ የአዲስ አበባዉ ነዋሪ አብዱቃድር መሃመድ ሌላዉ በዚሁ ስዕል ዓዉደር እይ ላይ ተሳታፊ ነዉ። እንደ አብዱቃድር በኢትዮጵያዉያን የሳዕልያን መድረክ በሕብረት የኢትዮጵያን ታሪክ አጉልቶ ለማዉጣት የተካሄደ የስዕል ዓዉደ ርዕይ እስከዛሬ አልተካሄደም። ይህ በአዲስ አበባ ሙዚየም የሚከፈተዉ « ዝክረ ዓድዋ »የስዕል እግዚቢሽን በአይነቱ ለመጀመርያ ጊዜ መሆኑ ይናገራል።

« በጥበብ ሥራዎቻችን አድዋን ለመዘከር የተነሳነዉ 14 ሰዓሊዎች ነን። በእርግጠኝነት ባልናገርም ስለ ዓድዋ ታሪክ በጥበብ ስራቸዉ ታሪክን ያሳዩ ሰዓሊዎች አሉ ብዬ አላስብም። ኢትዮጵያ ታሪክን በስዕሉ የሚያስቀምጥ ሰዓሊ የላትም ብዬ ነዉ የማስበዉ።  

በኢትዮጵያ የሚገኙ ሰዓሊዎች ሥራዎቻቸዉን ለእይታ ለማቅረብ ካለባቸዉ ችግር በተጨማሪ በተለይ የሥራ ቁሳቁስን ቀለምን ለማግኘት ያለባቸዉ  ችግር ከፍተኛ መሆን ሰዓሊ ብርቱካን ደጀኔ ሳትገልጽ አላላፈችም። በዓዉደ ርዕዩ ላይ የሚቀርቡት የኔ የጥበብ ሥራዎች የሚat,ኩሩት በተለይ በአድዋ ጦርነት ላይ የተዋጉ ወታደሮችን ታሪክ ስማቸዉን አጉልቶ ያላወጣቸዉ ግን በዓድዋ ድል ብዙ ድልን ያስመዘገቡ ኢትዮጵያዉያንን ይዘክራል።

  ሰዓሊ አብዱቃድር መሃመድ የኢትዮጵያ ሰዓሊዎች በጥበባቸዉ በተለይ በለኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ቢሰሩ የሚል ሃሳብም አቅርቦአል። ከዚህ ሌላ በኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ ሰዎች በተለይ ስዕልን ለመሳል የሚጠቀሙባቸዉን ቁሳቁሶች ለማግኘት ከፍተኛ ተግዳሮች እንዳለባቸዉ ተናግረዋል። ቃለ- ምልልስ የሰጡንን በ «DW» ሥም በማመስገን ሙሉ መሰናዶዉን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic