ኑኩርማ የጋና ብሔራዊ ጀግና | አፍሪቃ | DW | 26.02.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ኑኩርማ የጋና ብሔራዊ ጀግና

የተባበረች አፍሪቃ ተመሥርታ ማየት ያልሙ ነበር። ጋናን በኢንዱስትሪ የማስመንደግ ምኞትም ነበራቸዉ። ጋናዉያን የመጀመሪያዉን ፕሬዝደንታቸዉን ክዋሜ ኑኩርማን የዛሬ 50ዓመት ከስልጣናቸዉ በመፈንቅለ መንግሥት አወረዷቸዉ። እቅዳቸዉም ሳይሳካ ቀረ። ዛሬ መላዉ አፍሪቃ ያስታዉሳቸዋል። የሳቸዉን ራዕይ እና ሃሳቦችን በተመለከተ አስተያየቱ ግን የተለያየ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:17
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:17 ደቂቃ

ክዋሜ ኑኩርማ

«አደባባይ፤ አደባባይ፤ አደባባይ» በማለት አንድ ወጣት የሚኒባስ ወያላ በአክራ ጎዳናዎች ላይ ተጣራ። የተቻኮሉ የመሰሉ ሶስት ሰዎች ፈጠን ብለዉ ተሳፈሩ። ታክሲዉ በአዉቶቡሶች፣ ታክሲዎችን እና የቤት መኪናዎች ወደተጨናነቀዉ የዋና ከተማዋ ጎዳናዎች ዉስጥ ፈጥኖ ተቀየጠና ጉዞዉን ቀጠለ። «የክዋሜ ኑኩርማ አደባባይ» መሆኑ ነዉ። በአክራ ካሉ ዋና መንገዶች አንዱ የሆነዉ ይህ ስፍራ በሀገሪቱ የመጀመሪያ ጋናዊ ፕሬዝደንት ስም ነዉ የሚጠራዉ። ኑኩርማ ባለ ራዕይ፣ አምባ ገነን እንዲሁም ብሔራዊ ጀግና ናቸዉ ለጋናዎች። የዛሬ 50ዓመት ከስልጣን መንበራቸዉ ተገልብጠዉ እንዳልወረዱ ዛሬ ወገኖቻቸዉ በጎ በጓቸዉን ቢያወሩላቸዉ አይጠግቡም።

Ghana Kwame Nkrumah

በጎርጎሪዮሳዊዉ 1963 ለአፍሪቃ መሪዎች ንግግር ሲያደርጉ

«ኑኩርማ ከገነቡት ዛሬም እኛ ጥቅም እያገኘን ነዉ። የአኮሶምቦ ግድብ ዛሬም የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጭልናል።» ትላለች ወጣቷ ጋናዊት አሳቢያ አክኖር። ቀጠለች በቁጭት፤ «ኑኩርማ የረዥም ጊዜ እቅድ ነበራቸዉ። የአሁኑ ፖለቲከኞቻችን በእንደዚያ ዓይነት እቅድ ቢመሩ ኖሮ ሀገራችን ይበልጥ ባደገች ነበር።» ክዋሜ ኑኩርማ በጎርጎሪዮሳዊዉ 1909ዓ,ም መስከረም 21 ቀን የወርቅ አጥረኛ ከሆኑ አባት እና በግብርና ከሚኖሩ እናት ነዉ«የወርቅ ጠረፍ» በመባል በምትታወቀዉ በቀድሞዋ የእንግሊዝ የቅኝ ግዛት ጋና ወደዚህ ዓለም የመጡት። በካቶሊክ ሚሲዮን ትምህርት ቤት የተማሩት ኑኩርማ ቆየት ብለዉ ለረዥም ዓመታት በመምህርነት አገልግለዋል። የማወቅ ፍላጎት የነበረዉ የያኔዉ ወጣት ዩናይትድ ስቴትስ ሄዶ የመማር ምኞቱ ዉሎ አድሮ ተሳካ እና ለአስር ዓመታት ያህል አሜሪካ ዉስጥ እየተማረና እየሠራ ኖረ። በጎርጎሪዮሳዊዉ 1940ዎቹ አጋማሽ እንደገና ወደእንግሊዝ በመሻገር ህግ አጠና። እዚያ ነዉ የፓን አፍሪካኒዝምን ማለትም አፍሪቃን አንድ የማድረጉ ሃሳብ የተጠነሰሰዉ። ከዚያም ወደጋና በመመለስ የህዝብ አሰባሳቢ ፓርቲ የተሰኘዉን በማቋቋም፤ አድማ፤ እና አመፅን ይቀሰቅሱ ጀመር። መፈክራቸዉ «ነፃነት አሁኑኑ» የሚል ነበር። በጎርጎሪዮሳዊዉ 1950 ኑኩርማ በእንግሊዞች ታሠሩ። በቀጣዩ ዓመት በተካሄደ ምርጫ ፓርቲያቸዉ በከፍተኛ ድምፅ አሸነፈ እና ኑኩርማ ተፈቱ። ወዲያዉም የመንግሥት አስተዳደር ዉስጥ ገቡ። በ1952 በተመሳሳይ አቆጣጠር፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ። ያም ቢሆን ሥልጣኑ በብሪታኒያ መንግሥት ሥር ነበር። ከአምስት ዓመታት በኋላ ጋና ያለምንም ደም መፍሰስ ነፃነቷን ተጎናጸፈች። በጎርጎሪዮሳዊዉ 1960 የጋና ሪፑብሊክ ተብላ ኑኩርማ የመጀመሪያዉ ፕሬዝደንት ሆኑ።

Ghana Kwame Nkrumah

የጋናዉ የመጀመሪያ ፕሬዝደንት

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጋና የዓለም ከፍተኛ ካካዎ ላኪ ሀገር ናት። ግን እስካሁን ጥሬ ዕቃዎችን ለምርትነት የሚያበቃ ይህ ነዉ የሚባል ኢንዱስትሪ የላትም። ኑኩርማ በዘመናቸዉ በርካታ የመንግሥት ተቋማትን፣ የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ትምህርት ቤቶችንና የመሳሰሉትን ገንብተዋል። ሌሎች የአፍሪቃ ሃገራትም ከቅኝ ገዢዎቻቸዉ ነፃ የሚወጡበትን ትግል ደግፈዋል። በሄዱበት ሁሉ ኑኩርማ ማርክሳዊ ሶሻሊስት መሆናቸዉን በመግለፅ ያለመታከት የአፍሪቃ የጋራ ምክር ቤት እንዲመሠረት ይጥሩ ነበር።

«ከሌሎች መሰል የአፍሪቃ መሪዎች በተለየ ኑኩርማ የሃገራቱ ደህንነት ያሳስባቸዉ ነበር።» ይላሉ ጀርመናዊዉ የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪና በኑኩርማ ላይ ጥናት ያካሄዱት ክርስቲያን ኮህርስ። ደሀዎቹ ጋናዉያን ኑኩርማን እንደመሲህ የማምለክ ያህል ነዉ የሚመለከቷቸዉ፤ እንደዉም መዝሙር እና ጸሎትም ደርሰዉላቸዋል። የመወደዳቸዉን ያህል ታዲያ ብቸኛ፣ ተጠራጣሪ እና አስመራሪ ሰዉ ነበሩም ይሏቸዋል። ጋናዊዉ ፖለቲከኛ ህይወታቸዉ በሚከተሉት መርህ የታነፀ ነዉ፤ አይጠጡም አያጨሱምም። በትርፍ ጊዜያቸዉ ለመዝናናት ምን እንደሚያደርጉ ለጠየቃቸዉ ጋዜጠኛ «እሠራለሁ» ያሉ ቆፍጣና ነበሩ።

Ghana Gründungsvater Kwame Nkrumah

ኑኩርማ ከንግሥት ኤልሳቡጥ 2ኛ ጋር

ከሠርጋቸዉ ቀን በፊት ያላዩዋትን ግብፃዊት ወይዘሮ አግብተዉ ሶስት ልጆችም አፍርተዋል። አስገራሚዉ ባለቤታቸዉ አረብኛ እና ፈረንሳይኛ ዉጭ አይናገሩም፤ ኑኩርማ ደግሞ ሁለቱንም ቋንቋዎች አይችሉም። ያለ ቋንቋ ግን አብረዉ ኖረዋል። ኑኩርማ ሀገራቸዉን በጠንካራ ክንድ እንዳስተዳደሩ ይነገርላቸዋል። ጋና ነፃ በወጣች ማግስት ካለፍርድ ሂደት አንድ ሰዉ አምስት ዓመት እንዲታሠር ህግ ደንግገዋል፤ መንግሥትን ለመተቸት የሞከረም ይቀጣል። መገናኛ ብዙሃኑን ሁሉ ይቆጣጠሩ ነበር፤ ፓርቲያቸዉም በእያንዳንዱ ድርጅት ላይ የበላይነት ነበረዉ። የሀገሪቱንም አስተዳደር በአንድ ፓርቲ መሪነት እንዲፀና አድርገዋል። ከስልጣን የተገለበጡበት 50ኛ ዓመት አሁን ሲታሰብ ግን መላ ጋና ስለኑኩርማ ትናገራለች። በስማቸዉ ቤተመዘክር ተገንብቷል፣ በርካታ ጎዳናዎች በስማቸዉ ተጠርተዋል፤ ሳንቲሞች እና ቴምብሮችም ፎቷቸዉን ይዘዉ ወጥተዋል። የአፍሪቃ ኅብረት መቀመጫ በሆነችዉ አዲስ አበባም በኅብረቱ ደጃፍ ሀዉልታቸዉ ለታሪክ ተቀምጧል።

ሂልከ ፊሸር/ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic