ነፍስ አድን በጀርመን ባሕር ኃይል | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 27.04.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ነፍስ አድን በጀርመን ባሕር ኃይል

ስደተኞች በሜዲትራኒያን ባሕር ወደ አውሮጳ ለመሻገር ተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርጉ ይስተዋላል። ስደተኞቹን ከባሕር መስጠም ለመታደግ እና ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ከባሕር ክልሉ ለማባረር የጀርመን ባሕር ኃይል አባላት ከባድ ፈተና ነው የሚገጥማቸው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:16

ነፍስ አድን በጀርመን ባሕር ኃይል

ደመና አልባ፥ ጥርት ያለ ሰማይ። ፀሐይቱ ፍንትው ብላለች። በፍራንክፉርት ከተማ ስም ፍራንክፉርት አም ማይን (Frankfurt am Main) ተብላ የተሰየመችው የጀርመን ባሕር ኃይል መርከብ ማዕበሉን በቀላሉ ትቀዝፋለች። ለስደተኞች የሚሆን አየር ግን አይደለም። ከእንጨት ለተበጁ መናኛ ጀልባዎች ማዕበሉ ኃያል ነው። የጀርመን ባሕር ኃይል ንብረት የሆነችው ግዙፊቱ መርከብ ከሊቢያ ጠረፍ እምብዛም ከማትርቀው ከሲሲሊዋ ካግሊያሪ ወደብ ከተንቀሳቀሰች አንድ ቀን ኾኗታል። መርከቢቱ «ሶፊያ» የሚል ስያሜ በተሰጠው የአውሮጳ ኅብረት ተልዕኮ ስር ነው የምትንቀሳቀሰው።

«ሶፊያ» ይፋዊ ተልዕኮው ነፍስ አድን አይደለም። «የተልዕኮዋችን ዋነኛ ግብ ሕገ-ወጥ ስደተኞችን ከሰሜን አፍሪቃ ወደ አውሮጳ እንዳይፈልሱ መከላከል ነው» ይላሉ የመርከቢቱ ኃላፊ አንድሪያስ ሽሜክል። ኾኖም ቁጥሮች የሚያመለክቱት ሌላ ነው። በ«ሶፊያ» ተልዕኮ እስካሁን 13.000 ሰዎች ነፍስ አድን ርዳታ ተደርጎላቸዋል። ይኽ የኾነው 68 በመቶ ያህሉ ሕገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች በቁጥጥር ስር ውለውም ነው። እንደ መገናኛ ዘገባዎች ከሆነ፦ አደገኛው የባሕር ነውጥ ረገብ ብሎ ወደ አውሮጳ ለመፍለስ ትክክለኛ የሚሉትን ጊዜ የሚጠብቁ በርካታ ስደተኞች ሊቢያ ውስጥ ይገኛሉ።

ላምፔዱዛ አቅራቢያ ከ700 በላይ ስደተኞች ከሰጠሙ አንድ ዓመቱ ነው። ከጥቂት ቀናት በፊት በአደገኛው የባሕር ጉዞ ከ500 በላይ ስደተኞች ሳይሰጥሙ እንዳልቀሩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጧል። መሰል አደጋ ለመርከቢቱ ሠራተኞች አስጨናናቂ መኾኑን የ22 ዓመቱ ወጣት የመርከቢቱ ቴክኒሺያን ያንስ ይናገራል።

«ሲበዛ ያልተለመደ አይነት ግዳጅ ነው። ምክንያቱም ድንገት ሲመጡ ባልተጠበቀ መልኩ ብዙ ሆነው ነው። ባለፈው ከ700 በላይ ሰዎች ተጭነው የመጡበት ክስተት ከሁሉም የባሰው ነው። ሁኔታውን ለማያውቀው ውጥረት ውስጥ ነው የሚከተው። በበርካታ መቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አደጋ ሲጋረጥባቸው እዚህ ሁሉም ነው ጭንቀት የሚለቅበት። እያንዳንዱ ነገር በተገቢው መንገድ መሥራት መቻል አለበት። በስልጠና ወቅት ምን ማድረግ እንዳለብህ ያገኘኸው ነገር ይኖራል። እዚህ ግን ነገሩ የምር ነው። ያ ደግሞ ምን ጊዜም የበለጠ ያጨናንቃል»የ31 ዓመቷ ሌላኛዋ የጀርመን ባሕር ኃይል ሠራተኛ መርከቢቱ ላይ ተግባሯ ነፍስ አድን አገልግሎት መስጠት ነው። የጀልባ ስባሪዎችን ለማሠሥ ከባልደረቦቿ ጋር ላለፉት 36 ሠአታት ተሠማርተዋል።

«እዚህ እጅግ የከፋ ሰቆቃ ነው የምታየው፤ በእርግጥ ያን አፍጋኒስታን ውስጥም ታየዋለህ። ሰቆቃ እንደውም በደንብ አይገልጠውም። እነዚህ ሰዎች የከፋ መከራ እና ሥቃይ የደረሰባቸው መኾኑን ከገጻቸው ማንበብ ይቻላል። በዚያ ላይ እነዚህ ሰዎች ከጀልባዎቹ እንዴት እንደሚዘሉ መመልከት በራሱ ሁኔታው እጅግ ሲበዛ የሚያሳዝን እና ሊደብት የሚችል ነው።»

የመርከቢቱ የላይኛው ክፍል ላይ ቀይ እና ሰማያዊ መብራት ብልጭ ድርግም ይላል። የመርከቢቱ አዛዥ አንድሪያስ ሽሜክል ቁጥጥር በማድረግ ላይ ናቸው። የነፍስ አድን ርዳታ የሚያስፈልጋቸው ስደተኞች በቅድሚያ የሚያርፉት እዚህ ላይኛው ክፍል ውስጥ ነው። ርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ስደተኞች ከማዳን ሥራው ባሻገር ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ማባረሩ ሌላኛው የባሕረተኞቹ አስቸጋሪ ተግባር ነው።

«የደረስንበት ነገር ቢኖር ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችም እንደሚማሩ ነው። ትናንት ያደረጉትን ዛሬ አያደርጉትም። መጀመሪያ አካባቢ ላይ ስደተኞችን የጫነችው መርከብ የሊቢያን የባሕር ግዛት እስክትለቅ ድረስ አጅበው ይቀዝፉ ነበር። በኋላ ግን ደረሱበት፤ ለካ እዚያ አንዳች ነገር ሊያደርጉ የሚችሉ የባሕር ኃይል መርከቦች አሉ። ስለዚህ ወደዚያ መምጣታቸውን አቆሙ።»
ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን የግንኙነት መረብ ጫፍ ለምግኘት የመርከቢቱ ሠራተኞች ማድረግ የሚችሉት አንድ ነገር ቢኖር ከመስጠም ከተረፉ ስደተኞች መረጃ መሰብሰብ ነው። ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ከባሕረተኞቹ ጋር የሚያደርጉት ድብብቆሽ ግን መቋጫ አልተገኘለትም።

ዳንኤል ፔልስ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic