ነፃ የቢያፍራ መንግሥት የመመስረት ህልም | አፍሪቃ | DW | 27.05.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ነፃ የቢያፍራ መንግሥት የመመስረት ህልም

በናይጀሪያ የቀድሞ የቢያፍራ ፌዴራዊ ግዛት አስተዳዳሪ የነበሩት ኮሎኔል ቹኩዌሜካ ኦዱሜግጉ ኦጁኩ ይህንኑ በደቡብ ምሥራቃዊ የሀገሪቱ አካባቢ የሚገኘውን ግዛት ነፃ ሬፓብሊክ  ብለው ካወጁ የፊታችን ማክሰኞ 50 ዓመት ይሆነዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:10

ቢያፍራ

በጎርጎሪዮሳውያኑ 1967 ከናይጀሪያ ተገንጥላ ለሶስት ዓመታት ነፃ ሬፓብሊክ አቋቁማ የነበረችው ቢያፍራ ዛሬ በተለይ የምትታወሰው በዚያን ጊዜ በአካባቢው በተካሄደው እና ከአንድ ሚልዮን የሚበልጥ ሰው ህይወት ባጠፋው አስከፊ የርስበርስ ጦርነት እና በሰበቡ በተከተለው ሶስት ሚልዮን ሰዎችን ሰለባ ባደረገው  የረሀብ አደጋ  ነው። ይሁን እንጂ፣ የዚሁ አካባቢ ሕዝብ፣ በተለይም ወጣቱ፣ የዶይቸ ቬለ ካትሪን ጌንስለር እንደምትለው፣  አሁንም ነፃ የቢያፍራ መንግሥት ምሥረታ ህልሙ ገና አልጠፋም።  ቢያፍራ የሚባለው ሀገርም ከጠፋ ብዙ ጊዜው ነው። ያም ሆኖ ግን፣ በኤኑጉ ከተማ የሚኖረው ኪንግስሌይ ኦካ ለብዙ ጊዜ ተረስቶ የነበረውን ብሔራዊ መዝሙር ዜማ መስማት ራሱ በጣም ነው የሚያስደስታቸው። የ27 ዓመቱ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ከጎርጎሪዮሳውያኑ 1967 እስከ 1970 ዓም  ድረስ ነፃ ቢያፍራ በሚል ይታወቅ የነበረው ሀገር ተወላጅ ናቸው። እና የያኔዋ ቢያፍራ ዛሬም ራሷን ችላ የቆመች ሀገር እንድትሆን ይፈልጋሉ። የኢግቦ ጎሳ ተወላጅ የሆኑት ኦካ 185 ሚልዮን ሕዝብ በሚኖርባት እና 250 የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ባሉባት ናይጀሪያ ውስጥ የተገለሉ ያህል ይሰማቸዋል። ለዚሁ ላደረባቸው የመገለል ስሜት ከሰሜን ናይጀሪያ የሚወለዱት የሀገሪቱ ፕሬዚደንት መሀማዱ ቡሃሪ የሚመሩትን  መንግሥት ተጠያቂ አድርጓል።

« በመንግሥቱ ካቢኔ ውስጥ አንድም ምሥራቅ ናይጀሪያዊ የለበትም። ይህ ማለት፣ የምሥራቅ ናይጀሪያን ሕዝብ ለመግደል ቢያቅድ፣ እቅዳቸው ካላንዳች ችግር ተግባራዊ ይሆናል ማለት ነው።  የተማረ እና በቂ መረጃ ያላቸው ሰዎች ይህን አሰራር አይቀበሉም። ለመብታችን መታገል አለብን። መፍትሔው ቢያፍራ ነው። »

ይህን የኪንግስሌይ ኦካ ሀሳብ በተለይ በደቡባዊ ምሥራቅ ናይጀሪያ የሚገኙት ወጣቶች ይደግፉታል።

በየመንገዶች በአውቶቡስ ማቆሚያ ቦታዎች የተለጠፉ ስእሎችና ጽሁፎች የቀድሞው የደቡብ ምሥራቅ ናይጀሪያ ግዛት አስተዳዳሪ ቹኩዌሜካ ኦዱሜግጉ ኦጁኩ ከሁለት መፈንቅለ መንግሥት እና ከባድ የጎሳ ውዝግብ በኋላ ነፃ የቢያፍራ ሬፓብሊክ የመሰረቱበትን ጎርጎሪዮሳዊውን ግንቦት 30፣ 1967 ዓም ን ያስታውሳሉ። በደቡብ ምሥራቅ ናይጀሪያ የሚኖረው ህዝብ ነፃ የቢያፍራ ሬፓብሊክ ለመመስረት ፍላጎት እንዲያድርበት ያደረገው በሀገሪቱ መንግሥት  ላይ ያለው ቅሬታ ነው። በአቡጃ እና በሌጎስ የሚገኙት ባለስልጣናት በኒጀር ደለል የሚገኘውን የነዳጅ ዘይት ሀብት ያካባቢውን ተፈጥሮ ብክለትን ባስከተለ መንገድ መበዝበዝ እና ያካባቢውን ሕዝብ የዚሁ ሀብት ሽያጭ ገቢ ተጠቃሚ ያላደረጉት ሁኔታ ይጠቀሳል።

በምህፃሩ «ኢ ፒ ኦ ቢ» የተባለው የቢያፍራ ጥንታውያን ተወላጆች ንቅናቄ መሪ  ንናሚዲ ካኑ የቢያፍራ ጉዳይ  እጎአ ከ2015 ዓም ወዲህ ትኩረት እንዲያገኝ ባደረጉት ትግላቸው በወቅቱ የብዙዎች መነጋገሪያ ርዕስ ሆኗል።  የአንድ ወንጀለኛ ድርጅት አባል ናቸው በሚል ክስ ወህኒ ቤት ወርደው የነበሩት ካኑ   ባለፈው ሚያዝያ በዋስ ከእስር ቤት ከተፈቱ በኋላ ብዙ ሰዎች ካኑ ወደሚኖሩበት የወላጆቻቸው መኖሪያ ቤት ወደሚገኝባት  የኡሙአሂያ ጎረቤት ወደሆነችው የአቢያ ከተማ በመሄድ  ድጋፋቸውን እየገለጹ ይገልጻሉ።  ካኑ ለቢያፍራ ነፃነት ከመታገል ወደኋላ እንደማይሉ ይናገራሉ።

« ሕይወት ካለ ቢያፍራ  ሕይወት አይደለም። ናይጀሪያን ላለፉት 56 ዓመታት ሞክረናታል። ይሁንና፣ አንድም የተቀየረ ነገር የለም። አዲስ ነገር እንፈልጋለን። ቅን ገዢዎቹ ብሪታንያውያን ከመምጣታቸው በፊት ወደነበረበት ሁኔታ መመለስ እንፈልጋለን። አንድም ጦርነት አልነበረም።  እምነታችንን ለመከታተል መፍራት አልነበረብንም። ዛሬ ካኖ ውስጥ ይህን ብታደርግ ይገድሉሀል። »

Nigeria Biafra | Nnamdi Kanu

ንናሚዲ ካኑ

የካኖ ከተማ በብዛት ሙስሊሞች በሚኖሩበት ሰሜናዊ ናይጀሪያ የምትገኝ ሲሆን፣  በዚችው ከተማ ከፅንፈኛ ሙስሊም ቡድኖች ጋር ውጥረቱ ሁሌ እንደተካረረ ነው። እንደሚታወቀው፣ አሸባሪው የሙስሊም ፅንፈኞች ቡድን ቦኮ ሀራም ጠንካራ ሰፈሩን ያደረገው በዚሁ ሰሜናዊ ናይጀሪያ አካባቢ ነው። በደቡባዊ ናይጀሪያ ከሚኖሩት የኢግቦ ጎሳ አባላት መካከል ብዙዎቹ የክርስትና እምነት ተከታዮች ናቸው።  

ካኑ በኢግቦ ጎሳ ተወላጆች ላይ ይደርሳል ከሚሉት የመገለል ርምጃ በላይ ግን አብዝቶ የሚያስቆጣቸው  የናይጀሪያ ኤኮኖሚያዊ  ካለፉት አስር ዓመታት በላይ እድገት ማሳየት የቆመበት ሁኔታ ነው።   

« ተራው ሕዝብ በሀገሩ አንድም የሚሰራ ነገር በጣም መሮታል። ምክንያቱ ደግሞ፣ ናይጀሪያን የሚመሩት ብዙዎቹ ባለስልጣናት ከሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል የሚወለዱ የሀውሳ እና የፉላኒ ጎሳ አባላት በመሆናቸው ነው። እነዚህ ባለስልጣናት ምርታማነትን እንዴት ማስገነት እንደሚቻል አያውቁም። የሁሉንም ፍላጎት እና ትጽቢት ሊያሟላ የሚችል ኤኮኖሚያዊ ልማት የሚገኝበትን ሁኔታ ማመቻቸት አልቻሉም። »

ይህ ካኑ በሀውሳ እና በፉላኒ ጎሳ ዎች ላይ የሰነዘሩት ከባድ ወቀሳ ብዙዎችን አላስደሰተም። በመዲናይቱ አቡጃ የሚኖሩት የሰሜን ናይጀሪያ የጂጋዋ ከተማ ተወላጅ የሆኑትን ሰይድ ሙአሱን የመሳሰሉ  ሰዎች ወቀሳውን አልተቀበሉትም።

« ወደ ሰሜን ናይጀሪያ የሚሄድ ሰው፣ የኢግቦ ጎሳ አባላት በዚያ ንግዳቸውን በሰላም እንደሚያከናውኑ መመልከት ይችላል። ማንም ሰው በአካባቢም ሆነ በዞን ደረጃ አንድም እንቅፋት አይደቅንባቸውም። ራቅ ብለው በሚገኙ የሰሜን ናይጀሪያ መንደሮች ያሉት የኢግቦ ጎሳ ተወላጆች ከህብረተሰቡ ጋር በሰላም ነው የሚኖሩት።  ልጆቻቸው ልክ እንደሌሎቹ የመንደሩ ነዋሪዎች አንዳችም ልዩነት ሳያጋጥማቸው ወደ ትምህርት ቤት ይሄዳሉ። ሁኔታው ይህ ሆኖ ሳለ ታድያ፣ የመገለል ችግር ያጋጥመናል በሚል የሚሰነዝሩት ወቀሳ ከሀቅ የራቀ ነው። »

እንደ ሰይድ ሙአሳ አመለካከት፣ ችግር ሳይኖርባቸው ችግር አለ የሚሉ እና ለብቻቸው መሆን ከፈለጉ ሊሄዱ ይችላሉ። ይህ ዓይነቱ አስተያየት በኤኑጉ የሚገኙትን ኪንግስሌይ ኦካን የመሳሰሉትን የኢግቦ ተወላጆች ማስደሰቱ አልቀርም።

ቢያፍራ ነፃ ትሁን አትሁን የሚለው ክርክር ደምቆ በቀጠለበት ባሁኑ ጊዜም ግን ኪንግስሌይ ኦካ ይህን ምኞታቸውን እውን ለማድረግ የት ድረስ እንደሚሄዱ በግልጽ ያውቁታል።

« ለነፃነት ለመዋጋት ብዬ የጦር መሳሪያ አላነሳም። ለቢያፍራ ነፃነት የሚያስፈልገን የሀሳብ ትግል ነው። የቢያፍራ ነፃነት ተሟጋቾች ሀሳባቸውን በጋዜጦች ማስፋፋት ይችላሉ። ለዚሁ ዓላማ የሚታገሉ ወይም ዓላማውን ማራመድ የሚፈልጉ ደግሞ ካለ ጦር መሳሪያ ፣ የአደባባይ ተቃውሞዎችን ማዘጋጀት ይችላሉ። »

ይሁን እንጂ፣ እስካሁን ምን ያህል የደቡብ ምሥራቅ ናይጀሪያ ሕዝብ ነፃ የቢያፍራ ሬፓብሊክ ይቋቋም የሚለውን ንቅናቄ እና ሀሳብ እንደሚደግፍ በትክክል የሚያሳይ መዘርዝር የለም፤ በዚሁ ጥያቄም ላይ ሕዝበ ውሳኔ ማካሄድ ያስችል ይሆናል  የሚባል እቅድም አልወጣም።

አርያም ተክሌ

ልደት አበበ

Audios and videos on the topic