ነፃው የሃንጋሪ የትምህርት እድልና የኢትዮጵያውያኑ ፈተና | ወጣቶች | DW | 06.12.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ወጣቶች

ነፃው የሃንጋሪ የትምህርት እድልና የኢትዮጵያውያኑ ፈተና

ነፃ የትምህርት እድል ማግኘት የብዙ ተማሪዎች ምኞት ነው። አብዛኛውን ጊዜም ይህንን እድል የሚያገኙት ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ናቸው። ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ነፃ የትምህርት እድል አግኝታችኋል ተብለው ወደ ሀንጋሪ የሄዱ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ለመኖሪያ የሚሰጣቸው ገንዘብ በቂ ባለመሆኑ ከፍተኛ ፈተና ውስጥ ይገኛሉ። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:59

ነፃው የሃንጋሪ የትምህርት እድል ፈተና ሲሆን

ሙሉጌታ አለ ነፃ የትምህርት እድል አግኝተው ዘንድሮ ወደ ሀንጋሪ ከተላኩ ኢትዮጵያውያን አንዱ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በባህር ዳር ዩንቨርስቲ በመምህርነት ያገለግል የነበረው ሙሉጌታ ዛሬ በሀንጋሪ በፓኖኒያ ዮንቨርስቲ የኬሚካል ምህንድስና የድህረ ምረቃ ተማሪ ነው። በዚህ ዩንቨርስቲ ተመሳሳይ የትምህርት እድል አግኝተው ከመጡ ኢትዮጵያውያን ብቸኛው ቢሆንም በሀገሪቱ የተለያዩ ዮንቨርስቲዎች ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ጋር ተመሳሳይ ችግር ገጥሟቸዋል።  « የኢኮኖሚ ችግር ነው የገጠመን።  የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ሀንጋሪ ሲልከን ውል ይዘን ነው የመጣነው። ወደ ኢትዮጵያ ስንመለስ ሀገራችንን ለሁለት ወይም አራት አመት በእየዩንቨርስቲያችን እንድናገለግል። የሀንጋሪ መንግሥት አስተዋፅዎ ሲያደርግልን ላኪው ሀገር ደግሞ ለኑሮ መደጎሚያ ገንዘብ መስጠት አለበት ይላል።» እኛ ግን የምንኖረው የሀንጋሪ መንግስት በሚሰጠን 130 ዩሮ ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ትንሽ ነው ይላል ሙሉጌታ። ተማሪዎቹ ቋንቋ ቢችሉ በሳምንት 24 ሰዓት የመስራት የስራ ፍቃድ አላቸው።

Andrássy-Universität Budapest Bild 4 (ACHTUNG: Nur für Artikel über die Hochschule verwenden!)


ያገኙት የትምህርት እድል ቢያስደስታቸውም አጣብቂኝ ውስጥ እንደገቡ ያጫወተችን ሌላዋ ተማሪ በአዲግራት ዮንቨርስቲ ውስጥ በመምህርነት ታገለግል የነበረችው ለምለም ገብረ ማሪያም ናት። በህክምና ስር ሆኖ የምግብ ሳይንስ የዶክትሬት ተማሪ የሆነችው ለምለም ከድህረ ምረቃ ተማሪዎች የተሻለ ገንዘብ ከሚያገኙት ኢትዮጵያውያን ተርታ ትመደባለች። ለዶክትሬት ተማሪዎች የተመደበው ገንዘብ 450 ዶላር ነው። ይሁንና ሌላ ወጪ እንዳለባቸው ገልጻልናለች። « ጥናቶች እንሰራለን። ብዙ ቦታ እንሄዳለን። ሁሉንም ወጪ የምንሸፍነው በራሳችን ነው።» ትላለች። በአሁኑ ሰዓት ስራ የላትም። ይሁንና እድሌን ልሞክር ብዬ ስራ ለማግኘት ተመዝግቤያለሁ ትላለች ለምለም ። ከዋና ከተማዋ ቡዳፔስት ወጣ ብላ መኖሯ ብቻ ሳይሆን ቋንቋ አለመቻልም ሌላው ችግር መሆኑን የዶክትሬት ተማሪዋ ገልጻልናለች። ትምህርታቸውን ለመቀጠል ግን መስራት ብቸኛው አማራጭ ሆኖባቸዋል። « ሳይተኙ የአዳር ስራ ሰርተው ጠዋት ክላስ የሚገቡ አሉ። ስራም እንደተፈለገ አይገኝም።» 

Studierende der Andrássy-Universität Budapest (ACHTUNG: Nur für Artikel über die Hochschule verwenden!)

ለምለም ትምህርቷን ለማጠናቀቅ ገና አራት ዓመት ይቀራታል። ካሳሁን ደብረሰን በተባለ እንዲሁ ሀንጋሪ ውስጥ የሚገኝ አንድ ዩንቨርስቲ ውስጥ የሶሻል ወርክ ተማሪ ነው። በዚሁ ዩንቨርስቲ የሁለተኛ አመት ተማሪ የሆነው ካሳሁን ከዚህ በፊት በወልቂጤ ዩንቨርስቲ ነበር የሚሰራው። ሀንጋሪ ውስጥ ለኑሮ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማብቃቃት ሲታገል ዓመት እንዳለፈው ይናገራል።እስካሁን ስራ አላገኘም። በገንዘብ እጥረት ምክንያት ከሌላ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ጋርም መገናኘት የማይታሰብ ሆኖበታል። « ከሌላ ሀገር የመጡ ተማሪዎች ከሁለት ቦታ ገንዘብ ስለሚያገኙ በቂ ገንዘብ ስለሚያገኙ ብዙ ቦታ አውሮፓ ውስጥ የመዟዟር እድል አላቸው። እኛ ግን የትም ወጥተን አናውቅም።ያችው በወር የምናገኛትን ገንዘብ ስናቀናንስ ነው የምንኖረው»  የሚጎለውን ገንዘብ ለሟሟላት ካሳሁን ውጭ ከሚኖሩ ዘመዶቹ ማስቸገር እንዳለበት ገልፆልናል።

ተማሪዎቹ የኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ከዚህ በፊት ጠይቀው እንደነበር እና ተስፋ ተሰጥቷቸው እንደነበርም ሙሉጌታ እና ካሳሁን ገልጸውልናል። ይሁንና ጥያቄያችን ውሃ በላው ይላሉ። ተማሪዎቹን ለትምህርት በላካቸው በሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የውጭ ግንኙነት እና ስኮላርሽፕ ዳሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ ምትኩ በሬቻ የተማሪዎቹ ብሶት ትክክል እንደሆነ ለዶይቸ ቬለ ቢያረጋግጡም ለተማሪዎቹ ችግር አፋጣኝ መፍትሄ የላቸውም። « የሚሰጠው ገንዘብ በቂ አለመሆኑን አይተን ለተማሪዎቹ የድጎማ ገንዘብ እንዲደረግላቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ጥያቄ ቀርቦ እስካሁን ምላሽ አልተገኘም።» ይላሉ አቶ መላኩ። ከዚህም ሌላ « አሁን በሚሰጣቸው ገንዘብ መኖር አንችልም እና የግድ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ አለብን ብለው የሚሉ ካሉ የመመለስ ጥያቄ ማቅረብ ይችላሉ። እሱ ታይቶ ውሳኔ የሚሰጥበት ይሆናል።» ብለዋል። በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ምላሽ እንዲሰጠን በተደጋጋሚ ያደረግነው ሙከራ ምላሽ ባለማግኘቱ የነርሱን ሃሳብ በዘገባችን ለማካተት አልቻልንም።

ልደት አበበ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic