ነጻ የአየር ትኬት በደ/አፍሪቃ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን | ኢትዮጵያ | DW | 23.04.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ነጻ የአየር ትኬት በደ/አፍሪቃ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን

በደቡብ አፍሪቃ በስደተኞች ላይ የተቀሰቀሰው ተቃውሞና ጥቃት ከተስፋፋባቸው አካባቢዎች የአሌክሳንድራ ታዎንሺፕ በአገሪቱ ጦር ሰራዊት ተረጋግቷል። የኢትዮጵያ መንግስት ከደቡብ አፍሪቃ ወደ አገራቸው ለሚመለሱ ዜጎች ነጻ የአየር ትኬት እያዘጋጀ ነው ተብሏል።

በደቡብ አፍሪቃ ለከታታይ ሳምንታት በውጭ አገር ሰዎች በተለይም የሌሎች የአፍሪቃ አገራት ዜጎች ላይ ተቃውሞ ከተካሄደ በኋላ የአገሪቱ ጦር ለፖሊስ ድጋፍ ለመስጠት ወደ ከተሞች መግባቱን ኤ.ኤፍ.ፒ የዜና ወኪል ዘግቧል። ወታደሮች በሄሊኮፕተር በመታገዝ ባካሄዱት ብርበራ አደንዛዥ እጽና የተዘረፉ ንብረቶች ይዘው የተገኙ 11 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የደቡብ አፍሪቃ ፖሊስ ቃል-አቀባይ ሶሎሞን ማክጋሌ ተናግረዋል። የጸጥታ ሃይሎች አስራ አንድ ተጠርጣሪዎችን ካሰሩ በኋላ እስካሁን በመጤዎች ላይ የተፈጸመ ጥቃት የለም ተብሏል።

በደቡብአፍሪቃስርበሰደዱማህበራዊእናኢኮኖሚያዊችግሮች መነሾ በመጤዎች ላይ የተነሳው ተቃውሞ፤ጥቃትና ዘረፋ የዚምባብዌ፤ማላዊ እና ሞዛምቢክ ስደተኞች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። በስራ አጥነት የተማረሩትና በአማካኝ ወጣት በሆኑ ደቡብ አፍሪቃውያን በተፈጸመ ጥቃት ሰባት ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። ከሰባቱ ሟቾች መካከል አንዱ ኢትዮጵያዊ መሆኑን ያረጋገጡት በደቡብ አፍሪቃ ፕሪቶሪያ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ኋላፊ አቶ ኤልያስ ወርቁ « በቃጠሎና በዘረፋ የበርካታ ኢትዮጵያውያን ንብረት ወድሟል።» ብለዋል። በጥቃቱ የወደመውን ንብረት ማጣራት እንደሚካሄድና ኤምባሲው በአሁኑ ወቅት የዜጎቹን ደህንነት በማስጠበቅና ከጥቃት ማዳን ላይ ትኩረት ማድረጉንም አስረድተዋል።

ደቡብ አፍሪቃ ከአፓርታይድ አገዛዝ መውደቅ በኋላ ለአፍሪቃውያን የስራ እና የእድል ምድር ሆና በርካታ ስደተኞችን ተቀብላለች። ከሌሎች የአፍሪቃ አገራት የርስ በርስ ጦርነት እና ግጭት እንዲሁም በየአገሮቻቸው ከሚደርስባቸው ፖለቲካዊ ጫና የሸሹ አፍሪቃውያን በደቡብ አፍሪቃ የተሻለ የስራ እድል እና ገቢ ማግኘት አገሪቱን የስደተኞች መዳረሻ አድርጓት ቆይቷል። ይሁንና ደቡብ አፍሪቃ ሁልጊዜም ለስደተኞች ገነት አልነበረችም። በጎርጎሮሳዊው 2008 ዓ.ም. በተቀሰቀሰ ተመሳሳይ ተቃውሞ እንኳ 62 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። የደቡብ አፍሪቃ ፖለቲከኞች «ቀስተ-ደመናዋ አገር» ያሏት አገር አሁንም ሆነ ወደ ፊት ለስደተኞች ምቹ ለመሆኗ ጥርጣሬ ነግሷል። አቶ ኤልያስ ወርቁ በደቡብ አፍሪቃ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አመት እየጠበቀ የሚያገረሸውን የደቡብ አፍሪቃ ተቃውሞና ጥቃት ትኩረት ሰጥቶ በመከታተል ራሳቸውን ከአደጋ ሊጠብቁ ይገባል ብለዋል።

ደቡብ አፍሪቃ ክዋዙሉናታል በሚባለው ግዛት በመጤዎች ላይ ለተነሳው ተቃውሞና ጥቃት መነሾ ንግግር አድረዋል የተባሉት ንጉስ ዝዌሌቲኒ በይፋ ጥቃቱን ማውገዛቸው ለመቀዛቀዙ ምክንያት ነው ተብሏል። የደቡብ አፍሪቃ መንግስትና ፖለቲከኞችም ዘግይተውም ቢሆን መፍትሄ ፍለጋ መሯሯጥ ይዘዋል። ከክዋዙሉናታል ተነስቶ እስከ ጁሃንስበርግ የዘለቀው የስደተኞች ጥላቻ ለጊዜው በርዷል። በአገሪቱ የሰፈነው ፍትሃዊ ያልሆነ የሃብት ክፍፍል፤የስራ እጦትና ድህነት ግን ጥቃቱ እንዲያገረሽ ያደርገዋል የሚሉ ተንታኞች በርካቶች ናቸው።አቶ ኤልያስ ወርቁ ኤምባሲው ወደ አገራቸው መመለስ ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ነጻ የአውሮፕላን ትኬት ማዘጋጀቱን ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic