ኅዳር 6 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ  | ስፖርት | DW | 15.11.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

ኅዳር 6 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ 

በዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ግጥሚያዎች ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ የተፎካከረችው ጋና በስተመጨረሻ ማለፏን አረጋግጣለች። ከአውሮጳ ደግሞ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ የማጣሪያ ግጥሚያውን በሰፋ የግብ ልዩነት በድል አጠናቋል። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ሌዊስ ሐሚልተን ዳግም ወደ ድል አድራጊነቱ ተመልሷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:01

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ግጥሚያዎች ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ የተፎካከረችው ጋና በስተመጨረሻ ማለፏን አረጋግጣለች። ከአውሮጳ ደግሞ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ የማጣሪያ ግጥሚያውን በሰፋ የግብ ልዩነት በድል አጠናቋል። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ሌዊስ ሐሚልተን ዳግም ወደ ድል አድራጊነቱ ተመልሷል። አጠቃላይ ውድድሩ ሊጠናቀቅ ጥቂት ፉክክሮች በቀሩበት በአሁኑ ወቅት ተፎካካሪዎች እጅግ በነጥብ ተቀራርበዋል።

እግር ኳስ

ኳታር በምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ግጥሚያ ተሳታፊ ለመሆን የሚደረገው ፉክክር በአስደማሚ ውጤቶች እና ውዝግቦች ታጅቦ ቀጥሏል። በአፍሪቃ ወደማጣሪያው ያለፉ ሃገራት ታውቀዋል። ትናንት እና ከትናንት ወዲያ በነበሩ የማጣሪያ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ከምትገኝበት ምድብ ከደቡብ አፍሪቃ ጋር ተመሳሳይ 13 ነጥብ ያላት ጋና በተመሳሳይ የግብ ክፍያ እና እዳ ሆኖም ብዙ ባገባ በሚለው ማለፏን አረጋግጣለች። ትናንት ጋና ኬፕ ኮስት ስታዲየም ውስጥ በተከናወነው ግጥሚያ ደቡብ አፍሪቃ በኳስ ይዞታ በልጣ ብትታይም በ33ኛው ደቂቃ ላይ በአንድሬ አዩ በተቆጠረው ብቸኛ ግብ ተሸንፋለች።

የትናንቱን ሽንፈት የዳኞች አድልዎ አለበት በሚል የደቡብ አፍሪቃ እግር ኳስ ፌዴሬሽን (SAFA) ለሚመለከታቸው አካላት አቤት እንደሚል ዛሬ ዐስታውቋል። በዚህም መሠረት ደቡብ አፍሪቃ ለዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበራት ፌዴሬሽን (FIFA) እና ለአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF)አቤቱታዋን እንደምታስገባ ዛሬ ዐስታውቃለች። ጋና የማሸነፊያ ግብ ያገኘችው በአወዛጋቢው የፍጹም ቅጣት ምት ውሳኔ ነው። ይፋዊ የኾነ ማመልከቻ እንደሚያስገባ የጠቀሰው የደቡብ አፍሪቃ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፦ «ጨዋታውን የዳኙት አካላት በፊፋ እና ካፍ በደንብ እንዲመረመሩ እሻለሁ» ብሏል በመግለጫው።

ደቡብ አፍሪቃ ጆሐንስበርግ ከተማ ኦርላንዶ ስታዲየም ውስጥ በነበረው ያለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ እና የጋና ግጥሚያም ብቸኛዋን ግብ በ22ኛው ደቂቃ ላይ ለሀገሩ ያስቆጠረው ይኸው አንድሬ አዩ ነው። አቻ የምታደርገውን ግብ ጌታነህ ከበደ በ72ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ አሳርፏል።

ትናንት በዋና ከተማዋ ሐራሬ ናሽናል ስፖርትስ ስታዲየም ውስጥ ዋልያዎቹን የተጋጠመችው ዚምባብዌ በበኩሏ አንድ እኩል ተለያይታለች። ቀዳሚውን ግብ ለዚምባብዌ በ39ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ኩዳክዋሼ ማሃቺ ነው። መደበኛ ጨዋታው ሊጠናቀቅ አራት ደቂቃ ሲቀረው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አቻ የምታደርገውን ግብ አቡበከር ናስር አስቆጥሯል። በእርግጥ የኢትዮጵያ እና የዚምባብዌ ብሔራዊ ቡድኖች ከማጣሪያው ውጪ መሆናቸውን ያወቁት ቀደም ብለው ነበር። የጋና ደቡብ አፍሪቃን በልጣ ለማጣሪ ያው ማለፍ ግን በርካቶችን ያስደመመ አጋጣሚ ነበር።

እስከ እሁድ በነበሩ ጨዋታዎች፦ ማሊ፤ ጋና፤ ሴኔጋል እና የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ወደ ማጣሪያው ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። ግብጽ እና ሞሮኮም ቀድመው ማለፋቸው ታውቋል። ከእየ ምድባቸው አንድ አንድ ጨዋታ የሚቀራቸው እና የማለፍ ዕድል ያላቸው ሃገራት የሚከተሉት ናቸው።

ከምድብ «ሀ» በ13 ነጥብ የምትመራው አልጀሪያ እና በ11 ነጥብ የምትከተለው ቡርኪናፋሶ ነገ የሚያደርጉት የመጨረሻ ግጥሚያ አላፊውን የሚለይ ይሆናል። ከምድብ «ለ» ቱኒዝያ እና ኤኳቶሪኢል ጊኒ ተመሳሳይ 10 ነጥብ አላቸው። ኤኳቶሪያል ጊኒ ከሞሪታንያ እንዲሁም ቱኒዝያ ከዛምቢያ ጋር ነገ በሚያደርጉት ግጥሚያ አሸናፊው ይለያል። ዛምቢያ 10 ነጥብ ስላላት የማለፍ ዕድሏ ሙሉ ለሙሉ አልመከነም። ከምድብ «ሐ» 12 ነጥብ ያለው ናይጄሪያ እና ባለ 10 ነጥቡ ኬፕ ቬርዴ ነገ በሚያደርጉት ግጥሚያ አሸናፊው ወደ ቀጣዩ የዓለም ዋንጫ ማለፍ ይችላል። ናይጄሪያ አቻ መውጣት ብቻ ይበቃዋል።

በምድብ «መ»ም ቢሆን በ13 ነጥብ የሚመራው አይቮሪኮስት እና በ12 ነጥብ የሚከተለው ካሜሩን ነገ በሚያደርጉት ፍልሚያ የሚያልፈው ይለያል። በምድብ «ረ» ግብጽ እና ጋቦን የመጨረሺያ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ። ግብጽ 11 ነጥብ አለው፤ ጋቦን በ7 ነጥብ ተወስኗል። ሞሮኮ እና ጊኒ ቢሳዎም ነገ ይጋጠማሉ። ሞሮኮ 15 ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ጊኒ ቢሳዎ 5 ነጥብ ብቻ አለው። የቅድመ ማጣሪያቸውን ያለፉ ዐሥር ቡድኖች ከመጋቢት 12 እስከ መጋቢት 20 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የደርሶ መልስ ግጥሚያ ያከናውናሉ። አሸናፊ የሆኑ አምስት ቡድኖችም በቀጥታ ለኳታሩ የዓለም ዋንጫ ያልፋሉ።

ወደ ዓለም ዋንጫ ለማለፍ አውሮጳ ውስጥ በሚደረጉ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች ዛሬ ማታ ጣሊያን ከሰሜን አየርላንድ እንዲሁም ስዊዘርላንድ ከቡልጋሪያ ጋር ወሳኝ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።  ጣሊያን እና እንግሊዝ ለቀጣዩ የዓለም ዋንጫ የማለፍ ዕድል አላቸው። ትናንት በሠርቢያ 2 ለ1 የተሸነፈው የፖርቹጋል ቡድን ግን ወደ ዓለም ዋንጫ ለማለፍ በቀጣዩ የጎርጎሪዮሱ ዓመት የደርሶ መልስ ጨዋታ ማድረግ ይኖርበታል።  የክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ጓደኞቹን ሕልም ያጨናገፉት ሠርቢያዎች በአንጻሩ በ20 ነጥባቸው ከምድቡ አንደኛ በመሆን በቀጥታ ለዓለም ዋንጫ ማለፍ ችለዋል። ፖርቹጋል ከምድቡ በ17 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ስፔን እና ስዊድን ትናንት ባደጉት ወሳኝ ግጥሚያም የ40 ዓመቱ አጥቂ ዝላታን ኢብራሒሞቪችን በተቀያሪነት ያሳለፈችው ስዊድን 1 ለ0 ተሸንፋለች። በመጨረሻ ግጥሚያዋ አቻ መውጣት ብቻ ይበቃት የነበረችው ስፔን 86ኛው ደቂቃ ላይ አልባሮ ሞራታ ከመረብ ባሳረፈው ብቸኛ ኳስ በ19 ነጥብ ለዓለም ዋንጫ ማለፏን አረጋግጣለች። 15  ነጥብ ያላት  ስዊድን እንደ ፖርቹጋል ሁሉ የደርሶ መልስ ጨዋታ ይጠብቃታል።

የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በበኩሉ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጉዞውን ትናንት አርሜኒያን 4 ለ1 ድል በማድረግ አጠናቋል። አሰልጣኝ ዲተር ሐንሲ ፍሊክ፦ ምንም እንኳን በምድባቸው እጅግ ጠንካራ የተባለ ተፎካካሪ ባይገጥማቸውም ለ7 ጊዜያት በተከታታይ ድል በማድረግ 31 ኳሶችን ከመረብ ማሳረፍ አስችለዋል። የተቆጠረባቸው ሁለት ግቦች ብቻ ነው።

አሰልጣኝ ዲተር ሐንሲ ፍሊክ ለዚህ ስኬት ለመብቃት በቡድናቸው የሚገኙ ተጨዋቾችን ብቃት ለይተው ማወቃቸው በዋናነት ይጠቀስላቸዋል። በቡድናቸው ሌዎን ጎሬትስካ እና ዮሹዋ ኪሚሽ እንዲሁም በሒደት ወደ ቀድሞ ብቃቱ መመለስ የቻለው ሌሮይ ሳኔ ለውጤቱ ወሳኝ ተጨዋቾች ናቸው ማለት ይቻላል። በተለይ ሌዎን ጎሬትስካ በአማካይ ስፍራ ሲጫወት ልዩ ብቃት ይስተዋልበታል። አንዳንዶች በዚያ እንደውም ቦታ ላይ እንደ ሌዎን ጎሬትስካ የሚሆን የለም ሲሉም ይደመጣል። ሌላው የብሔራዊ ቡድኑ አንጋፋ ግብ ጠባቂ ማኑዌል ኖየር አስተዋጽዖም በከፍተኛነት ይጠቀሳል። ማኔዌል ኖየር የቀድሞ ብቃቱን በመመለስ በዓለማችን አሁንም ድንቅ ከሚባሉ ግብ ጠባቂዎች ተርታ እንደሚመደብ ማስመስከር ችሏል። እስካሁን በነበሩ ግጥሚያዎችም፦ ጀርመን፤ ዴንማርክ፤ ፈረንሳይ፤ ቤልጂየም፤  ክሮሺያ፤ ስፔን እና ሠርቢያ ማለፋቸውን ካረጋገጡ ቡድኖች ውስጥ ይገኛሉ።

አትሌቲክስ

ኢትዮጵያውያን ሁለት አትሌቶች በዓለም አትሌቲክስ የዓመቱ ተስፋ የተጣለባቸው ተተኪዎች (rising star) እጩ ዝርዝር ውስጥ መግባታቸው ባሳለፍነው ሳምንት ይፋ ኾኗል።  በሴቶች አትሌት ዘርፌ ወንድማገኝ፤ በወንዶች ደግሞ አትሌት ታደሰ ወርቁ ናቸው የታጩት። በእየ ምድባቸው የሚፎካከሩት አምስት አትሌቶች ናቸው።  በወንዶችም ሆነ በሴቶች የሽልማቱ አሸናፊዎች ማንነት ዓለም አቀፍ ባለሞያዎች በተገኙበት ይፋ የሚደረገው ከ15 ቀናት ግድም በኋላ ረቡዕ፣ ኅዳር 22 ቀን፤ 2014 ዓ.ም ነው።

አትሌት ታደሰ ወርቁ ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የዓለም 3000 ሜትር የሩጫ ውድድር ላይ አሸናፊ፤ በ5000 ሜትር ደግሞ የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ነው። በሦስት ሺህ እና ዐሥር ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድሮች ቀዳሚ ሰአት አስመዝግቧል። እንዲሁም በኢትዮጵያ የአዋቂዎች የ10 ኪሎ ሜትር ፉክክር ክብረወሰን ባለቤት ነው።

አትሌት ዘርፌ ወንድማገኝ በበኩሏ ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የዓለም 3000 ሜትር የመሰናከል የሩጫ ውድድር ላይ የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ናት። በተመሳሳይ የዕድሜ እና የስፖርት ዘርፍ ብሔራዊ ፉክክር ላይ ክብረወሰን ሰብራለች። በ3000 ሜትር መሰናከል የኦሎምፒክ ፍጻሜ ላይም ተሳታፊ ናት።

ከሁለት ዓመት በፊት በነበረው ምርጫ አትሌት ሰለሞን ባረጋ በእጩነት ቀርቦ አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1998 በተደረገው ውድድር አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ አሸናፊ ለመሆን በቅቷል። አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ደግሞ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2004 እና 2005 በተከታታይ በማሸነፍ እሱም በወንዶች የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ አትሌት መሆን ችሏል። ከዚያ ደግሞ አትሌት መሠረት ደፋር ከ14 ዓመት በፊት የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ሴት አትሌት ሆና አሸንፋለች። አትሌት ገንዘቤ ዲባባ እና አልማዝ አያናም እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2015 እና 2016 በተከታታይ ለዚሁ ድል በቅተዋል።

የመኪና ሽቅድምድም

በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የመርሴዲሱ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን ከተደጋጋሚ ሽንፈት በኋላ ወደ ድል ተመልሷል። ሳኦ ፖሎ ብራዚል ውስጥ በተከናወነው ሽቅድምድም ዋነኛ ተቀናቃኙ ማክስ ፈርሽታፐን ማሸነፍ ችሏል። በአንድ ሽቅድምድም ማሸነፍ 25 ነጥብ ያስገኛል። በእሁዱ የብራዚል ሽቅድምድም ሌዊስ ሐሚልተንን በመከተል የሬድ ቡል አሽከርካሪው ማክስ ፈርሽታፐንን የሁለተኛ ደረጃን ይዟል። ሌላኛው የመርሴዲስ አሽከርካሪ ቫለሪ ቦታስ በሦስተኛነት ውድድሩን አጠናቋል።

እስካሁን በተደረጉ ውድድሮች ማክስ ፈርሽታፐን 332.5 ነጥብ ሰብስቧል። ሌዊስ ሐሚልተን በበኩሉ 319.5 ነጥብ አለው። ቫለሪ ቦታስ 203 ነጥብ በመሰብሰብ በአጠቃላይ ተከታታይ ውድድሮች ፍጻሜ ድምር የማሸነፍ ዕድል ባይኖረውም ሦስተኛ ደረጃን ይዟል። ሌላኛው የሬድ ቡል አሽከርካሪ ሠርጂዮ ፔሬዝ በ178 ነጥብ የአራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የማክላረኑ አሽከርካሪ ላንዶ ኖሪስ ለፍጻሜው ድል ከሚፎካከሩት አሽከርካሪዎች ከእጥፍ በላይ ተበልጦ በ151 ነጥቡ አምስተኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል። አጠቃላይ ውድድሩ ሊጠናቀቅ ሦስት ፉክክሮች እየቀሩ በሁለቱ አሽከርካሪዎች መካከል ያለው ልዩነት የ13 ነጥብ ብቻ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች