ኅዳር 20 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ  | ስፖርት | DW | 29.11.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

ኅዳር 20 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ 

ለዓለማችን ምርጥ የእግር ኳስ ተጨዋች ፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ ውስጥ ምሽቱን የወርቅ ኳስ ሽልማት ይበረካታል። ሊዮኔል ሜሲ እና ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ለዐሥር ዓመት በተከታታይ የተምነሸነሹበትን ይህ ሽልማት ዘንድሮ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ይወስዳል የሚሉ ግምቶች ተበራክተዋል። የለም ከሊዮኔል ሜሲ ውጪ አይሆንም የሚሉም አልጠፉም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:21

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ለዓለማችን ምርጥ የእግር ኳስ ተጨዋች ፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ ውስጥ ምሽቱን የወርቅ ኳስ ሽልማት ይበረካታል። ሊዮኔል ሜሲ እና ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ለዐሥር ዓመት በተከታታይ የተምነሸነሹበትን ይህ ሽልማት ዘንድሮ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ይወስዳል የሚሉ ግምቶች ተበራክተዋል። የለም ከሊዮኔል ሜሲ ውጪ አይሆንም የሚሉም አልጠፉም። በእርግጥ አሸናፊው ከሰአታት በኋላ ይታወቃል። ማንቸስተር ዩናይትድ ትናንት የቸልሲ ግስጋሴን ጋብ አድርጎ ነጥብ ተጋርቷል። ማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናልም ድል ቀንቷቸዋል። ቅዳሜ ዕለት ሊቨርፑል በፍጹም የበላይነት በግብ ተንበሽብሾ አሸንፏል። በቡንደስሊጋው ባየር ሌቨርኩሰን ላይፕትሲሽን ድል አድርጎ የሦስተኛ ደረጃን ተቆናጧል። ባየርን ሙይንሽን እና ቦሩስያ ዶርትሙንድ አሁንም አንገት ለአንገት ተናንቀዋል። 

አትሌቲክስ

በቅድሚያም አትሌቲክስ፦ ጣሊያን ውስጥ ትናንት በተከናወነው የፍሎሬንስ ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ ፀሐይ ዓለሙ በአንደኛነት አሸናፊ ኾናለች። በወንዶች ፉክክር ድሉ ለኬንያውያን ኾኗል። በሴቶች የፍሎሬንስ የማራቶን ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ፀሐይ ዓለሙ ውድድሩን በአንደኛነት ለማጠናቀቅ የፈጀባት ጊዜ 2:27:17 ነው። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት መገርቱ ኢፋ ከፀሐይ በአራት ሰከንዶች ብቻ ተበልጣ የሁለተኛ ደረጃን አግኝታለች። ኬኒያዊቷ ሜርሲ ክዋምባው 2:27:32 በመሮጥ በሦስተኛ ደረጃ አጠናቃለች።  በወንዶች ተመሳሳይ ፉክክር ኬኒያዊው ሲብሪያን ኮቱት አሸናፊ የኾነው 2:08:59 በመሮጥ ነው። የሀገሩ ልጅ ሣሙኤል ሎሞይ ከ55 ሰከንድ በኋላ ተከትሎት በመግባት ሁለተኛ ወጥቷል። የቡሩንዲው ሯጭ ኦሊቨር ኢራባራቱ በ2:10:13 ሦስተኛ ሲወጣ፤ 2:11:49 የሮጠው የኤርትራው ሯጭ እቁበ ክብሮም ርእሶም የአራተኛ ደረጃን አግኝቷል። 

እግር ኳስ
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ትናንት በደረጃ ሰንጠረዡ በመሪነት የሚገኘው ቸልሲ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ባደረጉት እና ብርቱ ፉክክር በታየበት ጨዋታ አንድ እኩል ተለያይተዋል። ፈጣን እና የማሸነፍ እልህ በሁለቱም ቡድኖች ቢስተዋልም የቸልሲ ተጨዋቾች በተደጋጋሚ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ ግብ ክልል ሲመላለሱ ነበር። በዚህም ቸልሲ 15 ጊዜያት የማዕዘን ምት ሲያገኝ ማንቸስተር ዩናይትድ በአንጻሩ 2 የማዕዘን ምቶችን ማግኘት ችሏል። በአጠቃላይ የኳስ ይዞታ 66 ከመቶ በመያዝ 34 ከመቶ የነበረውን ማንቸስተር ዩናይትድ በልጦ ታይቷል። አማካዩ ጆርጂንሆ በተከላካይ የመጨረሻ መስመር ላይ ኾኖ የሠራውን ስህተት ተጠቅሞ ጄዶን ሳንቾ ቅልጥፍና እና ብቃት በተስተዋለበት ሁኔታ ለማንቸስተር ዩናይትድ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሯል። በ69ኛው ደቂቃ ላይ ግን ለቸልሲ በፍጹም ቅጣት ምት የተገነኘውን ኳስ ጆርጂኒሆ ከመረብ በማሳረፍ ጥፋቱን አካክሷል። 

በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየርን ሙይንሽን በ31 ነጥብ መሪነቱን አስጠብቋል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ30 ነጥብ ይከተላል። ባየር ሌቨርኩሰን 24 ነጥብ ይዞ በደረጃው ሦስተኛ ነው። አውግስቡርግ፤ አርሚኒያ ቢሌፌልድ እና ግሮይተር ፊዩርት ከ16ኛ እስከ 18ኛ መጨረሻ ተከታትለው ከታች ሰፍረዋል። ባየር ሙይንሽን ሌሮይ ሳኔ 71ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ብቸና ግብ አርሜኒያ ቢሌፌልድን ትናንት አሸንፏል። ላይፕቲሽ በባየር ሌቨርኩሰን 3 ለ1 መሸነፉም መነጋገሪያ ኾኗል። በኳስ ይዞታ እና ወደ ግብ በመጠጋት ላይፕትሲሽ በልጦ ቢታይም ድሉን ግን ለባየር ሌቨርኩሰን አሳልፎ ሰጥቷል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቮልፍስቡርግን 3 ለ1 ድል አድርጓል። ቅዳሜ ዕለት ኮሎኝ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን በሰፋ የግብ ልዩነት 4 ለ1 ሲያሸንፍ፤ በርካታ ግብ በተቆጠረበት የቅዳሜ ሌላ ጨዋታ ሆፈንሃይም ግሮይተር ፊዩርትን 6 ለ3 አደባይቷል። 

የወርቅ ኳሱ (Ballon d'Or) 
የፈረንሳይ እግር ኳስ መጽሄት በእየ ዓመቱ ለምርጥ የዓለማችን እግር ኳስ ተጨዋቾች የሚሸልመው የወርቅ ኳስ ማለትም ባሎን ዶእር ሽልማት ስነስርዓት ማምሻውን ይከናወናል። የሽልማት አሰጣጥ ስነስርዓቱ የሚካኼደው ፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ ውስጥ ከሰአታት በኋላ ነው።

 

በእጩነት ከቀረቡት የዓለማችን ምርጥ ተጨዋቾች መካከል የጀርመኑ ባየርን ሙይንሽን ቡድን አጥቂ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ይገኝበታል። ፖላንዳዊው አጥቂ በአንድ የጨዋታ ዘመን ለባየርን ሙይንሽን 41 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ የግብ ቀበኛነቱን ያስመሰከረ ተጨዋች ነው። በዚህም በቡንደስሊጋው በአንድ ዘመን በርካታ ግቦችን በማስቆጠር ክብረወሰን ማስመዝገብ ችሏል። የጀርመን የቀድሞ ምርጥ ተጨዋች ዝነኛው እና አንጋፋው ቤከን ባወር፦ የወርቅ ዋንጫው የሚገባው ለሮቤትር ሌቫንዶቭስኪ ነው ብሏል። ሌላኛው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን የረዥም ዘመን ግብ ጠባቂ ኦሊቨር ካን የወርቅ ዋንጫውን ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ የማይወስደው ከኾነ፦ «እጅግ የሚያበሳጭ» ነው ሲል ለማን እንደሚገባ አስረግጧል።

የባየር ሙይንሽኑ አጥቂ ጀርመናዊው ቶማስ ሙይለር በበኩሉ፦ «ሌቪ» በሚል ቁልምጫ የሚጠራው የቡድን አጋሩ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ የወርቅ ዋንጫውን መውሰድ እንዳለበት ተናግሯል። «ሌቪ ያቺን ነገር ማንሳት ይገባዋል፤ አከተመ!» ሲልም ዛሬ ማታ የሚሰጠው ሽልማት ለማን እንደሚገባ አስረግጧል። 

ሽልማቱ በሚሰጥበት ከተማ የምትገኘው ወኪላችን ሃይማኖት ጥሩነህ፦ ፈረንሳውያኑ የወርቅ ኳሱ ለማን ይገባል እያሉ እንደሆን ለማወቅ በስፖርት አፍቃሪው ኅብረተሰብ ዘንድ እና በመገናኛ አውታሮች አካባቢ ቅኝት አድርጋለች። ሃይማኖት፦ ፈረንሳውያንም እንደ ጀርመኖቹ የወርቅ ኳሱ ለሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ይገባዋል እያሉ ነው፤ ወይንስ የሀገራቸውን እግር ኳስ ስላደመቀላቸው አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ አድልተዋል?  በእርግጥ እነ ኬሊየን እምባፔ፣ ካሪም ቤንዜማንም የመሳሰሉ የሀገራቸው ድንቅ ተጨዋቾችም አሉ። ፈረንሳውያን በእርግጥ የወርቅ ኳሱን ማን ይወስዳል አሉ?

የወርቅ ኳስ ሽልማቱ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2008 አንስቶ ለቀጣይ ዐሥር ዓመት ከአንድ አጋጣሚ በስተቀር ለየት ባለ መልኩ ወይ ለክርስቲያኖ ሮናልዶ አለያም ለሊዮኔል ሜሲ ነበር የሚሰጠው። በእርግጥ ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት የክሮሺያው አማካይ ተጨዋች ሉካ ሞድሪች የወርቅ ኳሱን ማለትም ባሎን ዶእር ሽልማቱን ወስዷል። ባለፉት ዓመታት ግን የኮሮና ተሐዋሲ ስርጭት በመስፋፋቱ ሽልማቱ ሳይካኼድ ቀርቷል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ
 

Audios and videos on the topic