ኃይል የተቀላቀለበት ጽንፈኝነት | ባህል | DW | 27.05.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

ኃይል የተቀላቀለበት ጽንፈኝነት

ኢትዮጵያዊዉ ወጣት አሚር ዓማን፦ ኃይል የተቀላቀለበት ጽንፈኝነትን መልሶ ማጥቃት በሚል የተጀመረው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘመቻ አካል ነው። ኖርዌይ ውስጥ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ከሆኑት ሦስት ጓደኞቹ ጋር በመሆን ስለተሳተፉበት የድረ-ገጽ ዘመቻ አስተያየቱን ያካፍለናል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:03
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:03 ደቂቃ

ወጣት አሚር ዓማን

አሚር ዓማን ይባላል። የ24 ዓመት ወጣት ነው። ካለፈው አንድ ዓመት አንስቶ ነዋሪነቱን ሰሜን አውሮጳ ኖርዌይ አድርጓል። NLA የሚባል ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በድኅረ-ምረቃ ክፍል የከፍተኛ ትምህርቱን በመከታተል ላይ ይገኛል። የሚያጠናው ዓለም አቀፍ ጋዜጠኝነትን ነው። በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በተለይ ፌስቡክ ላይ ተሳትፎው የነቃ ነው። ያም ብቻ አይደለም በቅርቡ የአሜሪካን ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃይል የተቀላቀለበት ጽንፈኝነትን(Violent extremism) መልሶ ማጥቃት በሚል የጀመረው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ዘመቻ ላይም ተሳታፊ ነው።

የእንግሊዝኛው ሚሪያም ዌብስተር መዝገበ-ቃላት ጽንፈኝነትን ሲተነትን፦ «ብዙኃኑ ትክክል፣ አለያም ምክንያታዊ ብሎ ከሚጠቅሰው ሀሳብ እጅግ ጽንፍ የደረሰ አስተሳሰብን ማመን እና መደገፍ» ይለዋል። አሚር በበኩሉ ጽንፈኝነትን እንዲህ ያብራራል።

አሚር በዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የሚደገፈው ዘመቻ ውስጥ የተሳተፈው ከሌሎች ሦስት ኢትዮጵያውያን የዩኒቨርሲቲ ጓደኞቹ ጋር በመሆን ነው። ከ50 በላይ የተለያዩ ዩኚቨርሲቲዎች የዘመቻ ዕቅዳቸውን ባስገቡበት ውድድር በመሳተፍም የእነአሚር ቡድን ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ሊመረጥ ችሏል።

ከወጣት አሚር ጋር አንድ ቡድን የመሠረቱት ኢትዮጵያውያኑ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወጣት ተድላ የኔአካል፣ ምንይችል መሰረት እና ክብሮም ብርሃነ ናቸው። በተሰጣቸው ሁለት ሺህ ዶላርም ኃይል የተቀላቀለበት ጽንፈኝነትን መመከት የተባለውን ዘመቻ ከሚማሩበት ዩኒቨርሲቲ ጀመሩ።ታዳሚያኑ ጋር ለመድረስም በፌስቡክ ገጻቸው ባወጡት የጽሑፍ ውድድር 45 ተማሪዎች ጽሑፋቸውን ልከውላቸዋል። የ34ቱ ጽሑፎች መስፈርቶችን በማሟላታቸው ለውድድሩ ቀርበዋል። ከእነዚህም መካከል አንደኛ ለወጣ የ6000 ብር፣ ለሁለተኛ 4000 ብር እንዲሁም ለሦስተኛ 2000 ብር ሽልማት ማዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

ፈጠራ የታከለባቸው አጠር ያሉ አራት የቪዲዮ መልእክቶችንም የዘመቻው አካል ማድረጋቸውን አሚር ዓማን ገልጧል። በእርግጥም በፌስ ቡክ ገፃቸው ላይ እንደሰፈረው ከሆነ «ሃይማኖታዊ ክርክሮች ወደ ግጭት ያመራሉ» በሚል የቀረበው አጠር ያለ የአማርኛ የቪዲዮ መልእክት ብቻ በአንድ ወር ውስጥ ከ44 ሺህ በላይ ተመልካቾችን አግኝቷል።

በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ባደረጉት ጥናት መሠረት አሚር እና ጓደኞቹ ሦስት አበይት ነጥቦች ላይ ደርሰዋል። አንደኛ መጠይቁን የሞሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አብዛኛዎቹ «በማኅበራዊ የመገናኛ ዘርፎች ኃይል የተቀላቀለበት ጽንፈኝነት ፕሮፖጋንዳን መልሶ የሚታገል ትርክት ሊፈጠር ይገባል» ብለዋል።

ይኽን መሰል ጽንፈኝነትን ለመታገልም ኃላፊነቱ የግለሰቦችም የቡድናትም መሆን ይገባዋል ሲሉ አክለዋል። በሦስተኛ ደረጃ የመጠይቁ ተሳታፊዎች በማኅበራዊ የመገናኛ ዘርፎች የጽንፈኝነት ርዕዮተ-ዓለም ስርጸት በተለይ በፌስቡክ ተጽዕኖው እጅግ እንዳሳሰባቸው ጠቅሰዋል።

አነ ወጣት አሚር ዓማን የጀመሩትን ጥናት ወደ ፊት ሰፋ አድርገው ለመሥራት በማቀድ ኖርዌይ ውስጥ ከሚኖሩበት የክስርስቲያንሳንድ ከተማ ከንቲባ ጋር ተነጋግረዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic