ቼልሢይ የአውሮፓ ቁንጮ | ስፖርት | DW | 21.05.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ቼልሢይ የአውሮፓ ቁንጮ

ከእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቀደምት ክለቦች አንዱ የሆነው ኤፍ ሲ ቼልሢይ ሚዩኒክ ላይ የአውሮፓን ሻምፒዮና ሊጋ ዋንጫ በመውሰድ ከአትላንቲክ ባሻገር በአሜሪካ ጉባዔ ተቀምጠው የነበሩትን የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮንን ሳይቀር እንደ ልጅ አስፈንድቋል።

እንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቀደምት ክለቦች አንዱ የሆነው ኤፍ ሲ ቼልሢይ ሚዩኒክ ላይ የአውሮፓን ሻምፒዮና ሊጋ ዋንጫ በመውሰድ ከአትላንቲክ ባሻገር በአሜሪካ ጉባዔ ተቀምጠው የነበሩትን የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮንን ሳይቀር እንደ ልጅ አስፈንድቋል። ካሜሮን በቡድን-ስምንት ጉባዔ ዕረፍት ላይ ፍጹም ቅጣት ምቱን ከጀርመኗ ቻንስለር ጋር ሆነው በቴሌቪዥን ሲመለከቱ ከደስታ ብዛት ከአንጌላ ሜርክል ላይ እስከመጠምጠም ነበር የደረሱት።

ቼልሢይ የዘንድሮውን የእንግሊዝ ውድድር ደከም ብሎ ሲያሳልፍ በአውሮፓው ሻምፒዮና ሊጋ ግን በግማሽ ፍጻሜው ታላቁን ኤፍ ሲ ባርሤሎናን ማስወጣቱና ባለፈው ቅዳሜ ምሽት ፍጻሜ ደግሞ ባየርን ሙንሺንን በገዛ ሜዳው ድል መንሳቱ ብዙ የተጠበቀ አልነበረም። ሆኖም ቡድኑ መለያው በሆነው የመከላከል ስልቱ የአውሮፓ ግንባር-ቀደም ክለቦች ቁንጮ ለመሆን በቅቷል። ለጀርመኑ ቀደምት ክለብ ለባየርን ሙንሺን በአንጻሩ ከ 2001 ወዲህ በጋዛ ተመልካቾቹ ፊት ሻምፒዮን ለመሆን የነበረው ሕልም ቅዠት ሆኖ ቀርቷል።

ቡድኑ በአጠቃላዩ የጨዋታ ሂደት አየል ያለ መስሎ ቢታይም በተለይ የቼልሢይን በረኛ ፒተር ቼሽን ማንበርከኩ በጣሙን ከብዶት ነው የታየው። የባየርን መሪር ሽንፈት በቅርቡ ለሚጀምረው የአውሮፓ ዋንጫ ውድድር በመዘጋጀት ላይ በሚገኘው በጀርመን ብሄራዊ ቡድን ተልዕኮ ላይም ተጽዕኖ እናዳይኖረው ጥቂትም ቢሆን ማስጋቱ አልቀረም። ሆኖም በሌላ በኩል አሰልጣኙ ዮአኺም ሉቭ የሚያምነው ሽንፈቱ ከጥቂት ቀናት በኋላ እንደሚረሣ ነው።

«ሁኔታው በእግር ኳስ ጨዋታ አንዳንዴ ምን ሊያጋጥም እንደሚችል የሚያሳይ ነው። ጥሩ ተጫውቶ ከሜዳ ተሸንፎ መውጣት አለ። ይሄ ደግሞ በጣም አሳዛኝ ነገር ነው። ባየርኖች በመሠረቱ ጥሩ ጨዋታ ነው ያሳዩት። እርግጥ በፍጹም ቅጣቱ አፈጻጸም ላይ የመንፈስ ጥንካሬ አልነበራቸውም። ይህም ለሚዩኒክ፣ በአጠቃላይ ለጀርመንና እዚህ ላሉት እግር ካስ አፍቃሪዎች ሁሉ የሚያስቆጭ ነገር ነው»

ወደ ጨዋታው አካሄድ መለስ እንበልና በ 62,500 ተመልካቾች ፊት በተካሄደው ግጥሚያ ቶማስ ሙለር በ83ኛው ደቂቃ ላይ ለባየርን የመጀመሪያዋን ጎል ያስቆጥራል። ታዲያ ጨዋታው ሊያበቃ ሰባት ደቂቃዎች ብቻ ሲቀሩ 1-0 የመሩት የባየርን ተጫዋቾችም ሆኑ ደጋፊዎቻቸው ቼልሢይ እንደገና ይነሳል ብለው ጨርሰው አልጠበቁም። ግን የአይቮሪ ኮስቱ ኮከብ ዲዲዬር ድሮግባ በ 88ኛዋ ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት ያገኛትን ኳስ በአናቱ ገጭቶ ጎል በማስቆጠር 1-1 ሲያደርግ ጨዋታው ወዲያው መደበኛ ጊዜው አብቅቶ ይራዘማል።

አሁንም ለጎል የመጀመሪያውን ዕድል ያገኘው ፍጹም ቅጣት ምት የተሰጠው ባየርን ሙንሺን ነበር። ሆኖም ሆላንዳዊው አጥቂ አርየን ሮበን በ 93ኛዋ ደቂቃ ላይ የመታትን ኳስ የቼልሢይ በረኛ ቼሽ እንቅ አድርጎ በመያዝ ያከሽፋል። ከዚህ በኋላ ባየርን ሲያጠቃና ቼልሢይም ሲከላከል 120 ደቂቃው አብቅቶ ፍጹም ቅጣት ምት ይከተላል። ቼልሢይ በዚሁ በአጠቃላይ ውጤት 5-4 ሲያሸንፍ በተለይም ወሣኟን የመጨረሻ ፍጹም ቅጣት ምት ድሮግባ እንዳስቆጠረ የሚዩኒኩ ስታዲዮም በሃዘን ጸጥ ነበር ያለው። የቼልሢይ አሰልጣኝ ዴ-ማቴዎ ለጋዜጠኞች እንዳስረዳው ባየርን በመሠረቱ የበለጠ የጨዋታ ድርሻ ነው የነበረው።

«ባየርኖች ዛሬ ጥሩ ነበር የተጫወቱት። ምናልባትም ከኛ የበለጠ ዕድል ነበራቸው ለማለት ይቻላል። ሆኖም በመጨረሻ ወደ ፍጹም ቅጣት ምት ሲኬድ ግን ጥቂት ዕድል ያስፈልጋል። ነገሩ እንግዲህ የሎተሪን ያህል ነው። እናም በዛሬው ምሽት እኛ ከኤፍ ሲ ባየርን ይልቅ ዕድለኞች ነበርን»

የኤፍ ሲ ቼልሢይ ከፍተኛ ድል ለክለቡ ገንዘብ የሚያቀርበውን የሩሢያ ቢሊየነር ሮማን አብራሞቪችን እጅግ ለማስደሰቱም አንድና ሁለት የለውም። አብራሞቪች ክለቡን ለማጠናከር ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ነው ያፈሰሰው።

Flash-Galerie Haile Gebrselassie

አትሌቲክስ

በትናንትናው ዕለት እንግሊዝ ውስጥ ተካሂዶ በነበረው በታላቁ የማንቼስተር ሩጫ ሃይሌ ገ/ሥላሴ በአሥር ኪሎሜትር ውድድር በማሸነፍ የዓመቱን ፈጣን ጊዜ አስመዝግቧል። በዚሁ ሩጫ ጸጋዬ ከበደ ሁለተኛና አየለ አብሽሮም ሶሥተኛ ሲወጣ የኡጋንዳው ስቴፈን ኪፕሮቲች አራተኛ፤ እንዲሆን የኬንያው ፓትሪክ ማካዉ አምሥተኛ ሆነዋል። ለሃይሌ ገ/ሥላሴ ድሉ በማንቼስተር አምሥተኛው መሆኑ ነው። ሃይሌ በፊታችን ዕሑድ ደግሞ በኔዘርላንድ-ሄንገሎ በዚሁ ርቀት ይወዳደራል።

ይሄው ሩጫ በመጨው የለንደን ኦሎምፒክ በአሥር ሺህ ሜትር ከሚሳተፉት ሶሥት የኢትዮጵያ አትሌቶች መካከል አንዱ ለመሆን ፉክክር የሚደረግበትም ነው። ታላቁ አትሌት ሃይሌ በመጪው የለንደን ኦሎምፒክ ማራቶን የመሮጥ ዕድሉን ቀደም ሲል ማጣቱ ይታወቃል። በማንቼስተሩ የሴቶች ሩጫ የቀድሞይቱ የአሥር ሺህ ሜትር የዓለም ሻምፒዮን ኬንያዊቱ ሊኔት ማሣይ ስታሸንፍ ኢጣሊያዊቱ ናዲያ ኤጃፊኒ ሁለተኛ ወጥታለች። ሩጫውን በሶሥተኝነት የፈጸመችው ኬናያዊቱ ዶሪስ ቻንጌይዎ ነበረች።

ስንበቱን ሻንግሃይ ላይ ተካሂዶ በነበረው የአትሌቲክስ ዳያመንድ ሊግ ውድድርም የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች ጠንካራ ፉክክር በታየበት የአምሥት ሺህ ሜትር ሩጫ ሃጎስ ገ/ሕይወት ሶሥት ኬናያውያንን ከኋላው በማስከተል አሸናፊ ሆኗል። ከተቀሩት የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች መካከል ቀነኒሣ በቀለ አምሥተኛ ሲሆን የኔው አላምረውም ስድሥተኛ ወጥቷል። በሴቶች 1,500 ሜትር ደግሞ የኢትዮጵያ አትሌቶች ድርብ ድል ሲያስመዘግቡ ገንዘቤ ዲባባ አንደኛ ሆናለች። አበባ አረጋዊ ሩጫውን በሁለተኝነት ስትፈጽም ሶሥተኛ የወጣችው የሞሮኮዋ ተወዳዳሪ ኢብቲሣም ላኩዋድ ነበረች።

ኬንያውያት ከአንድ እስከ ስድሥት በተከታተሉበት በሶሥት ሺህ ሜትር መሰናክል ሩጫ ሚልካህ ቼሞስ ስታሸንፍ ሶፊያ አሰፋ ሁለተኛ ለመሆን በቅታለች። የአጭር ርቀት ሩጫውና ዝላዩ እንደተለመደው የአሜሪካና የጃሜይካ ልዕልና የሰመረበት ሆኖ አልፏል። በተረፈ በቅርቡ የኢስታምቡል የአዳራሽ ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የ 800 ሜትር አሸናፊ በመሆን ለኢትዮጵያ አዲስ ታሪክ ያስመዘገበው ሞሐመድ አማን ባለፈው ሣምንት አጋማሽ በደቡብ ኮሪያ የዴጉ ዓለምአቀፍ ውድድር በዚሁ ርቀት አሸናፊ ሆኖ ነበር። በሴቶች 1,500 ሜትርም እንዲሁ መስከረም አሰፋ ሁለተኛ ወጥታለች።

ቴኒስ

ሩሢያዊቱ ማሪያ ሻራፖቫ ትናንት በሮም ማስተርስ ፍጻሜ በማሸነፍ በስፋራው በተከታታይ ለሁለተኛ የወድድር ድሏ በቅታለች። በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ በሁለተኛ ቦታ የምትገኘው ማሪያ ሻራፖቫ ለዚህ ድል የበቃችው የቻይና ተጋጣሚዋን ሊ ናን 4-6,6-4,7-6 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ነው። ግጥሚያው በዝናብ ምክንያት ለሁለት ሰዓታት ያህል ተቋርጦ ነበር። የሴቶቹ ጨዋታ እንደምንም ሲፈጸም ባለፈው ዓመት የሮም ሻምፒዮን በኖቫክ ጆኮቪችና በራፋኤል ናዳል መካከል ሊካሄድ የታቀደው የወንዶች ፍጻሜ ግጥሚያ ግን በዝናቡ ሳቢያ ወደ ዛሬ መሸጋሸጉ ግድ ነበር የሆነበት።

ግጥሚያው ዛሬ ከቀትር በኋላ ሲካሄድ ናዳል በሁለት ምድብ ጨዋታ 7-5,6-3 አሸናፊ ሆኗል። የስፓኙ ኮከብ የሮምን ማስተርስ ለስድሥተኛ ጊዜ ለማሸነፍ የፈጀበት ጊዜ ሁለት ሰዓት ከሃያ ደቂቃ ነበር። ናዳል በሞንቴካርሎ ስምንቴና በባርሤሎናም ሰባቴ አሸናፊ ሲሆን በዘንድሮው የውድድር ወቅት መልሶ እያየለ በመሄድ ላይ ነው። የዛሬው ድሉ በቀጣዩ የፈረንሣይ-ኦፕን ለድል የመብቃት ከፍተኛ ግምት እንዲሰጠው አድርጎታል።

Bdt Radfahrer während der vierten Etappe der Giro Italien Rundfahrt

የቢስክሌት እሽቅድድም

በካሊፎርኒያ-ቱር የቢስክሌት እሽቅድድም ከስምንት ወራት በፊት የእግር ስብራት ደርሶበት የነበረው የኔዘርላንዱ ሮበርት ጌዚንክ ትናንት ስምንተኛውን ደረጃ በቀደምትነት በመፈጸም አሸናፊ ሆኗል። ጌዚንክ በአጠቃላይ ነጥብ የውድድሩ አሸናፊ ሲሆን ሁለተኛ የወጣው አሜሪካዊው ዴቪድ ዛብሪስኪ ነው። በጂሮ-ዴ-ኢታሊያ ደግሞ የኢጣሊያው ማቴዎ ራቦቲኒ ትናንት በ 150 ኪሎሜትር የተራራ እሽቅድድም በማሸነፍ ለመጀመሪያ የጂሮ ድሉ በቅቷል። የ 24 ዓመቱ ኢጣሊያዊ ያሸነፈው የስፓኙን ተወዳዳሪ ጆአኪም ሮድሪጌስን በፍጥነት በማምለጥ ነው። ሆኖም በአጠቃላይ ነጥብ ሮድሪጌስ በአንደኝነት መምራቱን ይቀጥላል።

በእግር ኳስ ለማጠቃለል በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን በውድድሩ መጀመሪያ ይህን ያህል ያይላል ብሎ ማንም ያላሰበው ክለብ ሞንትፔሊየር በመጨረሻው ቀን ለሻምፒዮንነት በቅቷል። ክለቡ ለመጀመሪያ ድሉ የበቃው ኦግዜርን 2-1 በመርታት ነው። የኦግዜር ደጋፊዎች ጨዋታውን ከአንዴም ሶሥቴ በዓመጽ ለማቋረጥ ሲሞክሩ ፖሊስ እስከመጥራት ተደርሶ ነበር። በነገራችን ላይ ኦግዜር የሊጋው መጨረሻ በመሆን ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን ተከልሷል።

SSC Neapel vs. Bayern München Flash-Galerie

የሤሪያ-አ ሻምፒዮና ቀደም በሎ በለየባት በኢጣሊያ ደግሞ የትናንቱ ሰንበት የብሄራዊው ዋንጫ ፍጻሜ የተካሄደበት ነበር። በዚሁ ፍጻሜ ግጥሚያ ናፖሊና ጁቬንቱስ ቱሪን ሲገናኙ ናፖሊ ዲየጎ ማራዶና የክለቡ ከከብ ከነበረበት ዘመን ወዲህ ለመጀመሪያ ታላቅ ድሉ በቅቷል። ናፖሊ በለየለት ሁኔታ አሸንፎ ዋንጫውን ሲወስድ ጁቬንቱስ ከዘንድሮው የሤሪያ-አ ሻምፒዮንነት ጋር ብሄራዊውን ዋንጫ ለመደረብ የነበረው ሕልም ዕውን አልሆነለትም።

በአውስትሪያ በአንጻሩ ዛልስቡርግ ሁለቱንም ዋንጫዎች መጠቅለሉ ተሳክቶለታል። የፖርቱጋል ብሄራዊ ዋንጫ ደግሞ ባልተጠበቀ ሁኔታ ከአካዴኪካ ዕጅ ወድቃለች። ዝቅተኛው ክለብ ትናንት በፍጻሜው ግጥሚያ ስፖርቲንግ ሊዝበንን 1-0 በመርታት ሲያሸማቅቅ ዋንጫውን ሲያገኝም ከ 74 ዓመታት ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ላይ እናተኩርና ከአንደኛው ዲቪዚዮን ወደታች ላለመውረድና ከሁለተኛው ወደ አንደኛው ከፍ ለማለት በሄርታ በርሊንና በዱስልዶርፍ መካከል የተካሄደው የመልስ ግጥሚያ ተመልካቾች ሜዳ በመግባታቸው መታወኩን አስመልክቶ የበርሊኑ ክለብ ጨዋታው እንዲደገም ያቀረበው ክስ ፍራንክፉርት ወሰጥ በሚገኘው የጀርመን እግር ኳስ ፌደሬሺን ፍርድቤት ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። ፍርድቤቱ ክሱን መሠረተ-ቢስ ሲል ብያኔውን ያስተላለፈው በዛሬው ዕለት ነው። በውቅቱ ውሣኔ መሠረት በርሊን ወደታች ሲከለስ ዱስልዶርፍ ደግሞ ወደላይ ወጪ ነው። እርግጥ ሄርታ ይግባኝ የማለት ዕድል አለው።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 21.05.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14zY2
 • ቀን 21.05.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14zY2