ቻይና፤ የኑሮ ውድነትና የማሕበራዊ ነውጽ አደጋ | ኤኮኖሚ | DW | 19.09.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ቻይና፤ የኑሮ ውድነትና የማሕበራዊ ነውጽ አደጋ

ቻይና ውስጥ በየአምሥት ዓመቱ የሚካሄደው፤ የአገሪቱ ኮሙኒስት ፓርቲ መደበኛ ጉባዔ በፊታችን ጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ ይከፈታል። ይህ የአገሪቱ የዕድገት መርህ የሚቀረጽበት ዓቢይ ጉባዔ የሚካሄደው በቻይና በተለይም የምግብ ዋጋ ከመጠን በላይ መናር በቀጠለበት ወቅት ነው።

default

እየተጠናከረ የመጣው የኑሮ ውድነት ማሕበራዊ ነውጽን እንዳያስከትል የቻይና መሪዎች ብርቱ ስጋት ላይ መውደቃቸው አልቀረም። የቻይና መንግሥት የዕህል አቅርቦቱን በመጨመር ከመጠን በላይ እየናረ በመሄድ ላይ የሚገኘውን የምግብ ዋጋ ለመገደብ የሚያደረገው ጥረት በወቅቱ ባለሥልጣናት እንደሚሉት በአካባቢ አየር ለውጥ ሳቢያ ሊሰምርለት አልቻለም። የዚህ ዓመቱም አዝመራ ብርቱ የማቆልቆል አደጋ ተደቅኖበት ነው የሚገኘው። የአካባቢ አየር ለውጥ ለቻይና የእርሻ አመራረት ችግርና እጥረት ብቸኛው ምክንያት ነው ሊባል ባይቻልም ዓቢይ ድርሻ እንዳለው ግን አንድና ሁለት የለውም።

የሕዝባዊት ቻይና የእርሻ መሬት እየመነመነ ነው የመጣው። በጉዳዩ የቀረበ ይፋ መረጃ እንደሚጠቁመው በዚህ ዓመት ብቻ በድርቅ የተመታው የሚታረስ መሬት ከ 11 ሚሊዮን ሄክታር በልጧል። ለቻይና ብሄራዊ ሸንጎ፤ ማለት ለአገሪቱ ም/ቤት የቀረበው ይሄው ዘገባ እንደሚያመለክተው ይህም ካለፈው ዓመት ሲነጻጸር በአማካይ በ 2.5 ሚሊዮን የላቀ መሆኑ ነው። እርግጥ በዓለም ላይ አንድ-አምሥተኛው፤ ማለት 1.3 ሚሊያርድ ሕዝብ ያላት ቻይና በዓለምአቀፍ ደረጃ ከሚታረሰው መሬት ሰባት ከመቶውን የምትጠቀም ሲሆን የምርት ዕጥረት ለነገሩ ያልተለመደ ነገር አይደለም።

የሚታረሰው መሬት እያመነመነ ነው የመጣው

ቻይና ባለፉት ዓመታት በምርት ረገድ በተከታታይ የደረሰባትን እጥረት እንደሆነው ሆኖ ስትወጣው ቆይታለች። አሁን በ 17ኛው የአገሪቱ ኮሙኒስት ፓርቲ ጉባዔ ዋዜማ ግን የአካባቢው አየር ለውጥ የደቀነው ችግር ከዋጋ መናር ወይም ከኑሮ ውድነት ማደግ ጋር ተጣምሮ ተጽዕኖው ከባድ እየሆነ ነው። ለአዲስ ማሕበራዊ ነውጽ ምክንያት እንይሆን የአገሪቱን መሪዎች ክፉኛ ማሳሰቡ አልቀረም። በዕውነትም ይህ ከወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ አይደርስም ሊባል አይቻልም። ዛሬ ከቻይና 31 ክፍለ-ሐገራት 22ቱ በድርቅ የተጠቁ መሆናቸው የችግሩን ክብደት አጉልቶ የሚያሣይ ጭብጥ ሃቅ ነው። የወደፊቱም ሁኔታ እምብዛም ተሥፋ ሰጭ ሆኖ አይገኝም።

የአገሪቱ የአየር ጠባይ ተመራማሪዎች የቀጠለው የአካባቢ አየር ለውጥ የባሰ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ነው የሚያስገነዝቡት። የአካባቢ አየር ሙቀት በአንዲት ዲግሪ መጨመር የምድርን ውሃ ትነት ሰባት በመቶ ከፍ ሊያደርግ እንደሚችል ነው የሚነገረው። የቻይና የአየር ጠባይ መርማሪ ተቋም ሃላፊ ሼንግ ጉዎጋን የሚተነብዩት የአካባቢው አየር ሞቃታ የአገሪቱን አዝመራ እስከ አሥር በመቶ እንደሚቀንሰው ነው። ይህም በወቅቱ ጥበት ደረጃ የዕህል አቅርቦቱን በ 50 ሚሊዮን ቶን ዝቅ የሚያደርግ ሲሆን የዋጋ ንረትን ይበልጥ የሚያሳድግ ይሆናል።

የማሕበራዊው ቁጣ መፈንዳት አሳሳቢነት

የአገር ውስጡ የዕህል ምርት ማቆልቆል በዓለምአቀፍ ገበዮች ላይ ያለው የምግብ አቅርቦት ጥበት ታክሎበት ለበለጠ የዋጋ መናር ምክንያት ነው የሚሆነው። በቻይና የምግብ ዋጋ ማናር የተጠቃሚውን ወጪ መንግሥት ካሰበው 3 በመቶ በላይ በ 5.6 ከመቶ እንዲያድግ ሲያደርግ ይህም ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ከፍተኛው መሆኑ ነው። ይህ ያለፈው ሐምሌ ወር ግምት ሲሆን የኤኮኖሚ ጠበብት አሃዙ በተከታዩ ነሐሴ ወር በተለይም በአሣማ ሥጋ መወደድ ሳቢያ ይብስ መናሩን ነው የሚናገሩት።

የዋጋ መናር በአገሪቱ ሊያስከትል የሚችለው ማሕበራዊ ቁጣ ብርቱ መዘዝ ሊኖረው እንደሚችል መንግሥት አላጣውም። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎች፣ ሠርቶ አደሮችና ምሁራን ቲየን-አን-ሜን አደባባይን ያጥለቀለቁበትን የኋላ ኋላ በሃይል የተቀጨውን የ 1989 ዓ.ም. መፍቀረ-ዴሞክራሲ ተቃውሞ የቀሰቀስውም የኑሮ መወደድ በሕዝብ ዘንድ የፈጠረው ቁጣ እንጂ ሌላ አልነበረም። በኮሙኒስቱ ፓርቲ ጉባዔ ዋዜማ በወቅቱ በአገሪቱ ባለሥልጣናት አዕምሮ ውስጥ የሚንሸራሸረውም ይሄው እንደገና ዕውን መሆኑን የሚፈሩት ዓመጽ ትውስት ነው።

የዓለም ገበያ የምግብ ዋጋ ተጽዕኖ

ሕዝባዊት ቻይና ባለፉት ጊዜያት የዋጋ መናርን ከውጭ ምርቶችን በማስገባት ስትቋቋም ቆይታለች። ግን ይህ የአሠራር ዘይቤ ዛሬ በውጭ ገበዮች ላይ ካለው የዕህል ዋጋ ንረት የተነሣ የሚያዋጣ ነገር አልሆነም። ቤይጂንግ በሌላ በኩል የዋጋ መናርን ለማረጋጋት የማዕከላዊ ባንኳን ወለድ በዚህ በያዝነው ዓመት ብቻ አራት ጊዜ ከፍ ማድረጉን ነው የመረጠችው። የአገሪቱ መሪዎች ባለፉት ጥቂት ወራትም የእርሻ ምርት ከፍ እንዲልና የዋጋ መናር እንዲገታ በከፍተኛ ደረጃ ቅስቀሣ ሲያደርጉ ቆይተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዌን ጂያባዎ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት እንደሚጥር ለሕዝብ ለማሣየት በዓመቱ መጀመሪያ ላይ የአገሪቱን የአሣማ ማርቢያዎችና የእርሻ ምርት ገበዮች እየተዘዋወሩ ጎብኝተው ነበር።
ዌን ያልተቋረጠ የዋጋ መናር በአገሪቱ ማሕበራዊ ዕርጋታ ላይ አደጋ ሊፈጥር እንደሚችል ሳያስጠነቅቁም አላለፉም። ችግሩን በመቋቋሙ ረገድ በወቅቱ የሚታየው ጭብጥ ዕርምጃ መንግሥት ለአሣማ አርቢዎች ድጎማ መስጠቱ ሲሆን ሌላው አዲስ ነገር ድንችን የመሳሰሉ ድርቅን ይበልጥ መቋቋም የሚችሉ ምርቶችን በማሳደጉ አማራጭ ላይ ማቅማማት መጀመሩ ነው። የቤይጂንግ መንግሥት የክፍለ-ሐገራት መስተዳድሮች ምግብ አምራቾችን፣ ታላላቅ ነጋዴዎችንና ቸርቻሪዎችን በዋጋ አተማመን ረገድ አጥብቀው እንዲቆጣጠሩ ባለፈው ወር አዞ ነበር። ጥያቄው ይህ ሁሉ ጭብጥ ፍሬ መስጠቱ ላይ ነው።

የመንግሥት ማረጋጊያ ዕርምጃዎች

መንግሥት ዓመጽ እንዳይፈነዳ ባደረበት ስጋት የተነሣ የማይሞክረው ነገር እንደሌለ የአገሪቱ ትምሕርት ሚኒስቴር ዩኒቨርሲቲዎች ለችግረኛ ተማሪዎች ድጎማ እንዲሰጡና የተማሪ ምግብ ቤቶች ዋጋም ተረጋግቶ መቀጠሉን እንዲያረጋግጡ በዚህ ሣምንት ያስተላለፈው ትዕዛዝ በግልጽ የሚያሣይ ነው። መፍቀረ ዴሞክራሲው ንቅናቄ የጀመረው በዩኒቨርሲቲዎች እንደነበር አልተረሣም። የቻይና የቅርብ ታዛቢዎች የአገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር የጂን ሬንኪንግ ባለፈው ሣምንት ከሥልጣን መወገድ ዕውነተኛ ምክንያትም ይሄው አልገታ ያለው የዋጋ መናር እንደነበር ያምናሉ። ጂን በፓርቲው ጉባዔ ዋዜማ ከተወገዱት በርካታ የመንግሥት ባለሥልጣናት መካከል አንዱ ሲሆኑ ከሴቶች ባልገዋል መባላቸው በአገሪቱ ፕሬስ ላይ ብቅ ያለው እንዳጋጣሚ ነበር።

ይሁንና ቤይጂንግ ውስጥ ተቀማጭ የሆኑ የውጭ ዲፕሎማቶች ለሚኒስትሩ መወገድ ዋናው ምክንያት የዋጋው መናር እንደሆነ ጨርሶ አይጠራጠሩም። ያም ሆነ ይህ በፕሬዚደንት ሁ ጂንታዎና በጠቅላይ ሚኒስትር ዌን ጂያባዎ ለሚመራው የቻይና መንግሥት ችግሩን መቋቋሙ ቀደምት የአጀንዳ ርዕስ እንደሆነ ለመለየት አያዳግትም። ሁለቱም መሪዎች በቻይና ያልተጣጣመውን የኤኮኖሚ ዕድገት ማስተካከሉንና የድሃውን ሰፊ ሕብረተሰብ የኑሮ ደረጃ ማሻሻሉን ቀደምት የፖለቲካ ጉዳይ አድርገው ይመለከታሉ። በመጪው የፓርቲ ጉባዔ ላይም ይሄው ጎልቶ እንደሚሰማ የብዙዎች ዕምነት ነው። በሌላ በኩል ቻይና ከያዘችው ፈጣን የኤኮኖሚ ዕርምጃ አንጻር የኑሮ ውድነቱን በቀላሉ ገትቶ መያዝ መቻሉ ብዙ ያጠያይቃል።