ቻይና፤ ስልታዊና የተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት | ኤኮኖሚ | DW | 17.11.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ቻይና፤ ስልታዊና የተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት

በዓለም ላይ በሕዝብ ብዛቷ ቀደምት የሆነችው ቻይና ዛሬ ብልህነትና ቁርጠኝነት በተመላው መንፈስ ተጽዕኖዋን በማስፋፋት ላይ ነው የምትገኘው። ቤይጂንግ በአሁኑ ጊዜ የምዕራቡን ዓለም ገበዮች በምርቶቿ ከማጥለቅለቋ ባሻገር በኢንዶ ቻይና አካባቢ የያዘችው የሃያል መንግሥትነት የኤኮኖሚ ሚናም በደቡብ-ምሥራቅ እሢያ አሜሪካን፣ አውሮፓንና ጃፓንንም ሣይቀር ቀስ በቀስ መሠረት እያሳጣ ነው። አቅጣጫና ግቧም ይሄው ከበለጸጉት ቀደምት መንግሥታት የመስተካከል የምጣኔ-ሐብት ልዕልናን ማረጋገጥ መሆኑ ይታወቃል።

ሕዝባዊት ቻይና ዛሬ በያዘችው የተፋጠነ የምጣኔ-ሐብት ዕርምጃ ባለፉት ጊዜያት የሰባትና ሥምንት በመቶ ዓመታዊ ዕድገት ስታደርግ ነው የቆየችው። የኤኮኖሚ ዕድገታቸው በአንድና ቢበዛ ሁለት በመቶ እንኳ በማይሞላ ተጎታች ዝግመት ላይ የሚገኘው ምዕራባውያን በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ መንግሥታት የቻይናን ዕርምጃ ሊከተኩት ቀርቶ ሊያልሙት እንኳ የሚችሉ ሆነው አይገኙም።

ለቻይና በምጣኔ-ሐብት ሃያልነት ላይ ላለመ ግብ አንቀሳቃሽ መንኮራኩር ሆኖ የሚገኘው አገሪቱ ከማንኛውም የውጭ ተጽዕኖ ለመላቀቅና ብልጽግናን ለማስፈን የምትችለው ከፍተኛ የኤኮኖሚ ዕድገት ደረጃ ላይ ስትደርስ ብቻ መሆኑን ጽኑ ግንዛቤ ማድረጓ ነው። ጃፓን እንደምን ሰለጠነች? ይህ አንዴ የዓለም መነጋገሪያ ተዓምር የነበረውን ያህል ዛሬ የቻይናም ዕርምጃ በዚያው መጠን ማስደነቅ የያዘ ጉዳይ ነው።

ደቡብ-ምሥራቅ እሢያይቱ ግዙፍ አገር ከተኛችበት ተነስታ የምታካሂደው ፈጣን ዕርምጃ ማንም የማያቆመው ራሷም ተመልሳ የማትገታው እየሆነ ሲያስገመግም ነው የሚገኘው። ዛሬ ከደረስንበት ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ሁኔታ አንጻር ለቻይና ዕርምጃ በአገሪቱ ከተሰረጸው ሃያል የመሆን ዕምነትና ፍላጎት ባሻገር ተጨባጭ ምክንያቶች ሆነው የሚገኙት ከበለጸገው ዓለም ሲነጻጸር የሠርቶ-አደሩ ደሞዝ ዝቅተኛ መሆን፣ የአመራረቱ ዋጋ ዝቅተኛነትና የዓለምን ገበያ ያጥለቀለቀው ምርት ርካሽነትም ናቸው።

የተለያዩ የቻይና የኢንዱስትሪ ምርቶች ያልገቡበት አካባቢ በዓለም ላይ ተፈልጎ አይገኝም። በጨቅላ ዕድሜ ላይ የሚገኘው የአውቶሞቢል ኢንዱስትሪዋም ምናልባት እንደ ጃፓን የዓለም ገበዮችን የሚያጨናንቅበት ጊዜ ሩቅ የሚሆን አይመስልም። በነገራችን ላይ የቻይና የውጭ ንግድ ትርፍ ባለፉት ዓመታት አቻ ባልተገኘለት ሁኔታ እየናረ ሲሄድ ነው የታየው። ይህ ደግሞ ብሄራዊውን የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ በማጠናከር ድህነትን በመቀነሱ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።

እርግጥ የኤነርጂና የጥሬው ምርት ፍላጎት እየተፋጠነ ከመጣው ዕርምጃ ጋር ተጣጥሞ ሊራመድ አለመቻሉ ለጊዜውም ቢሆን በኤኮኖሚው የዕድገት ሂደት ላይ ገቺ መሰናክል እንዳይሆን ማስጋቱ አልቀረም። ይሁንና የአገሪቱ ባለሥልጣናት ካለሙለት ዘላቂ ግብ ወደ ኋላ እንዲሉ ጨርሶ የሚገፋፋ አልሆነም። ምርጫው አንድ፤ መንገዱም አንድ ነው። ቻይና በመጪዎቹ ጥቂት አሠርተ-ዓመታት በዓለም ላይ በኤኮኖሚ ዕድገት የበለጸገች ሃያል መንግሥት ለመሆን የያዘችው ጉዞ ላንዳፍታ እንኳ የሚያጠያይቅ አይደለም።

ይህ ለመሆኑ ለምሳሌ አገሪቱ በትዕግሥትና በቁርጠኝነት ውስጥ-ውስጡን የደቡብ-ምሥራቅና ማዕከላዊ እሢያን አካባቢ ኤኮኖሚ ለመቆጣጠር የያዘችው ጥረት አንድ ምሥክር ነው። ሕዝባዊት ቻይና ዛሬ ከኢንዶ-ቻይና እስከ ማዕከላዊው እሢያ የምታራምደው በወዳጅነትና በትብብር መንፈስ ላይ የተመሠረተ ፖሊሲ የአካባቢውን አገሮች ድጋፍ እያገኘ፤ እየተስፋፋ የሚሄድ ጉዳይ ሆኗል።

የኢንዶ-ቻይናው ጦርነት ጥሎት ያለፈው አሻራ ገና ጨርሶ ባይወገድም በላኦስ፣ በካምቦጃ፤ በበርማና በተለይም በቪየትናም ዕድገትና ብልዕግና ቀስ በቀስ ማንሰራራት ይዟል። አብዛኛው ጸጋ ወደአካባቢው የሚዘልቀውም ከበስተሰሜን ከሕዝባዊት ቻይና ነው። በርካታ የቻይና ነጋዴዎች ዛሬ በሜኮንግ ወንዝ ዳርቻ ላይ በምትገኘው የላኦስ ዋና ከተማ ጭምር በአካባቢው ሰፍረዋል። ሕንጻ ተቋራጮቹ፤ ከቴሌቪዥን አንስቶ እስከ ልብስ ማጠቢያ መኪናና እስከ ሞተር ቢስክሌት አቅራቢ-ጠጋኞቹ፤ አውራ-ጉዳና ዘርጊዎቹም ሆኑ ግድብ ሠሪዎቹ ቻይናውያን ናቸው። በቻይና ዕርዳታ የሚቋቋሙት “Joint Venture” የጋርዮሽ ይዞታ ፋብሪካዎችም ጥቂቶች አይደሉም።

የንግዱን ዘርፍ ከተመለከትን የቻይና ምርቶች ረከስ ያሉ መሆናቸው በአካባቢው ሕዝብ ዘንድ ይበልጥ ተወዳጅ ያደርጋቸዋል። ለምሳሌ ያህል በቻይና የሚመረት አንድ ሞተር-ቢስክሌት ወይም ኩርኩር 200 ኤውሮ ገደማ ቢያወጣ ነው። ማነጻጸር ከተፈለገ ተመሳሳይ የጃፓን ምርት እጥፍ ዋጋን ይጠይቃል። ይህ ደግሞ ለአካባቢው ነዋሪ ከአቅም በላይ ነው።

ሕዝባዊት ቻይና ላኦስን፣ ካምቦጃንና ቪየትናም የመሳሰሉትን አገሮች ይህ ነው በማይባል ፍጥነት በኤኮኖሚና በፖለቲካ ግንኙነት ይበልጥ ከራሷ ጋር እያስተሳሰረች በመሄድ ላይ ናት። በተለያዩ የቻይና የወሰን ዳርቾች አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ተከፍቷል ለማለት ይቻላል። ታሪኩ የሚጻፈው ደግም ቤይጂንግ ውስጥ ነው። ቻይና ግቧን በተመለከተ ጠንካራ፤ በመስፋፋት ዘዴዋ ግን ተጨባጭ ሃቅን ያገናዘበች ሆና በደቡብ-ምሥራቅ እሢያ አካባቢ ተጽዕኖዋን በማጠንከር አሜሪካንና ጃፓንን ዋጋ እያሳጣች ስትሄድ ትገኛለች።

አሜሪካ በበኩሏ በእሢያ-ፓሢፊክ አካባቢ ግዙፍ ገበያ ለማስፈን የአካባቢውን መንግሥታት የኤኮኖሚ ሕብረት በአሕጽሮት አፔክን ለመፍጠር ራዕይዋን ላለፉት 16 ዓመታት ስታራምድ ነው የቆየችው። 21 መንግሥታትን የያዘው ይሄው ስብስብ ቻይናና ታይዋን፤ እንዲሁም ካናዳ፣ ቺሌና ሩሢያም የሚገኘት ሲሆን በአብዛኛው ቅራኔ የተጣባው መሆኑ በያጋጣሚው ታይቷል። አፔክን ከራሷ ጥቅም አንጻር አሰባስባ የያዘችው አሜሪካ ናት ሊባል ይችላል። በዚህም እስካሁን የእሢያ አገሮች በገበዮቿ ላይ ያለባቸውን ጥገኝነት መሣሪያ አድርጋ መጠቀሟ አልቀረም።

ሆኖም አሁን ግን ቻይና ይህን የዋሺንግተንን ጥረት ከንቱ እያደረገችው ስትሄድ ነው የሚታየው። ቤይጂንግ ሌላው ቀርቶ አሜሪካን በጃፓንና በደቡብ ኮሪያ ሣይቀር በመፈንቀል ዋነኛዋ የንግድ ሸሪክ ለመሆን በቅታለች። በአካባቢው ታይላንድ ከ 2001 እስከ 2003 ዓ.ም. ለቻይና የሸጠችው ምርት ወደ 87 በመቶ ሲያድግ በዚሁ ጊዜ ቻይና በአንጻሩ ያቀረበችው ምርትና የሰጠችው አገልግሎትም በ 53 በመቶ ከፍ ማለቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህም የእሢያ መንግሥታት ከዋሺንግተን ገሸሽ እያሉ በቻይና ላይ ማተኮር መያዛቸውን የሚያመለክት ነው።

ለነገሩ ምዕራባውያን ባለካፒታሎች የምንዛሪ ውድቀትን ባባባሱበትና ንብረታቸውን ባሸሹበት በእሢያው የ 1997 የኤኮኖሚ ቀውስ ወቅት አካባቢው በምዕራቡ ዓለም፤ በተለይም በአሜሪካ ላይ ጥርሱን ነበር የነከሰው። በጊዜው የማሌይዚያው ጠቅላይ ሚኒስትር ማሃቲር ሞሐመድ ድርጊቱን እድማ ሲሉ ብዙዎች በልባቸው ያሰቡትን ነበር የተናገሩት።

ቻይና በአንጻሩ በእሢያው ቀውስ ወቅት እንደ አሜሪካ ሣይሆን በችግር ሰዓት ፈጥኖ ደራሽ ታላቋ ወንድም አገር በመሆን ታማኝነትና ታቃፊነቷን ልታጠናክር በቅታለች። እሢያ ዛሬ በአጠቃላይ ማንም በማይገታው ፍጥነት እያደገች ሲሆን ሕዝባዊት ቻይናም በአካባቢው የምታልምለትን ግብ፤ የሃያል መንግሥትነቱን ሚና እየጨበጠች ነው የምትታየው። የቻይና የግንቢያ ሠራተኞች በ 2007 ዓ.ም. ተጥናቆ የደቡባዊቱን አባቢ ክፍለ-ሐገር የዩናንን ዋና ከተማ ኩንሚንግን ኢንዶ-ቻይናን አቋርጦ ከታይላንድ ርዕሰ-ከተማ ባንግኮግ የሚያገናኝ ርዝመቱ ሁለት ሺህ ኪሎሜትር የሆነ ፈጣን አውራ ጎዳና ለማነጽ በወቅቱ በአካባቢው አፈር-ድንጋይ እየገለበጡ ነው።

ወጪውን የምትሸፍነው ቤይጂንግ ስትሆን ቻይና ጎረቤቶቿ ላኦስ፣ በርማና ቪየትናም በመንገዶች፣ በባቡር ሃዲዶች፣ በኤሎክትሪክ መረብ ዝርጋታና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አዲስ የኤኮኖሚ ክልል ሆነው እንዲያብቡ ለማድረግ ካላት ሰፊ ውጥን አንዱ ነው። ቤይጂን የአካባቢው አገሮች የብልጽግናው ባለድርሻዎች እንዲሆኑ በማድረግ በአዋሣኝ ክፍለ-ሐገሮቿ ድህነትን ለመቀነስ፣ ለኢንዱስትሪ ምርቶቿም አዳዲስ ገበዮች መፈጠራችውን እንደምትሻ ጠቅላይ ሚኒስትር ዌን ጂያባዎ ብቅርቡ ያስረዱት ነገር ነበር።

እርግጥ የብልጽግና ተካፋይነቱ ማራኪ ቢሆንም የቻይና የተፈጥሮ ሐብት ጥም ጎረቤቶቿን ጥቂትም ቢሆን ማሳሰቡ አልቀረም። ቤይጂንግ ለምሳሌ ከሕንድ ውቂያኖስ በርማን አቋርጦ ቾንግኪንግ ወደተሰኘች ከተማዋ የሚዘልቅ የነዳጅ ዘይት ቧምቧ የመዘርጋት ውጥን እንዳላት ይነገራል። በወቅቱ በርማ ውስጥ አንድ ታላቅ ግድብ የምታንጸው ምናልባት ለዚሁ ማካካሻ ሣይሆን አልቀረም። የቧምቧው ግንቢያ ዓላማ በማላካ የባሕር መንገድ የሚያልፈውን ውድ የሆነና ለወታደራዊ ጥቃት የተጋለጠ የመርከብ ትራንስፖርት መተካት መሆኑ ይታመናል። በተለይ ከአሜሪካ ጋር ያላት ሽኩቻ የኤነርጂ አቅርቦቷን እንድታረጋግጥ ግፊት ያሳደረባት ነው የሚመስለው።


ያም ሆነ ይህ የቻይና የኤኮኖሚ ግፊት በማዕከላዊው እሢያ የቀድሞ ሶቪየት ሬፑብሊኮች ሣይቀር ሥር መስደድ የያዘ ጉዳይ ነው። በዚህም አካባቢ የቻይና ምርቶች በሰፊው ይራገፋሉ። አካባቢው ሰፊ ምርት ተቀባይ፤ መጪው ገበያ መሆኑን ደግሞ የተረዱት ምዕራባውያን የበለጸጉ መንግሥታት ብቻ አይደሉም። ቻይና የምትከተለው ስልታዊ የኤኮኖሚ ፖሊሲ፤ የርካሽ ምርትና የአገልግሎት አቅርቦቷ በአማካይና በረጅም ጊዜ ቀዳሚና ተመራጭ የሚያደርጋት ነው። ቻይና ከየት ወዴት? የኤኮኖሚ ዕርምጃዋ ቀጣይ፤ ግቡም የሚደረሰት መሆኑ ብዙም አያከራክርም። ጥያቄው ቆርጣ የተነሣችለት ብልጽግናና ልዕልና መቼ ዕውን ይሆናል ነው።