ቻይናውያን የፖለቲካ አፈንጋጮች በዩናይትድ ስቴትስ፣ | ዓለም | DW | 04.06.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ቻይናውያን የፖለቲካ አፈንጋጮች በዩናይትድ ስቴትስ፣

በቻይና መዲና በቤይጂንግ የሚገኘው ቲያናንሜን አደባባይ፣ ልክ የዛሬ 20 ዓመት የዘግናኝ ድርጊት ማዕከል፣ እንደነበረ ይታወሳል።

default

እ ጎ አ ሰኔ 4 ቀን 1989(ከ 20 ዓመት በፊት፣ በዛሬዋ ዕለት) የቻይና ጦር ሠራዊት በኅይል እርምጃ የገታው የዴሞክራሲ ንቅናቄ፣

እ ጎ አ ሰኔ 3 ቀን ሌሊቱን ለ ሰኔ 4 አጥቢያ ፣ 1989 ዓ ም፣ የቻይና ጦር ሠራዊት በራሱ ህዝብ ላይ በመዝመት፣ በዴሞክራሲ ንቅናቄ አባላት ላይ ፣ ደም የሚያንጣልል እርምጃ መውሰዱ አይዘናጋም፣ 52 ቀናት የተጠቀሰውን አደባባይ በቁጥጥራቸው ሥር በማድረግ ለዴሞክራሲ በር እንዲከፈት ሲጮኹ የነበሩ ቻይናውያን ጥረት በኅይል እርምጃ ተገታ። ብዙዎች የዴሞክራሲው ንቅናቄ ትጉኅ ተሳታፊዎች፣ አገር ለቀው ተሰደዱ ። አንዳንዶቹ፣ ከ 20 ዓመታት ወዲህም ቢሆን ትግላቸውን እንደቀጠሉ ናቸው። ጊ ሃዎ፣ ያቀረበውን ሐተታ ፣ ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል።

ከ 20 ዓመት በፊት የተፈጸመውን ድርጊት ከሚያስታውሱት አንዱ፣ ዶክተር ያንግ ጂናሊ ፣ እንዲህ ይላሉ።

«ከሰኔ 4 ቀን 1989 ወዲህ፣ ስሜታዊ እንደሆንኩ አገኛለሁ። የያኔውን ድርጊት ፣ ጥቃቅን ነገሮችን እንኳ ሳስታውስ በየጊዜው እንባ ነው የሚቀድመኝ። ይህ፣ ከተቃውሞው ንቅናቄ ወዲህ ያጋጠመ የህመም ምልክት ነው የሚመስለው።»

የያንግ ጂናሊ ህይወት ከቻይና ተማሪዎች እንቅሥቃሴ ጋር የተቆራኘ ነው። ሰኔ 4, 1989 ፣ ጎኅ ከመቅደዱ በፊት ሌሊቱን የህዝብ ነጻ አውጭ ጦር የሚሰኘው፣ የቻይና ጦር ሠራዊት በህዝቡ ላይ እሩምታ ተኩስ ሲከፍት ያኔ የ 26 ዓመት ወጣት ነበሩ። እርሳቸው እንዳሉት ጭፍጨፋ ነበረ የተካሄደው። የዴሞክራሲው እንቅሥቃሴ በኅይል እርምጃ ከተገታ በኋላ፣ ያንግ ጂላኒ ወደ አሜሪካ ተሰደዱ፣ በዚያም 3 ዓመት ቀደም ሲል የጀመሩትን የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን ቀጠሉ፣ በፖለቲካ ሳይንስ ፣ በተለይም በሰብአዊ መብት ረገድ በከፍተኛ ደረጃ ከተመረቁ በኋላ፣ ዶ/ር ጂናሊ በወጣትነታቸው ዴሞክራቲክ ቻይናን ለማየት የነበራቸው ጉጉት ባለመክሰሙ፣ የቻይናን ጉዳይ የሚከታተል ማኅበር አቋቋሙ። የማኅበሩ ዓላማ፣ በህዝባዊት ቻይና ለሰብአዊ መብት መጠበቅ ጥረት ማድረግ ነው። ይሁንና በ1989 ፣ ከአብዛኞቹ የትግል ባልደረቦቻቸው ከነበሩት ጋር ግንኙነቱ ተቋርጦባቸዋል።

«ያኔ በቦታው የተገኙት፣ ድርጊቱ በመንፈሳቸው ሠርጾ የገባ ወጣቶች ነበሩ ። ብዙዎች በንቅናቄው ማንጸባረቂያ ቦታ ተገኝተው የነበሩት በአሁኑ ጊዜ በትምህርት መስክ የተሠማሩ ናቸው። የመንግሥት ሠራተኞች ሆነዋል ወይም በንግድ ሙያ ተሠማርተዋል ማለት ነው።የያኔውን የአንቅሥቃሴ ተግባር ፣ ትዝታውን በኅሊናቸው ውስጥ ቀብረውታል ፣ ይህን ያደረጉት፣ በከፊል ከፍርኀት የተነሣ ሲሆን ምናልባት የኤኮኖሚ ጥቅም ዐይነ-ኅሊናቸውን ስልጋረደውም ሊሆን ይችላል።»

ደራሲው ሁ ፒንግ ኒው ውስጥ ይኖራሉ። በዚያም የቻይናውያን አፈንጋጮች መጽሔት ይታተማል ፣ «የቤይጂንግ ፀደይ » የተሰኘው!ፒንግ የቀቢጸ-ተስፋውን አዝማሚያ መገንዘብ አያዳግትም ይላሉ፣

«የዴሞክራሲው እንቅሥቃሴ የቻይናው ከፍተኛ ባለሥልጣን ዴንግ ዚያዖፒንግ፣ ከርእዮት እንዲያፈነግጡ ገፋፍቷል። ከኤኮኖሚ አኳያ፣ የማፍታቻ እርምጃ እንዲወደሰድ አድርገዋል ማለት ይቻላል። ህዝቡ በአሁኑ ጊዜ የተሻሉ አማራጮች አሉት። ለምን በፖለቲካው መስክ እርማጃ ማሳየት ይኖርብናል? በፖለቲካው ውስጥ ካልገባን የተደላደለ ኑሮ መኖር እንችላለን። በ 1989 ፣ ሁሉም ነጻነትና ዴሞክራሲ ይኖር ዘንድ ነበረ የጠየቁት። እነዚህ ጥያቄዎችበጭካኔ በጦር መሣሪያ ኃይል በተወሰደ እርምጃ ተደቁሰዋል። አሁን ህዝቡ፣ ራሱን ከአዲስ ሁኔታ ጋር አለማምዷል-ከፍርሃት የተነሣ ማለት ነው።»

«ቻይናውያን ገሓዳዊ ፈለግ ተከታዮች ናቸው። ብዙዎች የሀገር ፍቅር ስሜት የወቅቱ ፈሊጥ ነው ብለው ያስባሉ፣ አናት ሀገርን መውደድ ጠቀሜታም ያስገኛል። እዚህ ላይ የምናገረው የተሳሳተውን የአናት ሀገር ፍቅር በተመለከተ ነው። ሃቀኛዎቹ አገር ወዳዶችማ፣ በእሥር ቤት ነው የሚገኙት። አስመሳዮቹ አገር ወዳዶች ከመንግሥት በኩል በበጎ ዐይን ነው ይታያሉ። የሚደርስባቸው አደጋ የለም። ለሌሎቹ ሌላ ቃል አግኝቼአለሁ። «የሰብአዊ መብት አገር ወዳዶች» የሚሰኝ! ። እውነተኞቹ አገር ወዳዶች የቻይናን ህዝብ ይወዳሉ። መብታቸው ሲገፈፍ ሥቃዩ አብሮ ይሰማቸዋል። የሚቆሙት ለህዝቡ ነው። እውነተኛ የሀገር ፍቅር ይሏልም፣ ይህ ነው።

በቲያናንሜን አደባባይ፣ በኃይል እርምጃ ደም ከፈሰሰ ከ 20 ዓመት ወዲህ ፣ የቤይጂንግ መሪዎች ፣ የዴሞክራሲውን ንቅናቄ በአዲስ አመለካከት ይገመግማሉ ተብሎ አይታሰብም። እርግጥ ነው ፣ በፖለቲካው ሥርዓት ሰፊ መሠረት ያለው የተሃድሶ ለውጥ ማድረግ በተገባ ነበር! ።

ተክሌ የኋላ፣ ሸዋዬ ለገሠ