ቻይናና አፍሪቃ በጋራ ልማት አቅጣጫ? | ኤኮኖሚ | DW | 08.11.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ቻይናና አፍሪቃ በጋራ ልማት አቅጣጫ?

ሕዝባዊት ቻይና ከአርባ የሚበልጡ የአፍሪቃ መንግሥታት መሪዎችን ቤይጂንግ ላይ በማሰባሰብ በጋራ የኤኮኖሚ ጥቅም ላይ ያተኮረ ታሪካዊ ክብደት የተሰጠው ጉባዔ ባለፈው ሰንበት አካሂዳለች። የዓለም ባንክ ደግሞ በቅርቡ በአፍሪቃ ልማት ላይ ዓመታዊ ዘገባ አውጥቷል። መሥፍን መኮንን!

ሁ ጂንታዎ የአፍሪቃን መሪዎች ሲቀበሉ

ሁ ጂንታዎ የአፍሪቃን መሪዎች ሲቀበሉ

የቻይናው ጉባዔ የሁለቱን ወገን የንግድ ልውውጥ በመጪዎቹ አራት ዓመታት ውስጥ ወደ መቶ ቢሊዮን ዶላር ከፍ ለማድረግ የተወጠነበት ነበር። ቤይጂንግ ለአፍሪቃ አገሮች የአምሥት ቢሊዮን ዶላር ብድር ለመስጠትና ዕርዳታዋን በእጥፍ ለማሳደግም ቃል ገብታለች። የቻይናን በዚህ መጠን በአፍሪቃ ላይ ማተኮር ምን አመጣው፤ ዕድገት ለጠማው የአፍሪቃ ሕዝብስ ጠቀሜታው እስከምን ድረስ ነው?

“ያለ ቻይናና አፍሪቃ የተጣመረ ልማት በዓለም ላይ ሰላምና ዕድገት አይኖርም” ይህን ባለፈው ቅዳሜ በቤይጂንግ ሕዝባዊ ም/ቤት ውስጥ ለተሰበሰቡት የመንግሥታት መሪዎች የተናገሩት የቻይናው ፕሬዚደንት ሁ ጂንታዎ ነበሩ። የፕሬዚደንቱ አባባል ቻይና ከአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ጋር ላላት ግንኙነት ታላቅ ክብደት መስጠቷን የሚያመለክት ነው። እርግጥ ቤይጂንግ በአፍሪቃ ላይ በዚህ መጠን ማተኮሯ ያለምክንያት አይደለም።

በፍጥነት እያደገ የሚሄድ ኤኮኖሚዋ በተለይ በኤነርጂና በሌሎች የተፈጥሮ ሃብቶች ፍጆቷ በኩል የፈጠረው ችግር በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ይህን ፍላጎቷን ለማሟላት ደግሞ አፍሪቃ አስተማማኝ ምንጯ እየሆነች ነው የምትገኘው። ሕዝባዊት ቻይና ዛሬ በሱዳን ነዳጅ ዘይት ታወጣለች። ከሌሎች በርካታ የአፍሪቃ አገሮች፤ ነዳጅ ዘይት አምራቾች የሆኑትን ናይጄሪያንና ሊቢያንየመሰሉትን ጨምሮ የተለያዩ የወዳጅነት ውሎች በመፈራረምም በርካታ ፕሮዤዎችን እያራመደች ነው። በመንግሥታቱ ዘንድ ተቀባይነቷ እየጨመረ ሲሄድ በተለይ ቀላል የኢንዱስትሪ ምርቶቿን የምታግፍበት ገበያ እየሰፋ መሄዱም አልቀረም።
የቤይጂንግ መንግሥት እንዳስታወቀው የአገሪቱ የአፍሪቃ ንግድ ባለፈው ዓመት ወደ አርባ ቢሊዮን ዶላር ሊያድግ ችሏል። ይህም ከጎርጎሮሳውያኑ 1995 ዓ.ም. መጠን ሲነጻጸር በአሥር ዕጅ ከፍ ያለ መሆኑ ነው። በቤይጂንጉ ጉባዔ አኳያ በቻይና ኩባንያዎችና በአፍሪቃ መንግሥታት መካከል አዳዲስ የ 1.9 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ውሎች ሲፈረሙ ሂደቱ አዳጊ እንደሚሆን ጨርሶ አያጠራጥርም። ጥያቄው እየተስፋፋ ከሚሄደው ሽርክና ሰፊው ሕዝብ ተገቢውን ጥቅም ሊያገኝ ይችላል ወይ ነው።

ቻይና በተለይም የጥሬ ሃብት ፍላጎቷን ለማሟላት ስትል በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም በያዘችው መስፋፋት ሰብዓዊ መብትን ከሚረግጡ አምባገነን ገዢዎች ጭምር መተባበሯ ከያቅጣጫው ሳያስወቅሳት አልቀረም። ዋሺንግተን ላይ ተቀማጭ የሆነው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት Human Rights Watch ያለፈውን ሰንበት ጉባዔ ምክንያት በማድረግ ቤይጂንግ የሱዳን መንግሥት በዳርፉር ጦርነት ሊጠቀምበት የሚችል ዕርዳታን እንዳትሰጥ ጠይቋል። “አፍሪቃ የምዝበራ አገዛዝን የሚያጠናክር ሌላ የውጭ ሃይል አትፈልግም፤ የምትሻው ቻይናን ጨምሮ ሁሉም ሃያላን መንግሥታት ሰብዓዊ መብትን የፖሊሲያቸው ማዕከላዊ ጉዳይ ማድረጋቸውን ነው” ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ እንዳስገነዘበው።
ቻይና የአፍሪቃን የተፈጥሮ ሃብት ለመመዝበር የዕጅ አዙር ቅኝ-አገዛዝ መሰል የመስፋፋት ዘይቤ በመከተልም ተነቅፋለች። ቻይና በበኩሏ በሌሎች አገሮች ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት በሚል መርህ ግንኙነቷን የምታስፋፋ መሆኗን ነው የምትናገረው። ይሁንና የምዕራባውያን ኩባንያዎች ጥቅም ተቀናቃኝ እየሆነች መሄዷ ያብከነከናቸው የቀድሞ ቅኝ ገዥ መንግሥታት የቻይና ሂደት እስካሁን የሚከተሉትን ዘዴ ሁሉ ከንቱ የሚያደርግ በመሆኑ አልተዋጠላቸውም። ሰሞኑን ከነዚሁ ወገኖች ሲሰማ የሰነበተው ቻይና በአፍሪቃ ለሰብዓዊ መብቶች ከበሬታ አንዳች ደንታ እንደሌላት ነው። የዓለም ባንክ ፕሬዚደንት ፓውል ዎልፎቪትስም ሣይቀር የቻይና ባንኮችን ለአፍሪቃ ብዙ ገንዘብ በማበደር ሰብዓዊ መብቶችንና የተፈጥሮ ጥበቃን ችላ ብለዋል ሲሉ በቅርብ ወቅሰው ነበር። ዎልፎቪትስ አዲስ ብድር ወደ አፍሪቃ መጉረፉ ሙስናንና የዕዳ ሸክምን ሊያስፋፋ ይችላል ሲሉ ነው ያስጠነቀቁት።

በሌላ በኩል ምዕራባውያን ኩባንያዎች ከቻይና በተለየ መንገድ ለሰብዓዊ መብትም ሆነ ለአፍሪቃ የተፈጥሮ ይዞታ ሲጨነቁ ቆይተዋል ወይ? አወንታዊ ምላሽ ለመስጠት በጣሙን ያዳግታል። በናይጄሪያ የነዳጅ ዘይት አካባቢ በኒጀር ዴልታ ያለው ሃቅ ብቻ እንኳ እንደ አብነት ሊጠቀስ የሚችል ነው። ከዚህ አንጻር ምዕራቡ ዓለም በቻይና ላይ የሚሰነዝረው ትችት ለአፍሪቃ ከመቆርቆር ይልቅ ጥቅሜ ተነካ የሚል መንስዔ ያለው ነው የሚመስለው። ፍትሃዊ አያያዝ እንደነበረ አድርጎ ለመናገር አይቻልም። የቦትሱዋናው ፕሬዚደንት ፌስቱስ ሞጋኤ ለአፍሪቃ ጥቅም ቻይና ወይስ ምዕራቡ ዓለም፤ ልዩነቱን እንዲህ አስቀምጠውታል። “ቻይና በእኩልነት እንደምታስተናግደን ነው የምረዳው። ምዕራቡ ዓለም በአንጻሩ እንደቀድሞ ተገዢዎቹ አድርጎ የሚመለከተን መሆኑ ሃቅ ነው። እኔ ከምዕራቡ ይልቅ የቻይናን ዝንባሌ እመርጣለሁ” ብለዋል።

እርግጥ ቻይናም ቢሆን በሰብዓዊ መብት መጣስ ከምዕራቡ ዓለም የሚሰነዘረውን ወቀሣ አትቀበለውም። የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት አፈ-ቀላጤ ሊዩ ጂያንሻዎ ባለፈው ሰንበት ጉባዔ ዋዜማ የቤይጂንግን በሌሎች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት መሠረተ-ዓላማ ተመርኩዘው ለጋዜጠኞች እንዳስረዱት ቻይና ሌሎች አገሮች ማሕበራዊ ሥርዓቷንና ርዕዮቷን እንዲቀበሉ ለማስገደድ አትፈልግም። የቻይናና የአፍሪቃ ግንኙነት በወዳጅነትና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ነው። ስለዚሁ ፖሊሲ በቤይጂንግ የዓለምአቀፍ ግንኙነት ተቋም የአፍሪቃ ጉዳይ አዋቂ የሆኑት ዋንግ ሆንግዪ እንዲህ ይላሉ፤

“እንዴት ነው ከሌሎች አገሮች ጋር መተባበር የሚቻለው? በዚህ ጥያቄ ላይ ቻይና ከምዕራቡ ዓለም የተለየ አስተያየት አላት። በመጀመሪያ ደረጃ በሌሎች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት የሚለው የቻይና ፖሊሲ ከተባበሩት መንግሥታት ቻርታ የተጣጣመ መሆኑ ሊነገር ይገባዋል። ይህ ደግሞ የቻይና ዲፕሎማሲ መሠረት ሲሆን በተግባርም ፍቱን ነው። ፖሊሲው የአፍሪቃ መንግሥታትን ድጋፍ እያገኘ ሲሄድ በዚሁ የቻይናና የአፍሪቃ ግንኙነት ጽኑ ሆኖ እንደሚቀጥል አያጠራጥርም”

ዋንግ አያይዘው እንዳስረዱት አፍሪቃ ከምዕራቡ ዓለም ይልቅ ከቻይና በመተባበር የበለጠ ነው የምትጠቀመው። አንድ የአፍሪቃ መንግሥት ከቻይና ጋር ለመተባበር የፖለቲካ ቅድመ-ግዴታዎችን ማሟላት የለበትም። በዚህም የአፍሪቃ መንግሥታት ለዘላቂ ልማት የበለጠ ዕድል አላቸው ማለት ነው። እርግጥም አፍሪቃ ከቻይና ጋር በያዘችው የጠበቀ ግንኙነት በአጭርም ሆነ በረጅም ጊዜ ይበልጥ ተጠቃሚ እንደምትሆን ብዙም አያጠራጥርም።

ቻይና ዛሬ ምርቶቿን በአፍሪቃ በሰፊው በማራገፍ ብቻ ሣይሆን ቀለል ባለ ቅድመ-ግዴታ ብድር በማቅረብ፣ መንገዶችንና ሃዲዶችን በመዘርጋት፣ ትምህርቤቶችና ሆስፒታሎችን በማነጽ ወዘተ. በመዋቅራዊው ግንባታ ሰፊ አስተዋጽኦ ታደርጋለች። ምዕራባውያን ኩባንያዎች ይህን መሰሉን ተግባር የቻይናን ያህል በርካሽ ሊያከናውኑ ዝግጁ አለመሆናቸው ግልጽ ነው። ይህና በተረፈ ቻይና የቀድሞ ቅኝ ገዥ አለመሆኗ በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም የበለጠ ተቀባይነት ይሰጣታል። ባለፈው ሰንበት ለወትሮው ለየቅል ከሆኑት የአፍሪቃ መሪዎች ከአርባ የሚበልጡትን በቤይጂንግ ማሰባሰብ መቻሏ ሚስጥሩ ይሄው ነው።

የአፍሪቃ ልማት ገና ብዙ መሠረታዊ ችግሮች ቢኖሩትም በአንዳንድ አካባቢዎች ተሥፋ የሚሰጥ የተወሰነ ዕድገት መታየቱ አልቀረም። የዓለም ባንክ በቅርቡ ባወጣው የአፍሪቃ ልማት ዓመታዊ ዘገባ ጠንካራ ዕድገት መታየቱን አመልክቷል። በዘገባው እንደተጠቀሰው የውጭ ንግድ እየጨመረ ነው፤ የበለጠ ሕዝብ የትምሕርትና የጤና አገልግሎት ለማግኘትም በቅቷል። ይሁን እንጂ በሌላ በኩል የባንኩ የ 2006 ዘገባ እንደጠቆመው ድህነትን እስከ 2015 በከፊል ለመቀነስ በተባበሩት መንግሥታት የተጣለውን የሚሌኒየም ዕቅድ ማሟላቱ አሁንም ለብዙዎቹ አገሮች ፈተና ሆኖ ነው የሚገኘው።

ከአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ሕዝብ ግማሽ ገደማ የሚጠጋው ዛሬም የሚኖረው ድሃ ከሚያሰኘው መስፈርት በታች ዝቅ ብሎ ነው። ሃቁ ይህ ሆኖ ሳለ በወቅቱ ለተነገረለት ጠንካራ የኤኮኖሚ ዕድገት አንዱ ምክንያት የእርስበርስ ግጭቶች መቀነስ ነው። አንዳንድ አገሮችም የኤኮኖሚ ይዞታቸውን ሲያሻሽሉ ዓመታዊ ዕድገታችው ከአምሥት በመቶ በላይ ሊዘልቅ መቻሉ ተመልክቷል። ይሁን እንጂ የልማት ዕርምጃ ቢታይም ይህንኑ ቀጣይ ለማድረግ በበጎ አስተዳደር፣ በሲቪል ሕብረተሰብ አያያዝ፣ በግል ዘርፍ ልማትና በሕዝብ ዕድገት መስኮች የበለጠ ጥረት መደረጉ አስፈላጊ ነው፤ ባንኩ እንደዘገበው።
የተስማሚ መንገዶች ጉድለት፣ የወደቦችና ብቁ አለመሆናንና የኤሌክትሪክ ሃይል ጉድለትም የአካባቢው ኩባንያዎች ወደ ዓለም ገበዮች ለመዝለቅ የሚያደርጉትን ጥረት ማሰናከሉም ተጠቅሷል። በባንኩ ዘገባ መሠረት ከሚሌኒየሙ የልማት ግብ እንዲደረስ ከተፈለገ የአፍሪቃ መዋቅራዊ ወጪ በያመቱ በእጥፍ፤ ወደ 20 ቢሊዮን ዶላር ማደግ ይኖርበታል። በሌላ አነጋገር ከታሰበው ግብ እንዲደረስ በያመቱ ሰባት በመቶ ዕድገት መታየቱና አምሥት በመቶ መዋዕለ-ነዋይ በሥራ ላይ መዋሉ ግድ ነው። የባንኩ የአፍሪቃ ጉዳይ የኤኮኖሚ ባለሙያ ጆን ፔጅ እንዳስገነዘቡት በመዋቅራዊ ልማት ላይ የመዋዕለ-ነዋይ እጥረት ለምሳሌ ለወትሮው ጥሩ ልማት ሲያሣዩ በቆዩት በሞዛምቢክ፣ በጋና፣ በታንዛኒያ፣ በሩዋንዳና በኡጋንዳ ዕድገትን መግታት እየጀመረ ነው።

ባለሥልጣኑ እንደሚሉት የችግሩ መንስዔ ውስጣዊ ሣይሆን ዓለምአቀፉ ሕብረተሰብ ለነዚህ አገሮች መዋቅራዊ ችግር ተገቢውን ትኩረት አለመስጠቱ ነው። በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት ለአፍሪቃ የሚያቀርቡትን ዕርዳታ እስከ 2010 በ 25 ቢሊዮን ዶላር ለመጨመር የገቡትን ቃል ገቢር ቢያደርጉ አፍሪቃውያኑ አገሮች በመዋቅራዊ ግንባታ ላይ ለመግፋት በቻሉ ነበር። በሌላ በኩል ይሁንና ባለ ኢንዱስትሪ መንግሥታት ለአፍሪቃ አገሮች የሚሰጡት የልማት ዕርዳታ በ 2006 እና በ 2008 መካከል በአብዛኛው በዕዳ ስረዛና በአስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ተወስኖ ነው የሚቆየው። በአጠቃላይ የዓለም ባንክ እንዳመለከተው መዋቅራዊው ግንባታ፣ HIV-AIDS-ንና ወባን መቋቋሙ፣ እንዲሁም የፉክክር ብቃት ማዳበሩ ለአፍሪቃ የአማካይና የረጅም ጊዜ ፈተና ሆኖ ይቀጥላል።
በዘገባው መሠረት ጥናቱ ባተኮረበት በ 2004 ዓ.ም. የዕድገት ማቆልቆል ያሣየችው ዚምባብዌ ብቻ ናት። ባለፉት አሥር ዓመታት ከ 2.4 በመቶ አላለፈችም። የኤኩዋቶሪያል ጉኒ አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት በአንጻሩ 20.9 በመቶ በሆነ ዕድገት ላቅ ብላ መጥቋል። በርካታአገሮች በ 4.5 ከመቶ መጠን ዓመታዊ ዕድገታቸውን ሲጠብቁ ባለፈው ዓመት በነዳጅ ዘይት ዋጋ መናር ሳቢያ በክፍለ-ዓለም ደረጃ የ 2004 5.4 ከመቶ ዕድገት ወደ 4.3 ዝቅ ብሎ መገኘቱ ተመልክቷል። በሌላ በኩል የአፍሪቃ ቀደምት ኩባንያዎች የአምራችነት ብቃት ሕንድንና ቪየትናምን ከመሳሰሉት የእሢያ አገሮች የተስተካከለ ሆኖ መታየቱ ነው የተነገረው። የዓለም ባንክ አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት የአፍሪቃን ንግድ ለማጠናከር አንዳንድ መሰናክል የሆኑ ደምቦቻቸው ያስወግዱ ዘንድ ጠይቋል።

ባንኩ በአፍሪቃ አገሮች በራሳቸው መካከል የሚካሄደው ንግድ እንዲጠናከርም ለውጥ እንዲደረግ ያስስባል። ይህ ደግሞ በድሃው የሕብረተሰብ ክፍል ላይ ያተኮረ የመዋዕለ-ነዋይ ተግባራዊነትንና የክፍለ-ዓለሚቱን የተፈጥሮ ሃብት የተሻለ አጠቃቀም የሚጠቀልል ነው። አፍሪቃ አሁንም የድሃው ቁጥር ሲጨምር የሚታይባት ክፍለ-ዓለም የመሆኗ ሃቅ አልተቀየረም። ይህም ሆኖ ግን የዓለም ባንክ ዘገባ የጠቆመው በርካታ አገሮች ብዙ ሕዝብን ከድህነት እንዳላቀቁና ከሚሌኒየሙ ግብ ለመድረስ እንደሚችሉ ነው። እንደ አብነት ቦርኪና ፋሶ፣ ካሜሩን ፣ ኬፕ-ቬርዴ፣ ጋና፣ ሞዛምቢክ፣ ሤኔጋልና ኡጋንዳ ተጠቅሰዋል። ግን ይህ የክፍለ-ዓለሚቱ ዕውን ገጽታ አይደለም። በሽታ፣ ሙስናና የማሕበራዊ ፍትህ እጦት በጣሙን ያመዝናል።

ለማንኛውም በዓለም ባንክ ዘገባ ላይ ብዙ ሕዝብ ከድህነት አምልጧል መባሉ ሲሰሙት የሚወደድ ቢሆንም በጣሙን አሻሚ ግምት ነው። በአፍሪቃ ከፍተኛ ዕድገት ከታየባችው አገሮች መካከል አብዛኛውን ድርሻ የሚይዙት ናይጄሪያንና ሱዳንን የመሳሰሉት የነዳጅ ዘይት ያላችው አገሮች ናቸው። እርግጥ ከዚህ የተፈጥሮ ጸጋ የሚገኘው ገቢ የብሄራዊውን ምርት መስፈርት ከፍ እንደሚያድገው አንድና ሁለት የለውም። ቢሆንም አጠቃላዩን ገቢ በነፍስ ወከፍ በማከፋፈል የሕዝቡ የኑሮ ደረጃ አድጓል፤ ብዙዎችም ከድህነት ተሰናብተዋል ለማለት አይቻልም። ተጠቃሚዎቹ ጥቂቶች ናቸው።

ከዚህ ሌላ አፍሪቃ ውስጥ ለልማት እፎይታ ሰጡ የተባሉት ብዙዎች ውዝግቦች ተወግደዋል ቢባልም ምኑም ነገር አስተማማኝ አይደለም። የአንጎላው፣ የላይቤሪያውና የደቡብ ሱዳን ግጭት መፍትሄ ቢያገኝ የዳርፉርና የአፍሪቃ ቀንድ ቀውሶች ተተኪ ጠንቆች ሆነዋል። የሶማሊያ ውዝግብ ለመላው አካባቢ ወጥመድ እንዳይሆን ማስፈራቱ የተሰወረ ነገር አይደለም። አፍሪቃ ውስጥ ድህነትን የመቀነሱ ሃሣብ ገቢር እንዲሆን አሆንም ዞሮ ዞሮ ወሣኝ የሚሆነው ለግጭቶች ዋና መንስዔ የሆነው የበጎ አስተዳደር ጉድለት፣ የማሕበራዊ ፍትህ እጦትና ሙስና መወገድ ነው። ይህ ቢሟላ ልማትን ማፋጠኑና ድህነትን መቀነሱ የሚገድ አይሆንም።