ቶጎ፤ ህፃናትን ማዘዋወር በህግ አገደች | የጋዜጦች አምድ | DW | 25.08.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ቶጎ፤ ህፃናትን ማዘዋወር በህግ አገደች

ህፃናትን በህገወጥ መንገድ ከቦታ ወደቦታ የማዘዋወርን ተግባር የሚገታ ህግ በቶጎ መዉጣቱ ድርጊቱን ለማስቆም አንድ መፍትሄ መሆኑን የህፃናት መብት ተሟጋቾች ገለፁ። የአገሪቱ ባህልና የድህነት ሁኔታ ህፃናትን ለዚህ አይነቱ አደጋ እንዳጋለጠ የሚናገሩት የህፃናት መብት ተሟጋቾች በወንጀሉ ዉስጥ ቤተዘመዶችና ወላጆችም የሚሳተፉበት ሁኔታ መኖሩን አልሸሸጉም።

በየዓመቱ በርካታ ህፃናቶች በህገወጥ መንገድ ለተለያየ የጉልበት ብዝበዛ ወደሚዳረጉባቸዉ አገራት እንዳይወሰዱ የሚያደርገዉን ህግ ለማዉጣት ቀላል ጊዜ አይደለም ቶጉ የፈጀባት።
እንደ ደሊል ካፕጌሎ ላሉ የህፃናት መብት ተሟጋቾች ህፃናትን እያገቱ ከቦታ ቦታ የማዘዋወርን ጉዳይ የማስቆሙ ጥረት ተስፋ አስቆራጭ እየሆነ ሄዷል።
ይህን ችግር ለማስወገድ ይሆናል ያልነዉን አማራጭ ሁሉ ሞከርን ሁሉም ግን ዉጤታማ አልሆኑም ጭራሽ የሚወሰዱበት ህፃናት ቁጥር የሚጨምርበት ሁኔታ ነዉ የገጠመን ይላሉ ፕላን ቶጎ የተባለዉ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ባልደረባ ካፕጌሎ።
አሁን ጠንከር ያለ ህግ ከብዙ ቅስቀሳና የማስተማር ጥረት በኋላ በአገሪቱ ፀድቋል ያም የአገሪቱን ህፃናት ከዚህ አደጋ ይታደጋል ብለዉ ተስፋ አድርገዋል።
ህጉ የወጣዉ በያዝነዉ ወር መጀመሪያ አካባቢ ሲሆን ህፃናትን ከቦታ ቦታ በማዘዋወር የተከሰሰ እስከ አምስት ዓመት ፅኑ እስራት እንዲሁም ከ1,000 እስከ 2,000 ዶላር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት ይጠብቀዋል።
በዚያ ላይ በማዘዋወሩ ሂደት ህፃናት ቢሞቱ ወይም ቢሰወሩ ቅጣቱ እጥፍ የሚደረግ ሲሆን በወንጀሉ ተባባሪ በሆነ ግለሰብ ላይም ተግባራዊ ይሆናል።
ቀደም ሲል በቶጎ ድርጊቱን የሚከላከል ጠንካራ ህግ ስላልነበረ ወንጀል ፈፃሚዎቹ እንደባለሙያ በነፃ የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ እንደነበርና አሁን ግን ህጉን ተጠቅመዉ እንደሚያስቆሙት ነዉ የፍትህ ሚኒስትሩ ቼሳ አቢ የሚናገሩት።
የቶጎ ብሄራዊ ጉባኤ ፕሬዝደንት አባስ ቦንፎም ህጉ ባጠቃላይ ህፃናትን ከቦታ ወደቦታ በማዘዋወር ተግባር የተጠመዱትን፤ ከቤተሰብና ከቅርብ ዘመዶች ጀምሮ የሚወሰዱትን ልጆች የሚመለምሉ፤ የሚያጓጉዙና ማደሪያ የሚሰጡትን ሁሉ የማይምር መሆኑን አሳዉቀዋል።
አዲሱ ህግ ከአሁን በኋላ ልጆች ከወላጆቻቸዉና ወዴት እንደሚሄዱ ከሚገልፅ ህጋዊ ማስረጃ ጋር ካልሆነ በቀር ከአገር እንዳይወጡ የሚያግድ ነዉ።
ከዚህ በፊት በየዓመቱ 3,000 የሚሆኑ ህፃናት ከቶጎ ለጉልበት ብዝበዛ ወደሚዳረጉበት በተለይ ወደቤኒን፤ ቡርኪናፋሶ፤ ካሜሮን፤ ጋቦን፤ ጋና፤ አይቮሪኮስትና ናይጀሪያ ይወሰዱ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ህፃናትን ወደጎረቤት አገራት የማጓጓዙ ሂደትም ከባለስልጣናትና ከሚመለከታቸዉ አካላት እይታ ለመሸሸግ ሲባል በጨለማና በጫካ ዉስጥ የሚፈፀም ነበር።
ባለፈዉ ዓመት በመጋቢት ወር አንድ በብየዳ ስራ የተሰማራ ግለሰብ ወደአሜሪካ ለመሄድ የሚያስችለዉን 20,000 ዶላር ለማግኘት ሲል በአንድ ወገን ወንድሙ የሆነዉን ህፃን ለመሸጥ ሲደራደር ተይዟል።
በተመሳሳይ ሁኔታም አንዲት ሴት ከሁለት ግብረ አበሮቿ ጋር በያዝነዉ ዓመት በርከት ያሉ ታዳጊ ሴት ልጆችን ናይጀሪያ በቤት ሰራተኝነት ለማስቀጠር በቤኒን በኩል ስታቋርጥ በፓሊስ ቁጥጥር ስር ዉላለች።
ካፕጌሎ እንደሚሉትም ህፃናትን ከቦታ ቦታ የማዘዋወሩ ተግባር ከልጆቹ ቤተሰቦች ጋር ትዉውቅ ያላቸዉ ሰዎች በሚያበጁት የተቀናጀ ግንኙነት ነዉ የሚከናወነዉ።
ፕላን ቶጎ ባለፈዉ ግንቦት ባወጣዉ ዘገባ እንዳስታወቀዉ ወደሌላ ቦታ ከሚወሰዱት የቶጎ ባላገር ልጆች መካከል 12በመቶ የሚሆኑት ምንም ሳይከፍላቸዉ ወይም በዝቅተኛ ክፍያ ከአቅማቸዉ በላይ የሆነ ስራ ለመስራት ይገደዳሉ።
በአገሪቱ ያለዉ የድህነት ሁኔታ፤ ባህላዊ ምክንያቶችና በቶጎ ልጆችን በዘመዶች ቤት እንዲያድጉ የማድረጉ ልማድም ሁኔታዉን እንዳባባሰዉ ይነገራል።
በአገሪቱም 73 በመቶ የሚሆነዉ ዜጋ ከድህነት ወለል በታች የሚገኝና በቀን ከአንድ ዶላር ባነሰ ገቢ ኑሮዉን የሚመራ መሆኑንም መረጃዎች ያሳያሉ።