ቶቦሬ ኦቮሬ የዶይቼ ቨለ ″DW″ የ 2021 ዓ.ም ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ሽልማት አሸናፊ | አውሮጳ እና ጀርመን | DW | 03.05.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ እና ጀርመን

ቶቦሬ ኦቮሬ የዶይቼ ቨለ "DW" የ 2021 ዓ.ም ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ሽልማት አሸናፊ

ናይጄሪያ አቡጃ በሚገኘው ሴቶችን ለዝሙት ተዳዳሪነት ስራ ወደ ጣሊያን የሚያሸጋግር አንድ ደላላ ተዋወቀች:: ከበርካታ ሴቶች ጋርም በመርከብ ተጭና ወደ ቤኒን ጉዞ ጀመሩ:።ታዲያ በጉዞዋ የገጠማት ያልታሰበ አስደንጋጭ ክስተት ዘሬም ድረስ አስፈሪ ፊልሞችን ስታይ ከፍተኛ ጭንቀትን እንዲፈጥርባት የሥነ ልቦና ጠባሳን ጥሎባት አልፏል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:14

ቶቦሬ ኦቮሬ የ"DW" የ 2021 ዓ.ም ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ሽልማት አሸናፊ

 

የበርካታ ዓለማቀፍ ሽልማቶች አሸናፊና የፕሪምየም ታይምስ ከፍተኛ የምርመራ ጋዜጠኝነት ባለሙያዋ ናይጄሪያዊቷ ቶቦሬ ኦቮሬ የዘንድሮው እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር የ 2021 ዓ.ም የዶይቸ ቬለ "DW"ሐሳብን  የመግለጽ ነጻነት ሽልማት አግኝታለች።ቶቦሬ ማን ናት? ለዚህ ሽልማትስ እንዴት ተመረጠች? እንዳልካቸው ፈቃደ ከፍራንክፈርት ዝርዝሩን አዘጋጅቷል።

 

የናይጄሪያን ማህበረሰብ የታፈነ ብሶት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማድረስ የ 33 ዓመቷ የምርመራ ዘጋቢ ቶቦሬ በሕይወቷ ጭምር ተወራርዳ ከፍተኛ ተግባር ማከወኗ ለሽልማት እንዳበቃትም ተገልጿል:: በተለይም ማንነቷን ደብቃ በምስጢር መረጃዎችን ለማነፍነፍ ቀን እና በውድቅት ሌሊት ጭምር እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር ከ 2013 ዓ.ም ጀምሮ ከናይጄሪያ አቡጃና ሌጎስ እስከ አውሮጳ የተዘረጋውን እና በሺህዎች ለሚቆጠሩ ናይጄሪያውያ ወጣቶች ሞት፣  አካል ጉዳትና አስከፊ በሽታ ምክንያት የሆነውን በሀገሯ ምድር የሚፈፀመውን ድንበር ተሻጋሪ ሕገ ወጥ የዝሙት ተዳዳሪ ሴቶችና የሰዎች ድለላ ሽያጭና ዝውውር 'ሴክስ ትራፊኪንግ' እንዲሁም የሰውነት አካል ኮንትሮባንድ ´ህገወጥ ሽያጭ´አስከፊ ወንጀሎችን በማስረጃ ለማጋለጥ ብዙ ውጣ ውረዶችን አይታለች ፤ በርካታ ጥቃቶችንም ተጋፍጣለች:: ግፉአኑ ሰለባ የሆኑባቸውን በሰቆቃ ጩኸት የተሞሉ ከፍተኛ ጥበቃ የሚካሄድባቸውንም ካምፖች ተመልክታለች:: በአቅራቢያዋ የነበሩት ሴቶች ከሚደርስባቸው ጥቃት ለማምለጥ በአስፈሪ ውድቅት ሌሊቶች ሲኳትኑም ሰውነቷ በፍርሃት እስኪርድ አብራ ማስናለች:: ስቃይና መከራቸውን አብራ ኖራ ጣርና ሰቆቃቸውን ልታሰማ ከእነሱ እኩል ለአያሌ ጥቃቶች ተጋልጣለች:: አንዳንዴም የለበሰችው ጨርቅ በደም አበላ እስኪጨቀይና ከመከራው ብዛት አቅሏን ስታ እስክትወድቅ የችግሩን ገፈት ቀማሾች ሕመምና ሰቆቃ ተጋርታለች::

በአንድ ወቅት ያጋጠማት ሁለት በህገወጥ የሰውነት አካል ሽያጭ አዘዋዋሪዎች በጭካኔ ተበልተው መሬት የተጣሉ አካል አልባ ጭንቅላቶች አሳዛኝ የወንጀል ክስተትም ከሕሊናዋ የሚፋቁ አለመሆናቸውን ትናግራለች:: የምርመራ ዘገባዋን በጀመረች በጥቂት ወራት ውስጥም ናይጄሪያ አቡጃ በሚገኘው ሴቶችን ለዝሙት ተዳዳሪነት ስራ ወደ ጣሊያን የሚያሸጋግር አንድ ደላላ ተዋወቀች:: ከበርካታ ሴቶች ጋርም በመርከብ ተጭና ወደ ቤኒን ጉዞ ጀመሩ:: ታዲያ በጉዞዋ የገጠማት ያልታሰበ አስደንጋጭ ክስተት ዘሬም ድረስ አስፈሪ ፊልሞችን ስታይ ከፍተኛ ጭንቀትን እንዲፈጥርባት የሥነ ልቦና ጠባሳን ጥሎባት አልፏል:: ሁለት ሰዎች የሰውነት አካላቸው በህገወጥ መንገድ ስደተኞችን በሚያዘዋውሩ ወንጀለኞች ተቆራርጦ በጥቁር ገበያ ሲቸበቸብ በዓይኗ ካረጋገጠች በኋላ፤  ትልቋ የቤኒን የወደብ ከተማ ኮቶኑ እንደደረሰች በሙያ ባልደረቦቿ ከፍተኛ እገዛና ጥረት ከሞት ተርፋ ለማምለጥ ችላለች:: ቶቦሬ ከሰባት ዓመት በፊት ጀምሮ በምርመራ ዘገባ ሙያዋ ያጋጠማትን ይህን አስከፊ ተሞክሮ ስትተርክ ዓይኖቿ አሁንም በእንባ ይሞላሉ ፡፡በተለይም ላለፉት ሰባት ወራት ማንነቷን ደብቃ ይህን ድንበር ተሻጋሪ አስከፊ ወንጀል ለማጋለጥ ያደረገችው ድካም ዓለም ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው የተስፋ ብርሃንን የፈነጠቀ ሆኗል::

 

ድንበር ተሻጋሪው ህገወጥ የሰዎች ዝውውር በናይጄሪያ

 

በተለያዩ ግብረሰናይ ድርጅቶች የተካሄዱ ጥናቶች እንዳረጋገጡት ወደ አውሮጳና ምዕራባውያን ሀገራት በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ከሚፈልሱት የአፍሪቃ ስደተኞች መካከል ከአስሩ ስድስቱ ናይጄሪያውያን ናቸው:: ዓለማቀፉ የስደተኞች ድርጅት ጥናት እንደጠቆመው ደግሞ በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ከአፍሪቃ ወደ አውሮጳ ከሚጓዙት የናይጄሪያ ሴቶች 80 በመቶ የሚሆኑት ለዝሙት ባርነት ሰለባ የተጋለጡ ናቸው:: ከእነዚህም መካከል የቴቦሬ ጓደኛ አንዷ ስትሆን በ 1999 ዓ.ም አውሮጳ በከፍተኛ እንግልት ከደረሰች በኋላ በኤች.አይ.ቪ ኤድስ ቫይረስ መጠቃቷን ተናግራለች:: ይህን የቅርብ ወዳጆቿን ሰቆቃ ጭምር ካስተዋለች በኋላ ነበር ቴቦሬ ከ 2013 ዓ.ም ጀምሮ ከናይጄሪያ ወደ ጣሊያን በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ደላሎች ሲጓዙ የጥቃትና የጉዳት ሰለባ የሆኑ በሺህዎች የሚቆጠሩ ናይጄሪያውያንን የሕይወት ታሪክ በጥሞና ማጥናት የጀመረችው:: እራሷን ሕይወቱ ውስጥ ከታ ባካሄደችው ጥናት ያጋጠማት ሰቆቃ ጭንቀትና የአዕምሮ መታወክ ቢያስከትልባትም ያንን ሁሉ ፈተና በጽናት ተቋቁማና ማህበረሰቡ በሴቶች ላይ ያለውን የተዛባ አመለካከት ሰብራ የወገኖቿን መከራና እንግልት ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ ይፋ አድርጋለች::

"በዚህ ታሪክ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ድኗል:: አሁን ወደ አልጋዬ ሄጄ በሰላም መተኛት እችላለሁ:: የተጻፈው ኃይለ-ቃል ችግሮችን ዳር እስከዳር በማስተጋባት ድምጽ ለሌላቸው መቆም አስችሎናል:: የምርመራ ጋዜጠኝነት ለእኔ ዓላማ ያለው ኑሮ ነው" ብላለች ቴቦሬ ከዶይቼ ቨለ ጋር ባደረገችው ቃለ-መጠይቅ::

 

ታሪኩን እየኖሩ መዘገብ

ቶቦሬ የምርመራ ዘገባዋን ከመጀመሯ አስቀድሞ የሚድያው ዋና አዘጋጅ በናይጄሪያ የሕገወጥ የወሲብ ሽያጭ ሰለባ የሆኑ ሴቶችን በማነጋገር ማንነቷን ደብቃ ጉዳዩን ከስር መሰረቱ አጣርታ የምርመራ ዘገባ እንድታቀርብ አንድ ተልዕኮ ሰጣት:: በወቅቱ ስለተሰማት ስሜት ከዶይቼ ቨለ ጋር ባደረገችው ቃለ-መጠይቅ ስትገልፅ በትውስታ መለስ ብላ ፈገግ እያለች "በግንባራቸው ላይ አይጽፉም:: በቃ ሕገወጥ የሰዎች ተዘዋዋሪ መሆኔ ነው" አልኩ ብላለች::ለእርሷ ጉዳዩ ያን ያህል አሳሳቢነት አልነበረውም-“እኛ እራሳችን በችግሩና በሂደቱ ውስጥ ማለፍ ነበረብን ፣ ያ ካልሆነ ግን ታሪኩ ምኞት-አልባ ይሆናል ” ብላለች ቶቦር ቆፍጠን ባለ ድምጽ::ቴቦር በሥራዋ ውስጥ ድርድር የሚባል ነገር ቦታ የለውም ፡፡ የዶይቼ ቨለ "DW" ዋና ዳይሬክተር ፒተር ሊምቦርግ እንዳሉት "የቶቦር ድፍረት የተሞላበት ዘገባ የዘንድሮውን የዶይቼ ቨለ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ሽልማት ሊያቀዳጃት ችሏል፡፡""ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ሽልማት ጋዜጠኞች በስራቸው ውስጥ የግልጽነትን አስፈላጊነት በጉልህ እንዲረዱ የሚያሳይ ሲሆን በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ተጨባጭ ሁነት ነቅሶ ለማውጣት ያለንን ድፍረት ትጋትና ቁርጠኝነትም የሚያጠናክር ነው:: ሽልማቱ ቴቦሬን የበለጠ እንድትተጋ ደስታ እንዲሰማትና በስራዋ እንድትተማመን ይረዳታል ብዬ አምናለሁ" ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል:: የሙያ አጋሯ ጋናዊው የምርመራ ዘጋቢ አናስ አርሜያው አናስ በበኩሉ " ቶቦሬ ማናቸውንም ድንገተኛ መሰናክሎችና ሁኔታዎችን የመቋቋም ብቃቷ የጋዜጠኝነት ክህሎቷ ማሳያ ነው ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል:: "አንድ ሰው ቶቦሬ የሄደችበትን ጠመዝማዛ መንገድና ውጣ ውረድ ሲያይ ስራዋን በመሃል ታቋርጣለች ብሎ ማሰቡ አይቀርም:: ሆኖም የበለጠ ጠንክራ ሁሉም አስተሳሰብና ግምት ስህተት መሆኑን በተግባር አስመስክራለች:: ካሳለፈችው መከራ በፍጥነት አገግማ ወደ ጥንካሬዋ መመለሷም ትኩረትን የሚስብና የሚደነቅ ሌላው ጉዳይ ነው" በማለት አድናቆቱን ተናግሯል::

የቴቦሬ ስኬት

ገና ከልጅነቷ ጀምሮ ግጥሞችን፣  መጣጥፎችንና ልዩ ልዩ ሥነጽሁፎችን የመጻፍ ከፍተኛ ዝንባሌ የነበራት ቴቦሬ በናይጄሪያ ትልቋ የንግድ ከተማ ሌጎስ በእንግሊዘኛ ቋንቋና በሥነጽሁፍ እንዲሁም በጋዜጠኝነት ሙያ ከፍተኛ ትምህርቷን የተከታተለች ሲሆን በሳይኮሎጂ የትምህርት ዘርፍም የማስትሬት ዲግሪ ምሩቅ ናት:: በህገወጥ የሰዎች ዝውውርና በሴቶች ጥቃት ዙሪያ ላበረከተችው ከፍተኛ የምርመራ ዘገባዋም የኖቤል ሽልማት አሸናፊውን የናይጄሪያዊው ፀሐፊ ተውኔትና ባለቅኔ ዎሌ ሾይንካ ሽልማትን ጨምሮ በርካታ የእውቅና ሰርተፊኬቶችን አግኝታለች:: ወጣቷ ባለሙያዋ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤት ተማሪ ሳለች አንዲት የክፍል ጓደኛዋ አባትን ሕልፈተ ሕይወት ተከትሎ በአካባቢው በባህላዊ እምነት የታወቀ ግለሰብ ለሰውዬው ሞት ምክንያቱ ባለቤቱን ተጠያቂ ማድረጉን ተከትሎ የደረሰባቸው እንግልት አስቆጥቷት ይህን ኢ-ፍትሃዊ ድርጊት በግልጽ አጥብቃ በመቋወሟ በህብረተሰቡ ዘንድ ዝም እንድትል የደረሰባት ከባድ ተጽዕኖ በቀሪ ዘመኗ ለድምጽ አልባና ለተጨቆኑ ወገኖቿ ድምጿን ለማሰማት እንዳነሳሳት በቃለ መጠይቆቿ ላይ በተደጋጋሚ ትገልጻለች:: በአሁኑ ወቅትም ናይጄሪያ በሚገኝ በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችና የሴቶች ጥቃት ወንጀሎች ተከላካይ ግብረሰናይ ድርጅት ውስጥ በማገልገል ላይ መሆኗን ለማወቅ ተችሏል::

እንዳልካቸው ፈቃደ

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic