1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትግራይ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮች እሮሮ

ረቡዕ፣ መጋቢት 4 2016

በትግራይ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮች አሁንም ወደ መኖሪያችን ባለመመለሳችን ለከፋ ሁኔታ ተዳርገናል ሲሉ ገለጡ ። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከሰላም ስምምነቱ በኋላም ጭምር መፈናቀሉ መቀጠሉን ገልጧል ።

https://p.dw.com/p/4dThI
Äthiopien | Camps von Vertriebenen
ምስል Million Haileselasie/DW

ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ እንሻለን ሲሉ ምሬታቸውን ገልጠዋል

በትግራይ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮች አሁንም ወደ መኖሪያችን ባለመመለሳችን ለከፋ ሁኔታ ተዳርገናል ሲሉ ገለጡ ። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከሰላም ስምምነቱ በኋላም ጭምር መፈናቀሉ መቀጠሉን ገልጧል ። በቅርቡ ከ12 ሺህ በላይ አዳዲስ ተፈናቃዮች መመዝገባቸውንም አስተዳደሩ አክሏል ። በትናንትናው ዕለት ብቻ 28 የትግራይ ተወላጆች ከሑመራ እና አካባቢው ተፈናቅለው ወደ ሸራሮ መግባታቸውን የአከባቢው አስተዳደር ገልጧል።  ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ ተጨማሪ አለው ።

በኢትዮጵያ መንግስት እና የትግራይ ኃይሎች መካከል ይደረግ የነበረው ጦርነት ከቆመ ዓመት ከመንፈቅ ቢሆነው በጦርነቱ ምክንያት ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በትግራይ የሚገኙ ዜጎች ግን አሁንም ወደቦታቸው የሚመለሱበት ዕድል አላገኙም። ከቆዩት ተፈናቃዮች በተጨማሪ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ጭምር መፈናቀሉ መቀጠሉን የሚገልጠው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በቅርቡ ከ12 ሺህ በላይ አዳዲስ ተፈናቃዮች መመዝገባቸውን ይገልፃል።

የትግራይ ሰሜን ምዕራብ ዞን ሸራሮ ከተማ የኮምኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረመድህን ኪሮስ በቅርብ ሳምንት ከአንድ ሺህ በላይ፣ በትናንትናው ዕለት ብቻ ደግሞ 28 የትግራይ ተወላጅ ተፈናቃዮች፥ ከሑመራ ወደ ሸራሮ መግባታቸውን ይናገራሉ።

ይህ ዜጎችን የማፈናቀል ተግባር እንዲቆም እና መንግስት ትኩረት እንዲሰጠውም ሐላፊው ጨምረው ገልፀዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁን ላይ በመጠልያ ያሉ ተፈናቃዮች እንደሚሉት ከፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት በኋላ ወደቀድሞ መኖርያቸው ሊመለሱ በተስፋ ሲጠብቁ የነበረ ቢሆንም ከውሉ በኋላ ጭምር መንግስት ለተፈናቃዮች ጉዳይ ትኩረት አልሰጠም፣ ይቀርብ የነበረ እርዳታ እንኳን እየተቆራረጠ፣ ኑሮአቸው ይበልጥ አስከፊ እንዳደረገው ይገልፃሉ። ከምዕራብ ትግራይ ተፈናቅለው በሽረ ፀሐዬ የተፈናቃዮች መጠልያ ጣብያ ካሉት መካከል የሆኑት ያነጋገርናቸው አቶ ካሕሳይ አስፈሃ፥ መንግስት እንደዜጎች የሚገባንን እያደረገልን አይደለም ይላሉ።

ትግራይ ክልል ተፈናቃዮች በከፊል ።
ትግራይ ክልል ተፈናቃዮች በከፊል ። ፎቶ፦ ከክምችት ማኅደር ምስል Million Hailesilasse/DW

«የኢትዮጵያ መንግስት እንደዜጎቹ የሚያየን ከሆነ ችግራችን ሊገነዘብ ይገባል። ደኅንነታችን አረጋግጦ ወደቦታችን ይመልሰን» በማለት ተፈናቃዩ አቶ ካሕሳይ ይገልፃሉ።

በትግራይ ስለሚገኙ ተፈናቃዮች  ሁኔታ በቅርቡ ሪፖርት አውጥቶ የነበረው የኢትዮጵያ ስብአዊ መብት ኮምሽን ከምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብ እና ደቡብ ትግራይ ተፈናቅለው በተለያዩ መጠሊያዎች በሚገኙ ተፈናቃዮች ላይ የተለያዩ በደሎች መድረሳቸው የሚያነሳ ሲሆን በምግብ እጥረት ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች በርካቶችም ለሞት የተጋለጡ መሆኑ ያወሳል።

ሌላው በመቐለ ከሚገኘው 70 ካሬ የተፈናቃዮች መጠልያ ያነጋገርናቸው ተፈናቃይ አቶ ጊደይ ንጉሡ ለዓመታት የዘለቀው የትግራይ ተፈናቃዮች ሰቆቃ ሊያበቃ የሰላም ስምምነት የደረሱት አካላት ይሥሩ ይላሉ።

ትግራይ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቃዮች ምሬታቸውን እየገለጡ ነው
ትግራይ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቃዮች ምሬታቸውን እየገለጡ ነው ። ፎቶ፦ ከክምችት ማኅደርምስል Million Haileselassie/DW

«በትግራይ አስተዳደር በኩልም ቢሆን በቂ ትኩረት እያገኘን ነው ብዬ አላስብም። የፌደራል መንግስቱ ረስቶናል። የፌደራሉ መንግስት ባለስልጣናት ሲመጡ ጥያቄአችን፣ ችግራችን እናቀርባለን። መፍትሔ ይሰጣቹሀል ይላሉ፣ ከዛ በኃላ ግን የሚደረግ ነገር የለም። ተረስተናል። አሁን ተፈናቃዮ በዘላቂነት እንዲሆንለት የሚፈልገው የሚፈልገው ወደ ቀዩው መመለስ ነው» ይላሉ ተፈናቃዮ አቶ ጊደይ።

በአሁኑ ወቅት በሁሉም አካበቢ ያለ ተፈናቃይ  አስቸኳይ የምግብ፣ ውኃ እና ሌሎች መሰረታዊ አቅርቦቶች እንደሚያስፈልገው የሚያነሱት ተፈናቃዮቹ በዘላቂነት ግን ወደቦታቸው መመለስን ይሻሉ። በትግራይ ባሉ ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ ዙርያ ከፌደራል መንግስቱ ባለስልጣናት ማብራሪያ ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረግነው ጥረት ለግዜው አልሰመረም።

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሃንስ ገብረ-እግዚአብሄር