1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትግራይ ክልል በረሐብ ሰዎች እየሞቱ ነው

ረቡዕ፣ መስከረም 16 2016

በትግራይ ክልል በረሃብ ምክንያት በርካቶች እየሞቱ መሆኑ ተገለፀ ። በክልሉ በተደረገ ጥናት ከጦርነቱ በኋላ በረሐብ መሞታቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር 1,329 መሆኑ ተዘግቧል ። በዛሬው ዕለት ብቻ በረሐብ የተነሳ አንዲት በ20ዎቹ መጀመሪያ የምትገኝ ሴት መሞቷን አንድ ተፈናቃይ ለዶይቸ ቬለ (DW)ተናግረዋል ።

https://p.dw.com/p/4WrQa
ትግራይ ክልል፤ መቀሌ
ትግራይ ክልል ረሐብ በርካቶችን ገድሏልምስል Million Haile Selassie/DW

ዛሬ እንኳን በረሐብ አንዲት በ20ዎቹ የምትገኝ ሴት መሞቷ ተገልጿል

በትግራይ ክልል በረሃብ ምክንያት በርካቶች እየሞቱ መሆኑ ተገለፀ። በክልሉ በተደረገ ጥናት ከጦርነቱ በኋላ በረሐብ መሞታቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር 1,329 መሆኑ ተዘገበ ። አሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ምንጭ እንደዘገበው ከሆነ፦  የሟቾቹ ቁጥር የታወቀው ከነሐሴ 9 እስከ ነሐሴ 23 ድረስ ባሉት ለሁለት ሳምንታት  በተደረገ ጥናት መሆኑን ጠቁሟል ። በክልሉ የሚገኙ የጤና ባለሞሙያዎች እና ምሁራን በጋራ ጥናቱን ያከናወኑትም በ88 የተለያዩ ቦታዎች እና በ643 የተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ መሆኑን ተገልጿል ። በዛሬው ዕለት ብቻ በረሐብ የተነሳ አንዲት በ20ዎቹ መጀመሪያ የምትገኝ ሴት መሞቷን አንድ ተፈናቃይ ለዶይቸ ቬለ (DW) ተናግረዋል።  በትግራይ በተለይም በጦርነቱ ምክንያም ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ለረሃብ ተጋልጠው እንዳለ ይገልፃሉ። 

ከጦርነቱ መቆም በኋላ ማኅበራዊ ቀውሶች

በትግራይ ክልል ከጦርነቱ መቆም በኋላም ቢሆን ጦርነቱ የፈጠራቸው የተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች በስፋት ዕየታዩ ሲሆን፥ በተለይም ረሃብ ለበርካቶች ሞት ምክንያት ሆኖ እንዳለ የተለያዩ ጥናቶች እና ከኅብረተሰቡ የተሰበሰቡ መረጃዎች ያመለክታሉ። በቅርቡ በትግራይ ክልል የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች እና መቐለ ዩኒቨርሲቲ በጋራ የሠሩት ጥናት እንደሚያመለክተው ጦርነቱ ካስቆመ የፕሪቶርያው ስምምነት በኋላ ባለው ጊዜ ብቻ በትግራይ ክልል ከ1,320 በላይ ስዎች በረሃብ ምክንያት መሞታቸው ያመለክታል። 

በትግራይ ክልል ዋነኛ የሞት መንስኤ ረሃብ ሆኖ እንዳለ የሚገልፁት አጥኚዎቹ፥ ከስምምነቱ በኋላ ጥናት በተደረገባቸው ቦታዎች ከሞቱት ሰዎች መካከል 68 በመቶ የሚሆኑት የሞቱት ከረሃብ ጋር በተያያዘ እንደሆነ ተመላክቷል። በትግራይ ክልል በረሃብ ምክንያት በየዕለቱ እየሞቱ ካሉ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በጦርነቱ ምክንያት ከቀዬአቸው ተፈናቅለው አሁንም በየመጠልያው ያሉ ተፈናቃዮች መሆናቸው ይገለፃል። 

በትግራይ ክልል፤ መቀሌ
በትግራይ ክልል፤ መቀሌ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያምስል Million Haile Selassie/DW

ተፈናቃዮች በተለይ ረሐቡ ጸንቶባቸዋል

በተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ ተፈናቃዮችእንደነገሩን በእድሜ የገፉ አዛውንቶች፣ ጨቅላ ህፃናት እና የቆየ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ረሃብ ተጨምሮባቸው ይበልጥ እንደሚጎዱ እና ለሞትም እንደሚጋለጡ ነግረውናል። በዛሬው ዕለት ያነጋገርናቸው በመቐለ ሰብዓ ካሬ የተፈናቃዮች መጠልያ የሚኖሩ ከምዕራብ ትግራይ በ2013 ዓመተ ምሕረት የተፈናቀሉ የቤተሰብ መሪ አቶ ጊደይ ንጉስ እንዳሉት በመጠልያቸው በዛሬው ዕለት እንኳን አንዲት በሀያዎቹ መጀመርያ የምትገኝ ሴት ከረሃብ ጋር በተገናኘ ምክንያት መሞትዋ ገልፀውልናል። 

ከመቐለ ውጭ በሽረ እና ዓብይ ዓዲ ከተሞች የሚገኙ ተፈናቃዮችም ለረዥም ግዜ እርዳታ ባለማግኘታቸው ለከፍተኛ ረሃብ ተጋልጠው እንዳለ ይገልፃሉ። በሽረ ፀሃዬ ትምህርት ቤት ተጠልለው ያሉ አቶ ገብረአምላክ የተባሉ ያነጋገርናቸው ተፈናቃይ በበኩላቸው ከግንቦት ወር ወዲህ ባለው ግዜ እርሳቸው የሚያውቋቸው በርካቶች በረሃብ ምክንያት መሞታቸው ይናገራሉ። 

ርዳታው መቋረጡ ችግሩን አባብሶታል

በትግራይ ክልል ተፈናቃዮች በከፊል
በትግራይ ክልል ተፈናቃዮች በከፊል ደሳሳ መጠለያዎች ፊት ይታያሉምስል Million Haileselasie/DW

ሌላው በማይወይኒ የተፈናቃዮች መጠልያ ያለው ሁኔታ የገለፁልን ተፈናቃይ መብራህቱ ወልደአረጋይ የምግብ ርዳታ አቅርቦት ክልከላው ከቀጠለ ካለፈው በባሰ መጪው ጊዜ ይበልጥ አሳሳቢ ነው ይላሉ። አቶ መብራህቱ "በእኛ መጠልያ እንኳን፥ በረሃብ ምክንያት እግራቸው ያበጠ፣ ለበሽታ የተዳረጉ፣ ከአልጋ የማይነሱ በርካቶች አሉን። ህፃናት ተርበው ሲያለቅሱ ነው የሚውሉት። አንዳንድ በጎ ፍቃደኛ እየመጡ ከሚሰጡን የተወሰነ ምግብ ውጪ ይህ ነው የሚባል ርዳታ የለም። በዚህ ከቀጠለ እየመጣ ያለው የከፋ አደጋ መሆኑ አሁን ላይ ሆኖ መመልከት ይቻላል" ይላሉ።

ዓለምአቀፍ ለጋሾች ተፈናቃዮች ጨምሮ በትግራይ ለሚገኙ ርዳታ ፈላጊዎች ያቀርቡት የነበረ ርዳታ መጭበርበሩ እና መዘረፉ ተከትሎ፣ አቅርቦቱ ካቋረጡ ከ8 በላይ ወራት አልፈዋል። የፌደራሉ መንግስት እና የክልሉ አስተዳደር ጨምሮ ሌሎች አካላት የተቋረጠው የምግብ እርዳታ አቅርቦት እንዲቀጥል በተደጋጋሚ ጥሪ ያቀርባሉ።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ-እግዚአብሔር