«ትግሌ» ሂስ የታከለበት ህትመት | ባህል | DW | 04.02.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

«ትግሌ» ሂስ የታከለበት ህትመት

ከጎርጎሪዮሳዊዉ 1933ዓ,ም እስከ 1945 ጀርመንን የገዛዉ አምባገነን መሪ የግዛቱን ሥርዓት በተመለከተ አሳትሞት የነበረዉ መጽሐፍ ከሞተ ከ 70 ዓመታት በኋላ ከምሑራን ትችትና ማብራርያ ጋር ዳግም ታትሟል። እንዳይታተም ታግዶ የነበረዉና «ትግሌ» የሚል ርዕሥ የያዘዉ ይህ መጽሐፍ የበርካታ አንባብያንን ትኩረት እንደሳበም ነዉ የተነገረለት።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 17:06

«ትግሌ» ሂስ የታከለበት ህትመት


ስለመጽሐፉ ዝርዝር የዶይቼ ቬለዋ ሃይከ ሙንደ የዘገበችዉን ይዘን፤ በጀርመን ታዋቂ ከሆኑት ደራሲና የታሪክ ምሁር ልጅ ዶክተር አስፋወሰን አስራተ ጋር ቃለ-መልልስ አድርገን መሰናዶ ይዘናል ።

«ትግሌ» ሂስ የታከለበት ህትመት ይላል በጀርመን ሃገር በሁለት ጥራዝ የቀረበዉና ስድስት ኪሎ የሚመዝነዉ የአዶልፍ ሂትለር ዳግም የታተመዉ መፅሐፍ። መጸሐፉን ለአንባብያን ለመጀመርያ ጊዜ ለማስተዋወቅ የተደረገዉ ዝግጅት ራድዮ ጣብያችን በሚገኝበት፤ በቦን ከተማ በሚገኝዉ የታሪክ ቤተ- መዘክር «Haus der Geschichte» ዉስጥ ነበር። በዚህ የመጽሐፍ ማስተዋወቅያ ሥነ-ስርዓት ላይ እጅግ በጉጉት የተሞሉ ወደ 500 የሚሆኑ ሰዎች ተገኝተዉ ነበር።ሥነ-ስርዓቱ ላይ ቦታ ለመያዝ የነበዉ ግፍያም ከፍተኛ እንደነበረ ነዉ የተገለፀዉ፤ የተዘጋጀዉ አዳራሽ ባለመብቃቱ ዝግጅቱ በታሪክ ቤተ-መዘክሩ መግቢያ ላይ በሚገኘዉ ኮሪደር ለእድምተኛዉ በስክሪን እንዲተላለፍም ተደርጎ ነበር። በዝግጅቱ ላይ ከሙንሽን የመጽሐፉ አሳታሚ ድርጅትና የፕሮዤዉ ተጠሪ ክርስትያን ሃርት ማን፤ የሙንሽን የታሪክ ተቋም ዳይሬክተር አንድርያስ ቪርሺንግ፤

እንዲሁም ከሃይደልበርግ ዩንቨርስቲ የስነ-ጽሑፍ ጉዳዮች ተመራማሪዉ ሂልሙት ኪዝል ተጋብዘዉ ነበር። በዝግጅቱ የመድረክ መሪ የነበሩት የፊደራል ጀርመን የታሪክ ቤተ-መዘክር ፕሬዚዳንት ቫልተር ሁተር ከጎርጎረሳዉያኑ ጥር 8, 2015 ዓ,ም ጀምሮ ገበያ ላይ የዋለዉ ይህ አዲስ ህትመት የአንባብያንን ቀልብ መሳቡን ተናግረዋል።ይህ ሁለት ጥራዝ መጽሐፍ ለገበያ በቀረበ በመጀመርያዉ እለት ብቻ 4000 ሺህ ጥንድ ጥራዝ ተሸጦአል። መጽሐፉን ለመግዛት የሚፈልገዉ ሰዉ ቁጥር በመጨመሩ ለሁለተኛ ጊዜ 15 ሺህ መጻሕፍት ታትሞአልም፤ በቀጣይ የገዥዉ ቁጥር በመጨመሩ ለሦስተኛ ህትመት ዝግጅት ላይ መሆኑን ቫልተር ሁተር ተናግረዋል። የዚህ መጽሐፍ ይዘት ምን ይሆን? ከርዕሱ ጀምሮ እንዲያስረዱን በጀርመን ታዋቂ የሆኑት ደራሲና የታሪክ ምሁር እንዲሁም የአፍሪቃና መካከለኛዉ ምስራቅ ጉዳዮች አማካሪ ልጅ ዶክተር አስፋወሰን አስራተን ጠይቀናቸዉ ነበር።


«Mein Kampf የኔ ትግል ማለት ነዉ። የኔ ትግል ብሎ አዶልፍ ሂትለር መጽሐፍ ያወጣዉ በእስር ቤት ለስምንት ወራት ከሚያዝያ 1924 -- ታህሳስ 1924 ዓ,ም ባሉት ጊዜያት በቆየበት ጊዜ ነዉ። ለመታሰር የበቃዉ ደግሞ ያካሄደዉ መንግሥት ግልበጣ ስላልተሳካለት ነዉ። ይህ ትግሌ ብሎ አርስት የሰጠዉ መጽሐፍም በደቡባዊ ጀርመን ባቫርያ ዉስጥ ባለዉ ላንድስ በርግ በምትባል ከተማ በሚገኝ እስር ቤት ዉስጥ ሆኖ ነዉ። ጸሐፊዉ እሱ ይሁን እንጂ በእጁ እንዲተይብ ያደረገዉ በዛን ጊዜ የእሱ ጸሐፊ የነበረዉ ሩዶልፍ ሂስ የተባለዉ ጀርመናዊ ነዉ። በኋላ የናዚ ፓርቲ የሂትለር ምክትል ሆኖ ፓርቲዉን ሲመራ ነበር። በመጨረሻም በማይታወቅ ሁኔታ የሁለተኛዉ ዓለም ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ለሚስጥር ጉዳይ ተብሎ ወደ እንግሊዝ አገር ሄዶ እዝያ አዉሮፕላን ወድቆ ከዝያ በኋላ መጀመርያ በእንጊሊዝ ከዝያ በኋላ፤ ያዉ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት በኋላ በርሊን ዉስጥ ታስሮ የሞተ ሰዉ ነዉ። የመጽሐፉ አወጣጥና አመጣጥ ይህ ነዉ። »እንግዲህ እንደነገሩን አዶልፍ ሂትለር ሊያካሂድ የነበረዉ የመንግሥት ግልበጣ ባለመሳካቱ ምክንያት ለእስር ተዳርጎ ነዉ በስምንት ወር ጊዜ ዉስጥ ነዉ፤ አንደኛዉን የመጽሐፍ ክፍል የፃፈዉ። ሁለተኛዉን የመጽሐፍ ክፍል የፃፈዉ ደግሞ ስልጣን ከያዘ በኋላ ስልጣን ላይ ሳለ እንደሆነ ነዉ የተነገረዉ፤ እና ይህ እንዴት ነዉ?

«ትክክል ነዉ መቼም መጽሐፉን ያነበበዉ ሰዉ መጽሐፉ በጣም ችክ ያለ አስቸጋሪ አጻጻፍ እንደተጻፈ ይረዳል። እኔ ጀርመን ሃገር እንደመጣሁ በ 1940 ዓ,ም እንግሊዝ ሃገር የታተመን መጽሐፍ ጥንታዊ ጽሑፎች መሰብሰብያ ቤተ-መዘክር ዉስጥ አግንቺ ነዉ ያነበብኩት። አቀራረቡና ጽሑፉ ችክ ባለ አገላለጽ የቀረበ ነዉ። ከሁሉ በላይ የመጽሐፉ እንብርት ምንድን ነዉ ብለን የጠየቅን እንደሆነ ፤ ለአይሁድ ሕዝብ ያለዉን ጥላቻ ነዉ በመጽሐፉ ያስቀመጠዉ። ለጀርመን ኤኮኖሚ ቀዉስና ችግር አይሁዶች ናቸዉ ሲል ይኮንናል፤ አንደኛዉ የዓለም ጦርነት እንዲቀሰቀስ ያደረጉት በዓለም ላይ የሚገኙት የአይሁድ መሪዎች ናቸዉ ሲልም በመጽሐፉ አስቀምጦአል። ሂትለር ይህን ጥላቻ ነዉ ለጀርመን ሕዝብ ያበረከተዉ። እናም በመጨረሻ እነዚህ ሰዎች ካልጠፉ አዉሮጳ ዉስጥ ሰላም አይገኝም በሚል ነዉ መጽሐፉን የሚደመድመዉ። ሂልተር በስልጣን ላይ ሳለ ይህን እዉን አድርጎአል። ተሰምቶ በማይታወቅ አገዳደል ስድስት ሚሊዮን አዉሮጳዉዊ አይሁዳዉያን ሕይወታቸዉን በማጎርያ ካንፕ እንዲያልፍ አድርጎአል። »

ይህ መጽሐፍ ከወጣ በኋላ ደግሞ ጀርመንን በተቆጣጠሩት በእነዚህ አራቱ ኃያላን ሃገራት ማለት በዩኤስ አሜሪካ፤ ሩስያ፤ እንግሊዝና ፈረንሳይ እንዳይታተም ተከልክሎ ነበር። አሁን ደግሚ ለህትመት በቅቶአል። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?
« መከልከሉ በዝያን ጊዜ ትክክክል ነዉ ያኔ ሀገር ሁሉ ባለመርጋቱ ነዉ ኃያላኑ ሃገራት መጽሐፉ እንዳይታተም የከለከሉት። አሁን ለህትመት የደረሰዉ በጀርመን ህግ መሰረት አንድ ሰዉ መጽሐፍ ሲጽፍ ለ 70 ዓመታት የደራሲዉ መብት የተጠበቀ ነዉ። ከሰባ ዓመት በኋላ ግን የማሳተም መብቱ ስለሚነሳ ፤የአዶልፍ ሂትለር መጽሐፍም ከሰባ ዓመት በኋላ ነዉ በጀርመን ህግ መሰረት ፈቃድን አግኝቶ እንዳለ ሳይሆን አዲሱ ትዉልድ እንዳይታለል ከትችትና ከማብራርያ ጋር በአዲስ ለመታተም የበቃዉ። መጽሐፉ በታወቁ ምሁራንና የታሪክ አዋቂዎች መክረዉበት ማብራርያቸዉን አክለዉበት ነዉ ለአንባቢያን የቀረበዉ። »እርሶ እንደጠቀሱት ዘገባዎችም እንዳሳዩት ይህ መጽሐፍ በጀርመን ሃገር ከማብራርያ ጋር ነዉ የወጣዉ ።ግን በሌላዉ ዓለም ሃገራት ትክክለኛዉ ቅጅ በቋንቋቸዉ ተተርጉሞ መጽሐፍ መደብር መግዛት እንደሚቻል ነዉ የተመለከተዉ። በሌላ በኩል ይህ መጽሐፍ የአንባብያንን ቀልብ በመሳቡ የገዥዉ ቁጥር እጅግ ከፍተኛ መሆኑም ተገልጾአል።

«አዎ ሌሎች ሃገር ዉስጥ ለምሳሌ በእንጊሊዘኛ ድሮም ጀምሮ ነበረ። በስዊድን ቋንቋም ተተርጉሞአል፤ በሌሎችም የአዉሮጳ ቋንቋዎች ተተርጉሞአል። እነዚህ ሃገራት በቀጥታ የተተረጎመዉ ቅጂ እንዲገኝ ያደረጉበት ምክንያት ምናልባትም ይህ ምንም አይነት ነገር አይመጣብንም፤ በርግጥ ሃገር ዉስጥ አንዳንድ እብድ ቢኖርም የሃገሪቱን ፀጥታ ሊነሳ የሚችል ኃይል አይኖርም፤ የሚል መንፈስን ስለያዙ ነዉ፤ በሌሎች የአዉሮጳ ሃገራት እንዲታተምና ለአንባቢ እንዲቀርብ የተደረገዉ።»
እና ይህ መጽሐፍ እዚህ ጀርመን ዉስጥ ለትምህርት ለማገናዘብያ ጥቅም ላይ እንደሚዉል ተመልክቶአል። ይህን እንዴት ያብራሩልናል? እንዴትስ ይገለጻል?


«ትክክል ነዉ። ጀርመኖች መቼም ስለ ሁለተኛዉ ዓለም ጦርነት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በታሪክ በትምህርት መልክ መሰጠት የተጀመረዉ በእኔ እድሜ ነዉ፤ ማለት እችላለሁ። እንዲያዉም በዉጭ ያሉት የጀርመን ትምህርት ቤቶች ጀርመን ሃገር ካሉት ትምህርት ቤቶች ይልቅ ልቀዉ ይገኛሉ። እኔ በ 1968 ዓ,ም ወደ ጀርመን ሃገር ስመጣ ስለ ናዚ አገዛዝና ስለ ሂትለር ፤ ስለ ሁለተኛዉ ዓለም ጦርነት በደንብ አዉቅ ነበር። የገረመኝ የኔ ጓደኞች የሆኑ በጀርመን ሃገር ትምህርታቸዉን የተከታተሉ፤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን ሲያጠናቅቁ በታሪክ የተማሩት እስከ አንደኛዉ የዓለም ጦርነት ድረስ ብቻ ነዉ። እናም በጀርመን ከ 70 ዎቹ ዓመታት በኋላ ነዉ በት/ቤትም ሆነ በሰፊዉ የዚህ የ 2 ተኛዉ ዓለም ጦርነት ጉዳይና ስለ ሂትለር ሁኔታ ማንኛዉም ርመን እንዲያዉቀዉ የተደረገዉ። በዚህ ረገድ ሆሎኮስት የሚባለዉ ፊልምና ሌሎች ሁለተኛዉን የዓለም ጦርነት አስመልክቶ የተሰሩ የሆሊዎች ፊልም ተዋንያን የሚጫወቱበት ፊልም በ 70 ዎቹ መጀመርያ ላይ በ 1974 ዓ,ም አካባቢ ሲታይ በህዝብ ዘንድ የመጣዉ አስተሳሰብና ትምህርት የብዙዉን የጀርመን ህዝብ ዓይን የከፈተ ነዉ ማለት ይቻላል። እስከዝያ ድረስ ግን አብዛኞቹ እድሚያቸዉ ገፋ ያሉ ጀርመናዉያን አዎ ተገደን ነዉ፤ ሌላ ምን የማድረግ አማራጭ ነበረን? ምን እናድርግ ? የዉጭዉ ጭቆና ስለበዛብን ነዉ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ላይ የደረስነዉ እያሉ ምክንያት ይፈልጉ ነበር። ያ ፊልም ከታየ በኋላ ሁሉም ትዉልደ ጀርመኖች በእዉነቱ ዓይናቸዉን መክፈት ጀመሩ ማለት ይቻላል። እና እንደኔ አስተሳሰብ ይህ የናሽናል ሶሻሊዝም ስርዓት የማይመጣበት አንድ የዓለም ሃገር አለ ብዩ ብናገር ጀርመን ነዉ፤ ብዩ በርግጠኝነት መናገር እችላለሁ። በርግጥ አሁንም ቢሆን 1- 2 % የሚሆኑ አንዳንድ እብድ ድርጅቶች አሉ። ነገር ግን ከኔ ትዉልድ በኋላ የመጣዉ ጀርመን በአብዛኛዉ 95 % ማለት ይቻላል ከዚህ ነጻ ነዉ»


ሂትለር ትዉልዱ ኦስትርያዊ ነዉ ግን ጀርመን ሃገር መጥቶ ይህን ክስተት ማካሄድ የቻለበት ተቀባይነት ያገኘበት ነገር ምንድን ነዉ?
« አንደኛ ኦስትርያ ይወለድ እንጂ በ 1ኛዉ የዓለም ጦርነት የተዋጋዉ የጀርመንን መለዮ ለብሶ ነዉ። ሁለተኛ እርግጥ በጎርጎረሳዉያኑ 1924 ዓ,ም መንግስት ግልበጣ አድርጎ እስር ቤት ሲደርስ የዛን ጊዜ የኦስትርያ ተወላጅ ቢሆንም ወደ 29 – 30 ዓመት ሲሞላዉ ብራዉን ሽቫይግ የምትባል የጀርመን ከተማ ዉስጥ የጀርመን ዜግነትን እንዲያገኝ ተደርጎአል። ስለዚህ 1933 ዓ,ም ስልጣን ላይ ሲወጣ ምርጫ ሲደረግ የጀርመን ዜግነትን ይዞ ነበር።»
ጀርመን በናዚ ታሪክ አንገቱን የደፋበት ነዉ። ግን አሁን ጀርመኖች በዓለም የፖለቲካዉም ሆነ የኤኮነሚ መድረክ ቀደምቱን ቦታ የያዙ ናቸዉ። አሁን በዓለማችን በተከሰተዉ የስደተኞች ቀዉስም ከፍተኛ ሰብዓዊነት በማሳየታቸዉ በዓለም ከፍተኛ ክብርን አግኝተዋል። ግን የዚህ መጽሐፍ መታተም ለጥቂት ቀኝ አክራሪዎች ጥንካሪ ይሰጣቸዉ ይሆን ብለዉ ያምናሉ?
« በፍጹም እስከዛሬ ድረስ የሂትለር ተከታዮች ነን ብለዉ የሚናገሩ «NDP» ን የመሳሰሉ ፓርቲዎች በጀርመን እስካሁን ድረስ ምንም ያመጡት የፈየዱት ነገር የለም። በጣም ቀኝ ክንፍ የምንለዉ ፓርቲ በየምርጫዉ እንዳንየዉ ከ 3 -4 % በታች ድምጽን ነዉ የሚያገኙት። ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ የመጽሐፉ መታተም በጀርመን ለዉጥ ያመጣል ብዬ ጨርሶ አላስብም ። ጀርመን አሉ ከሚባሉ የዲሚክራሲ ሥነ-ስርዓት ከሰፈነባቸዉ የዓለም ሃገራት ዉስጥ የመጀመርያዉን ቦታ ይዛ የምትገኝ ሃገር ናት ብዩ አምናለሁ። »


2000 ገጾች ያሉትና «ትግሌ» የሚል ስያሜን የያዘዉ ዳግም ከምሁራን ማብራርያና ትችት ጋር በአዲስ ታትሞ ከሦስት ሳምንት በፊት አንባብያን እጅ የደረሰዉ የሂትለር መጸሐፍ ሳይንሳዊ ማብራርያ የታከለበት 3500 የግርጌ ፍችን እንደያዘ መጸሐፉን እንደገና ያሳታሙት የታሪክ ምሁራን ቡድን መሪ ክርስትያን ሃርትማን ተናግረዋል። ሂትለር ያሳተመዉ ዋናዉ መጽሐፍ 780 ገጾች እንዳሉትም ተዘግቦአል። «ትግሌ» ሂስ የታከለበት ህትመት በሚል ስለወጣዉ መጽሐፍ በጀርመን ታዋቂ ከሆኑት ደራሲና የታሪክ ምሁር ልጅ ዶክተር አስፋወሰን አስራተ ጋር ያደረግነዉን ሙሉ ቃለ-መልልስ የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ


ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic