ትውልደ ኢትዮጵያውያን በብሔራዊ ቡድን ተሳትፎ | ስፖርት | DW | 22.04.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

ትውልደ ኢትዮጵያውያን በብሔራዊ ቡድን ተሳትፎ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከረጅም ዓመታት በኋላ ለአፍሪቃ ዋንጫ ባለፈበት ወቅት ቡድኑን በማጠናከር ውጭ ያሉ ጥቂት ተጫዋቾች ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር ተቀላቅለው ነበር። እንደበርካታ የስፖርት ቤተሰብ እምነት በቡድኑ ውስጥ የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:12

ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንዲጫወቱ ፕሮፖዛል አስገብቻለሁ ምላሽ አላገኘሁም

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከረጅም ዓመታት በኋላ ለአፍሪቃ ዋንጫ ባለፈበት ወቅት ቡድኑን በማጠናከር ውጭ ያሉ ጥቂት ተጫዋቾች ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር ተቀላቅለው ነበር። እነዚሁ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች እንደበርካታ የስፖርት ቤተሰብ እምነት በቡድኑ ውስጥ የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል።  ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን በብሔራዊ ቡድን አካቶ ማጫወቱ እንደተፈለገው እየተሠራበት እንዳልሆነ ነው የሚነገረው። ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ውስጥ ከተካተቱት ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች አንዱ ዴቪድ በሻህ ነው። ዴቪድ በሻህ የተወለደው ጀርመር ኮሎኝ ከተማ ነው። ዴቪድ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንና በኢትዮጵያ ቡና ክለብ ለሁለት ዓመታት የእግር ኳስ ሕይወቱን አሳልፏል። በጉልበት ጉዳት ከሦስት ዓመት በፊት እግር ኳስን ያቆመው ዴቪድ በአሁኑ ሰዓት የእግር ኳስ የማማከር ሥራን ይሰራል። ዴቪድ እንደሚለው ከብዙ ልፋት በኋላ በውጭ ሀገራት የሚጫወቱ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እግር ኳስ ተጫዋቾችን አድራሻ አሰባስቦ ለብሄራዊ ቡድኑ ተሰልፈው እንዲጫወቱ ከአስር ወራት በፊት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አድራሻቸውን የያዘ ዝርዝር ፕሮፖዛል አስገብቻለሁ ሆኖም ምንም ምላሽ አላገኘሁም ይላል። «አስር ወር በፊት ለፌዴሬሽን ፕሮፖዛል ሰጥቻለሁ፤ ስካውቲንግ ዲፓርትመንት ለመክፈት። ከኢትዮጵያ ውጭ የሚጫወቱ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለብሄራዊ ቡድኑ እንዲጫወቱ ለማድረግ ምንም የአድራሻ ግንኙነት የለም። እኔ ይሄንን ክፍተት ለመሙላት በመፈለጌ ምክንያት ስካውት ዲፓርትመንት መስራት አስቤያለሁ። በተለያዩ ሀገራት የሚጫወቱ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን 33 ያህል ተጫዋቾች አግኝቻለሁ።» ዴቪድ እንደሚለውም የመጀመሪያው ደብዳቤ ልናገኘው አልቻልንም በሚል ከሶስት ወራት በፊት በድጋሜ ደብዳቤ እንዳስገባ ይናገራል። ዴቪድ ከፌዴሬሽኑ ጋር በጋራ አብሮ የመስራት ሀሳብ እንዳለው እንጂ ምንም ጥቅም እንዳማይፈልግ፤ ሆኖም የፌዴሬሽኑን ሎጎ የሚፈልገው ለተጫዋቾች ምልመላ ይረዳው ዘንድ ለሚኖረው የደብዳቤ ግንኙነት ብቻ እንደሆነ ይገልጻል። «በነጻ ለመስራት ነው፤ ምንም ክፍያ አልፈልግም። ሎጎውን ለምጠቀመው ለስካውት ዓላማ ለመጠቀም ብቻ ነው። ኢሜል ወይም ደብዳቤ ላይ ለስካውቱ ስራ ማለት ነው። ፕሮፖዛሉ ላይም በጽሁፍ ተቀምጧል። ቴክኒክ ኮሚቴም የህግ ባለሙያም አግኝቻለሁ። ተነጋገርን ከዛ ግን ምንም መልስ አልተሰጠኝም። በስልክም እዛም ሄጄ አናግሬአለሁ፤ ሁሉንም ሞክሪያለሁ።»

እንደ አቶ ባህሩ ጥላሁን ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ፕሮፖዛሉ ተቀባይነት ቢያገኝም በፌዴሬሽኑ ሎጎ መጠቀም የሚለው ግን በዚህ መልክ ሊያሰራ እንደማይችልና ጉዳዩ ህግ ክፍል እንዳለ ገልጸዋል። ሆኖም የጉዳዩ ባለቤት የሆነው ዴቪድ አዲስ ከመጡ የፌዴሬሽኑ ሃላፊዎች ጋር በአካል ተገናኝቶ እንዳልተነጋገር ተናግረዋል። «ምንም እንኳን ስራውና ሃላፊነቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቢሆንም እንደዚህ አይነት ቅንነትና ፍላጎት ካለ በሚል ተቀባይነት በማግኘት ጉዳዩ ለህግ ክፍል ገባ። በፌዴሬሽኑ ሎጎ መጠቀም የሚሉ ነገሮች ተቀምጠዋል። እነዚህ ነገሮች ደግሞ አንድ ህጋዊ ተቋም ከህግ አንጻርም ትክክል ስላልሆነ ይሄን ለማድረግ እንቸገራለን የሚል ነገር ነው የነበረው። እዛ ላይ እንደቆመ ነው። የጽ/ቤት ሃላፊዎች ስላሉ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት ግንኙነት አልፈጠረም በቀጥታ ወደ ሚዲያ ነው የሄደው። አሁን እኛ በራችን ክፍት ነው፤ መተው ማነጋገር የሚቻልበት እድል አለ» የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በውጭ ሀገራት የሚጫወቱ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች በብሄራዊ ቡድን ለማሳተፍ ጥሪ የሚያደርገው አንዳንድ ሰዎች በሚሰጡን ጥቆማና በአጋጣሚዎች በምናገኘው አድራሻ በቀጥታ ግንኙነት እያደረግን ነው ይላሉ አቶ መኮንን ኩሩ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቴክኒካል ዳይሬክተር። «ጀርመን ፣  ፈረንሳይ ፣ ጣሊያን የሚጫወቱ በርካታ ስም ያላቸው ልጆች አሉ። እንግዲህ የተገኙ አማራጮችና አጋጣሚዎች በመጠቀም እነዚህ ልጆች ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እንዲያገለግሉ የመስራት ስራዎችን እንሰራለን።» የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች የሆነው ዴቪድ በሻህን 38 በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚጫወቱ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾችን ዝርዝር ፕሮፖዛል የማስገባቱን ጉዳይ እንዲህ ይላሉ። «ኤጀንሲ ከፍቶ እየተንቀሳቀሰ ያለበት ሁኔታን አስታውሳለሁ። አባትና ልጁን አግኝቻቸው አውርተን ነበር። ወደ ጽ/ቤት ሄዶ ነበር። ከዛ በሃላ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ አላውቅም።  እውቀትና ልምድ ያላቸው ዝግጁ የሆኑ ተጫዋቾች ናቸው። ብሄራዊ ቡድናችንን ከማጠናከር አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብዮ ነው የማስበው።» ስራው ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጠቃሚ መሆኑን ገልጸው፤ ብሄራዊ ቡድኑን ከማጠናከር አንጻር አስተዋጽኦ እንዳለው አቶ መኮንን ያምናሉ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ህጉ አይፈቅድም ባለው የሎጎ ጉዳይ ላይ ዴቪድ በሻህ ተጠይቆ፦ ያለሎጎም መስራት እንደሚችል ተናግሯል። በተጨማሪም ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ተጫዋቾች በኢትዮጵያ የብሄራዊ ቡድን ለመጫወት ለውድድር ብቻ የሚያገለግል የኢትዮጵያዊ ዜግነት ፓስፖርት ተሰጥቸው እንደሚጫወቱ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ይገልጻሉ። ይኽንን ለማጣራት ፌዴሬሽኑን ጠይቀን ነበር። በወቅቱ የነበሩ አካላት ምላሽ ሊሰጡበት ይችላሉ እኔ እስካለሁበትና መናገር የምችለው የኢትዮጵያ ፓስፖርት የሌለው ሰው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ወክሎ መጫወት አይችልም ሲሉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ባህሩ ጥላሁን ምላሽ ሰተውናል።


ነጃት ኢብራሒም
ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች