ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሳይንቲስት | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 25.02.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሳይንቲስት

ፕሮፌሰር ሶስና ሀይሌ ይባላሉ።የቁስ ሳይንስና የምህንድስና ሊቅ ሲሆኑ፤የመጀመሪያውን ጠጣር የአሲድ ነዳጅ ለዓለም ያስተዋወቁ ሳይንቲስት ናቸው።ከዚህ በተጨማሪ በዘርፉ ከ200 በላይ የምርምር ፅሁፎችን አሳትመው በ14ቱ የባለቤትነት መብት አግኝተዋል። በሳይንሱ ዘርፍ ባበረከቱት አስተዋፅኦም የበርካታ ሽልማቶች ባለቤት ናቸው።

ፕሮፌሰር ሶስና ሀይሌ፤ ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የሳይንስ ሊቅ

ፕሮፌሰር ሶስና ሀይሌ ትውልዳቸው አዲስ አበባ እድገታቸው ደግሞ አሜሪካን ሀገር ነው።ፕሮፌሰሯ የቁስ ሳይንስና የምህንድስና ሊቅ ሲሆኑ፤የመጀመሪያውን የጠጣር የአሲድ ነዳጅ ለዓለም ያስተዋወቁ ሳይንቲስት ናቸው።ከዚህ በተጨማሪ በዘርፉ ከ200 በላይ የምርምር ፅሁፎችን አሳትመው በ14ቱ የባለቤትነት መብት አግኝተዋል።ለነዚህ ስራዎቻቸውም በርካታ ሽልማቶችን አግኝተዋል።የዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዝግጅት እኝህን ሳይንቲስት ያስተዋውቃል።
ፕሮፌሰር ሶስና  ሀይሌ በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆኑ አሜሪካዊ የቁስ ሳይንስና የምህንድስና ሊቅ ናቸው።ያም ሆኖ ስኬታቸው አልጋ በአልጋ አልነበረም።በኢትዮጵያ በ1966 ዓ/ም በነበረው አብዮት አባታቸው እውቁ የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ጌታቸው ሀይሌ የደርግን መንግስት በመቃወማቸው የጥቃት ሰለቫ በመሆን ክፉኛ ቆስለው ለህክምና ከነ ቤተሰባቸው ሀገር ለቀው ሲወጡ ፕሮፈሰር ሶስና ገና የ10 ዓመት ልጅ ነበሩ።የአባታቸው ክፉኛ መጎዳትና የዕድሜ ልክ የአካል ጉዳተኛ መሆን የመጡበት ሀገር የተለየ ባህል፣ ቋንቋና የቀለም ልዩነት በዚያ በልጅነት  ዕድሚያቸው የተጋፈጡት አሁንም ድረስ የሚያስታውሱት ፈተና ነበር። 
«እውነት ለመናገር ልጆች የበለጠ ችግርን ይቋቋማሉ  ብዬ አስባለሁ። አላውቅም። ማለቴ  ተቋቋምነው።በእርግጥ በጣም አስቸጋሪ ጊዜ ነበር።ነገር ግን ለወላጆቼ የበለጠ ከባድ ጊዜ ነበር ብዬ አስባለሁ። በጣም በልጅነት ዕድሜዬ ነው  ዩኤስ መኖር የጀመርኩት።ትንሽ ትንሽ አስታውሳለሁ።ብዙ አስፈሪ አልነበረም ።ነገር ግን በጣም እንግዳ ነገር ነበር።ኢትዮጵያ የት እንደምትገኝ የሚያውቅ የለም።ትምርት ቤት መስራት ይችላሉ ብለው አይጠብቁም።ወደ መካከለኛ ክፍል ይወስዱናል።ግን ተቋቋምነው።አሰቃቂ የሆነብኝ የሀገርና የማኅበረሰቡ ፍራቻ ሳይሆን በአባቴ ላይ የደረሰው ነው።»


ይህንን ፈተና ተቋቁመው ግን ፕሮፌሰር ሶስና  በቁሳዊ ሳይንስና በምህንድስና በጎርጎሪያኑ 1986 የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን  ከአሜሪካው የማሳቹሴት የቴክኖሎጅ  ዩንቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በ1988 ከካሊፎርኒያ በርክሌይ ዩንቨርሲቲ እንዲሁም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በ1992 ከማሳቹሴት ዩንቨርሲቲ በተመሳሳይ የትምህርት መስክ አግኝተዋል። 
 በንድፈ ሀሳብ የቀሰሙትን ዕውቀት ወደተግባር ለመለወጥም በታዳሽና በዘላቂ የሀይል አቅርቦት ቴክኖሎጂ ዘርፍ በርካታ ምርምሮችን አድርገዋል።በጎርጎሪያኑ  1990ዎቹ መገባደጃ ላይም «ሱፐር ፕሮቶኒክ» የተባለ አዲስ ውህድ በመጠቀም የመጀመሪያውን ጠጣር የአሲድ ነዳጅ  በእንግሊዝኛው አጠራር  «ሶሊድ አሲድ ፊውል ሴል»በመፍጠር ለዓለም አስተዋውቀዋል።እሳቸው እንደሚሉት ፈጠራው ከሀይል አማራጭነቱ በተጨማሪ የአካባቢ ብክለትን የሚከላከል ጭምር ነው።
«የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጫ መንገድ ነው።ስለዚህ በኢንዱስትሪ በበለፀገው ዓለም የቅሪተ አካል ነዳጅን እንጠቀማለን።ፔትሮሌምን፣ ዘይትን የድንጋይ ከሰልን፣ ፣የተፈጥሮ ጋዝ እና ነዳጅ እንጠቀማለን። እኔ የፈጠርኩት ግን መኪናዎች ከሚጠቀሙት ተለምዷዊ ሞተር ጋር ሲነፃፀር በጣም ንፁህ በሆነ መንገድ የኤሌክትሪክ ኃይልን ማመንጨት የሚችል ነው። መኪና የሚንቀሳቀሰው ውስጡ ያለውን ነዳጅ በማቃጠል ነው። ይህ ሂደት ብዙ ብክለትን ያስከትላል። ስለዚህ  ጠጣር ነዳጁ  ኤሌክትሪክ  እንዲያመርት በማድረግ በተለየ መንገድ የመጠቀም ዘዴ ነው ።ያም  በአከባቢ ጥበቃ ረገድ የበለጠ ዘላቂ ነው።»  


ፈጠራው በመላው ዓለም እየጨመረ የመጣውን የኤለክትሪክ ሀይል ፍላጎት ለማሟላት አስፈላጊ ሲሆን፤፤እንደ ኢትዮጵያ ታንዛኒያና ዩጋንዳ ላሉ ብዙ የፀሐይ ብርሃንና  የውሃ ኃይል  ላላቸው የምስራቅ አፍሪቃ  ሀገራት የኤለክትሪክ ሀይል አቅርቦትን ለማሻሻል የሚያስፈልገው፤የተሻለ የኤሌክትሪክ ፍርግርግ  ወይም ደግሞ የሀይል ማከማቻ ቢሆንም፤  በተለያዬ ሁኔታ የውሃ መቀነስ ቢያጋጥም፤እሳቸው የፈጠሩት የሀይል አማራጭ  እንደ ባትሪ ሊያገለግል እንደሚችልም ያስረዳሉ።
«እውነት ለመናገር ያለው  የውሃና የፀሀይ ሀይል አቅም የሀይል ፍላጎትን ለማሟላት በቂ  ነው።የሚያስፈልገው የሀይል ማከማቻ ነው። በተለይ ለፀሀይ ሀይል።የውሃ ሀይልም ቢሆን የተወሰኑ ዓመታት ዝናብ ሊኖር  የተወሰኑ ዓመታት ደግሞ ዝናብ ሊጠፋ ስለሚችል፤የረዥም ጊዜ ማከማቻ ያስፈልጋል።ስለዚህ በቤተሙከራ የሰራናቸው መሳሪያዎችና ጠጣር የአሲድ ነዳጅ  ልክ እንደ ባትሪ ሊሰሩ ይችላሉ።ለአስፈላጊ  ጊዜ ሀይልን ያከማቻሉ።ያለ ብዙ ቴክኒካዊ ስራ የሀይድሮጅን ነዳጅ የመፍጠር አቅም አላቸው።ከዚያም የሀይድሮጅን ነዳጅ በመጠቀም ኤለክትሪክ ማምረት ይቻላል።» 
ሳይንቲስቷ ከጎርጎሪያኑ 1993 ጀምሮ በዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት፣ከ1996 ጀምሮ  በካሊፎርኒያ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት  የቁሳቁስ ሳይንስ ፕሮፌሰር በመሆን ለ 18 ዓመታት ያገለገለገሉ ሲሆን፤ በ2012 ዓ/ም በኢንጂነሪንግ እና በተግባራዊ ሳይንስ ክፍል ውስጥ ሊቀመንበር ሆነው ከተሾሙ ሁለት የመጀመሪያ ሴቶች አንዷ ናቸው። ከ 2015 ዓ/ም  ወዲህ ደግሞ በችካጎ በኖርዝ ዌስት  ዩኒቨርስቲ  በማስተማር ላይ ይገኛሉ።ከዚህ የማስተማር ስራቸው በተጨማሪ በፈጣን ባትሪዎች ፣መፈተሻዎች ወይም «ሴንሰሮች» የኤለክትሪክ ፓምፖች  እና ጠጣር የአሲድ ነዳጅ ላይ፣ «ቴርሞኤሌክትሪክ» እና «ፌሮኤሌክትሪክ»በተባሉ ሙቀትና ብረት ነክ  ኤለክትሪካዊ ቁሶች ላይ፣  እንዲሁም ለአነስተኛና ተንቀሳቃሽ  የሀይል ማመንጫዎች በሚሆኑ የመሣሪዎች  ላይ ምርምር ያደርጋሉ።አነስተኛ ዋጋ ባላቸው ግብዓቶች ላይ እሴት በመጨመር ወደ ምርት እንዲለወጥም ይሰራሉ። እነዚህ ስራዎቻቸው የሀይል አቅርቦትና አማራጭ መስክ ወደ አዳዲስ ግንዛቤ እና አፈፃፀም  እንዲሄድ አድርጓል።ከዚህ በተጨማሪ የፕሮፌሰር ሶስና ስራዎች በዓለም ላይ እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማርካት ነፋስንና የፀሐይ ብርሃንን በመጠቀም ረገድ አዳዲስ መንገዶችን ፈጥረዋል።ፕሮፌሰሯ በመስኩ ከ200  በላይ የምርምር ፅሁፎችን ያሳተሙ ሲሆን፤በ14ቱ  የባለቤትነት መብቶችን ይዘዋል ፡፡


በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ ዕድል ላላገኙ  የማህበረሰብ ክፍሎች በሳይንስ ዘርፍ የትምህርት እና የምርምር እድሎችን እንዲያገኙ በማድረግ ንቁ ተሳታፊ ናቸው።ከዚህ አኳያ   በሳይንሱ ዘርፍ የሴቶች ተሳትፎ  ዝቅተኛ መሆን ዓለምን ብዙ አሳጥቷል ይላሉ።
  «ዓለም በቀላሉ ሊጠቀምባቸው የሚችሉ ብዙ ነገሮች አሉ።ነገር ግን በዚህ አስፈላጊ ጥረት ውስጥ ግማሹን የዓለም ህዝብ አለማካተት  በጣም ብዙ ጠቃሚ ነገሮችን ያሳጣል።ለሴቶች ለራሳቸውም ይህ አስደሳች ሙያ ነው።አስፈላጊ ግንቶችን መስራት ዓለምን የመለወጥ ተፅዕኖ አለው። ስለዚህ ማንንም መከልከል ተገቢ አይደለም። እኔ ለሴቶች የምመክረው ሞክሩት ትወዱታላችሁ። ሌሎች አትችሉም እንዲሏችሁ አትፍቀዱ።እኔ ሁል ጊዜ በሆነ መንገድ አንዳንድ አስተማሪዎች የሆነ ነገር መስራት እንደማልችል ሲያስቡ፤ ያ በጣም ነው የሚያስደስተኝ።ምክንያቱም እነሱ የተሳሳቱ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በጣም  በርተቼ ነው የምሰራው።» 
በሙከራና በንድፈ-ሃሳባዊ ምርምር አማካኝነት መሰረታዊ የሳይንስ ዕውቀትን በማስጨበጥ ለሙያው ላባረከቱት አስተዋፅኦ በርካታ ሽልማቶችን አግኝተዋል።ከነዚህም ጥቂቶቹ  በሳይንሱ ዘርፍ ለሰው ልጆች ህይወት መሻሻል ላበረከቱት አስታዋፅኦ በጎርጎሪያኑ 2010 ካገኙት የሰብአዊነት ሽልማት ጨምሮ፤ በጎርጎሪያኑ 1994 የብሔራዊ ሳይንስ ፋውንዴሽን ብሔራዊ የወጣት ተመራማሪ ሽልማትን፣በ1997 ቲ ኤም ኤስ ሮበርት ላንሲግ ሃርዲ ሽልማትን፣በ2000 ዓ/ም ከአሜሪካ የሴራሚክ ማኅበረሰብ ሽልማትን፣ በ2001 ዓ/ም የጄ.ቢ.ዋግነር ሽልማት ከኤለክትሮ ሜካኒካል ማኅበረሰብ  ተሸልመዋል። በማስተማርና በማማከር ስራ ላቅ ያለ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የቁስ ሳይንስና የምህንድስና የሳይንስ ሊቃውንት በአሜሪካዊ የቁስ ሳይንስ  ሊቅ ዴቪድ ተርንቡል ስም በሚሰጠው ሽልማትም የ2020 ተሸላሚ ናቸው።


የዓለም አቀፍ የቁስ ሳይንስ ምርምር ማህበረሰብ፣የአፍሪካ እንዲሁም  የኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚ ባልደረባም ናቸው።ፕሮፌሰር ሶስና ሀይሌ በርትቶ በመስራት የሚያምኑ ሳይንቲስት፣ እናት፣አማካሪና መምህር  ሲሆኑ፤ የወላጆቻቸው ትልቅ ድጋፍ  የስኬታቸው  ቁልፍ  መሆኑን ይገልፃሉ።ስኬትና ስራ መጨረሻ የለውም የሚሉት ፕሮፌሰር ሶስና፤ለወደፊትም  ይህንኑ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ይገልፃሉ።
«አባቴ 88 ዓመቱ  ነው።ግን ሁል ጊዜም  ይሰራል። ምክንያቱም ሊሰሩ የሚገባቸው ብዙ ህትመቶች እንዳሉ ያውቃል። ሊፃፍ የሚችል  ብዙ ታሪክ አለ። ሊሰራ የሚችል ብዙ  ነገር አለ።ስራ አያልቅም። እናም ለውጥ ማምጣት የምትችል ሰው ሆኖ ከተሰማህ በትክክል መቀዛቀዝ አትፈልግም።»ብዙ የሚከናወኑ ነገሮች አሉ።  እናም እንዳልኩት ይህንን ችግር የመፍታት አቅም እንዳለህ ከተሰማህ ፣ያንን ፍጥነት መቀነስ በእውነቱ መልካም አይደለም።ቤተሙከራዬ  ውስጥ  አነስተኛ ጅምር  ስራ  አለኝ። አሁንም እውነተኛ ቴክኖሎጂን ለመስራት እየሞከርን ነው። ከዩኒቨርሲቲ  ትምህርት እና  በምርምር ደረጃ  ከምንሰራው በተጨማሪ ከእነዚህ ነገሮች ውስጥ የተወሰኑት በእውነተኛው ዓለም ለውጥ እንደሚያመጡ ተስፋ አደርጋለሁ ፡፡ »

ሳይኒቲስቷ በቁስ ሳይንስ ዘርፍ ያደረጉትን አበርቶት በማድነቅ የአሜሪካው ኒውስ ዊክ መፅሄት በ2008 ዓ/ም «ሊታዩ ከሚገባቸው 12 ሰዎች ውስጥ አንዷ» በሚል ሰይሟቸው ነበር።የተለያዩ የዓለም መገናኛ ብዙሃንም «ታሪክ ሰሪዋ»» በሚል ስራዎቻቸውን በማወደስ ዘግበዋል።ለቃለ መጠይቁ ፕሮፌሰር ሶስና ሀይሌን እናመሰግናለን።

ፀሀይ ጫኔ 
ሒሩት መለሰ
 

Audios and videos on the topic