ትውልደ አፍሪቃውያን ስለ ጀርመን ምርጫ  | አፍሪቃ | DW | 26.09.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ትውልደ አፍሪቃውያን ስለ ጀርመን ምርጫ 

አፍሪቃውያን ጀርመናውያኑ ራሳቸውን ብቁ ካላደረጉና በልበ ሙሉነትም በጀርመን ፖለቲካ ውስጥ ለመሳተፍ ካልተዘጋጁ በጀርመን የሚፈልጉት ለውጥ ሊመጣ አይችልም የሚሉም አሉ። ከቀድሞው አሁን በጀርመን ፖለቲካ የአፍሪቃውያን ተሳትፎ ተለውጧል።ለውጡ ግን አዝጋሚ ነው።ይህን ለመቀየር ደግሞ የአፍሪቃውያን ጀርመናውያን ጥረት ወሳኝ ነው ይላሉ ጋናዊው ጆምቤይ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:51

«ቦታው ታግለን የምናገኘው እንጂ ፣ማንም አዘጋጅቶ የሚሰጠን አይደለም።»

የጀርመን ብሔራዊ ምርጫ ለአፍሪቃውያን ጀርመናውያን ጥያቄዎች መልስ ሊሰጥ እንደሚገባ ዶቼቬለ ያነጋገራቸው አፍሪቃዊ መሰረት ያላቸው ጀርመናውያን ተናገሩ። አፍሪቃውያን ጀርመናውያኑ እንደሚሉት የጀርመን ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ፓርቲዎች የአፍሪቃውያን-ጀርመናውያንን ጥያቄዎች መመለስ ይጠበቅባቸዋል።በሌላ በኩል ይህ ፍላጎታቸው እንዲሟላ፣ በጀርመን ፖለቲካ ውስጥ ቦታ መያዛቸው ወሳኝ መሆኑን የሚናገሩት እነዚህ የጀርመን ዜጎች ፣ይህን ለማሳካት  ከእስካሁኑ ይበልጥ መጣር እንደሚገባቸው ያሳስባሉ።  
ከአንድ ዓመት በፊት ይፋ በሆነ አሃዛዊ መረጃ መሰረት ጀርመን ውስጥ  መሠረታቸው አፍሪቃ የሆነ ዜጎች ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በላይ ይገመታል።የአብዛኛዎቹ መኖሪያም ትላልቆቹ የጀርመን ከተሞች፤ ሀምቡርግ ፣ዳርምስታት ፣ፍራንክፈርት ፣ሙኒክ ፣ብሬመን ፣ኮሎኝና በርሊን ናቸው።እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች በጀርመን ዘረኝነትና ሌሎች አግላይ እርምጃዎች በእለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ላይ ተጽእኖ እንደሚያሳድሩባቸው ይናገራሉ።እነዚህና የመሳሰሉት የአፍሪቃውያን ጀርመናውያን ችግሮችና ስጋቶች በጀርመን ፖለቲካ ውስጥ እምብዛም ትኩረት አለማግኘታቸው ደግሞ ያሳስባቸዋል።የ20 ዓመትዋ ሌና ክዊንከ ካሜሩናዊት  ጀርመናዊት ናት። በውጭ ዜጎች ላይ ጥቃት የሚያደርሱ ቀኝ ጽንፈኞች ያመዝኑባታል በምትባለው በቀድሞዋ የምሥራቅ

ጀርመን ከተማ ሀለ ነው የምትኖረው ። በከተማ ስም በሚጠራው በሀለ ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምሕርትዋን የምትከታተለው ሊና በሚቀጥለው ዓመት ትምሕርትዋን ትጨርሳለች።ሊና በምትኖርበት ሀለም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ፣የቆዳ ቀለማቸው በተለየ ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ በደሎች ያሳስቧታል።
«ከውጭ የመጣ ወይም የተለየ መልክ ላለው ሁኔታው አስፈሪ ነው።በሀለም ብዙ የሚያነጋግሩ ጉዳዮች አሉ።የተለየ የቆዳ ቀለም ባላቸው ዜጎች ላይ ኢፍትሀዊ ተግባራት ይፈጸማሉ።  ጀርመናዊ እንደሆነ ለሚሰማው የተለየ መልክ ላለው ሰው ነገሩ «ጣፋጭና መራራ» የሚባል ዓይነት ነው።ምክንያቱም ቤቴ እንዳለሁ ይሰማኛል፤ ደኅንነቴ እንደተሰጠበቀም አስባለሁ።ይሁንና ይሄ፣ሁሌም የሚሆን አይደለም።በሰዎች ላይ መጥፎ ነገሮች እንደሚፈጸሙ እሰማለሁ።በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ መገኘትና በራስም ሲደርስ ፣ለተበደሉ ሰዎች መቆም፣ ብዙ ሰዎች ወጥተው እንዳይናገሩ ለውጥም እንዳያመጡ የሚገድብ በጣም ከባድ ችግር ነው።» 
በሊና አስተሳሰብ የአፍሪቃውያን ጀርመናውያን ችግሮችን ሊፈታ የሚችለው ፖለቲካው ነው። በርስዋ እምነት ፖለቲካው ከአሁኑ የበለጠ ሰብዓዊነትን ማካተት ይገባዋል።ስለ ዘረኝነትም ሊነጋገር ይገባል።ሌሎችም ፖለቲከኞች ሊያተኩሩባቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉ ትላለች ሊና ።
« ፖለቲካው ብዝሀነትን ሊያካትት ይገባል።በቡንደስታግ መቀመጫ ባይኖራቸውም የአፍሪቃውያን ጀርመናውያን የተለያዩ ድምጾች መሰማት አለባቸው።የዳያስፖራው ብቻ ሳይሆን እዚህ ያሉ የውጭ ዜጎች ድምጽ በሙሉ መሰማት አለበት።ጀርመን ውስጥ በየቦታው አፍሪቃውያን አሉ።ሆኖም ድምጻቸው አይሰማም።ይህ ያሳዝናል።»
በሌላ በኩል አፍሪቃውያን ጀርመናውያኑ ራሳቸውን ብቁ ካላደረጉና በልበ ሙሉነትም በጀርመን ፖለቲካ ውስጥ ለመሳተፍ

ካልተዘጋጁ በጀርመን የሚፈልጉት ለውጥ ሊመጣ አይችልም የሚሉም አሉ።ጋናዊው ዴስሞን ጆምቤይ በሰሜን ጀርመንዋ የወደብ ከተማ ሀምቡርግ ለአፍሪቃውያን ስደተኞች የምክር አገልግሎት የሚሰጠው ቶፕ አፍሪካ የተባለ ድርጅት መስራችና ሃላፊ ናቸው።በርሳቸው አስተያየት ከቀድሞው አሁን በጀርመን ፖለቲካ የአፍሪቃውያን ተሳትፎ ተለውጧል።ለውጡ ግን አዝጋሚ ነው።ይህን ለመቀየር ደግሞ የአፍሪቃውያን ጀርመናውያን ጥረት ወሳኝ ነው።
«ከዓመታት በፊት አፍሪቃውያን በጀርመን የፖለቲካ መድረክ ውስጥ አልነበረንም።አሁን ግን ብዙ ነገሮች ተቀይረዋል። እንዳለመታደል ሆኖ ለውጡ ግን ፈጣን አይደለም።ሆኖም አሁን እንደተገነዘብነው  ብዙ መስራት አለብን እንቅስቃሴያችንም በመጠኑም ቢሆን ከኃይል ጋር መሆን አለበት።የምንፈልገውን ማወቅ አለብን።ይህን ለማግኘት ደግሞ መንቀሳቀስ ይገባናል።ህዝቡ ለኛ የእድል በሮችን ከፍቶልናል።በኔ እምነት ወጣቱ ትውልድ ወደ ፖለቲካው ዘልቆ መግባት አለበት።ይህ መሪነትንም ይመለከታል።ከጀርመናውያኑ ጋር በአግባቡ መነጋገር መቻልንም ይጨምራል።ለዚህ መዘጋጀት አለባቸው።ይህ ቦታ ታግለህ የምታገኘው ነው። ማንም አዘጋጅቶ የሚሰጠን አይደለም።»

ሊና እንደምትለው ደግሞ መብቶችን የማይገድበውን የጀርመን ዴሞክራሲን አለአግባብ በመጠቀም የሚፈጸሙ በደሎች አስከፊ ናቸው ።ለዚህ አባባሏም በሕግ የተደገፉ ነገር ግን በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ የምትላቸውን ጉዳዮች ታነሳለች።በአሁኑ ጊዜ በአንዳንድ ጽንፍ የያዙ ጉዳዮች ላይ አስተያየት መስጠት እንኳን አደገኛ ሊሆን ይችላል የምትለው ሊና ከምንም በላይ ሊደረግ ይገባል የምትለውንም ገልጻለች።
«እንደሚመስለኝ ሁሉንም ማዳመጥ አለብን ።በዚያው መጠን በጀርመን አንዳንድ ነገሮች ጽንፍ የያዙ ናቸው ።በጀርመን ነጻ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት አለን።አንዳንድ ነገሮች በሕግ ትክክል ናቸው ።ሆኖም በኔ አመለካከት ከሞራል አንጻር ስናያቸው ትክክል አይደሉም።»
ጋናዊው ጆምቤይ ፣ አፍሪቃዊ ጀርመናውያን ከጀርመን ኅብረተሰብ ጋር ይበልጥ የመዋሀዳቸውን አስፈላጊነት  ይበልጥ አጽንኦት ይሰጣሉ።ርሳቸው እንደሚሉት ይህ ካልሆነ ጥያቄዎቻቸው መልስ ሊያገኙ አይችሉም
«አፍሪቃው ማኅበረሰብ ሊያስተውል የሚገባው በአንድ ስርዓት ውስጥ የሚኖሩ ከሆነ ሚና ሊኖራቸው ይገባል።የኅብረተሰቡ አካል መሆን አለባቸው የጀርመን ፓስፖርት የመንቀሳቀስ መብት ብቻ አይደለም የሚሰጠው ።የመወሰን መብት ፣በውሳኔ የመሳተፍ መብት፣ ድምጽ የመስጠት መብት ጭምርም  ይሰጣል።ውሳኔያችሁ ጀርመን ሌላ ቅርጽ እንድትይዝ ሊረዳ ይችላል።»
በጀርመን ፖለቲካ የአፍሪቃውያን -ጀርመናውያን  ተሳትፎ አለ የሚባል አይደለም።በጣት የሚቆጠሩ አፍሪቃውያን ናቸው ለፌደራሉ የህዝብ እንደራሴዎች ምክርቤት አባልነት የበቁት። ከመካከላቸው አንዱ ሴኔጋላዊ ጀርመናዊው የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ SPD አባል ካራምባ ድያቢ ናቸው። የሀለ ከተማን በመወከል ከዛሬ ስምንት ዓመት አንስቶ በጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት መቀመጫ አላቸው።ዲያቢ በዛሬው ምርጫ ተወዳድረዋል። የዛሬ ስምንት ዓመት ለዚህ ሃላፊነት የተመረጡት ሌላው አፍሪቃዊ መሰርት ያላቸው የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ CDU ን ወክለው የተወዳደሩት ጀርመናዊው ቻርልስ ሁበር ናቸው።  

ኂሩት መለሰ 
 

Audios and videos on the topic