ትዉስታ የቀድሞዉ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት | ዓለም | DW | 24.08.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ትዉስታ የቀድሞዉ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት

የመልዕክተኞቹ ጓድ ከፕሬዝዳትነት ሊ ምዩንግ ባክ ጋር ተወያቷል።ኪም በፕሬዝዳትነት ዘመናቸዉ ሁለቱን ኮሪያዎች እቀራረበዉ ነበር።በሞታቸዉ አስታረቋቸዉ።

default

ኪም ዴ ጁንግ

24 08 09

በወጣትነት ዘመናቸዉ እሁለት የተገመሠ-ሐገር ሕዝባቸዉን በሰላማዊ መንገድ ለማዋሐድ በመሞከራቸዉ ታስረዋል። ተግዘዋል።ሕዝባቸዉን ከኮሚንስቶች-ጭቆና ከጄኔራሎች ረገጣ ነፃ ለማዉጣት በመታገል-ማታጋል፤ የሰላማዊ ትግልን ፋይዳ በማስተማራቸዉ ነብሰ ገዳዮች ዘምተዉባቸዋል።ሞት ተበይኖባቸዋል። በመሪነት ዘመናቸዉ የሐምሳ ዘመኑን የጦር አርግበዉ-የመልካም ግንኙነት መሠረት ጥለዋል።ለሕንዶች-ጋንዲ፣ ለአሜሪካኖች ኪንግ፣ ለደቡብ አፍሪቃዉያን ማንዴላ ከነበሩ-ወይም ከሆኑ እሳቸዉ በርግጥ ለኮሪያዎች የሰላማዊ ትግል አባት ነበሩ።ኪም ዴይ ጆንግ።ሞቱ።ትናንት ተቀበሩ።ቅንጫቢ ምግባር ዉርስ-ቅርሳቸዉ ያፍታ ቅኝታችን ትኩረት ነዉ።አብራችሁኝ ቆዩ።

በ1948 (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) በሰወስቱ ሐገራት የሆነዉ-ሁነት በርግጥ የጊዜ-ሁኔታዎች ግጥምጥሞሽ እንጂ የሰወስቱን ሰዎች-አንድም ሰወስትምነትን ለማብቀል ልዩ ሚልኪ አልነበረም።በዚያ አመት ጥር ማብቂያ ሕንዳዊዉ የሠላማዊ ትግል መርሕ መሥራች።የነፃነት፤ የእኩልነት፥የፍትሕ ተማጓች ሞሐንደስ ካራምቻድ ጋንዲ ተገደሉ።

በዚያዉ አመት ወጣቱ ጥቁር አሜሪካዊ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁንየር ባጭር ለቀረ እድሜዉ ግን የዘመን ሒደት ለማይሽረዉ መርሑ ጅምር የመጀመሪያ እዉቀት ከገበየበት ከሞርሐዉስ ኮሌጅ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመረቀ።ሕንዶች በታላቁ የነፃነት ትግል መምሕራቸዉ ሞት የተቆራመዱበት ያ አመት ለደቡብ አፍሪቃዉያን እና ለደቡብ ኮሪያዉያን የመልካም ዘመን ብርቀት መስሎ ነበር።-በሁለቱም ሐገራት ምርጫ ነበር።

ተስፋዉ ግን ወዲያዉ ተቀጨ።

ሰኔ-1948 ደቡብ አፍሪቃ በተደረገዉ ምርጫ የነጮችን የበላይነት የሚያቀነቅነዉ ብሔራዊ ፓርቲ ሥልጣን ይዞ እስከዚያ ዘመን ድረስ የሕግ ከለላ ያልተሰጠዉን የነጭ ዘረኞችን ግፍ የመንግሥት ይፋ መርሑ አደረገዉ። ጠቅላይ ሚንስትር ዳንየል ፍራንቼስ ማለን የሚመሩት ሥርዓት በደነገገዉ ሕግ መሠረት ጥቁሩ ደቡብ አፍሪቃዊ ከእንስሳ ባልተናነሰ መረገጥ-መገፋቱ አሰመርሯቸዉ ለፍትሕ-እኩልነት ትግል ቀደመዉ ከተሰማሩት ወጣቶች አንዱ አፍሪቃዊ ጋንዲ ይሆናል ብሎ ያሰበ በርግጥ አልነበረም።

በ1948 ተጀምሮ-በ1960ዎቹ ግሞ፥ በ1990ዎቹ ለአኩሪ ድል የበቃዉን ትግል በግንባር ቀደምትነት የመሩ፥ ያስተባበሩት፥ ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉት ኔልሰን ሮሊሕላሕላ ማንዴላ በርግጥ የጥቁሮች ትግል ቀንዲል፥የሰላም የእኩልነት፥ የይቅር ባይነት አብነት ሆኑ።

የነጭ ዘረኞቹን ፓርቲ ለስልጣን ያበቃዉ የደቡብ አፍሪቃ ምርጫ በተደረገ በሁለተኛ ወሩ ደቡብ ኮሪያ ላይ የተደረገዉ ምርጫ የዩናይትድ ስቴትስ የሰወስት አመታት ወታደራዊ አገዛዝ እንዲያበቃ ምክንት በመሆኑ ለደቡብ ኮሪያዎች እንጭጭም ቢሆን የጥሩ ተስፋ ምልክት ነበር።የምርጫዉ ሒደትና ዉጤት እስከዚያ ዘመን ድረስ በአንድ የጃፓን የመርከብ ኩባንያ ተቀጥሮ ጠቀም ያለ ገንዘብ ያጠራቀመዉን የሃያ ሰወስት አመቱን ወጣት ቀጣሪዉን ኩባንያ ለመግዛት የሚችልበትን ብልሐት ከማሰላሰል ሐሳቡ አናጣበዉ።

የወጣት ልቡን የሰረቀዉ ፖለቲካ ለሞት ሥጋት፥ ለግዞት-እስራት ዳርጎት፥ በሐምሳ-ሁለት ዘመናት ሒደት ካበሰለ፥ ካሸበተ፥ እድሜም፤ በጎ ምግባርም፥ ብሥለት ብልሐትም፥ ሥልጣንም ለአንቱታ፥ ለአለም ታላቅ የሰላም ሽልማት ኖቤል ካበቃቸዉ በሕዋላም ትግሌ ይቀጥላል አሉ።

«በአልፍሬድ ኖቤልስ ፍላጎትና መርሕ መሠረት በኮሪያ እና በመላዉ አለም ሠብአዊ መብት እንዲከበር ነፃነት እንዲሰፍን አበክሬ እታገላለሁ።በኮሪያ ሕዝብ መካካል እርቀ-ሠላም እንዲወርድ ትብብር እንዲሰፍን አቅሜ የሚፈቅደዉን በሙሉ አደርጋለሁ።»

ኪም ዴ ጁንግ-ሁለት ሺሕ።

እንደ ብዙዎቹ ወጣቶች ሁሉ ኮሪያ እሁለት እንደተከፈለች፥ የጃፓን ቅኝ ገዢዎች በሐይል ያስወጡት የዩናይትድ ስቴትስና የሶቬት ሕብረት ወታደሮች ሰሜንና ደቡብ እንደተፋጠጡ በ1948 የተደረገዉ ምርጫ የሕዝቡን ነፃነት፥ትክክለኛ ፍላጎት ማንፀባረቁን ያ ወጣት መጠራጠሩ አልቀረም።

ወጣቱ ፖለቲካ እያነፈነፈ፥ ሐብት-እያጋበሰ ያንን ኩባንያ ሲገዛ ብዙዎች የፈሩት ደረሰ።ዋሽንግተን-ሞስኮዎች ኮርያ ልሳነ ምድር በተከሏቸዉ ተከታዮቻቸዉ አማካይነት ሚሊዮኖችን ካረገፈዉ፤ አለምን ካነካካዉ ጦርነት ገቡ።1950።በጦርነቱ መሐል ገና ፖለቲካ በቅጡ ያልሰረፀዉ ወጣት ወደፊት ከሚጋረጣቸዉ ብዙ ፈተናዎች የመጀመሪያዉን አንድ አለ።የኮሚንስት ወኪሎች አፍነዉ ወደ ሰሜን ሊያሻግሩት ሲሉ ለጥቂት አመለጠ።

Südkorea Präsident Kim Dae Jung

የቀብሩ ሥነ-ስርዓት

ዘግናኙ ጦርነት በተኩስ አቁም ዉል በረገበ ባመቱ ጠቅልሎ ፖለቲካዉን ተቀየጠ።-1954።በ1961 ለምክር ቤት አባልነት ተመረጡ።ከእንግዲሕ አንቱ ናቸዉ።ወዲያዉ ግን ሲቢላዊዉን መንግሥት በሐይል አስወገደዉ ሥልጣን የያዙት የሐገሪቱ የጦር ጄኔራሎች ምክር ቤቱን ዘጉት።ኪም ተስፋ አልቆረጡም።የጄኔራል ፓርክ ቻንግ ሒ አምባገነናዊ መንግሥት በፈቀደዉ ምርጫ በ1963 እና 67 ተሳትፈዉ የምክር ቤት እንደራሴ ሆኑ።

የተቃዋሚዎች ልሳን ሆነዉ የቆዩት ኪም አምባገነናዊዉ መንግሥት የፈጠረባቸዉን መሰናክል ሁሉ ተቋቁመዉ በ1971 በተደረገዉ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጄኔራል ፓርክ ክፉኛ ተፈታትነዋቸዉ ነበር።ይሕ ለጄኔራሉ ታላቅ ድፍረት ነዉ።ኪም አላረፉም የፓርክ መንግሥት ዩሺን በሚል ስም ያወጣዉን ሕገ-መንግሥታዊ መርሕ በይፋ ተቹት።ለትችታቸዉ ዋጋ የኮሪያ ማዕከላዊ የስለላ ድርጅት (KCIA) ነብሰ ገዳዮች ጃፓን ድረስ አሳደዉ ሊያጠፏቸዉ ነበር።አመለጡ።

ሁለቱ ኮሪያዎች መዋሐዳቸዉ አይቀርም የሚል ጠንካራ እምነት አላቸዉ።ዉሕደቱ ግን በሰላማዊ ድርድር፥ በምጣኔ ሐብታዊ ትስስር እንጂ በሐይል ሊመጣ አይችልም ባይ ናቸዉ።ይሕ በፕሬዝዳትነት ዘመናቸዉ የፀሐይ-ነፀብራቅ በሚል ሥም ገቢር ያደርጉት መርሐቸዉ ብዙዎች ካሰቡት በላይ ብዙ ለወጥ አምጥቷል።

«ሰሜን ኮሪያዎች ለወደፊቱ በጣም ይቀየራሉ።ደቡቦች በጣም ከፍተኛ የሆነ እርዳታ ወደ ሰሜን እየላኩ ነዉ።እነዚሕ የርዳታ ቁሳቁሶች «ኮሪያ የተሰራ-Made in koraa/ የሚል ፅሁፍ አላቸዉ።ድሮ ሰሜን ኮሪያዎች ሥለ ደቡቦች የሚያዉቁት ከመንግስታቸዉ ፕሮፓጋንዳ የሚሰሙትን ብቻ ነበር።አሁን ደቡብ ኮሪያ መሻሻሏን እራሳቸዉ ያዩታል።እናም እነሱም እንደ ደቡቧ ማደግ ይፈልጋሉ።»

ይሕ እምነታቸዉ ወንጀል ሆኖ ከግድያ ሙከራ ባመለጡ በሰባተኛዉ አመት ኮሚንስት በሚል ወንጀል ሞት ተበየነባቸዉ።የጄኔራል ጄኦን ዱ ሕዋን መንግሥት ያስፈረባቸዉ የሞት ቅጣት ለማስነሳት ከዩናይትድ ስቴስ መሪዎች እስከ ከሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርዕሠ-ሊቃነ ጳጳሳት ዳግማዊ ዩሐንስ ጳዉሎስ ከአዉሮጳ እስከ ጀርመን መሪዎች ተረባርበዉ ነበር።

ኪም በፕሬዝዳትነት ዘመናቸዉ በርሊንን ሲጎበኙ በተለይ የጀርመን መሪዎቹን ድጋፍ አልዘነጉትም ነበር።

«የሞት ቅጣት በተፈረደብኝ ወቅት በርካታ ጀርመናዉያን ተከራክረዉልኛል።በተለይ መራሔ መንግሥት ቪሊ ብራንት፥ ፕሬዝዳት ሪቻርድ ፎን ቫይስሴከር፥ ሔልሙት ሽሚት እና ሐንስ ዲትሪሽ ጌንሼር የዋሉልኝን አልረሳዉም።የነሱ ድጋፍ ባይኖር ኖሮ ዛሬ እኔ በሕወይት አልኖርም ነበር።ጀርመንን በጣም አመሰግናለሁ።»

የሞት ቅጣቱ ወደ ሃያ አመት እስራት፥ እስራቱ ወደ ግዞት ተለወጦላቸዉ አሜሪካ ተሰደዱ።ከጥቂት አመታት በሕዋላ ሐገራቸዉ ሲገቡ እንደገና የቁም እስረኝነት ተበየባቸዉ።በ1987 ተለቀዉ ለሁለተኛ ጊዜ ለፕሬዝዳትነት ተፎካከሩ አልሆነላቸዉም።በ1992 አሰለሱ-ተሽነፉ።በ1997 ተወዳደሩ አሸነፉ።የእስያዉ ማንደላ የሚል ቅፅል የወጣላቸዉም ያኔ ነበር።የፀሐይ ነፀብራቅ ባሉን መርሐቸዉ መሠረት ሁለቱን ኮሪያዎች፥ ዩናይትድ ስቴትስና ሰሜን ኮሪያን አቀራርበዉ እራሳቸዉም የያኔዋ የአሜሪካ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ማድሊን ኦልብራይትም ፒዮንግያንግን እስከመጎብኘት ደርሰዋል።

ፕሬዝዳት ቡሽ ሰሜን ኮሪያን በሰይጣን ዛቢያነት እስከወነጀሉበት ጊዜ ድረስ በኪም ጥረት ፒዮንግ ያንግ የኑክሌር መርሐ-ግብሯን አቋርጣም ነበር።ዛሬ በርግጥ ነበር-ነዉ።

ሰሜን ኮሪያ ከሁለት ሳምንት በፊት የጦር ልምምድ የጀመሩትን የዋሽንግተን-ሶል ጠላቶችዋን በኑክሌር እንደምትዋጋ ስታስጠነቅቅ ነበር። ለኪም ቀብር ግን በሰራተኞች ፓርቲ ዋና ፀሐፊ በኪም ኪ-ማን የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድኗን ወደ ሶል ላከች።የመልዕክተኞቹ ጓድ ከፕሬዝዳትነት ሊ ምዩንግ ባክ ጋር ተወያቷል።ኪም በፕሬዝዳትነት ዘመናቸዉ ሁለቱን ኮሪያዎች እቀራረበዉ ነበር።በሞታቸዉ አስታረቋቸዉ።

ነጋሽ መሀመድ ፣ ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic