ትዉስታ-አዲስ አኩስቲክ የጃዝ ቡድን በጀርመን | ባህል | DW | 25.10.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ባህል

ትዉስታ-አዲስ አኩስቲክ የጃዝ ቡድን በጀርመን

በ50ቹ እና በ60ዎቹ አመታት በኢትዮጵያ የዘመናዊ ሙዚቃ ዳብሮ በወጣበት ዘመን ከተደመጡት ሙዚቃዎች መካከል በአዲስ አኩስቲክ በጥበባዊ የጃዝ ሙዚቃ ቅላጼ፤ በአዲስ የተቀናበረዉን ሙዚቃ ይዘን ቀርበናል።

በ50ቹ እና በ60ዎቹ አመታት በኢትዮጵያ የዘመናዊ ሙዚቃ ዳብሮ በወጣበት ዘመን ከተደመጡት ሙዚቃዎች መካከል በአዲስ አኩስቲክ በጥበባዊ የጃዝ ሙዚቃ ቅላጼ፤ በአዲስ የተቀናበረዉን ሙዚቃ ይዘን ቀርበናል። ባለፉት ሳምንታት አዲስ አኩስቲክ የሙዚቃ ቡድን አባላት እዚህ በጀርመን በተለይም በኮለኝ እና ፍራንክፈርት ከተማ «ትዉስታ» በሚል መረሃ-ግብራቸዉ በባህላዊ እና ዘመናዊ የሙዚቃ መሳርያ በሚያቀናብሩት በኢትዮጵያ ጥንታዊ ሙዚቃ አሳፍረዉ፤ ኢትዮጵያን ለሚያዉቅ በሃሳብ ወደ ኢትዮጵያ አስጉዘዉ በዉዝዋዜ ሲያስቦርቁ፤ በትዝታ ሲያነጉዱ፤ ኢትዮጵያ ሄዶ ለማያዉቀዉ ታዳሚ ደግሞ «እዉነት ኢትዮጵያዉያን የጃዝ ሙዚቃን እንዲህ ዉብ አድርገዉ ይጫወታሉ?» በሚል ጥያቄ ሲያስደምሙ፣ ደግሞም ሲያስደንሱ የማታ የማታ ደግሞ በዚያዉ በዉብ የሙዚቃ ድግሳቸዉ ምዕራባዉያኑን ወደ ኢትዮጵያ ሲጋብዙ ሰንብተዋል። በሙዚቃዉ ድግስ መግብያ ኢትዮጵያን ጀርመን ፎሩም በመባል የሚታወቀዉ የኢትዮጵያ እና የጀርመናዉያን የዉይይት ማህበር አዲስ አኩስቲክ የጃዝ ባንድን ወደ ጀርመን በመጋበዝ የኢትዮጵያን ባህል በማስተዋወቅ ላይ መሆኑን ገልጾአል። አስር ቀናት ግድም ሙዚቃዉን ለጀርመናዉያኑ ሲያስተዋዉቅ የቆየዉ አዲስ አኩስቲክ የሙዚቃ ቡድን፤ የኢትዮጵያዉያን ተማሪዎች እና ምሩቃን ማህበር በጀርመን ፍራንክፈርት ላይ በአካሄደዉ ጉባኤ ላይ ተገኝተዉም፤ የጉባኤዉን ተካፋዮች ሲያዝናና አምሽተዋል። በኢትዮጵያ የሙዚቃ አለም ከ ዛሬ 54 ዓመታት ጀምሮ በማገልገል ላይ ያሉት ብቸኛዉ የማንዶሊን ተጫዋች አየለ ማሞ፤ ማንዶሊን የተሰኘዉን የሙዚቃ መሳርያቸዉን ይዘዉ ወደ መድረክ ሲቀርቡ እድምተኛዉ በደማቅ ጭብጨባ ነበር የተቀበላቸዉ። አንጋፋዉ ከያኒ አየለ ማሞ በመድረክ ማንዶሊንን ከመጫወት የሙዚቃ ቡድኑን በድምፅ ከማጀብ ባሻገር በዉዝዋዜያቸዉ የእድምተኛዉን ቀልብ ስበዉ ነበር ያመሹት ። የአዲስ አኩስቲክ የጃዝ ሙዚቃ መስራች እና የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መምህር ወጣት ግሩም መዝሙር፤ የሙዚቃ ቡድኑ የዛሬ አራት አመት ግድም እንደተመሰረተ እና በአብዛኛዉ አዲስ አበባ ከተማ ዉስጥ በሳምንት አንድ ግዜ የሙዚቃ ድግሳቸዉን እንደሚያሳዩ አጫዉቶናል። የሙዚቃ ምሁሩ ወጣት ግሩም መዝሙር፤ ከአዲስ አኩስቲክ የጃዝ ቡድን ጋር በጣይቱ ሆቴል ጃዝ አንባ በተሰኘዉ የሙዚቃ ስብስብ ስር የጃዝ ትዕይንቱን በሳምንት አንድ ግዜ ያሳይ እንጂ በተለያዩ የሙዚቃ ዘርፎች ስር በተለያዩ ክለቦች ሙዚቃን እንደሚጫወት እንዲሁም ትምህርትም እንደሚሰጥ ነግሮናል። ኢትዮጵያን የሚጎበኙ ጀርመናዉያን ጣይቱ ሆቴል የጃዝ አንባን ድግስ ካዩ በኋላ፤ ኢትዮጵያን ለሚጎበኘዉ ለሌላዉ ጀርመናዊ ፌስ ቡክ በተሰኘዉ የማህበረሰብ መገናኛ መረብ ላይ ስለ አዲስ አኩስቲክ የጃዝ ሙዚቃ በመግለዝ ጃዝ አንባን እንድታዩ እንዳያመልጣችሁ እያሉ መልክት ሲለዋወጡ ተስተዉሎአል። በአሁኑ ሰዓት አኩስቲክ ጃዝ ባንድ ወደ አገር ቤት ተመልሶ የሙዚቃ ድግሱን ለማሳየት ወደ ቻይና ለመጓዝ ዝግጅት ላይ እንደሆነም ተነግሮአል። አዲስ አኩስቲክ በሃምሳዎቹ እና በስድሳዎቹ በኢትዮጵያ ተወዳጅነት የነበራቸዉን ሙዚቃዎች በባህላዊ እና በዘመናዊ የሙዚቃ መሳርያ በማቀናበር ሙዚቃዉ በምዕራባዉያኑ ጆሮም እንዲቆረቆር እንዲሆን አድርጎ «ትዉስታ» የሚለዉን የሙዚቃ አልብም ለገበያ አዉሎአል። በሙዚቃ ድግሱ ምሽት የተገኘዉ አብዛኛዉ ጀርመናዊ ታዳሚ፤ ኢትዮጵያን በስራ ጉዳይ የሚያዉቅ አልያም፤ ኢትዮጵያዊ ባልንጀራ ያለዉ በመሆኑ ነበር። አዲስ አኩስቲክ የጃዝ የሙዚቃ ቡድን፤ ለስራ ጉዳይ ዉጭ ካልወጣ በስተቀር ዘወትር አርብ ምሽት በጥንታዊዉ የጣይቱ ሆቴል የሙዚቃ ድግሱን እንደሚያሳይ በመግለጽ፤ የሙዚቃ አፍቃሪዎችን ይጋብዛል። ለዶቼ ቬለ ራድዮ ጣብያም «ትዉስታ» የሚለዉን የሙዚቃ አልብሙን ለማስታወሻ ሰትዋል። እኛም አመስግነን ተቀብለናል፤ ስራቸዉንም ይበል ብለናል። ሙሉ ቅንብሩን ያድምጡ!

አዜብ ታደሰ

ሸዋዪ ለገሰ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 25.10.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/16WBG
 • ቀን 25.10.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/16WBG