1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትኩረት የሳበው አዲሱ ልውጥ የኮሮና ተሐዋሲ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 16 2015

የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ስፍራውን ወስዶ የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ቀንሶለት ስለነበረው ኮቪድ 19 ዳግም መነገር ጀምሯል። በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የበጋ ወቅት እየተገባደደ ስፍራውን ለቅዝቃዜ ሊያስረክብ በተቃረበበት በዚህ ጊዜ አዲስ የኮሮና ልውጥ ተሐዋሲ በአራት ሃገራት መገኘቱ ተሰምቷል። ተመራማሪዎችም የተሐዋሲውን ባህርያት ለማጥናት እየተጣደፉ ነው።

https://p.dw.com/p/4VRlw
ፎቶ ከማኅደር፤ ኮሮና ተሐዋሲ
የዓለም የጤና ድርጅት BA.2.86 የሚል ስያሜ የሰጠው ልውጥ የኮሮና ተሐዋሲ በአራት ሃገራት መገኘቱን ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ይፋ አድርጓል። ፎቶ ከማኅደር፤ ኮሮና ተሐዋሲ ምስል Michael Bihlmayer/CHROMORANGE/picture alliance

ትኩረት የሳበው አዲሱ ልውጥ የኮሮና ተሐዋሲ

ትኩረት የሳበው ልውጡ የኮሮና ተሐዋሲ

ከሁለት ዓመት በላይ የዓለምን እንቅስቃሴ ገትቶ የከረመው ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወሬው በቀዘቀዘበት በዚህ ወቅትአዲስ የተከሰተው ልውጥ ተሐዋሲ ማነጋገር ጀምሯል። ልውጡ የኮሮና ተሐዋሲ በወረርሽኝ መልክ ከሆነ ሀገር ተነስቶ የሚያዳርስ ሳይሆን በየሀገሩ ያለው ወይም የነበረው ተሐዋሲ አይነቱን እየለዋወጠ ሊከሰት እንደሚችል ነው የዓለም የጤና ድርጅት የገለጸው። አስቀድሞ ተሐዋሲው በመላው ዓለም ተሰራጭቶ በየሃገራቱ የእንቅስቃሴ ገደብ በነበረበት ወቅት ብዙዎች አንዳች መከላከያ የሚሆን መድኃኒት ተገኝቶ እንደልብ ለመንቀሳቀስ ሲመኙ ነበር። ያኔም ቢሆን የህክምና ባለሙያዎች ተሐዋሲው አይነቱን እየለዋወጠ አብሮ ይከርም እንደሆነ እንጂ ተጠራርጎ ይወገዳል የሚል ግምት እንደሌላቸው ይገልጹ ነበር። አሁን በአራት ሃገራት የተገኘው ልውጡ ተሐዋሲ የባለሙያዎቹን ማሳሰቢያ ያረጋገጠ ይመስላል።

ፎቶ ከማኅደር ፤ በብሪታንያ የበጋ ወቅት መዝናኛ ብሪንግተን የባሕር ዳርቻ
የኮቪድ 19 ክትባት ለብዙዎች በመዳረሱ እና በተሐዋሲው የሚያዙም ሆኑ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር የመገናኛ ብዙሃንን ዋነኛ ትኩረት መሆኑ በመቅረቱ ብዙሃኑ ኅብረተሰብ ተሀዋሲው ስለመኖሩ ወደመጠራጠር እያዘነበለ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ መጠቀም ትቷል። ፎቶ ከማኅደር ፤ በብሪታንያ የበጋ ወቅት መዝናኛ ብሪንግተን የባሕር ዳርቻምስል Gareth Fuller/empics/picture alliance

የዘርፉ ተመራማሪዎችም የልውጡን ተሐዋሲ ባህሪያት ለማጥናት ጥድፊያ ላይ መሆናቸውን የዓለም የጤና ድርጅት ገልጿል። በድርጅቱ ኮቪድ 19ን የመከላከል እንቅስቃሴ የሚመለከት ዘርፍ አስተባባሪዋ ዶክተር ማሪያ ፋን ኬርኮቭ ስለ ልውጡ ተሐዋሲ እንዲህ ይላሉ።

 «ልውጦቹ ተሐዋስያን ከሌላ ሀገር ወይም ከሌላ ቦታ ሊመጡ ይችላሉ የሚለው አስተሳሰብ የተሳሳተ ይመስለኛል፤ አደገኛም ነው። ምክንያቱም ችግሩ ሌላ ቦታ ነው ተብሎ ይታሰባል። ሆኖም ግን ተሐዋሲው በአሁኑ ጊዜ በጣም እየተሰራጨ በመሆኑ ቀስ በቀስ እየተቀየረ ነው።»

ፎቶ ከማኅደር፤ የዓለም የጤና ድርጅት አርማ
የዓለም የጤና ድርጅት BA.2.86 የሚል ስያሜ የሰጠው ልውጥ የኮሮና ተሐዋሲ በአራት ሃገራት መገኘቱን ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ይፋ አድርጓል። ፎቶ ከማኅደር፤ የዓለም የጤና ድርጅት አርማምስል XinHua/picture alliance

ባለፈው ሳምንት ይፋ እንደተደረገው በጣም የተለየ የተባለው ልውጥ ተሐዋሲ በአራት ሃገራት ማለትም፤ በዴንማርክ፤ እስራኤል፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ዩናይትድ ስቴትስ ተገኝቷል።

የዓለም የጤና ድርጅት ለአዲሱ ልውጥ ተሐዋሲ BA.2.86 የሚል መለያ ሰጥቶታል። ሃገራትም በየበኩላቸው ክትትል እያደረጉ ስያሜውን እንዲንዲሰጡ በማመልከትም የየራሳቸውን ምዝገባ እንዲያካሂዱም አሳስቧል።  

አሜሪካን ውስጥ የተሐዋሲው ስርጭት መጨመር

ዩናይትድ ስቴትስ የበሽታዎች ቁጥጥር እና መከከል ተቋም CDC ለኅብረተሰቡ ላከው በተባለውና በየማኅበራዊ መገናኛው በተራጨው ማሳሰቢያ  XBB የሚል ስያሜ የተሰጠው አዲሱ ልውጥ ተሐዋሲ የህመም ምልክቶቹ ከወትሮው የተለዩ እና ሰዎች መያዛቸውን ሳያውቁ በፍጥነት ሊዛመት የሚችል አይነት እንደሆነ ያመለክታል። ባለፉት ዓመታት ኮቪድ 19 ወረርሽኝ በማኅበረሰቡ የዕለት ተዕለት ሕይወትም ሆነ ጤና ላይ ያስከተለው ከባድ ተጽዕኖ ያሳሰባቸው ወገኖች ያ አስጨናቂ ጊዜ ዳግም የመምጣቱ አዝማሚያ ይሆን በሚል ሰግተው መረጃውን ሲቀባበሉ በመመልከታችን ስለመረጃው ተአማኒነት እና በአሁኑ ጊዜ አሜሪካን ውስጥ የተሐዋሲውን ስርጭት ይዞታ እንዲያብራሩልን በዩናይትድ ስቴትስ ቨርጂኒያ ግዛት የውስጥ ደዌ ህክምና ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ያሬድ ወንድምኩንን ጠየቅን። እሳቸው እንደሚሉት ካለፈው ሰኔ ወር አንስቶ ባሉት ጊዜያት የተሐዋሲው ስርጭት ከፍ ብሏል። እንዲያም ሆኖ ልውጡን ተሐዋሲ ከግምት በማስገባት የተዘጋጁ የተሻሻሉ ክትባቶች በመጪው መስከረም ወር እንደሚወጣ መታወቁም የመከላከሉን አቅም ያጠናክራል ብለው ስባሉ።

ፎቶ ከማኅደር፤ ፋይዘር ኩብንያ ያዘጋጀው የኮቪድ 19 ክትባት
የተሐዋሲውን የመለዋወጥ ባህሪ ከግምት በማስገባት የሚዘጋጁ የተሻሻሉ ክትባቶች በመጪው መስከረም ወር እንደሚወጣ መታወቁም የመከላከሉን አቅም ያጠናክራል የሚል ተስፋ አለ። ፎቶ ከማኅደር፤ ፋይዘር ኩብንያ ያዘጋጀው የኮቪድ 19 ክትባት ምስል Ezra Acayan/Getty Images

አሁን አሜሪካን ውስጥ እየተሰራጨ የሚገኘውየኮሮና ተሐዋሲ አይነት ኦሚክሮን የተባለው መሆኑን የገለጹት የህክምና ባለሙያው እስከዛሬ የሚያገለግሉት የህክምናውም ሆነ የምርመራው ስልቶች ለዚህም እንደሚረዱ ነው የሚያስረዱት።

ስጋቱ ምን ይመስላል?

በአራት ሃገራት ውስጥ ስለተገኘው ልውጥ ተሐዋሲ ማብራሪያ የሰጡት በዓለም የጤና ድርጅት ኮቪድ 19ን ለመከላከል የሚደረገውን እንቅስቃሴ የሚመለከተውን ዘርፍ የሚያስተባብሩት ዶክተር ማሪያ ፋን ኬርኮቭ እንደሚሉት አሁን የተገኘው ልውጡ ተሐዋሲ ፤ «በመላው ዓለም ላይ ተጽዕኖ የሚያመጣ አይነት አይደለም።»

በተለያዩ ሃገራት የተገኙትን ልውጥ ተሐዋስያን በተመለከተም የተለያየ ባህሪያቸውን፣ የዕድገታቸውን ሁኔታ፤ ያላቸውን የተለየ ቅርጽ፣ የአደገኛነታቸውን ይዞታ እንዲሁም እስካሁን ያለውን የመከላከል አቅም ማለትም ምርመራው፤ ህክምናውም ሆነ ክትባቱ ያለውን አቅም ተመራማሪዎቹ እያጠኑ መሆኑንም አመልክተዋል። እስካሁን በተገኘው መረጃ መሠረትም በፍጥነት የመተላለፍ አቅማቸው ከፍተኛ መሆኑ ተደርሶበታል ነው ያሉት ባለሙያዋ። ያም ሆኖ ግን አሁንም ጥናት ምርምሩ መቀጠሉን አመልክተዋል።

 «በቅርብ ክትትላችንን እንቀጥላለን፤ ለዚህም በተለይም በህክምናውም ሆነ በክትባቱ በኩል ለውጥ ማድረግ ያስፈልግ እንደሆነ መረጃዎችን ለማግኘት ብዙ ጥናቶች መደረግ ይኖርባቸዋል። እስካሁን ግን የተለወጠ ነገር አላገኘንም፤ ሆኖም ግን ይህንን መከታተል ይኖርብናል።»

ኮሮና ተሐዋሲ በወረርሽነቱ ዓለም ባዳረሰበት ወቅት በምርምሩም ሆነ በህክምናው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ሰዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ከመምከር ጎን ለጎን ተሐዋሲው በቀላሉ እንደማይወገድ ሲያሳስቡ ነበር። የመተንፈሻ አካላትን በመጉዳት ለከፋ ችግር ብሎም ለሞት የሚዳረገው ኮቪድ 19 ፕሮፌሰር ያሬድ እንደሚሉትም አብሮን መክረሙ የማይቀር ነው።

ፎቶ ከማኅደር፤ የኮሮና ተሐዋሲ መመርመሪያ
ለምርመራ ሲያገለግል የነበረው ስልት ለልውጡ የኮቪድ 19 ተሐዋሲ አይነቶች አሁንም እየሠራ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ። ፎቶ ከማኅደር፤ የኮሮና ተሐዋሲ መመርመሪያምስል Rouelle Umali/Xinhua/picture alliance

ምንም እንኳን አይነቱ አዲስ ነው ስለተባለው ልውጥ የኮሮና ተሐዋሲ ተመራማሪዎች ያሉት ነገር ባለመኖሩ አሁን ብዙ መረጃ ባይኖርም ያለውን የኮቪድ 19 መከላከያም ሆነ ህክምናው በተመለከተ በቂ ልምድ መገኘቱን ነው ፕሮፌሰር ያሬድ አጽንኦት የሰጡት። ምንም እንኳን ተሐዋሲው እየተለዋወጠ አብሮን የሚቆይ መሆኑ የታወቀ ቢሆንም በየአካባቢው ከታየው ተሞክሮ በመነሳት ኅብረተሰቡም የተሻለ ግንዛቤ ማግኘቱ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ባይ ናቸው።

ስለተሐዋስያን ጠባይ እና ምንነት የሚመራመሩ ባለሙያዎች ማንኛውም ተሐዋሲ ወደሰዎች አካል ሲገባ በተለያዩ ምክንያቶች እራሱን እንደሚለውጥ ያመለክታሉ። በኮሮና ተሐዋሲም የታየው ይኸው ነው። ምንም እንኳን አሁን የተሻለ የምርመራም ሆነ ህክምና እንዳለ ቢነገርም መዘናጋት ለችግር እንደሚዳርግ ግን የሁሉም ምክር ነው። ለሰጡን ማብራሪያ ፕሮፌሰር ያሬድ ወንድምኩንን እናመሰግናለን።

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ