ትኩረት የሳበዉ የዚምባቡዌ ምርጫ | የጋዜጦች አምድ | DW | 30.03.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ትኩረት የሳበዉ የዚምባቡዌ ምርጫ

ሐሙስ ዕለት ማለትም ነገ የሚካሄደዉ የዚምባቡዌ ምርጫ ከመቼዉም በበለጠ ሁኔታ ነዉ የዓለምን ትኩረት የሳበዉ። በያዙት የማይነቃነቅና የማይለወጥ የመሬት ፓሊሲ ምክንያት ቅኝ ገዢዎቻቸዉ የነበሩትን ወገኖች ያስከፉት አዛዉንቱ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ አሁንስ ከስልጣን አይለቁም ይሆን የሚል ስጋት በብዙዎች ላይ አሳድረዋል።

ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ከሃራሬ በስተደቡብ 220 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘዉ ጉቱ ከተማ የምረጡኝ ቅስቀሳ ሲያደርጉ

ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ከሃራሬ በስተደቡብ 220 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘዉ ጉቱ ከተማ የምረጡኝ ቅስቀሳ ሲያደርጉ

ነገ ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀዉ የዚምባቡዌ አዲስ ምርጫ ከመቼዉም በተለየ ሁኔታ የምርጫ ቅስቀሳዉ እየተካሄደ የሚገኘዉ በሰላማዊ መንገድ ነዉ።
ከእርስ በርስ የደም መፋሰስ የፀዳዉ ይህ የምረጡኝ ቅስቀሳ በሁለቱም ተፎካካሪ ወገኖችና ደጋፊዎች ላይ እስከ ዛሬ አደጋ አለማስከተሉ ብዙዎችን ያስገረመ ክስተት ሆኗል።
በአፍሪካ አገሮቻቸዉን ከቅኝ ግዛት ካላቀቁ መሪዎች በአሁኑ ጊዜ በስልጣን ላይ የሚገኙት ሙጋቤ ለምርጫ ቅስቀሳቸዉ በተዘዋወሩበት የዚምባቡዌ ክፍላተ ሃገራት ሁሉ የሚሉት አንድ ነገር ነዉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌየር የዲሞክራሲያዊ ለዉጥ እንቅስቃሴ የተሰኘዉን ተቃዋሚ ፓርቲ በመደገፍ የዚምባቡዌን ህልዉና እየተቀናቀኑ መሆኑን መግለፅ።
የምርጫ ዘመቻቸዉንም ፀረ ብሌየር የሚል ስያሜ የሰጡት ሮበርት ሙጋቤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከብሪታንያ ጋር የነበራቸዉ ግንኙነት እየሻከረ በመምጣቱ ቅስቀሳቸዉ ብሪታንያን በመቃወም ላይ አተኩሯል።
ሆኖም የተቃዋሚዉ ፓርቲ መሪ ሞርጋን ሳቫንጊሬ ባደረጉት ቅስቀሳ ይህ የምርጫ ዉድድር ስለብሌየር ሳይሆን ለተራቡት ዚምባቡዌያዉያን ምግብ ስለማቅረብ፤ ሰማይ ጠቀሱን የስራዓጥ ቁጥር ስለመቀነስና ከ25 ዓመት በፊት የነበረዉን የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት ወደቦታዉ ስለመመለስ ነዉ የሚል ምላሽ ሰጥተዋቸዋል።
አንዳንድ የፓለቲካ ተንታኞችም ይህ ዘዴ ህዝቡ በቅኝ ገዢዎቹ ላይ የነበረዉን ጥላቻ በማነሳሳት የዛኑ ፒኤፍን እድሜ ለማራዘም ነዉ ይላሉ።
ሙጋቤ ብሌየርንም ሆነ አገራቸዉን ቢጠሉ እዉነት አላቸዉ። ከሶስት አመት በፊት በዚምባቡዌ በተካሄደዉ ምርጫ ተመልሰዉ ስልጣን ላይ በወጡበት ጊዜ ብሌየር መራሽ በሆነዉ ሌበር ፓርቲ አሳሳቢነት ዚምባቡዌ እገዳ ተጣለባት።
ብሌየር ገና ስልጣን ላይ ሲወጡ የእሳቸዉ የግራ ክንፍ ሌበር ፓርቲ ከደቡብ አፍሪካ ነጭ ዘረኞች ጋር በመፋጠጡ የበርካታ ጥቁር አፍሪካዉያን ወዳጅ ተደርጎ ነበር።
ሆኖም ብሌየር ፅህፈት ቤታቸዉ ገብተዉ ሲረጋጉ በዚምባቡዌ ለድሃ ገበሬዎች መሬትን ለማከፋፈል የታሰበዉን ፕርግራም በመቃወም የገንዘብ ድጋፋቸዉን ነፈጉ።
ከዚህ በተጨማሪም በዚምባቡዌ ስላለዉ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ተደጋጋሚ ተቃዉሞ ማሰማት ቀጠሉ።
ሙጋቤም ብሌየርና ሚኒስትሮቻቸዉ በገዛ አገራቸዉ ምን መስራት እንዳለባቸዉ ሊነግሯቸዉ እንደማይችሉ ጠንከር ባለ መንገድ ገለፁ። ያም በቋፍ የነበረዉን ግንኙነት የባሰ ለየለት።
ለጊዜዉ ግን ዉጤቱ ምንም ቢሆን ምን በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ከዚህ በፊት የነበረዉ አይነት የደም መፋሰስ ባለመኖሩ ዚምባቡዌያዉያን እፎይ ብለዋል።
የምርጫ አስፈፃሚ የሆኑት ባለስልጣናት እንደሚሉት በየክፍለ ሃገሩ ሰላም ነግሷል እንዲህ ያለ የመቻቻል ባህል በመስፈኑም ተደስተዋል።
ፓሊስም በበኩሉ የምርጫ ቅስቀሳ በተደረገባቸዉ አካባቢዎች ሁሉ የተገደለ ሰዉ የለም ተቃዋሚዎችም በነፃነት እየተዘዋወሩ ቅስቀሳ እያደረጉ ነዉ ብሏል።
የተቃዋሚዉ ፓርቲ የህግ አካል እንደሚለዉ ደግሞ የሙጋቤ ታማኝና አፍቃሬ ዛኑፒኤፍ በሆኑ ወጣቶች አንድ ደጋፊ ለሞት በሚያደርስ ሁኔታ ተደብድቧል።
ፓሊስ ግን አደጋዉ የደረሰዉ ከፓለቲካ ጉዳይ ጋር በተገናኘ አይደለም በማለት አስተባብሏል።
የአህጉሪቱ መሪዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከተሉት የመጡትን የነፃና ፍትሃዊ የምርጫ ሂደት ሙጋቤም ለመጠቀም ቁርጠኝነት አሳይተዋል።
ከመቼዉም ጊዜ በለተየ አዲስ የምርጫ ህግ አገሪቱ ዉስጥ ከመቅረፅ ሌላ ለተቃዋሚዎቻቸዉ በመገናኛ ብዙሃን የመጠቀም ዕድል ሳይቀር ሰጥተዋል በቂ ባይባልም።
ሆኖም ተቃዋሚዎቹ ከዚህ የተረጋጋ የምርጫ ቅስቀሳ ጀርባ በዕለቱ የምርጫ ማጭበርበር እንደሚኖር እርግጠኛነን ማለት ጀምረዋል።
እነሱ እንደሚሉት ምንም እንኳን የተጋነነ መጋጨት በይፋ ባይታይም በየገጠሩ የዲሞክራሲያዊ ለዉጥ እንቅስቃሴ ፓርቲን ቢመርጡ አደጋ እንደሚደርስባቸዉ ማስፈራራት እየተፈፀመ ነዉ።
ይህ ምርጫ የ81 አመቱ የነፃነት አርበኛና የመጀመሪያ የዚምባቡዌ ፕሬዝዳንት ከሶስት አመት በኋላ ጡረታ የሚወጡት ፕሬዝዳንት ሙጋቤ የመጨረሻ መዘጋጃ ወቅት ነዉ።
ቅስቀሳቸዉም በተለይ ገዢ ፓርቲያቸዉ የማይነጥፍ ድጋፍ በሚያገኝበት የዚምባቡዌ ደቡብ ምስራቅ አካባቢ ያተኮረ ቢሆንም በሌላዉ አካባቢም የማይናቅ ደጋፊ አላቸዉ።
በነገዉ እለት ለሚካሄደዉ ምርጫም 5.8 ሚሊዮን መራጮች የተመዘገቡ ሲሆን የምርጫ ስርዓቱ ከንጋቱ አንድ ሰዓት ላይ ጀምሮ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ ያበቃል።