ትኩረት በአፍሪካ | ኢትዮጵያ | DW | 08.05.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ትኩረት በአፍሪካ

የዓለም ፕሬስ ቀን ባለፈው ማክሰኞ በመላው ዓለም ተከብሯል። የተለያዩ የፕሬስና የጋዜጠኞች መብቶች ተሟጋች ድርጅቶች በተለይም ምስራቅ አፍሪካ የፕሬስ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ እንደመጣ ይፋ አድርገዋል።

default

ባለፈው ማክሰኞ በኢትዮዽያ ዕለቱን ለማስታወስ በተዘጋጀው ስብሰባ ላይ የተፈጠረውና ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገተው ዓለም ዓቀፍ ድርጅት ሲፒጄ በመንግስት የተጠለፈ በሚል ያወገዘው ክስተት በሳምንቱ መነጋገሪያ ሆኗል። ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት አር ኤስ ኤፍ ኢትዮዽያን ጨምሮ በአፍሪካው ቀንድ ሀገራት የፕሬሱ ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል ሲል አስታውቋል። ትኩረት በአፍሪካ ቀዳሚ አድርጎ የሚመለከተው ጉዳይ ነው። በሌላ በኩል የአልቄይዳው መሪ ኦስማ ቢን ላደን ባለፈው ሰኞ አቦታባድ በተሰኘች የፓኪስታን ከተማ በአሜሪካ ኮማነዶዎች ከተገደሉ በኋላ በዓለም ዙሪያ የተለያዩ ስሜቶች ተፈጥረዋል። ተቃውሞና ደስታ ከየአገሩ ተሰምቷል። በፓኪስታን፤ በየመን፤ በአፍጋኒስታንና በሌሎች ሙስሊም ሀገራት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አደባባይ ወጥተው ቢን ላደን መገደላቸውን ተቃውመዋል። የአሜሪካንን እርምጃ አውግዘዋል። በአፍሪካም የኦስማ ቢን ላደን መገደል ድብልቅልቅ ያለ ስሜቶችን ያስተናገደ ሲሆን በተለይ በአፍሪካው ቀንድ ላይ የሚኖረው እንደምታ እያነጋገረ ነው። የኦስማ ቢን ላደን መገደልና የአፍሪካው ቀንድ ሀገራት ነዋሪዎች አስተያየት ትኩረት በአፍሪካ ሁለተኛው ርዕሰ ጉዳይ አድርጎ ወደ እናንተ የሚያደርሰው ይሆናል። ለዝግጅቱ መሳይ መኮንን።

ማንተጋፍቶት አመሰግናለሁ። ማክሰኞ ዕለት የተከበረው የዓለም የፕሬስ ቀን መገናኛ ብዙኃን በ21ኛው ክፍለ ዘመን፤ አዲስ ግንባር አዲስ መሰናክል በሚል መሪ ቃል በመላው ዓለም ተከብሯል። ከፕለት ወደ ዕለት ፈተናዎች እየበረከቱ አፈናው እየተጠናከሩ እንደመጡ በመግለጽ የተለያዩ የፕሬስና የጋዜጠኞች መብቶች ተሟጋች ድርጅቶች ሪፖርት አውጥተዋል። የአፍሪካው ቀንድ በከፋ የፕሬስ አፈና ውስጥ መግባቱንና መንግስታት ከምንጊዜው በላይ የፕሬስ ጨቋኝ ሆነው እንደታዩ ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች አር ኤስ ኤፍ አስታውቋል። በአር ኤስ ኤፍ የአፍሪካው ክፍል ሃላፊ አምብሮይስ ፒየ በአፍሪካው ቀንድ ጋዜጠኛ መሆን ከባድና ዋጋ የሚያስከፍል ከሆነበት ደረጃ ላይ ደርሷል ይላሉ።

«በዚህኛው የዓለምና የአፍሪካ ክፍል ያለው ሁኔታ በጣም የሚያሰጋ ደረጃ ላይ ይገኛል። ካለፉት ዓመታት ጀምሮ እየተናገርን እንዳለነው ሁሉ ይህ የአፍሪካው ቀንድ በአፈና ውስጥ ያለ፤ ቅድመ ሳንሱር በከፍተኛ ደረጃ የሚካሄድበት፤ ቀጠና ነው። ከተቀረው የዓለም ክፍል በከፋ ሁኔታ ጋዜጠኛ መሆን ፍጹም አዳጋችና ከባድ የሆነው በዚሁ የአፍሪካ ክፍል ነው። በሶማሊያ፤ በኢትዮዽያ፤ በሱዳን፤ በኤርትራ፤ በጅቡቲም ጭምር ጋዜጠኛ መሆን እጅግ ፈታኝ ነው።»

ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የፕሬስ ቁንጮ ጠላት ተደርጋ እየተወቀሰች ያለችው ኤርትራ ናት። የድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት አር ኤስ ኤፍ የአፍሪካው ክፍል ኃላፊ እንደሚሉት ኤርትራ ያለው የፕሬስ ሁኔታ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ሁሉ የከፋ ነው።

«እንደሚታወቀው ኤርትራ በአፍሪካው ቀንድ ፕሬስ በፍጹም ጭቆና ውስጥ ነው ያለባት ሀገር ናት። ኤርትራ ውስጥ ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብት የሚሞከር አይደለም። ላለፉት አስር ዓመታት የማይቻል ቢኖር ይህን መብት ማግኘት ነው። ነጻም ሆነ ገለልተኛ ፕሬስ የለም።ከ30 በላይ ጋዜጠኞች እስር ቤት ያስገባች ሀገር ናት። ለዚያች ትንሽ ሀገር ይህ ቁጥር በጣም ከፍተኛ ነው።»

ሶማሊያ ኤርትራን ተከትላ የፕሬሱ አያያዝዋ የከፋባት ሁለተኛዋ የአፍሪካው ቀንድ ከፍል ተብላለች- በድንበር የለሹ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት አር ኤስ ኤፍ ሪፖርት። ሶማሊያ በተለይ የጦርነቱ ሁኔታ ፕሬሱን እንዳሽመደመደውና ጋዜጠኞች የሚገደሉባት ሁለተኛዋ የዓለም ክፍል በሚል ትብጠለጠላለች። ሱዳን የሰሜን አፍሪካው የተቀጣጠለ የህዝብ አብዮት የከፋውን የፕሬስ ገጽታዋን የባሰ እንዲሆን እንዳደረገባት አር ኤስ ኤፍ አስታውቋል። አዲስ የተፈጠረችው ደቡብ ሱዳን የሰሜኑን አርዓያ ከተከተለች ቀጠናውን ለፕሬስ ፈጽሞ የማይመች ሊያደርገው እንደሚችልም ስጋቱን ገልጿል። ሌላዋ የፕሬስ ጨቋኝ ተብላ የምትወቀሰው ሀገር ኢትዮዽያ ናት። በየጊዜው ሪከርዷ እየተበላሸ ከነጭራሹም ከዓለም 10 አፋኝ ሀገሮች ምድብ የተሰለፈችው ኢትዮዽያ የግሉ ፕሬስን በማዳክምና በማጥፋት፤ የኢንተርኔት ቁጥጥሯን በማጥበቅ፤ ነጻ ሀሳቦች እንዳይንሸራሸሩ ትልቅ መሰናክል በመሆን በተለያዩ የሰብዓዊና የፕሬስ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች ክስ ይቀርብባታል። በቅርቡ የዓለም ዓቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ሲፒጄ እንዳወጣው መረጃ ከሆነ ኢትዮዽያ ከዓለም 10 የኢንተርኔት አፋኝ ሀገራት ብቸኛዋ አፍሪካዊ ሀገር ሆና ተቀምጣለች። የድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች አር ኤስ ኤፍ የአፍሪካው ክፍል ሃላፊ አምብሮይስ ፒየ በኢትዮዽያ ያለው የፕሬስ ሁኔታ ያሳስበናል ይላሉ።

«በኢትዮዽያ በባህላዊውም ሆነ ኢንተርኔትን በመሳሰሉት የዘመኑ የመገናኛ አውታሮች ላይ የሚደረገውን የፕሬስ ማነቆ በቅርበት እየተከታተልን ነው። ከሁለት ወራት በፊት ኢትዮዽያ በኢንተርኔት ላይ የምታደርገውን አፈና አጽንኦት ሰጥተን የተቃውሞ መግለጪያ አውጥተን ነበር። በኢትዮዽያ መንግስት በጋዜጠኞች ላይ የሚያደርገው ክትትል ያሳስበናል። ይህ ክትትልም ሆነ የፕሬስ አፈናው እንዲቆም የኢትዮዽያ መንግስት ባለስልጣናትን በይፋ ጠይቀናል። የጋዜጠኞችን መብት እንዲያከብር፤ የግሉ ፕሬስ ላይ ያሳረፈውን ዱላ እንዲያነሳም ጠይቀናል።አሁንም ቢሆን የኢትዮዽያ መንግስት ሀሳብን በነጻ የመግለጽንና የመገናኛ ብዙሃን በነጻነት የመነቀሳቀስ መብቶችን እንዲያከብር ጥሪ እናደርጋለን።»

ባለፈው ማክሰኞ በተከበረው የዓለም የፕሬስ ቀን ላይ ኢትዮዽያ ውስጥ የተፈጠረው ክስተት ብዙዎችን አነጋግሯል። ዓለምዓቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ሲፒጄ ማክስኞ በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል የተዘጋጀው የፕሬስ ቀን ስብሰባ በመንግስት ጠለፋ ተደረገበት ሲል መግለጪያ አውጥቷል። በዕለቱ ጥናታዊ ወረቀት እንዲያቀርቡ ፕሮግራም የተያዘላቸውን ጋዜጠኞችና ባለሙያዎች ከመድረክ በማስወረድ መንግስት ራሱ ያዘጋጃቸውን አቅራቢዎች ተክቶ ስብሰባውን ጠልፏል በማለት ነው ሲፒጄ ድርጊቱን ያወገዘው የኢትዮዽያ መንግስት ግን ያስተባብላል። በእርግጥ የአፍሪካው ቀንድ ሀገራት ከፕሬስ አንጻር ስማቸው እንዲህ በመጥፎ ቢነሳም ከመሃላቸው በመልካም አያያዛቸው የሚወደስ አልጠፋም። ኬኒያ በአንጻራዊ መለኪያ የተሻለ የፕሬስ አያያዝ ያለባት ሀገር ተብላ ውዳሴ ተችሯታል። የድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች አር ኤስ ኤፍ የአፍሪካው ክፍል ሃላፊ አምብሮይስ ፒየም በዚህ ይስማማሉ።

«በምስራቅ አፍሪካ ኬንያ የተሻለ የፕሬስ ይዞታ ነው ያላት። ከሌሎቹ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በተለየ መልኩ በኬኒያ ጋዜጠኛ መሆን አስቸጋሪ አይደለም። በእርግጥ እንዲዚህ ሲባል ለጋዜጠኞች ፍጹም የተመቸች ማለት አይደለም። ጫና ይኖራል። የሚታሰርም ይናራል። ግን እንደሌሎቹ ሀገራት በከፍተና ቁጥር የሚታሰሩባትና የሚከሰሱባት አይደለችም።»

አድማጮች ባለፈው ማከሰኞ የተከበረውን የዓለም የፕሬስ ቀን መነሻ አድርገን የአፍሪካውን ቀንድ ሀገራት የፕሬስ ሁኔታ የቃኘንበት ትኩረት በአፍሪካ የመጀመሪያው ርዕሰ ጉዳያችን በዚሁ ተጠናቋል። በሁለተኛነት ወደያዝነው ርዕስ እናልፋለን። እዚያው ምስራቅ አፍሪካ ላይ ቆይተን ከኦስማ ቢን ላደን መገደል ጋር በተያያዘ የአፍሪካውያንን ስሜት በአጭሩ እንመለከታለን።

---------------------------------------------------

ዕሁድሊት አቦታባድ በተሰኘች የፓኪስታን ከተማ ለ10 ዓመታት በአሜሪካን ሲታደኑ የነበሩት ኦስማ ቢን ላደን ተገደሉ። ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ፤ ይህንን በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው ለዓለም ነገሩ። ከዚያን ቅጽበት የጀመረ በዓለም ዙሪያ የተለያዩ አስተያየቶችና ስሜቶች ሲንጸባረቁ ነበር ሳምንቱ የዘለቀው። አሜሪካውያን አደባባይ ወጥተው ደስታቸውን ለመግለጽ የኦባማን መግለጪያ እንኳን አልጠበቁም። ኒውዮርክና ዋሽንግተን በደስታ ደመቁ። የዚያኑ ሌሊት። የኦስማ ቢን ላደን የመገደል ዜና ለአፍሪካ በተለይም ለምስራቁ ክፍል በአንድም ይሁን በሌላ ተጽዕኖ ማሳደሩ አልቀረም። እ.ኤ.አ በ1998 በናይሮቢና በታንዛኒያ ዳሬሰላም የአሜሪካን ኤምባሲዎች ላይ ለተፈጸመውና ለ230 ሰዎች ሞት ምክንያንት ለሆነው የቦምብ ጥቃት በቀጥታ እጃቸው እንዳለ የሚነገርላቸው ኦስማ ቢን ላደን ናቸው፤ በእርግጥ ዕሁድ ሌሊት የተገደሉት። ኬኒያውያን በኦስማ ቢን ላደን መገደል የተሰማቸውን ደስታ ከመግለጽ ይልቅ ሌሎች ጥቃቶች ስለመኖራቸው ይፈራሉ። አንድ የናይሮቢ ነዋሪ የበቀል በትር ቢኖርስ ሲል ስጋቱን ይገልጻል።

«አሜሪካ የፈጸመችው ተግባር ትልቅ ስኬት ነው። ይሁንና ግን ጥቃት ሊሰነዘርብን እንደሚችል እየሰማን ነው።የበቀል እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ። ምክንያቱም መሪያቸው ተግድሏልና።»

NO FLASH Afghanistan Terror Osama Bin Laden

ሌላኛው ኬኒያዊ ደግሞ ኦሳማ ቢን ላደን ከሚገደሉ ይልቅ ቢያዙ ይመረጥ ነበር ይላል።

«በህይወት ለተረፉት ትልቅ እፎይታ ነው። እኔ ግን የሚሻል የሚመስለኝ በህይወት ቢያዝ ነበር። ምክንያቱም እሱን መግደል ማለት ለሌሎቹ ተከታዮቹ እንደ ጀግና ሊወሰድ ይችላል። ይህም በርካታ ቢን ላደኖች እንዲፈለፈሉ ያደርጋል። እንዲህ ከሆነ ደግሞ የበለጠ ቀውስ ብጥብጥ ግድያና የሽብር ጥቃት ሊኖር ይችላል።»

ዳግላስ ዲዲአሎ እ.ኤ.አ በ1998 በናይሮቢ የአሜሪካን ኤምባሲ በተፈጸመው የሽብር ጥቃት ሁለት ዓይኖቹን አጥቶአቸዋል። የኦስማ ቢን ላደን መገደል ብዙም ያስደሰተው አይመስልም። ወደር የሌለው ደስታዬ ቢያዝ ኖሮ ነበር ነው የሚለው።

«በግሌ በመገደሉ ደስተኛ አይደለሁም። በህይወት ቢያዝ ኖሮ ያቺ ቀን ለኔ የደስታ ቀን ትሆን ነበር። ምክንያቱም መገደሉ ሌሎች ቢን ላደኖችን ይፈጥራል ብዬ እስጋለሁ። ያ ደግሞ ዳግም ሰላማችንን እንድናጣ ያደርገናል።»

በእርግጥ ከደስታና ከስጋት ጋር የተደበላለቀው የኬንያውያን ስሜት ጥርጣሬም አልተለየውም። አንዳንድ ኬንያውያን የኦስማ ቢን ላደን መገደልን ያመኑ አይመስሉም።

«ሞቷል ብዬ አላምንም። ምክንያቱም ከዚህ ቀደም ለ6 ጊዜ ገድለነዋል ብለው ተናግረው ነበር። እናም አሁን አስክሬኑ በእጃችን አለ ብለው እየተናገሩ ነው። እንደዚያ ከሆነ ፎቶግራፉን ያሳዩን። ስለምናውቀው በቀላሉ እንለየዋለን። ያኔ የሚሉትን ልነቀበል እንችላለን። በተረፈ ግን ግድለነዋል የሚሉት እውነት አይደለም። ምክናያቱም ስድስት ጊዜ ገለናል ብለዋል።»

አልቄይዳ በረጅም እጁ ያተራምሳታል የሚባልላት ሌላዋ የምስራቅ አፍሪካ ሀገር ሶማሊያ ናት። አልሸባብ የተሰኘውና የምዕራቡ ዓለም ድጋፍ ያለውን የሽግግር መንግስት ለማጥፋት የሚፋለመው ቡድን የአልቄይዳ ተላላኪ በመሆኑ በኦሳማ ቢን ላደን መገደል ይዳከም ይሆን የሚል ጥያቄ መነሳቱ አልቀረም። በእርግጥ የአጃንስፍራንሱ ዘጋቢ ሙስጠፋ ሀጂ እንደሚለው የሽግግር መንግስቱ የቢን ላደን መገደል ለሶማሊያ ሰላም ወሳኝ ነው ብሎ ያምናል።

አንዳንድ የሞቃዲሾ ነዋሪዎች በኦስማ ቢን ላደን መገደል የተደሰቱ መሆናቸውን ገልጸዋል። ሆኖም አብዛኛው የሚለው ብዙም ለውጥ አያመጣም ነው።

ድምጽ

በእርግጥ የኦስማ ቢን ላደን መገደል የሶማሊያን ሰላም አንዲት ስንዝር ወደፊት አያራምደውም የሚለው አስተያየት ከተለያዩ ወገኖች ይሰማል። የግድያው ዜና እንደተሰማ በሞቃዲሾ ጎዳናዎች ነጭ በመልበስ የሀዘን ስሜታቸውን የገለጹት አንዳንድ የአልሸባብ ተዋጊዎች በአዲስ ስልት ጥቃት ሊፈጽሙ እንደሚችሉ ይነገራል። በአፍሪካ የሰላምና ጸጥታ እንዲሁም ግጭት አፈታት ጥናት ተቋም የታንዛኒያው ዳይሬክተር ኮስማስ ባሃሊ አልሸባብ ስጋት መሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል ባይ ናቸው።

«በሶማሊያ ሰላም ለማስከበር የተሰማሩት ሀገራት የተጠናከረ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ እየተናገሩ ናቸው። ትክክል ናቸው። አልሸባብ አሁን ስልቱን ሊቀይር ይችላል። እናም የጥንቃቄ እርምጃ ከወዲሁ ሊያስቡበት ይገባል። አልሸባብ የተጠናከረና ብርቱ ሃይል ሆኖ መውጣት ይፈልጋል። ጥቃቱን በተጠናከረ ሁኔታ ሊቀጥል ይችላል። የምስራቅ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን የዓለም ስጋት መሆኑ አይቀርም።»

ሌላው ኦስማ ቢን ላደን መገደል ጋር በተያያዘ የተጠናከረ ተቃውሞ የተሰማው ከወደ ሱዳን ናት። በአንድ ወቅት ኦስማ ቢን ላደን ማረፊያ የነበረችው ሱዳን፤ በመዲናዋ ካርቱም ከ1000 ሺህ በላይ ሰዎች አደባባይ ወጥተው አሜሪካንን ሲያወግዙ፤ ግድያውንም ሲቃወሙ ውለዋል።

አድማጮች ትኩረት በአፍሪካ ይህን ይመስል ነበር። ሳምንት በተመሳሳይ ፕሮግራም በሌሎች ርዕሰች እጠብቃችኃለሁ። ጤናይ ስጥልኝ።

መሳይ መኮንን

መስፍን መኮንን

Audios and videos on the topic