ትኩረት በአፍሪቃ | ኢትዮጵያ | DW | 19.09.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ትኩረት በአፍሪቃ

በዛሬው ትኩረት በአፍሪቃ ዝግጅታችን Human rights watch በኢትዮጵያ በእስረኞች ላይ ቁም ስቅል ይፈፀማል ማለቱን ተከትሎ ከድርጅቱ ከፍተኛ ተመራማሪ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ ሰፊ ቦታ ይሰጠዋል። በጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ የሚያጠነጥን መሰናዶም ይዘናል። የጋዜጦች አምድ ዝግጅታችን በይልማ ሀይለ ሚካኤል ተሰናድቷል።

ሰላም አልባዋ ሶማሊያ

ሰላም አልባዋ ሶማሊያ

የብሪታንያ መንግስት በሽብር ተግባር የተጠረጠሩ ኢትዮጵያውያንን በግዳጅ ወደ ሀገራቸው ለመላክ የኢትዮጵያ መንግስት በተጠርጣሪዎቹ ላይ ቁም ስቅል እንደማይፈፀምባቸው ማረጋገጫ መስጠቱን አምኖ መቀበሉን በመቃወም Human rights watch አስጠነቀቀ። በአንፃሩ የኢትዮጵያ መንግስት ቃል አቀባይ አቶ በረከት ስምኦን ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ከአዲስ አበባ እንደተናገሩት መግለጫው ከሰብአዊ መብት ጋር ተያያዥነት የሌለው የፖለቲካ ጨዋታ ነው ሲሉ አጣጥለውታል። እንደ Human rights watch መግለጫ ከሆነ ብሪታንያና ኢትዮጵያ ተጠርጣሪዎችን ለመለዋወጥ የተፈራረሙት የዛሬ ዘጠኝ ወራት ገደማ ነው። ተጠርጣሪዎቹ ወደ ኢትዮጵያ ቢላኩ በመንግስት በኩል ቁም ስቅል ሊፈፀምባቸው ይችላል ያሉት በHuman rights watch የአፍሪቃ ጉዳይ ከፍተኛ ተመራማሪዋ ሚስ ሌስሊ ሌስካው ለብሪታንያ መንግስት ማስጠንቀቂያ መላካቸውንም ገልፀዋል።

የሶማሊያ ወቅታዊ ጉዳይ

የተባበሩት መንግስታት አርማን የለጠፉ ሁለት ነጫጭ ካሚዮኖች በቀጥታ ወደ ሞቃዲሾ ዋናው አየር ማረፊያ አቀኑ። ሾፌሮቹ አጥፍቶ ጠፊ ሶማሊያውያን ናቸው። አየር ማረፊያውን በመጠበቅ ላይ የነበሩት ደግሞ ከኡጋንዳና ቡሩንዲ የተውጣጡ የአፍሪቃ ሰላም አስከባሪ ሀይላት። ሶማሊያውያን አጥፍቶ ጠፊዎቹ አታለው ወደ አየር ማረፊያው መግባት በቻሉበት ወቅት በአየር ማረፊያው የሰሠላም አስከባሪው ሀይላት በሶማሊያውያን መካከል ድርድር ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ነበሩ። አጥፍቶ ጠፊዎቹ ወደ አየር ማረፊያው ማስገባት የቻሏቸውን ሁለት የተባበሩት መንግስታት ነጫጭ ካሚዮኖች አጎኑ። እናም የራሳቸውን ጨምሮ የአስራ ሰባት የአፍሪቃ ሠላም አስከባሪ ሀይል አባልትና የአራት ሠላማዊ ሰዎችን ህይወት ቀጠፉ። በዕለቱ ለሞት ከተዳረጉት ሰላም አስከባሪ አባላት መካከል የሰላም ድርድሩን ለማካሄድ ደፋ ቀና ይሉ የነበሩት የቡሩንዲ ሀይል ምክትል አዛዥ ይገኙበታል። ዋና አዘዡ ቀላል የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸው ከሞት ሊተርፉ ችለዋል።

ዩኤስ አሜሪካ ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት አላቸው ከምትላቸው የአልሸባብና ሂዝቡል ኢስላም ደፈጣ ተዋጊዎች አንዱ ማለትም የአልሸባብ ቡድን ጥቃቱን በሀላፊነት መውሰዳቸው ተሰምቷል። ሁለቱ የእስልምና ሀይማኖት ፅንፈኛ ቡድኖች ቀደም ሲል ሰፊ የጥቃት ኢላማቸውን በኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ላይ አነጣጥረው እንደነበር መግለፃቸው ይታወቃል። የኢትዮጵያ ሰራዊት ከሶማሊያ ከወጣበት ጊዜ አንስቶ ፅንፈኞቹ ሙሉ ለሙሉ የጥቃት ኢላማቸውን በሶማሊያ መንግስትና የአፍሪቃ ሠላም አስከባሪ ሀይላት ላይ እንዳዞሩ ታውቋል።

የሐሙሱ ጥቃት ከመፈፀሙ ቀደም ብሎ ዩናይትድ ስቴትስ የምስራቅ አፍሪቃ ዋነኛ የአልቃይዳ አቀንቃኝ በሚል ስታድነው የነበረውን ኬንያዊ ሰኞ ለት ሶማሊያ ምድር ውስጥ መግደሏ ይታወቃል። ከየመን ቤተሰቦች የተገኘው የኬንያ ተወላጁ ሳለህ አሊ ሳለህ ናብሀንን ጨምሮ ሌሎች የአልቃይዳ ተጠርጣሪዎችን ሶማሊያ ውስጥ የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ ሀይል በሁለት ሂሊኮፕተሮች ታጅቦ ነበር የደመሰሰው።

የሳለህ አሊን መገደል በማረጋገጥ አልሸባብ የበቀል እርምጃ እንደሚወስድ ከሀሙሱ ጥቃት ሶስት ቀናት በፊት ዝቶ እንደነበርም ይታወቃል። አልሸባብ የአፍሪቃ ሠላም አስከባሪ ሀይላት ሙሉ በሙሉ ከሶማሊያ ምድር እስካልወጡ ድረስ ጥቃት መፈፀሙን እንደሚገፋበትም ዝቷል። የአፍሪቃ ህብረት በበኩሉ አሁን በሶማሊያ ምድር ከሚገኙት የቡሩንዲና ኡጋንዳ ሰላም አስከባሪዎች በተጨማሪ ሌሎች ስምንት ሺህ አባላትን ወደ ሶማሊያ ለማምጣት ይሻል። ያን ለማሳካትም አባል ሀገራት የሰላም አስከባሪ ሀይላት እንዲልኩ ቢወተውትም እስካሁን ድረስ ግን የተፈለገው ቁጥር ሊሟላ እንዳልቻለ ታውቋል።

MS/YH