1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትንባሆን ያለማጨስ ዕለት

ማክሰኞ፣ ግንቦት 21 2010

ፈረንሳይ ካፈለው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የአጫሽ ዜጎቿ ቁጥር በ1 ሚሊየን መቀነሱን ይፋ አድርጋለች። ትንባሆ በተለይ በልብ እና የመተንፈሻ አካልት ጉዳት ብሎም ለድንገተኛ የደም ዝውውር መታወክ እንደሚዳርግ ሃኪሞች ያሳስባሉ። በየዓመቱም በትንባሆ መዘዝ ከ7 ሚሊየን የሚበልጡ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጣሉ።

https://p.dw.com/p/2yYkM
EU-Parlament Abstimmung Tabakrichtlinien Schockbilder
ምስል Imago/teutopress

ትንባሆና ሱስ

ለልብ እና ከልብ ጋር ለተያያዘ የጤና ችግር እንደሚያጋልጥ የሚያሳስብ መሪ ቃል ነው ለዘንድሮው ትንባሆን ያለማጨስ ቀን በዓለም የጤና ድርጅት የተመረጠው። የዛሬ 14 ዓመት ገደማ በዓለም የጤና ድርጅት አሳሳቢነት ትንባሆ ላይ ቁጥጥር እንዲደረግ የተደረሰውን ስምምነት ብዙ ሃገራት ተቀብለውታል። ምንም እንኳን ባጠቃላይ ትንባሆን ሰዎች እንዳይጠቀሙ ማድረግ ባይችሉም የተለያዩ ሃገራት ልዩ ልዩ ስልቶችን በመጠቀም ፍላጎት እንዲቀንስ ጥረት ያደርጋሉ። የትንባሆ መጠቅለያዎች ላይ የሚያስከትለውን የጤና ጉዳት የሚያሳዩ ፎቶዎችን፤ ትንባሆ ገዳይነቱን የሚያስገነዝቡ ጽሑፎችን ይለጥፋሉ። ሰዎች በርከት ብለው በሚሰበሰቡባቸው የተለያዩ ስፍራዎች እንዳይጨስም ደንግገዋል።

 ኢትዮጵያም ከሁለት ዓመታት በፊት በአንዳንድ ከተሞች ተመሳሳይ ድንጋጌ ማድረጓ ተነግሯል። ተግባራዊነቱ እንዴት ይሆን ብለን በዋትስፕ አድራሻችን ከደረሱን አስተያየቶች አስተያየት ጥቂቱ እንዲህ ይላሉ፤

«የሚከለክል ሕግ ወጥቷል ግን በአግባቡ አንዳንድ ቦታ ላይ አይተገበርም» አንዱ፤ ሌላኛው፤ «ተብሎ ነበር ግን ሥራ ላይ አልዋለም» እንዲሁም ሌላው ደግሞ «አዲስ አበባ ላይ አልተተገበረም።» ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ትንባሆ በየዓመቱ ከሰባት ሚሊየን የሚበልጡ ሰዎችን ሕይወት እንደሚቀጥፍ የሚናገረው የዓለም የጤና ድርጅት ከዚህ መካከል 900 ሺው ቀጥተኛ አጫሽ አለመሆኑን አፅንኦት ይሰጣል። ለዚህም ነው ሰዎች በተሰበሰቡበት ስፍራ እንዳይጨስ የሚደነግግ ሕግ እንዲኖር ግድ ያለው። አቶ ወንዱ በቀለ የማትያስ ካንሰር ሶሳይቲ መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። ኢትዮጵያም ይህን ሕግ ማጠናከር ላይ ናት ይላሉ።

Bildergalerie Rauchverbot
ምስል picture-alliance/AP Photo/Ng Han Guan

«ይሄ ሕግ እንግዲህ ከሚያነሳቸው ነጥቦች አንዱ ሕዝብ በተሰበሰበበት ቦታ የማጨሻ ቦታ እንኳን እንዳይፈቀድ የሚከለክል ነው። ዋናው አላማ ምንድነው የሚያጨሱ ሰዎች የማጨሻ ስፍራ ቢፈቀድላቸው፤ የማጨሻ ቦታው የማያጨሱ ሰዎችን እንዳይደርስ ማድረግ በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ በየስርቻው እንደዚህ አይነት ነገር መፍቀድ ስለማይቻል ተብሎ ነው የገባው እንግዲህ ይሄ አሁን ወደፓርላማ እየሄደ ነው የእኛ ሕግ እዚህ ሀገር ውስጥ ይሄንን የተመን ሕግ ወደኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የሚተረጉመው ሀገራዊ ሕግ እየሠራን ለው ያለነው ከኢትዮጵያ ምግብ መድኃኒት እና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ጋር አሁን ሚኒስትሮች ምክር ቤት አካባቢ ነው ያለው። »

በቅርብ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ የትንባሆ ተጠቃሚነትና ሱሰኝነትን የተመለከተ ሀገር አቀፍ ጥናት መካሄዱን ለመረዳት ችለናል። እንደጥናቱ ከሆነም የትንባሆ ሱስ ተጠቂዎቹ በአብዛኛው ወንዶች ናቸው። ከጥናቱ በመነሳትም ዶክተር ሰሎሞን ተፈራ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአእምሮ ህክምና ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር፤ የስነልቡና ተለይም በአልክሆል እና እፆች ሱስ ህክምና ልዩ ሃኪም ቁጥራቸውን በመቶኛ ያሰሉታል።

«ወንዶች ወደ ስድስት ከመቶ አካባቢ ነው ሴቶች ላይ ዜሮ ነጥብ ሁለት ከመቶ ነው ያገኘነው። ስለዚህ በአብዛኛው በትንባሆ ሱስ ወይም በሲጋራ ሱስ የተጠቁ ዜጎቻችን አንዶች ናቸው ብዬ መናገር እችላለሁ።»

E-Cigarettes Elektrische Zigarette
ምስል Getty Images

ሰዎች ትንባሆን መጠቀም በጤናቸው በኤኮኖሚ አቅማቸውም ሆነ በማኅበረሰቡ ውስጥ በሚኖራቸው መስተጋብር ላይ የሚኖረውን አሉታዊ ተፅዕኖ መዝነው በፍላጎታቸው አላጨስም ብለው ለመወሰን የሚያስችላቸው አቅም ሁሉም ላያገኙ እንደሚችሉ የሚታይ ነው። ያኔ የሃኪም ርዳታ ማግኘት ይችላሉ ነው የሚሉት የስነልቡና በተለይም በአልክሆል እና እፆች ሱስ የተጠመዱ ሰዎችን በህክምና የሚረዱት ዶክተር ሰሎሞን ተፈራ። እንዲህ አይነቱ የህክምና አገልግሎት ኢትዮጵያ ውስጥ ከተጀመረ ጥቂት ዓመታት ብቻ በመሆኑ ግንዛቤው አለመስፋፋቱ ሰዎች ከሱስ ለመላቀቅ ቢፈልጉም ረዳት የሚያገኙ ስለማይመስላቸው መሆኑንም አፅንኦት ሰጥተዋል።

ከነገ በስተያ ሐሙስ ዕለት የዓለም ትንባሆ ያለማጨስ ቀን ሲታሰብ አዲስ አበባ ላይ የተደነገገውን ሕዝብ በሚሰበሰብበት ስፍራ እንዳይጨስ የሚለውን ሕግ በአግባቡ በሥራ የተረጎሙ ጥቂት ሆቴሎች እንደሚሸለሙ ለመረዳት ተችሏል። ሙሉ ቅንብሩን ከድምፅ ዘገባዉ ያድምጡ።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ