ትንባሆ የማይጨስበት ዕለት | ጤና እና አካባቢ | DW | 31.05.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

ትንባሆ የማይጨስበት ዕለት

ባለማጨስዎ እናመሰግናለን! በአንዳንድ ቦታዎች ሲገቡ የሚያነቡት ትህትና የተላበሰ ማሳሰቢያ ነዉ። ዛሬ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ትንባሆ የማይጤስበት ዕለት ነዉ።

default

ምን ያህሉ ሱሰኛ ይህን አድርጓል እሱን ለባለጉዳዮቹ እንተወዉ። ትንባሆ ማጨስ ግን በተለይ ድምፅ አልባ ለሚባሉት እንደልብና መተንፈሻ አካላትን ለከባድ የጤና ችግር ብሎም ህይወትን ለማጥፋት የሚዳርጉ መዘዞችን የሚያስከትል መሆኑን ሃኪሞች በየጊዜዉ ያሳስባሉ። በሩሲያ በየዕለቱ በአማካኝ እያንዳንዱ ሩሲያዊ 17 ሲጋራ እንደሚያጨስ የአገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዛሬ ይፋ አድርጓል። በዓለም ትንባሆን በከፍተኛ ደረጃ ከሚጠቀሙ ሀገራት ግንባር ቀደም በተባለችዉ ሩሲያ ማጨስ ለበርካቶች የጤና ችግር ምክንያትና ያለዉንም ህመም ለማባባስ ተጠያቂ ነዉ ተብሏል። በሞስኮ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የሚኒስቴር መስሪያቤቱ ከፍተኛ ዶክተር ግሪጎሪ ኦንሼንኮ የትንባሆ ቸብቻቢ ማፍያዎች የ400 ሺ ሩሲያዎችን ነፍስ የእነሱን ገቢ ለማስጠበቅ ባሪያ አድርገዋል ሲሉ በምሬት መናገራቸዉን የጀርመን የዜና ወኪል ከስፍራዉ ዘግቧል። በሩሲያ በተለይ የወጣት፤ ታዳጊ ብሎም ሴት አጫሾች ቁጥር ከአዉሮጳዉያኑ 2005ዓ,ም ወዲህ እጅግ መጨመሩም ተነግሯል። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴሩ ጥናት እንዳመለከተዉም ከአስሩ ሩሲያዊ ሶስቱ በቋሚነት ካለ ትንባሆ አይኑ አይከፈትም።

Dossierbild Rauchverbot Nichtraucherschutz 1

ለዚህ ነዉ የጤና ባለሙያዎችና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሰዎችን በገዛ ፈቃዳቸዉ የወራሳቸዉ የሚጋብዙትን የጤና እክል ለመቀነስ ሲሉ ጠንከር ያሉ ማስታወቂያዎች በየትንባሆ ካርቶኑ ላይ እንዲፃፍ ቅስቀሳ ያካሄዱት። እዚህ ጀርመን አገርም ከየትንባሆ ማስታወቂያም ሆነ ፓኮ ላይ ማጨስ ይገድላል፤ የሚል ማስፈራሪያ ደመቅ ብሎ ይፃፋል። ሩሲያ ዉስጥም ይህ ተጠይቋል። እንደዉም ዶክተር ኦንሼንኮ ያሉት በየፓኮዉ ላይ በትንባሆ ጭስ የተጎዱ የሰዉነት ክፍሎችን ምስል ለማዉጣት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። እሳቸዉ እንደሚሉት ሌሎች ሀገራትን ይህን ስልት ተጠቅመዉ በሲጋራ ሱስ የተጠመዱ ዜጎቻቸዉን ቁጥር መቀነስ ችለዋል። የሩሲያ መንግስት በተለይ የወጣት አጫሾችን ቁጥር ለመቀነስ የተጠናከረ ዘመቻ ለማድረግ አቅዷል። በነገራችን ላይ የዓለም የጤና ድርጅት ይህን ዕለት አስመልክቶ ይፋ እንዳደረገዉ፤ በየዓመቱ በዓለማችን ስድስት ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች በትንባሆ ምክንያት ያልቃሉ። ከዚህ ቁጥር መካከል 600 ሺዎቹ ራሳቸዉ ባጨሱት ሳይሆን ሌሎች ባጨሱት መዘዝ ህይወታቸዉ ያልፋል። ይህ የሆነዉ ደግሞ መንግስታት የትንባሆ ሱሰኞች ሌሎችን በጭሱ እንዳይጎዱ የሚረዳ ህግ ስለሌላቸዉ ነዉ ሲል የዓለም የጤና ድርጅት ወቅሷል። እንደድርጅቱ ዘገባ ትንባሆ በአጫሾቹ ላይ የሚያሳርፈዉን የጤና እክል ይፋ ለማዉጣት ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ ተጠቃሚዎቹ ችግሩን የሚረዱት ጉዳቱ ስር ከሰሰደ በኋላ ነዉ። አሁን የሚታየዉ በትንባሆ መዘዝ የሚከተለዉ የጤና እክል ተባብሶ ከቀጠለም ከአዉሮጳዉያኑ 2030ዓ,ም ጀምሮ በእሱ ምክንያት በየዓመቱ የሚያልቀዉ ሰዉ ብዛት ወደስምንት ሚሊዮን ይጠጋል።

Symbolbidl Zigaretten Zigarettenberg Raucher Kippe Zigarette

በ21ኛዉ ክፍለ ዘመን የሰዉ ልጅ ሊቆጣጠረዉ በሚችል እክል ይህን ያህል ሰዉ በየዓመቱ እንደዋዛ ህይወቱ ማለፉ ያሳሰበዉ የተመድ ከአምስት ዓመታት በፊት ባሳለፈዉ ዉሳኔ መሠረት ሀገራት የትንባሆ ተጠቃሚዎችን ቁጥር የሚቀንስበትን መንግድ እንዲቀይሱ፤ የትንባሆ ማስታወቂያዎችን እንዲቀንሱ፤ ጭሱም የማያጨሱትን እንዳይጎዳ መፍትሄ እንዲፈልጉ ጠይቋል። በዚሁ መሠረትም እስካሁን 172 መንግስታትና የአዉሮጳዉ ኅብረት ይህን ስምምነት ፈርመዋል። ቀደም ሲል በዓለም የጤና ድርጅትና በሌሎችም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተጠና ጥናት ግሪኮች አለያም ስሎቬኒያኖች ከዓለም ለረዥም ዓመታት ትንባሆን በማጨስ የሚታወቁ እንደሆኑ ያመለክታሉ። ዛሬ ይህን አስመልክተዉ ከተሰሙ ዘገባዎች አንዱ ይህን ይላል፤ በኒዉዚላንድ እስረኞች ከነገ ጀምሮ ትንባሆ ማጨስ የተከለከሉ ሲሆን በምትኩ ካሮት እንዲበሉ ታዝዘዋል። በአገሪቱ ወህኒ ቤት ከሚገኙት 8,700 እስረኞች መካከል ሁለት ሶስተኛዉ አጫሽ ነዉ። ሲጋራ በእስር ቤት ይዞ መገኘት ህገወጥ መሆኑ በተገለፀባት ኒዉዚላንድ ወህኒ ቤቶች ለእስረኞች በየዕለቱ ሁለት ሁለት ካሮት እንዲሰጡ ትዕዛዝ ተላልፏል። የታራሚዎች ማኅበር ለዘጋቢዎች እንደገለጸዉ አጫሾች ከትንባሆዉ ጭስ በተጨማሪ ይበልጥ የሚፈልጉት አፋቸዉ ዉስጥ የሚከቱት ነገር እስከሆነ ድረስ ካሮቱን ካገኙ ሲጋራ አይፈልጉም። ይህ ምን ያህል እዉነትነት እንዳለዉ የሚያዉቁት አጫሾች ቢሆኑም፤ የኑዉዚላንድ እስረኞች ትንባሆን እንዳያስታዉሱ ከካሮት በተጨማሪ በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሊጠመዱ ነዉ። ይቅናቸዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

መሳይ መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

ተዛማጅ ዘገባዎች