ትራንስ አትላንቲክ ነጻ ንግድ | ኤኮኖሚ | DW | 10.07.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ትራንስ አትላንቲክ ነጻ ንግድ

በዩ ኤስ አሜሪካና በአውሮፓ ሕብረት መካከል የሚካሄደው ትራንስ አትላንቲክ የንግድና መዋዕለ ነዋይ ሽርክና ውል ድርድር ባለፈው ሰኞ ዋሺንግተን ላይ ተጀምሯል።

ድርድሩ የተከፈተው የአሜሪካ ብሄራዊ የጸጥታ ተቋም የስለላ ተግባር በአውሮፓ ሕብረት ውስጥ ያስከተለው ቁጣ በጋረደው ሁኔታ ነው። በዓለም ላይ ታላቁ የሚሆነውን የነጻ ንግድ ክልል ለመፍጠር ቀደም ብሎ የታቀደው ድርድር የአሜሪካው የጸጥታ ተቋም የአውሮፓውያንን ሰፊ የስልክና የኢንተርኔት ዳታዎች በመጥለፍ በፈጸመው ድርጊት ሊከሽፍ ብዙም አልቀረውም ነበር። እርግጥ የጀርመን የምጣኔ-ሐብት ምርምር ኢንስቲቲዩት ባልደረባ ጋብሪዬል ፌልበርማይር እንደሚሉት ቅራኔው ምናልባትም ጥቂትም ቢሆን ተጋኖ መቅረቡ አልቀረም።

«በበኩሌ እንደማስበው የወቅቱ የአሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት ውዝግብ ከሌሎች ሃገራት ጋር ከምናውቀው የስለላ ችግር ሲነጻጸር በጣም አነስተኛ ነው። ይልቁንም ከቻይና ጋር ያለው የኤኮኖሚ ስለላ ችግር ከአሜሪካው በአሥርና በመቶ ዕጅ የበለጠ ነው ለማለት ይቻላል»

ድርድሩ በታሰበው ጊዜ ለጀመር የቻለው የአውሮፓ ሕብረት ከትራንስ አትላንቲኩ የንግድ ድርድር ጎን ለጎን በስለላው ድርጊት ላይም ንግግር እንዲደረግ ያቀረበው ጥያቄ በዋሺንግተን ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ነው። በዚሁ የተነሣም ከንግዱ ድርድር ባሻገር በዋሺንግተኑ የፍርድ ሚኒስቴር የሁለቱ ወገን ተጠሪዎች ተገናኝተው በስለላው ጉዳይ ተነጋግረዋል። ብራስልስ በበኩሏ ዋሺንግተን ሕግን የማትከተል ከሆነ በከባድ ድርድር በሁለቱ ወገኖች መካከል በሰፈኑ የዳታ ልውውጦች፤ ማለትም የአየር መንገድ ተጓዦችን ዳታና የባንክ መረጃዎችን ትብብር ለማቆም እንደምታስብበት አሜሪካን አስጠንቅቃለች። የአውሮፓ ሕብረት ቁጣ ስር የሰደደ መሆኑ እንግዲህ የተሰወረ ነገር አይደለም፤ የጀርመኑ የፖለቲካ ሣይንስ ባለሙያ ሽቴፋን ቢርሊንግ እንደሚያስረዱት።

«እርግጥ ነው ግንኙነቱ ታውኳል። አሜሪካኖች አንገታቸውን እጅግ ረዘም አድርገው ከመስኮት ባሻገር በማውጣት የተጋነነ የስለላ ድርጊት ማካሄዳቸው ግልጽ ነው። በተለይም በዋሺንግተን የሚገኘውን የአውሮፓ ሕብረት ውክልና በመሰለሉ ረገድ! ይህ ደግሞ አውሮፓውያን በትዕግስት የማይመለከቱት ነገር ነው። እርግጥ በጉዳዩ ሁለቱም ወገኖች ሃቀኛ መሆናቸውን መናገሩም ይከብዳል»

ለማንኛውም የአውሮፓ ሕብረት የውስጥ ጉዳይ ኮሜሣር ሴሢሊያ ማልምስትሮ በስለላው ሳቢያ የጋራ መተማመን መቀነሱን በማመልከት አሜሪካ ይህንኑ መልሶ ለማስፈን እንድትጥር ነው ያስገነዘቡት። ቢርሊንግ እንደሚሉት ለነገሩ የአሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት ችግር አሁን ድንገት የተከሰተ ነገር አይደለም።

«በአሜሪካና በጀርመን መካከል ያለው ችግር ረዘም ያለ ጊዜ አልፎታል። ሁለቱ ወገኖች የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ካከተመ ወዲህ የድሮውን መሰል የመተማመን ግንኙነት አልነበራቸውም። በአሜሪካ ዓይን አውሮፓውያኑ፤ በተለይም ጀርመናውያን ያን ያህል አመኔታ የሚጣልባቸው አልነበሩም። የአፍጋሃኒስታንን ተልዕኮ ወይም የሊቢያን ሁኔታ እናስታውስ። ጀርመናውያን በነዚህ ሃገራት ረገድ የነበራቸው ሚና በአሜሪካ አመለካከት ጥርጣሬ የተመላው ነበር። በአንጻሩም አሜሪካ በናቶ አማካይነት የዓለምአቀፉ የፖለቲካ ስርዓት ዘብ ለመሆን የምታደርገውን ሁሉ ጀርመን በጥርጣሬ ስትመለከት ነው የቆየችው»

ከኤኮኖሚው አንጻር ዩ ኤስ አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት በትራንስ አትላንቲኩ የንግድና የመዋዕለ-ነዋይ ሽርክና ውል በሁለቱ ታላላቅ ኤኮኖሚዎች መካከል የንግድ መሰናክሎችን ለማስወገድና ከፊናንሱ ቀውስም በጋራ ለመላቀቅ ያልማሉ። የአሜሪካው የንግድ ተጠሪ ማይክል ፍሮማን ትራንስ አትላንቲኩ የንግድ ሽርክና ለሁለቱ ወገን ኤኮኖሚና ግንኙነት፤ እንዲሁም ከዚያም ባሻገር ለዓለምአቀፉ የንግድ ስርዓት ታላቅ ጠቀሜታ እንዳለው ነው ባለፈው ሰኞ ምሽት በድርድሩ መክፈቻ ላይ የተናገሩት።

ትራንስ አትላንቲኩ የንግድ ድርድር የስለላው ቅራኔ ሳይታከልበት እንኳ መሰናክል የበዛው እንደሚሆን ነው የሚታመነው። ከፊናንሱ ዘርፍ እስከ እርሻ ምርቶች ንግድ ሁለቱ ወገኖች የሚለያዩባቸው ጉዳዮች ብዙዎች ናቸው። የሆነው ሆኖ በጉዳዩ ከስምምነት ቢደረስ የነጻው ንግድ ክልል 820 ሚሊዮን ሕዝብን በመጠቅለል በዓለም ላይ ታላቁ ይሆናል። ለግንዛቤ ያህል ባለፈው ዓመት በአሜሪካና በአውሮፓ ሕብረት መካከል የተደረገው የምርትና የአገልግሎት ልውውጥ በአንድ ትሪሊየን ዶላር የሚገመት ነው። ትራንስ አትላንቲኩ መዋዕለ ነዋይም በ 2011 ዓ-ም 3,7 ትሪሊየን ዶላር ደርሶ ነበር።

በለንደን የኤኮኖሚ ፖሊሲ ምርምር ማዕከል የቀረበ ጥናት እንደሚያመለክተው ትራንስ አትላንቲኩ የንግድና የመዋዕለ ነዋይ ሽርክና ቢሰፍን ለአውሮፓ ሕብረት ኤኮኖሚ 119 ቢሊዮን ኤውሮና ለአሜሪካም የ 95 ቢሊዮን ኤውሮ ተጨማሪ ጥቅም የሚያስገኝ ነው የሚሆነው። ውሉን ከተቻለ እስከ 2014 ዓ-ም ድረስ ለማስፈን ይታሰባል።

በዩ ኤስ አሜሪካና በአውሮፓ ሕብረት መካከል የነጻ ንግድ ክልል ለማስፈን የተያዘው ጥረት መንስዔና ግቡ ምን ሊሆን ይችላል? በዓለም ኤኮኖሚ ይዞታና በዓለም ንግድ ድርጅት ላይስ የሚኖረው ተጽዕኖ ምንድነው? እነዚህና መሰል ጥያቄዎች በኤኮኖሚው ዘርፍ ባለሙያዎች መካከል ስፊ ውይይት መቀስቀሳቸው አልቀረም። ከትራንስ አትላንቲኩ ጎራ ባሻገር ራቅ አድርጎ ለታዘበ በእርግጥም የሁለቱ የበለጸጉ ወገኖች ትስስር በዓለም ኤኮኖሚ ላይ ይህ ነው የማይባል ታላቅ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ሰፊ ዕምነት አለ።

በዓለም ንግድ ድርጅት ላይ የሚኖረው ግፊትም ቀላል አይሆንም። ሁለቱ ታላላቅ የንግድ ሃይላት በመካከላቸው የአካባቢውን ውል ካሰፈኑ በዚሁ የዓለም ንግድ ድርጅት ዓለምአቀፍ ደምቦች ይበልጥ ተጽዕኖ እንደሚገጥማቸው የሚጠበቅ ነገር ነው። የዶሃው የልማት ድርድር ዙርም በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸጉትና በተፋጠነ ዕድገት ላይ በሚገኙት ሃገራት ቅራኔ የተነሣ ተሰናክሎ አንደቀጠለ መሆኑ የሚታወቅ ጉዳይ ነው።

እንግዲህ የትራንስ አትላንቲኩ ሽርክና ጥረትም ይሄው መሰናክል የፈጠረው ነገር ሣይሆን አልቀረም። ዩ ኤስ አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት የሚሞክሩት በዓለምአቀፍ ደረጃ ያጡትን ጥቅም በአካባቢ ሽርክና አማካይነት መልሶ ለማግኘት ነው። ከዚህ አንጻር የዓለም ኤኮኖሚን ስርዓት ወይም የዓለም ንግድ ድርጅትን ደምቦች በአዲስ መልክ ለማርቀቅ መሞከራቸው የሚጠበቅ ይሆናል። በሌላ አነጋገር ትራንስ አትላንቲኩ ድርድር በንግግሩ ጠረጴዛ ዙሪያ አብረው ባልተሰየሙት ሃገራት ላይ ሁሉ ማለቂያው የማይታወቅ ተጽዕኖ ይኖረዋል ማለት ነው።

የሁለቱ ወገን የአካባቢ ውል የስብስቡ ዓባል ባልሆኑት ሃገራት ላይ አድልዎን ሊያሰፍንና ወደ አውሮፓም ሀነ ወደ አሜሪካ የውጭ ንግድ ገበዮች እንዳይገቡ ሊያግድ የሚችል ነው። ወቅታዊ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ለምሳሌ ሜክሢኮን፣ ካናዳን፣ ጃፓንን፣ እንዲሁም ሰሜንና ምዕራብ አፍሪቃን የመሳሰሉት የቅርብ ተጎጂዎች ናቸው። እርግጥ የተለያዩ የአካባቢ ስምምነቶችን አንድ ለማድረግ ቢቻል ይህ ተጽዕኖ ለዘብ ሊል የሚችልም ነው።

ዩ ኤስ አሜሪካ በወቅቱ በፓሢፊክ አኳያ ትራንስ አትላንቲኩን የመሰለ ግዙፍ የአካባቢ ነጻ ንግድ ክልል ለማስፈን በመደራደር ላይ ትገኛለች። የነዚሁ የትራንስ አትላንቲኩና የትራንስ ፓሢፊኩ ክልሎች መተሳሰር ቢፈጠር እንግዲህ የጋራ ደምቦች ያሉት ግዙፍ የነጻ ንግድ አካባቢን ሊያስከትል ይችላል። ግን በአካባቢ ስምምነቶች አማካይነት እንበል በጓሮ በር ለዓለም ኤኮኖሚ ዓለምአቀፍ ደምቦችን የመፍጠር ሙከራ ፍሬያማ ነወይ? ዕርምጃው ብዙ ቴክኒካዊ እክሎች ሲኖሩት በተለይም ችግሩ ጎልቶ የሚታየው በተፋጠነ ዕድገት የሚራመዱትና አዳጊ እየተባሉ የሚጠሩት ሃገራት የስብስቡ ዓካል መሆን በሚሹበት ጊዜ ነው። ዕጣቸው ደምብ አቅራቢነት ሣይሆን ደምብ ተቀባይነት ብቻ ይሆናል።

አዲሱ የዓለም ኤኮኖሚ ደምብ እነዚህ ሃገራት ገና ስብስቡን ሳይቀላቀሉ የሰፈነ ጉዳይ ሆኖ ይገኛል። ለዚህ በወቅቱ በቻይና የትራንስ ፓሢፊኩን ድርድር አስመልክቶ በመካሄድ ላይ ያለው ስር የሰደደ ክርክር ጥሩ ምሳሌ ነው። በዚህ ሁኔታ የታሪክን ጉዞ አቅጣጫ ለውጦ ወደ ኋላ ላለመመለስ መጠንቀቁ ተገቢ ይሆናል። ቢዘገይ የያዝነው ምዕተ-ዓመት ከገባ ወዲህ በዓለም ላይ ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ፤ ከሰሜን ወደ ደቡብ መሠረታዊ የሆነ የኤኮኖሚ ሃይል ሽግሽግ መደረጉ ሊረሣ አይገባውም።

ከዚህ አንጻር ብራዚልን፤ ሕንድን ወይም ቻይናን የመሳሰሉት በመጠናከር ላይ የሚገኙ ሃገራት በደምብ ተቀባይነት ተወስነው ለመኖር መፍቀዳቸው ሲበዛ ያጠያይቃል። ምናልባትም ሊከተል የሚችለው በአካባቢው የንግድ ክልሎች መካከል የመጋለል ሁኔታ ነው። ይህ እንዳይሆን የበለጸጉት መንግሥታት በሚያደርጉት የለውጥ ጥረት ወደፊት በተለይም በተፋጠነ ዕድገት ላይ ከሚገኙትና ከአዳጊዎቹ ሃገራት ጋር ባለው የኤኮኖሚ ግንኙነት ዋነኞቹ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን መገንዘባቸው ተገቢ ነው። ስለዚህም የዓለም ንግድ ድርጅት አማራጭ የሌለው ሆኖ መቀጠል ይኖርበታል።

በትራንስ አትላንቲኩ የንግድ ድርድር የተጀመረው እንቅስቃሴ የዶሃውን የድርድር ዙርም ከግቡ ለማድረስ ጥቅም ላይ ቢውል የሚጠቅም ነገር ነው። ይህ በቅርብ ጊዜ ካልተሣካ የዶሃን ጉዳይ መክሸፍ በይፋ ከማወጅ የተሻለ ሌላ ምርጫ አይኖርም። እርግጥ የዓለም ንግድ ድርጅት የጥገና ለውጥ ያስፈልገዋል። እስካሁን የድርጅቱ ውሣኔ በመላው ዓባል ሃገራት ድምጽ ብቻ የሚያልፍ መሆኑ ፍቱን እንዳይሆን አድርጎት ነው የቆየው። ይህ የድርድር ዘይቤ አብቅቶ ድርጅቱ በተለያየ ፍጥነት ማምራት የሚችልበት ሁኔታ መፈጠሩ የሚበጅ ሣይሆን አይቀርም።

በወቅቱ በአሜሪካና በአውሮፓ ሕብረት መካከል የተጀመረው ድርድር በዓለም ንግድ ድርጅት ውስጥ ፍቱን ደምቦችን ለማስፈን፤ ምናልባትም ለዶሃው ዙር ጭምር ገንቢ ሁኔታን ሊፈጥር ይችል ይሆናል።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic