ትራምፕ እና አፍሪቃ | አፍሪቃ | DW | 26.06.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ትራምፕ እና አፍሪቃ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ አንስቶ ስለ ልማት እርዳታ  ቅነሳ እና በአፍሪቃ ለቤተሰብ ፕሮጀክት የሚውለው የአሜሪካውያን ገንዘብ ገደብ እንዲበጅለት ከመጠየቅ በስተቀር አፍሪቃን ያነሱበት ጊዜ የለም። ለመሆኑ አዲሱ የአሜሪካን አስተዳደር ስለ አፍሪቃ አቋሙ ምንድነው? 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:54

ትራምፕ እና አፍሪቃ

የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በአስተዳደር ዘመናቸው ለዩናይትድ ስቴትስ የውጭ መርህ አፍሪቃ አስፈላጊ መሆንዋን ያጎሉ ነበር። ኦባማ በሥልጣን ዘመናቸው 4 ጊዜ አፍሪቃን ጎብኝተዋል። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግን ሥልጣን እንደያዙ ከአፍሪቃ መሪዎች ለናይጀሪያ፣ ለደቡብ አፍሪቃ እና ለኬንያ መሪዎች ጥቂት የስልክ ጥሪዎች አድርገው ነበር። ከዚያን ወዲህ ዋይት ሀውስ በሀገር ውስጥ አወዛጋቢ ጉዳዮች በሩስያ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በሰሜን ኮሪያ ጉዳዮች በመጠመዱ አፍሪቃ በመሠረቱ ከዋሽንግተን አጀንዳ ውስጥ የወጣች ነው የሚመስለው። አንዱ ችግር ትራምፕ በአሜሪካን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አፍሪቃን ለሚመለከቱ የሥራ ቦታዎች ሰው አለመመደባቸው ነው ይላሉ መቀመጫውን ዋሽንግተን ያደረገው አትላንቲክ ካውንስል የተባለው የጥናት ተቋም ባልደረባ ብሮንዌይን ብሩተን። 
«የአፍሪቃ ፖሊሲ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ አይዘጋጅም። በረዳት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ ነው የሚዘጋጀው። እናም ረዳት ሚኒስትር በቦታው ካልተመደበ በመሠረቱ የአፍሪቃ ፖሊሲ ሊኖር አይችልም። »

ነገሮችን ለማባባስ የትራምፕ የውጭ መርህ በአጠቃላይ የጋራ እሴቶችን ወይም የረዥም ጊዜ ልማትን መሠረት ላደረገ ስልታዊ ህብረት ብዙ ትኩረት አይሰጥም። ከዚያ ይልቅ የሚመርጡት በሁለትዮሽ ስምምነት ለአገራቸው የአጭር ጊዜ ጥቅም ቅድሚያ መስጠትን ነው። ብሩተን ይህ ለአፍሪቃ አምባገነኖች መልካም ዜና ነው ይላሉ ።
«በኦባማ ዘመነ ስልጣን የተገለሉ መንግሥታት ነበሩ። ዚምባብዌ ሱዳን ኤርትራ እና እነዚህን የመሳሰሉ መንግሥታት ስለ ሰብዓዊ መብቶች ብዙም የማይጨነቅ ከሌሎች መንግሥታት ጋር ግንኙነቱ በጥቅም ላይ የተመሠረተ ፕሬዝዳንት በመኖሩ የሚጠብቁት ብዙ ነው ፤ ደስተኛም ናቸው። »
ከዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አጥኚዎች አብዛኛዎቹ ከአፍሪቃ መነጠሉ ቻይና ህንድ እና ብራዚል ሊሞሉት የቋመጡለትን የጥቅም ክፍተት ያስከትላል የሚል ስጋት አላቸው።

ባለፈው ሳምንት ዋሽንግተን ውስጥ የተካሄደው የዩናይትድ ስቴትስ እና የአፍሪቃ የንግድ ጉባኤ ተሳታፊዎች ይህን ስሜት ሲያንጸባርቁ ነበር። ከመካከላቸው ናይጀሪያዊው ጠበቃ አዮዴሌ ኩሳሞቱ አንዱ ናቸው። 
« ከአፍሪቃ የጥሬ ሀብት ሽምያ አለ። ከእስያ ቻይና ገስግሳለች። ለአፍሪቃ እና በአፍሪቃ እጅግ ብዙ እየሰራች ነው።»
የሞሮኮ የንግድ ማህበረሰብ ተወካይ አብዱ ሱሌይ ድዮፕ አሜሪካኖች አመለካከታቸውን መቀየር አለባቸው በመባሉ ይስማማሉ።
«ዩናይትድ ስቴትስ ስለ አፍሪቃ የምትከተለውን እናደገና እንድታጤነው እንፈልጋለንል። እርዳታም ሆነ አንዳንድ ድጎማዎች አንፈልግም። ንግድን በማዳበር እና በጋራ ስምምነቶች ለእውቀት ሽግግር  እውነተኛ ትብብር ነው የምንፈልገው። የዩናይትድ ስቴትስን ያህል ጥንካሬ ባይኖረንም ለወደፊት ትክክለኛ አጋር መሆን እንችላለን።»
በእርግጥ ንግድ አዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት በኦባማ ዘመነ ሥልጣን የነበረውን መርህ የሚቀጥልበት መስክ ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ሃሳቦችንም ተግባራዊ ማድረግ የሚጀምረበት ነው የሚሆነው እንደ ዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባልደረባ ብራያን ኖይቤርት 

«አፍሪቃ በመሠረተ ልማት ላይ መዋዕለ ንዋይ ስታፈስ በአብዛኛዎቹ የአፍሪቃ ገበያዎች ብዙ የንግድ እድሎች አሉ ።በቴክኖሎጂ እና በምርቶች እና በአገልግሎት ዘርፍም ለአሜሪካን ኩባንያዎች እድሎች አሉ።  ብዙ የአፍሪቃ ሀገራትም ምርቶቻቸውን ለአሜሪካን ገበያ ያቀርባሉ።  »
ከዚህ ሌላ የአሜሪካን ጦርም አለ። በኦባማ ጊዜ እንኳን አሜሪካን በአፍሪቃ የስለላ መረቧን እና  እና አሸባሪ በምትላቸው ኃይላት ላይጥቃት ለማድረስ አፍሪቃ ውስጥ ያሏትን የጦር ሰፈሮች ቁጥር ጨምራለች። ትራምፕ ደግሞ ጦሩ ሚመስለውን እንዲወስን በመፍቀድ  ከዚህም በላይ ሊያደርጉ እንደሚችሉ አሜሪካን ኢንተርፕራይዝ ኢኒስትቲትዩት የተባለው የወግ አጥባቂው የጥናት ተቋም ባልደረባ ኬቲ ሲመርማን ያስረዳሉ ።
«ከትራምፕ አስተዳደር አንዳንድ ለውጦች ሲደረጉ አይተናል። በዚህ ረገድ ከሁሉም ዋነኛው በሶማሊያ የአሜሪካን ኃይሎች በቦታው ላይ የሚገኙ አጋሮችን ለመጠበቅ አሁን በአሸባብ ላይ አፀፋ ጥቃቶችን ማካሄድ ይችላሉ።»

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች