ትራምፕ በእስራኤል ጉብኝታቸዉን ጀመሩ | ዓለም | DW | 22.05.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ትራምፕ በእስራኤል ጉብኝታቸዉን ጀመሩ

የእስራኤል ጉብኝታቸዉን ዛሬ የጀመሩት የዩ ኤስ አሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመካከለኛዉ ምስራቅ ሰላም ይወርድ አንድ የጋራ ጥረት ማድረግ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቀረቡ። ትራምፕ በእስራኤል ቴል አቪብ ላይ ባደረጉት ንግግር በቀጣናዉ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን አንድ ልዮ እድል መኖሩ እንደታያቸዉ ገልፀዋል።

ትራምፕ እስራኤል እንደገቡ በቅድምያ ከሃገሪቱ መሪዎች ጋር ከተገናኙ በኋላ በነገው እለት በምዕራባዊ ዮርዳኖስ ዳርቻ በምትገኘው ቤተልሔም  ከፍልስጤማውያን ፕሬዚዳንት ማህሙድ አባስ ጋር ይገናኛሉ። የዩኤስ አሜሪካ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን እንዳስታወቁት፣ የሦስቱ ሃገራት ርዕሳነ ብሔር እና መራህያነ መንግሥት ግንኙነት ቆየት ብሎ ወደፊት ይደረጋል።  የእስራኤል የፀጥታ ምክር ቤት ትራምፕ እስራኤል ከመግባታቸዉ ጥቂት ቀደም ሲል በፍልስጤማውያን ላይ አርፈው የነበሩ አንዳንድ፣ ለምሳሌ በምዕራባዊው ዳርቻ በእስራኤል ቁጥጥር ስር በሚገኙ አካባቢዎች በሚከናወን የግንባታው ዘርፍ ላይ የተጣሉ ገደቦችን አላልቶዋል።  

የዩኤስ አሜሪካዉ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሳዉዲ አረብያ ጉብኝታቸዉ ከሃገሪቱ ጋር  ወደ 110  ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሳርያ ግዥ ዉልን ከተፈራረሙ በኋላ ኢራን በአሜሪካ ርምጃ ላይ ወቀሳ አሰማች። ቴህራን የሚገኘዉ የኢራን መንግሥት  ዩኤስ አሜሪካ «የኢራንን ጠላቶች የማነሳሳት  » እና « በመካከለኛዉ ምስራቅ ለሚገኙ አሸባሪዎች የጦር መሳርያ የመሸጥ ርምጃ» ታካሂዳለች ሲል ድርጊቱን  አዉግዞአል። የኢራን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር «የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ በተደጋጋሚ ማሰማት በያዙት መሰረተ

ቢስ ወቀሳ አረባውያት ሃገራት የጦር መሳርያ እንዲገዙ ቀስቅሰዋል» ፣ በቀጠናዉ ላይ ለበርካታ አስር ዓመታት የዘለቀዉን የሃይማኖት ቅራኔንም አጋግለዋል ሲል ባወጣዉ መግለጫ ጠቅሶአል።   ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሳዉዲ አረብያ በተካሄደዉ የሙስሊም አሜሪካ ጉባዔ ላይ ተገኝተዉ በጉባዔው የተካፈሉት መሪዎች በሙስሊም ጽንፈኞች አንፃር እንዲታገሉ ጥሪ አቅርበዋል። ትራምፕ ካካባቢው ሃገራት ጋር የጠበቀ አጋርነት ለመፍጠር ያላቸውን ፍላጎትም በንግግራቸው  አጉልተዋል። 
« እዚህ የምንገኘዉ ሌሎች ሰዎች እንዴት እንደሚኖሩ ፤ ምን መስራት እንዳለባቸዉ ፤ እንዴት መሆን እንዳለባቸዉ ወይም እንዴት ማምለክ እንዳለባቸዉ ለመንገር አይደለም።  ይልቁንም እዚህ የመጣነዉ በመተማመን እና በጋራ እሴቶች ላይ የተመሰረተ አጋርነትን ለመፍጠር ነዉ። » 

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ