ቴዲ እና የሙዚቃው ገበያ   | ኤኮኖሚ | DW | 10.05.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

ቴዲ እና የሙዚቃው ገበያ  

የቴዎድሮስ ካሳሁን 'ኢትዮጵያ' የሙዚቃ አልበም 500,000 ኮፒዎች ባለፈው ሳምንት ለገበያ ቀርበዋል። ድምፃዊው ለአምስተኛ የስቱዲዮ አልበሙ 5 ሚሊዮን ብር እንደተከፈለው ተሰምቷል። የኢትዮጵያ የሙዚቃ ገበያ ለሌሎች ባለሙያዎች ይኸን ያክል ገንዘብ ይከፍል ይሆን?

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:48

ለባለሙያዎቹ ያልበጀው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ገበያ

አዲስ አበባ ለቀናት የቴዎድሮስ ካሳሁንን አዲስ የሙዚቃ አልበም ከ50-70 ብር ስትሸምት ከርማለች። የቴዎድሮስ አምስተኛ የሙዚቃ ሥራ የሆነው እና 'ኢትዮጵያ' የሚል ሥያሜ የተሰጠው ሙዚቃ የተተመነው ግን 30 ብር ብቻ ነበር። አልበሙ ለገበያ በቀረበበት ዝናባማ ማለዳ የታክሲ አሽከርካሪዎች፤ መጻሕፍት ነጋዴዎች እና ሊስትሮዎች ጭምር የሙዚቃ ነጋዴ ሆነው ተስተውለዋል። በየመንገዱ የተቀለሱ ጊዜያዊ ድንኳኖች የድምፃዊውን ሥራ ለአድናቂዎቹ ቸብችበዋል። የኢትዮጵያን አንድነት አጥብቆ የሚያቀነቅነው ቴዎድሮስ ካሳሁን አዲሱ ሥራው ለገበያ ከመቅረቡ በፊት እንደ ወትሮው የአተካሮ ማዕከል መሆኑ አልቀረም። ቴዎድሮስን የሰላም እና የወንድማማችነት ሰባኪ አድርገው የሚቀበሉ አድናቂዎቹ የሥራዎቹን ተቺዎች በማህበራዊ ድረ-ገፆች ሲያብጠለጥሉ ከርመዋል። እጅጉን ቀዝቃዛ የሆነውን የኢትዮጵያ የሙዚቃ ገበያ በማነቃቃቱ ረገድ እንደ ቴዎድሮስ ካሳሁን የተካነበት ያለ አይመስልም። በግጥሞቹ የሚያነሳቸው ርዕሰ-ጉዳዮች፤ ሥራዎቹ ለገበያ የሚቀርቡባቸው ወቅቶች ፖለቲካዊ ትኩሳት እና የሚቀሰቀሱት እሰጥ አገባዎች የአንድ ሰሞን መነጋገሪያ ሆነው ያልፋሉ። 
አስራ አራት ሙዚቃዎች ላካተተው አዲሱ የሙዚቃ አልበም ቴዎድሮስ 5 ሚሊዮን ብር እንደተከፈለው ተሰምቷል። 500,000 ኮፒዎች በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ለሙዚቃ  አፍቃሪዎች ቀርበዋል። ለሙዚቃ ሥራው የተከፈለው የገንዘብ መጠን ለኢትዮጵያ የሙዚቃ ገበያ አዲስ ነው። የኢትዮጵያ የሙዚቃ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ዳዊት ይፍሩ አሁን ለቴዎድሮስ ካሳሁን የሙዚቃ ሥራ የተከፈለው የገንዘብ መጠን በድንገት «ያሻቀበ» ነው የሚል እምነት አላቸው። 

የቴዎድሮስ ካሳሁንን አዲስ ሙዚቃ ገዝተው ያከፋፈሉት ወገኖች በሌሎች የንግድ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ እና ትርፍን ዓላማቸው ያደረጉ መሆናቸው ተሰምቷል። የሙዚቃ አልበሞች ገዝተው በማከፋፈል ላይ የተሰማሩት ድምፃዊው በጠየቀው የገንዘብ መጠን ባለመስማማታቸው ገሸሽ ማለትን መርጠዋል። የኢትዮጵያን ሙዚቃ በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች የተከፈለው ገንዘብ መጠን በግብይቱ የእድገት ሂደት የተፈጠረ አይደለም ሲሉ ይተቻሉ። ገበያው ለሌሎች ባለሙያዎች ወይም የሙዚቃ አልበሞች ተመሳሳይ አሊያም ተቀራራቢ ክፍያ ሊፈፅም ይችላል? በክፍያው ዘላቂነት ላይ መናገር «አልችልም» የሚሉት የአምባሰል ሙዚቃ ቤት ባለቤት አቶ ፍቃዱ ዋሪ ግብይቱ የሚወሰነው በአሳታሚው ሥሌት ነው ባይ ናቸው።
የሙዚቃ ሥራቸውን ይዘው ወደ ገበያው ብቅ የሚሉ ባለሙያዎች ከአልበም ሽያጭ ጎን ለጎን በመድረክ ሥራዎች እና የማስታወቂያ ስምምነቶች ወጪያቸውን ለማካካስ ሲታትሩ ይስተዋላል። አቶ ዳዊት ይፍሩ የሙዚቃ ገበያው ለሥመ-ጥሮቹም ይሁን ለወጣት ድምፃውያን የበለጠ ፈታኝ እየሆነ ሄዷል የሚል ሥጋት አላቸው።

እንደ አቶ ዳዊት አባባል አሁን ባለው ገበያ የሙዚቃ አልበም ብቻ በመሸጥ ማትረፍ የሚታሰብ አይደለም። ለዓመታት የሙዚቃ ሲዲዎች በመነገድ ይተዳደር የነበረው ብሩክ አብዲ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ገበያ ከባለሙያዎቹ ይልቅ ለነጋዴዎቹ የሚያደላ ሆኗል እያሉ ከሚወቅሱት መካከል አንዱ ነው። ሙዚቃ ማሳተም እና ማከፋፈል በጥቂት ኃይለኞች እጅ ወድቋል የሚለው ብሩክ የግብይት ሥርዓቱ ፈፅሞ ሊለወጥ ይገባል ብሎ ይከራከራል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ድምፃውያን የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን ለገበያ ለማቅረብ የቢራ ፋብሪካዎችን ደጅ መጥናት ጀምረዋል። የሙዚቃ ሥራዎችን ስፖንሰር ከሚያደርግ የቢራ ፋብሪካ ጋር የሚሰሩ አንድ ባለሙያ ወደ አስር የሚጠጉ ድምፃውያን ይኸንንው ሥምምነት ፍለጋ ደጅ ሲጠኑ መመልከታቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ባለሙያዎቹ «የማስታወቂያ ሥምምነቱ ሙዚቃውን ጥገኛ ያደርገዋል» የሚል ሥጋት አላቸው። አብዛኞቹ የሙዚቃ ባለሙያዎች ሥራዎቻቸውን ለገበያ የሚያቀርቡት በማስታወቂያ ሥምምነት እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ፍቃዱ ዋሪ አሰራሩ ቢያንስ የሙዚቃ ሥራዎቹ ለገበያ እንዲቀርቡ አስችለዋል ሲሉ ይናገራሉ።
ዘመን አመጣሹ ቴክኖሎጂ  የኢትዮጵያን የሙዚቃ ግብይት ድንገት ደርሶ መንገድ አስቶታል። ለዘመናት የሙዚቃ ባለሙያዎች ሥራዎቻቸውን ለገበያ የሚያቀርቡበት ማግኔቲክ ካሴት ሙሉ ከሙሉ ከገበያ ወጥቷል። የዲቪዲ እና ሲዲ ማጫዎቻዎችም ለአያያዝ እና አጠቃቀም ቀላል በሆኑት የፍላሽ ዲስኮች ወደ ጎን እየተገፉ ነው። አቶ ዳዊት አዲሱ ቴክኖሎጂ የድሮውን የፊሊፕስ፤ ሶኒ እና ፓናሶኒክ ካሴቶች ብቻ ሳይሆን ለረዥም

ዓመታት የሙዚቃ ሥራዎችን የሚያሳትሙ እና የሚያከፋፍሉ ነጋዴዎችን ጭምር ከገበያው ማስወጣቱን ይናገራሉ። 

የኢትዮጵያ የሙዚቃ ገበያ ወትሮም ለባለሙያዎቹ ተገቢውን ክፍያ አይከፍልም እየተባለ ይወቀሳል። አገሪቱ ጆሮ ገብ ዜማ የፃፉ ተወዳጅ የሙዚቃ ግጥም የደረሱ ባለሙያዎች ሲቸገሩም ታዝባለች። የቀድሞው የሙዚቃ ሲዲ ነጋዴ ብሩክ ከ20 ዓመት በፊት ለገበያ የቀረቡ የሙዚቃ ሥራዎች ዛሬም በገበያው ለሽያጭ ቀርበው ቢቸበቸቡም ከነጋዴው አልፎ ባለሙያዎች የሚገባቸውን አለማግኘታቸውን ታዝቧል። አቶ ዳዊት ይፍሩም ከቀድሞው «የተለወጠ ነገር የለም» ባይ ናቸው። 
የቴዎድሮስ ካሳሁን 'ኢትዮጵያ' የሙዚቃ አልበም ለገበያ በበቃ በጥቂት ሰዓታት ልዩነት ያለ ድምፃዊው ፈቃድ በዩቱዩብ ተጭኖ ለዓለም ተሰራጭቷል። ድምፃዊው አቤቱታውን ለጉግል ካቀረበ በኋላ የተወሰኑት ሙዚቃዎች ከዩቲዩብ ቢጠፉም እዚህም እዚያም አሁንም መገኘታቸው ግን አልቀረም። ኢንተርኔት ይዞት የመጣው አዲስ አገልግሎት እና የቅጂ መብት አለመከበር ዛሬም ለኢትዮጵያ የሙዚቃ ገበያ ፈታኝ ችግሮች ሆነዋል። አገሪቱ በ1997 ዓ.ም. የቅጂ እና ተዛማጅ መብቶች አዋጅ ብታወጣም በገበያው ላይ ይኸነው የሚባል ለውጥ ሲያመጣ አልታየም። በኢትዮጵያ የሙዚቃ ባለሙያዎች ማኅበር የኮፒ ራይት ሶሳይቲ ለማቋቋም በጥረት ላይ መሆኑን የተናገሩት አቶ ዳዊት ይፍሩ ገቢራዊ ሲሆን ባለሙያዎች ተገቢውን ጥቅማ ጥቅም ያገኛሉ የሚል ተስፋ ሰንቀዋል።
እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ  

Audios and videos on the topic