ቴሬዛ ሜይ እና ስብእናቸው | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 14.07.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

ቴሬዛ ሜይ እና ስብእናቸው

አንድ የቀድሞ የወግ አጥባቂ ፓርቲ አባል ሜይን ሲገልጿቸው « እንደፈለጉ የማያደርጓት ሴት» ነበር ያሏቸው ። ለዚህ ሃላፊነት የበቁት ሜይ፣ አዲሲቷ ማርግሬት ታችተር ፣ ወይም ሁለተኛዋ «ብረቷ እመቤት » መሆን አለመሆናቸው እያጠያየቀ ነው ። የዶቼቬለው የንስ ፒተር ማርክዋርድት፣ ሜይ ሥራ ላይ ሲመጣ ቀላል ሰው አይደሉም ይላል ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:10

ቴሬዛ ሜይ እና ስብእናቸው


አዲሷ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ መንግሥት የመመሥረት ሃላፊነታቸውን ትናንት ማምሻውን ከንግሥት ኤልሳቤጥ በይፋ ከተረከቡ በኋላ ወዲያውኑ የካቢኔያቸውን አባላት በመሰየም ሥራቸውን ጀምረዋል ። ብሪታንያውያን ከአውሮፓ ህብረት ለመውጣት በህዝበ ውሳኔ ካሳወቁ በኋላ ከሥልጣን የተሰናበቱትን ዴቪድ ካሜሩንን የተኩት ሜይ ማናቸው ? አቋማቸውስ ምንድነው ? የዶቼቬለውን የየንስ ፒተር ማርክዋርድትን ዘገባ ኂሩት መለሰ አጠናቅራዋለች ።
ሙሉ ስማቸው ቴሬሳ ሜሪ ሜይ ነው ። ለጠቅላይ ሚኒስትርነት የበቁበት መንገድ ያልተጠበቀ እና ፈጣንም ነበር ። ከዛሬ ሦስት ሳምንት በፊት ብሪታንያውን ከአውሮፓ ህብረት ለመውጣት ባሳለፉት ውሳኔ ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን ከሥልጣን እንደሚወርዱ ካሳወቁ በኋላ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት በእጩነት የቀረቡት ሜይ ከሦስት ቀናት በፊት ነበር የወግ አጥባቂ ፓርቲ መሪነትን የተረከቡት ። ከሁለት ቀናት በኋላ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ተሾሙ ። እስከትናንት ድረስ ላለፉት ስድስት ዓመታት የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ነበሩ ። ሜይ በተሳናባቹ በካሜሩን ካቢኔ ብቻ ሳይሆን ከዚያ በፊት

በነበሩት መሪዎች የሥልጣን ዘመንም በልዩ ልዩ ሃላፊነቶች ሰርተዋል ።ቴሬሳ ሜይ ብሪታንያን ከጎርጎሮሳዊው 1979 እስከ 1990 ከመሩት « ብረቷ እመቤት» ከሚባሉት ከማርጋሬት ታቸር ቀጥሎ በብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሾሙ ሁለተኛዋ ሴት ናቸው ።ታችተር ሥልጣን ላይ በወጡ በ37 ዓመቱ ለዚህ ሃላፊነት የበቁት ሜይ፣ አዲሲቷ ማርግሬት ታችተር ፣ ወይም ሁለተኛዋ «ብረቷ እመቤት » መሆን አለመሆናቸው እያጠያየቀ ነው ። የዶቼቬለው የንስ ፒተር ማርክዋርድት እንደሚለው ሜይ ሥራ ላይ ሲመጣ ቀላል ሰው አይደሉም። የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሉ የፖሊስ በጀት ከተቀነሰ እና የሥራ ቦታዎች ከተሰረዙ በኋላ በፖሊሶች ማህበር ጉባኤ ላይ ሃሳባቸውን ለማስቀየር የተደረገው ሙከራ አለመሳካቱ የዚህ አንዱ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ።ቴሬሳ በጉባኤው ላይ እቅጩን ነበር የተናገሩት
«የኔ ሥራ፣ያለውን ነገር እንዳለ መናገር እንጂ እኛ ሊሆን እንደምንፈልገው አድርጌ መናገር አይደለም ።»

ያኔ የማህበሩ አባላት አጉረምርመውባቸው ነበር ። ሆኖም ቴሬሳ ሜይ በራሳቸው መንገድ ነበር የተጓዙት ።አንድ የቀድሞ የወግ አጥባቂ ፓርቲ አባል ሜይን ሲገልጿቸው « እንደፈለጉ የማያደርጓት ሴት» ነበር ያሏቸው ። ከአሁኑ መንግሥት በፊት ሥልጣን ላይ በነበረው በጥምሩ መንግሥት የኤኮኖሚ ሚኒስትር የነበሩት ሊብራል ዲሞክራቱ ቪንስ ኬብል ደግሞ የሜይ ፖሊሲዎች ወዳጅ አልነበሩም ። ሆኖም ለቀድሞዋ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትርን በራስ መተማመናቸው ያከብሯቸዋል።
« ብቃት አላቸው ፣ በውሳኔያቸው የሚጸኑ እና የማይታጠፍ አቋም ያላቸው ሴት ናቸው ። ይህንንም ለምሳሌ ካቢኔው በኢሚግሬሽን ፖሊሲ ባካሄደው ንግግር ላይ አይተናል ። እኔንም በሚመለከተኝ የውጭ ዜጋ ተማሪዎች ቪቫ ጉዳይ ላይ የገንዘብ ሚኒስትሩን ጆርጅ ኦስቦርን እና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ዴቪድ ካሜሩንን ይቃወሙ ነበር ።ያኔ አግባቢ ሃሳብ ላይ ለመድረስ የተደረጉትን ሙከራዎች በተደጋጋሚ ሲያግዱ ነበር ። »
ታዲያ ሜይ በርግጥም ሁለተኛ ብረቷ እመቤት ይሆኑ ይሆን ? የአንገሊካን ቤተክርስቲያን ቄስ ልጅ የሆኑት የ59 ዓመትዋ ሜይ ከታቸር የተለዩም ሊሆኑ ይችላሉ ። የገበያውን ኤኮኖሚ በፍጥነት ሲያሳድጉ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የነበረውን ህዝብ ወደ ጎን ትተውት ነበር ሲሉ ታችተርን የተቹት ሜይ በ2002 ዓም ሌላ ማህበራዊ ፖሊሲ ጥሪ አቅርበው ነበር ።

« በገበያ ላይ ብቻ እምነት የለንም ። በማህበረሰቡ ላይ እንጂ በግለኝነት ላይ ብቻ እምነት የለንም ፤ ይልቁንም በማህበረሰቡ ላይ እንጂ ። መንግሥትን አንጠላም ፤የመንግሥት ብቻ የሆነውን ድርሻ ግን እንመዝናለን ። የታደሉ ጥቂቶች ብቻ ሳይሆኑ ፣ ሁሉም፣ በህይወታቸው ውስጥ ቦታ ያለው ጉዳይ ሁሉ ይመለከታቸዋል ብለን እናምናለን ።»
በርግጠኝነት ማርግሬት ታቸር ይህን ሊሉ አይችሉም ። ይህን አባባላቸውን ሜይ ትናንት የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሹመት እንደተቀበሉ ባሰሙት ንግግርም ደግመውታል ።ታዲያ ቴሬሳ ሜይ ለዘብ ያሉ ወግ አጥባቂ ይባሉ ይሆን? አንዳንዶች ተስፋ እንደሚያደርጉት ከአውሮፓ ህብረት ለመውጣት የብሪታንያ ህዝብ ካሳለፈው ውሳኔ ከብሬግዚት መውጫስ ይፈልጉ ይሆን ? በመሠረቱ ሜይ ከህዝበ ውሳኔው በፊት ብሪታንያ ከህብረቱ ጋር እንድትቆይ ነበር የሚፈልጉት ። ከውሳኔው በኋላ ግን ዳግም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ የቀረበውን ጥያቄ እንደማይቀበሉ በግልጽ አሳውቀዋል ።
« ብሬግዚት ማለት ብሬግዚት ነው ። ይህንንም በተሳካ ሁኔታ እንወጣዋለን ። በአውሮጳ ህብረት ውስጥ የመቆየት ምንም ዓይነት ሙከራ አይደረግም »

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች