ታጣቂ ቡድኖች በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ የደቀኑት ስጋት | አፍሪቃ | DW | 12.07.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ታጣቂ ቡድኖች በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ የደቀኑት ስጋት

በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ የብረቱ ትግል ከተጀመረ ከአንድ ዓመት ተኩል ገደማ በኋላም በብዙው የሀገሪቱ አካባቢ በቀድሞ ሙሥሊሞች የሴሌካ ዓማፅያን እና በአንፃራቸው በሚንቀሳቀሱት የፀረ ባላካ ሚሊሺያዎች መካከል ግጭቱ አሁንም እንደቀጠለ ነው። ሀገሪቱም ከግጭት አዙሪት መውጣት ተስኗታል። መንግሥትም ቀውሱን የማስቆም አቅም ተጓድሎት ይገኛል።

የቀድሞ ሙሥሊሞች የሴሌካ ዓማፅያን ሰሜናዊውን እና ምሥራቃዊውን የሀገሪቱን አካባቢ፣ ተቀናቃኞቻቸው የፀረ ባላካ ሚሊሺያዎች ደግሞ መዲናይቱን ባንጊን እና አካባቢዋን ተቆጣጥረዋል። የተለያዩት ብሔር ብሔረሰቦች ቡድኖች ለፖለቲካ ሥልጣን እና የተወሰነውን የሀገሪቱ የተፈጥሮ ሀብት ለመቆጣጠር የጀመሩት ትግል አሁን በብዙ የሀገሪቱ አካባቢዎች ወደ ሀይማኖታዊ ግጭት ተቀይሮ ተስፋፍቶዋል። በተለይ በገጠሩ አካባቢ አስከፊ ግጭት እየተፈፀመ መሆኑ ነው። ባጠቃላይ ሁኔታው አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን እና በሀገሪቱ የቀጠለውን ግድያ ማስቆም የሚችል በቂ ኃይል አለመኖሩን ዋና ጽሕፈት ቤቱ በደቡብ አፍሪቃ የፕሪቶርያ ከተማ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም ተንታኝ ፖል ሳይመን ሄንዲ አስታውቀዋል።

« የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ጊዚያዊ ሁኔታ ተለዋዋጭ ነው። በወቅቱ በሀገሪቱ በቂ ዓለም አቀፍ ሰላም አስከባሪ ኃይል የለም፣ በዚያ የተሠማሩት «ሶናጋሪ» በሚል መጠሪያ በሚታወቀው የፈረንሳይ ተልዕኮ ውስጥ ፣ እንዲሁም፣ በምሕፃሩ «ሚስካ» የተባለው የአፍሪቃ ህብረት ተልዕኮ ውስጥ የተጠቃለሉት ወታደሮች ፣ ምንም እንኳን ብዙ ግምት ባያገኝላቸውም፣ ግዙፍ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል። »

እንደሚታወቀው፣ በወቅቱ በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ 2,000 የፈረንሳይ፣ 6,500 የአፍሪቃ ህብረት እና ወደ 700 የሚጠጉ የሌሎች የአውሮጳ ሀገራት ወታደሮች ይገኛሉ። ይህም ሆኖ ግን በሀገሪቱ የፀረ ባላካ ሚሊሺያዎች እና የቀድሞ የሴሌካ ዓማፅያን የኃይል ተግባር ሊገታ አልቻለም።

የዚሁ የቀጠለው ግጭት መዘዝ ዋነኛ ቀማሽ የሆነው፣ እንደ ፖል ሳይመን ሄንዲ አስተያየት፣ መከረኛው ሲቭል ሕዝብ ነው። የተመድ የሚያወጣቸው ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት፣ ግማሹ የሀገሪቱ ሕዝብ፣ ማለትም፣ ወደ 2,2 ሚሊዮን የሚጠጋው በሰብዓዊ ርዳታ ላይ ጥገኛ ነው። ከአንድ ሚልዮን የሚበልጠውም በሽሽት ላይ ይገኛል። በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ የተመድ አስቸኳይ ርዳታ አስተባባሪ ወይዘሮ ክሌር ቡርዧ ካለፉት ጥቂት ቀናት ወዲህ በተለይ በሲቭሉ ሕዝብ ላይ እንደገና ተባብሶ የቀጠለው ግጭት እጅግ እንዳስደነገጣቸው ገልጸዋል።

« በሲቭሉ ህዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለው አስከፊ ጥቃት በፍፁም ተቀባይነት የለውም፣ ለዚሁ ጥቃት ተጠያቂ የሆኑትን ሁሉ የሲቭሉ ሕዝብ ከለላ የሚያገኝበትን ሁኔታ እንዲያከብሩ እና ለደህንነታቸውም ዋስትና እንዲሰጡ እጠያቃለሁ። የኃይሉ ተግባርም ማቆም አለበት። »

አዲሱ ጥቃት ቤት የሚኖርበትን አካባቢውን እየሸሸ የሚወጣውን ሕዝብ ቁጥር ከፍ አድርጎታል። በደቡባዊ የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ በባምባሪ ግዛት ባለፈው ሰኔ ወር ጥቃቱ እንዳዲስ ከተጠናከረ ወዲህ ቢያንስ 20,000 ሰዎች ቤታቸውን ለቀው መሸሽ ተገደዋል። በዚሁ ግዛት የፀረ ባላካ ታጣቂ ሚሊሺያዎች እና የቀድሞ የሴሌካ ዓማፅያን 50 ሰዎች መግደላቸውን የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አሰከባሪ ጋድ አባላት አስታውቀዋል። ያይን ምስክሮች ለዜና ምንጮች እንደነገሩት፣ በሳምንቱ መጀመሪያ ሰኞ ዕለትም የሴሌካ ዓማፅያን በአንድ የባምባሪ ካቶሊክ ቤተ ክርስትያን ደጃፍ ባጠቃላይ 12,000 ተፈናቃዮች የተጠለሉባቸውን ድንኳኖች ባጠቁበት እና በእሳት ባጋዩበት ጊዜ ቢያንስ 24 ሰዎች ገድለዋል።

በክርስትያኖቹ እና በሙሥሊሞቹ ሚሊሺያዎች መካከል የቀጠለው የኃይል ተግባር በብዛት ክርስትና እምነት ተከታዮች የሚኖሩበትን የባምባሪን ግዛት እስከ ጥቂት ሳምንታት በፊት ድረስ አልነካም ነበር። ባለፈው ሚያዝያ መጨረሻ ግን የተመድ ከፀረ ባላካ ጥቃት ለመከላከል ሲሉ ከመዲናይቱ ባንጊ እና አካባቢዋ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሙሥሊም የሀገሪቱ ዜጎችን ወደ ባምባሪ ባሰፈሩበት ጊዜ ሁኔታው ወዲያኑ ነበር የተቀየረው።

እርግጥ፣ የተመድ እንዳስታወቀው፣ በወቅቱ በባንጊ ውጥረቱ በመጠኑ ረገብ ብሏል። ይሁንና፣ አሁንም ከ11,000 የሚበልጡ ተፈናቃዮች በዚያ ይኖራሉ። ባለፉት ስድስት ወራት ብቻም ወደ 150,000 የሚጠጉ የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ዜጎችም ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል። ይህም ወደ ውጭ ሀገራት የተሰደዱትን የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ዜጎችን ቁጥር በጠቅላላ ወደ 370,000 ከፍ አድርጎታል።

ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ውስጥ እልባት ሊገኝለታ ላልቻለው ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ ለሆነው ውዝግብ በሀገሪቱ የሚገኘው የተፈጥሮ ሀብት ምክንያት ነው ይላሉ የዓለም አቀፉ የፀጥታ ጥናት ተቋም ተንታኝ ፖል ሳይመን ሄንዲ።

« የጦር መሳሪያ የታጠቁት ተቀናቃኝ ቡድኖች በተለይ ግዙፍ የማዕድን ሀብት ንጣፍ የሚገኝባቸውን አካባቢች ተቆጣጥረዋል። በዚሁ አካባቢ እጅግ ብዙ ወርቅ እና አልማዝ የሚገኝ ሲሆን፣ እነዚህኑ ማዕድናት በሕገ ወጥ መንገድ በመሸጥ የሚገያኙትን ገቢ ለኃይሉ ተግባራቸው ማራመጃ ይጠቀሙበታል። »

የተቀናቃኞቹ ሙሥሊም የቀድሞ የሴሌካ ዓማፅያን እና ፀረ ባላካ ሚሊሺያ ቡድኖች መሪዎች በተለይ ሲቭሉን ሕዝብ መድረሻ ላሳጣው አስከፊ ጥቃት tተጠያቂ አለመሆናቸውን በተደጋጋሚ ሲያስታውቁ ተሰምተዋል፣ ምክንያቱም አንዳንድ የነዚሁ ቡድኖች አባላት በማ፣ አ፣ ሬ፣ ውስጥ ሰላም ለማውረድ በመጣር ላይ ባለው በሽግግሩ መንግሥት ውስጥ በይፋ ይሰራሉ። የቀድሞ ሴሌካ ዓማፅያን መሪ አብዱላዬ ኢሴኒ ቡድናቸው ካለፈው ታህሳስ ወዲህ ውጊያ ማቆሙን በማስታወቅ፣ በሀገሪቱ ለሚታየው ጥቃት ተጠያቂዎቹ ከቁጥጥር ውጭ የሆኑ ቡድኖች ናቸው ሲሉ፣ የፀረ ባላካዎቹ ተጠባባቂ አስተባባሪ ሲልቬስትር ያጉዙ ደግሞ አጥቂዎቹ ተራ ወንጀለኞች ወይም ከወህኒ ያመለጡ እስረኞች መሆናቸውን ይናገራሉ።

« በፀረ ባላካ ስም ወንጀል እና ጥቃት እንዲፈፅሙ ለተራ ወንጀለኞች ገንዘብ የሚከፍሉ ፖለቲከኞች አሉ። »

ይህም ቢሆን ግን ቡድናቸውን ትጥቅ በማስፈታት ለመበተን ዕቅድ እንደሌላቸው ነው ያጉዙ አክለው የገለጹት።

« ሚሊሺያዎች አይደለንም፣ እኛ ቡድናችንን ያቋቋምነው ትውልድ ሀገራችንን ለመከላከል ነው። እና በምን ምክንያት ነው ቡድናችንን መበተን ያለብን? የሴሌካ ዓማፅያን አሁንም በሀገሪቱ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ነው እኮ። »

ሲልቬስትር ያጉዙ ለዶይቸ ቬለ በሰጡት ቃለ መጠይቅ እንዳስታወቁት፣ የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ የሽግግር መንግሥት ጠንካራ የጦር ኃይል ስለሌለው፣ ሀገሪቱን ከሴሌካ ዓማፅያን ጥቃት ነፃ ለማውጣት ቆርጦ ተነስቶዋል የሚሉት ፀረ ባላካ ቡድናቸው ራሱን ወደ ፖለቲካ ፓርቲ ለመቀየር እንደሚፈልግ አስታውቀዋል።

« በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ውስጥ እንደገና ሰላም የሚያወርድ አንድ ድርጅት እናቋቁማለን። የሀገሪቱ ዜጎች ፀረ ባላካ የሚለውን ስም መስማት ስለማይፈልጉም፣ ለቡድናችን ሌላ ስም የመስጠት ዕቅድ ይዘናል። »

እንደሚታወሰው እአአ መጋቢት 2013 ዓም የሴሌካ ዓማፅያን ክርስትያኑን ፕሬዚደንት ፍራናስዋ ቦዚዜን በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን አውርደው በሚሼል ጆቶዲያ ተክተዋቸው ነበር፣ ይሁንና፣ ጆቶዲያ በሀገሪቱ ፀጥታ እና መረጋጋት ሊያወርዱ ባለመቻላቸው ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ባረፈባቸው ግፊት ከዘጠኝ ወራት በኋላ ሥልጣናቸውን መልቀቅ ተገደዋል። ግን፣ ካትሪን ሳምባ ፓንዛ የሽግግሩ መንግሥት ፕሬዚደንት ከሆኑ በኋላም ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ልትረጋጋ አልቻለችም። የቀድሞ የመዲናይቱ ባንጊ ከንቲባ የነበሩት እና ዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ አክብሮት ያተረፉት ፕሬዚደንት ሳምፓ ፓንዛ ካለፈው ጥር ወር ወዲህ ከምዕራቡ ዓለም ግዙፍ ድጋፍ ቢያገኙም፣ እስካሁን በሀገሪቱ አንድም ታጣቂ ቡድን የጦር መሳሪያ ትጥቁን አልፈታም፣ በማ፣አ፣ሬ፣ ዕርቀ ሰላም ለማውረድ የተጀመረውን ጥረት ማሳካት የሚቻልበትን መንገድ ለማስገኘት ከተፈለገ ታጣቂዎቹ የጦር መሳሪያቸውን የሚፈቱበት ድርጊት ቀዳሚው መሆን እንዳለበት የአፍሪቃ ህብረት የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤት ኮሚሽነር እስማኤል ሼርጉዊ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ዓለም አቀፉ አገናኝ ቡድን በአዲስ አበባ ባካሄደው ጉባዔ ወቅት አስታውቀዋል። ለዚህም፣ ይላሉ ሼርጉዊ፣

« የሀገሪቱ መንግሥት ሚሊሺያ ቡድኖቹን የጦር መሳሪያ ትጥቃቸውን ለሚያስፈታበት ጥረቱ ርዳታ ማቅረብ አስፈላጊ መሆኑን ግልጽ አድርገናል፣ ለግማሹ ያህል የሀገሪቱ ሕዝብ ሰብዓዊ ርዳታ የማቅረብ ፈታኝ ሁኔታ መኖሩን ጠቁመናል። ከዚሁ ጎንም፣ እአአ ከፊታችን ሀምሌ 23 እስከ ሀምሌ 25 ድረስም የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክን የዕርቀ ሰላሙን ድርድር ሂደት ለማንቀሳቀስ፣ የውዝግቡን መንሥዔ ለመለየት እና የሀገሪቱን ልማት ለማራመድ የሚያስችል የብራዛቪል መድረክ የተሰኘ ጉባዔ ለማካሄድ ወስነናል። »

በዚሁ ሂደት ላይ ከጥቂት ወራት በኋላ ይሠማራል የሚባለው እና 12,000 ወታደሮችን የሚያጠቃልለው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ ወሳኝ ሚና እንደሚይዝ በዓለም አቀፉ አገናኝ ቡድን ምክክር ከተሳተፉት መካከል አንዱ የሆኑት የተመድ ምክትል ዋና ፀሐፊ ኤርቬ ላድሱ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

« በአሁኑ ወቅት እየተከተልነው ያለነው ፖሊስ በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ውስጥ በምሕፃሩ «ሚስካ» ተብሎ በሚታወቀው ተልዕኮ ስር የተጠቃለሉትን የአፍሪቃ ህብረት ወታደሮች እአአ የፊታችን መስከረም 15፣ 2014 ዓም በሚሠማራው በምህፃሩ «ሚኑስካ» በሚባለው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ ውስጥ ማዋኃድ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪም በ«ሚኑስካ» ውስጥ መሪ ሚና ከሚይዙት ለ«ሚስካ» ወታደሮች ካቀረቡት ሀገራት ጋ ባንድነት በመሆን ከመላ አፍሪቃ እና ከሌሎች አህጉራት በተቻለ ፍጥነት ለ«ሚኑስካ» ወታደሮች የሚያዋጡ ሀገራትን እናፈላልጋለን። እንደሚታወቀው፣ የተመድ ፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት 10,000 ወታደሮች እና 1,820 ፖሊሶች እንዲጠቃለሉበት ወስኖዋል። »

ዓለም አቀፉ የማዕከላይ አፍሪቃ አገናኝ ቡድን እና የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ባለሥልጣናት የተመድ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ሥምሪት ሀገሪቱን ሊያረጋጋ እና በመጪው የካቲት ምርጫ ሊደረግ የሚችልበትን ሁኔታ ሊያመቻች እንደሚችል ተስፋ አሳድሮዋል። ተስፋቸው እውን ሊሆን መቻሉ እንግዲህ ወደፊት የሚታይ ይሆናል።

አርያም ተክሌ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic