ታዳጊው ዓለምና የፊናንሱ ቀውስ ተጽዕኖ | ኤኮኖሚ | DW | 09.09.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ታዳጊው ዓለምና የፊናንሱ ቀውስ ተጽዕኖ

በዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ክፉኛ የተመታው የባንክ ዘርፍ የከሰረው ከስሮ የተቀረው ቀስ በቀስ መልሶ በማገገም ላይ ሲሆን ቀውሱ ከማብቂያው ደረጃ ላይ ሳይደርስ አልቀረም የሚለው ተሥፋ ከቀን ወደቀን እየዳበረ በመሄድ ላይ ነው የሚገኘው።

default

እርግጥ በዚህ በለለጸገው በምዕራቡ ዓለም በመጠኑም ቢሆን ተሥፋ ሰጭ የኤኮኖሚ ዕርምጃ አዝማሚያ ይታይ እንጂ በሌላ በኩል ቀውሱ በታዳጊ አገሮች ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ግን በቀላሉ የማይበገር ሆኖ እንደቀጠለ ነው። የተባበሩት መንግሥታት የንግድና የልማት ጉባዔ UNCTAD ባለፈው ሰኞ ጀኔቫ ላይ ይፋ ያደረገው የያዝነው 2009 ዓ.ም. የዓለም ንግድ ዘገባ እንዳመለከተው የዓለምአቀፉ ኤኮኖሚ ቀውስ መዘዝ ገና አልተወገደም።

አሜሪካ ውስጥ ከአንድ ዓመት በፊት በሌህማን-ብራዘርስ የመዋዕለ-ነዋይ ባንክ መንኮታኮት የጀመረው የፊናንስ ተቋማት ክስረት ጋብ እያለ ቢሄድም ያስከተለው የኤኮኖሚ ቀውስ አሻራ ግን ገና አልተሰወረም። የበለጸጉት መንግሥታት ከአሜሪካ እስከ አውሮፓ በብዙ ሚሊያርድ የሚቆጠር ገንዘብ በማፍሰስ ብሄራዊ ኤኮኖሚያቸውን መልሶ ለማነቃቃትና ቀውጢውን ጊዜ ለማለፍ በሚያደርጉት ጥረት እንደቀጠሉ ነው። ባንኮችንና አምራች ኩባንያዎችን ከክስረት ለማዳን፤ እንዲያም ሲል የሥራ አጦችን ቁጥር መበራከት ለመግታት መረባረቡ ባለፈው አንድ ዓመት የተለመደው ነገር ሆኖ ቆይቷል።

ችግሩን በጋራ ለመወጣትና ከሰባ ዓመታት ወዲህ የተከሰተው ይህን መሰል ሃያል የፊናንስ ቀውስ ከእንግዲህ እንዳይደገም ዓለምአቀፍ መቆጣጠሪያ ደምቦችን ለማስፈን በመንግሥታት ደረጃ የሚደረገውም ጥረት አልተቋረጠም። ዕርምጃዎቹን ጭብጥ ለማድረግ በቡድን-ሃያ መንግሥታት ዘንድ የሚደረገው ተከታይ የመሪዎች ጉባዔም በቅርቡ በአሜሪካ ፒትስበርግ ላይ የሚካሄድ ሲሆን ባለፈው ሰንበት ለንደን ላይ በሚኒስትሮች ደረጃ ተካሂዶ የነበረው የዝግጅት ስብሰባ ውጤት እንዳሳየው ዕርምጃው አሁንም አዝጋሚ ነው።
የበለጸጉትና ራመድ ያሉት የቡድን-ሃያ መንግሥታት የፊናንስ ሚኒስትሮች የዓለም ኤኮኖሚ እስኪያገግም ድረስ የኤኮኖሚ ማነቃቂያ ዕርምጃቸው እንዲቀጥል ሲስማሙ ከብዙ ክርክር በኋላ ለባንክ አስተዳዳሪዎች የሚከፈለው አበል ከአጭር ይልቅ በረጅም ጊዜ ስኬት ላይ የተመሰረተ እንዲሆንም ከአንድነት ደርሰዋል። ሃሣቡን በመደገፍ ጀርመንና ፈረንሣይ በአንድ በኩል ዋሺንግተንና ለንደን ደግሞ በሌላ ወገን ሆነው ሲከራከሩ ነው የቆዩት። ይህ አሁን ተደረሰበት የተባለው አንድነት ፒትስበርግ ላይ ወደ ጭብጥ ዕርምጃነት መለወጥ አለመለወጥ መቻሉ ለጊዜው አይታወቅም። ጠብቆ መታዘቡ ግድ ይሆናል። ሆኖም የፈረንሣይ የፊናንስ ሚኒስትር ክሪስቲን ላጋርድ በበኩላቸው የማያሻማ ደምብ የማስፈኑ ጥረት ፍሬ እንደሚሰጥ ነው ያረጋገጡት።

“ሁኔታውን በጥንቃቄ ለመከታተልና ከግቡ ለማድረስ ቁርጠኞች ነን። የፊናንሱን ዘርፍ ደምቦች በአዲስ መልክ ማስፈኑ በጣሙን አስፈላጊ ነው። ለባንክ አስተዳዳሪዎች በገፍ ገንዘብ መከፈሉ ያሳፍራል። እናም በአሁን መልኩ እንዲቀጥል ልንተወው የምንችለው ነገር አይደለም”
የለንደኑ የቡድን-ሃያ የፊናንስ ሚኒስትሮችና የባንክ አስተዳዳሪዎች ስብሰባ የተስማማበት ሌላው ጉዳይ የዓለም ባንክንና ዓለምአቀፉን የምንዛሪ ተቋም IMF-ን የታዳጊ አገሮችን አብሮ የመወሰን አቅም በሚያጠናክር ሁኔታ መጠገን ነው። መጪው የፒትስበርግ ጉባዔ የተጠቀሱትን ለውጦች ገሃድ ማድረግ ከቻለ ታላቅ ዕርምጃ ነው የሚሆነው። እርግጥ ታዳጊዎቹ አገሮች በቀውሱ ከባድ ተጽዕኖ ታጅበው ምናልባትም ለረጅም ጊዜ ይቀጥላሉ።
በተባበሩት መንግሥታት የንግድና የልማት ጉባዔ ዩንክታድ ዓመታዊ ዘገባ መሠረት የዓለም ንግድ በዚህ ዓመት 11 ከመቶ እንደሚያቆለቁል ይጠበቃል። በዚህ ይበልጥ ተጎጂዎቹ ደግሞ ታዳጊዎቹ አገሮች ናቸው። በመሆኑም የንግድና የልማት ጉባዔው በ 2009 የዓለም ንግድ ዘገባው አጥብቆ ያሳሰበው ታዳጊዎቹ አገሮች እንዲረዱና የሜሌኒየሙ ግቦችም ከዓይን እንዳይሰወሩ ነው። የዩንክታድ ቀደምት የምጣኔ-ሐብት ባለሙያ ጀርመናዊው ሃይነር ፍላስቤክ የዘገባውን መልዕክት ለዶቼ ቬለ እንዳስረዱት ቀውሱ እየተወገደ ነው ለማለት ገና ጊዜው አይደለም።

“መልዕክቱ የፊናንሱን ቀውስ ገና አላስወገድም የሚል ነው። በወቅቱ ስለ መውጫ ስልታዊ ዕርምጃዎች ከመናገር መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ጀርመንን በተመለከተ የመንግሥቱን ዕዳ መቼ እንደገና መቀነስ፤ መቼ ወለድን ማሳደግ መቻሉ በሁለት ሣምንት ውስጥ ከሚካሄደው ፌደራል ምርጫ በኋላ መነጋገሪያ ርዕስ እንደሚሆን አያጠራጥርም። አሁን ለሁሉም ጊዜው አይደለም። ዕንደ ዕውነቱ በወቅቱ በፊናንስ ገበዮች ላይ የምንታዘበው ሁሉ ከዕውነተኛ የማገገም ደረጃ የደረሰ አይደለም”

በተጨማሪ ከፍጆትና ከመዋዕለ ነዋይ እንቅስቃሴ አንጻርም በወቅቱ ግልጽ የሆነ ማገገም ለዓይን ቀርቦ አይታይም። ዘገባው በተለይ ጠበቅ ያለ ዕርምጃ የጠየቀው ደግሞ በፊናንስ ገበዮች ላይ ነው። እነዚሁ ቡድን-ሃያ መንግሥታትና ጀርመንም በያዙት ጥረት መንፈስ ጠንካራ ደምቦች ሊጣሉባቸው ይገባል።

“በፊናንስ ረገድ የሚደረግ ቁመራን መከልከል ይቻላል። አስፈላጊ ነገር አይደለም። ገበዮችን ለማረጋጋት አንዳች አስተዋጽኦ ሊያደርግም አይችልም። እርግጥ አንድ ሁለት ካዚኖዎች ክፍት ሆነው ሊቀጥሉ ይችላሉ። ግን እንደገና ከዚህ መሰል አደገኛ ሁኔታ ላይ እንዳንወድቅ ዋና ዋናዎቹን መዝጋት ያስፈልጋል”

በዓለምአቀፉ የንግድና የልማት ጉባዔ አመለካከከት የመለዋወጫ ምንዛሪዎችን ግንኙነት ልዝብ የሚያደርግ አዲስ ስርዓት መስፈኑም አስፈላጊ ነው።

“በምንዛሪው ገበያ ላይ አሁን ጭብጥ ሃሣብ እናቅባለን። ማለት አሁን የመለዋወጫ ተመንን ማስቀመጥ ብቻ ሣይሆን ከየሃገራቱ የዋጋ ንረት ልዩነቶች ጋር ማጣጣምም አስፈላጊ ነው። ይህ ለገበዮች መተው የለበትም”

በተባበሩት መንግሥታት የንግድና የልማት ጉባዔ ዩንክታድ ዕምነት እንዲህ ብቻ ነው የምንዛሪውን ቀውስና በዚሁ የተዛባውን ሚዛን ምልክቶች ብቻ ሣይሆን ምክንያቶቹን መቋቋም የሚቻለው። ይህ ደግሞ አጣዳፊ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም የዩንክታድ ዘገባ እንደሚያመለክተው የዓለም የኤኮኖሚ ድርሻ በዚህ ዓመት 2,5 ከመቶ፤ የዓለም ንግድም ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ከአሥር በመቶ በላይ ያቆለቁላል ተብሎ ነው የሚጠበቀው።

በተለይ ታዳጊ አገሮች ተጎጂዎቹ ሲሆኑ የተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ግቦችም አደጋ ላይ ናቸው። የዓለም ሕብረተሰብ በሚሌኒየም ውጥኑ በምድራችን ላይ በከፋ ድህነትና ረሃብ የሚኖረውን ሕዝብ ቁጥር እስከ 2015 ዓ.ም. በግማሽ ለመቀነስ መነሣቱ ይታወቃል። ዩንክታድ ከወቅቱ ሁኔታ አንጻር ሃሣቡ ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር ታዳጊዎቹ አገሮች ለምሳሌ በዕዳ ቅነሣ ወይም ምሕረት መረዳት ይኖርባቸዋል ባይ ነው። ግን ነገሩ ቀላል አይደለም።

“ሁኔታው በጣሙን አሳሳቢ ነው። እናም በዓለምአቀፍ ደረጃ ኤኮኖሚን መልሶ ለማነቃቃት ከተያዘው ጥረት አንጻር የልማት ዕርዳታን ቀጣይ ለማድረግ የግድ ጽናትና ቆራጥነት ያስፈልጋል”

የዩንክታድ ባለሙያ ሃይነር ፍላስቤክ አያይዘው እንደሚሉት የአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃም ችላ መባል የሌለበት ጉዳይ ነው። በጉባዔው የ 2009 የንግድና የልማት ዘገባ ላይ የልማት ግቦችን ከአካባቢ አየር ለውጥ ጋር ማጣጣሙ እርስበርሱ አይቃረንም ሲል ተመልክቷል። እንዲያውም ዓለምአቀፉ ለውጥ አዳዲስ የኤኮኖሚ መንገዶችን ሊከፍት የሚችል ነው። ከአካባቢ አየር ይዞታ ጋር የተስማማ ፖሊሲ በታዳጊ አገሮች ሳይቀር ከተፋጠነ ዕድገት ተዛምዶ ሊራመድ ይችላል።

“መንግሥታትና ሕብረተሰብ የአካባቢ አየር ጉዳትን በ 50 ዓመታት ውስጥ ለማስወገድ እንደሚፈልጉ ግባቸውን ሲነድፉ ይህ ተገቢ መብታቸው ነው። ሂደቱ በመዋቅራዊ ለውጥ ላይም ተጽዕኖ ይኖረዋል። ገቢን ያሳድጋል፤ የሥራ መስኮች እንዲስፋፉ ያደርጋል፤ ሌሎች ነገሮችም!”

ዩንክታድ በዓለም ዙሪያ ንግድና ልማትን ወደፊት ለማራመድ ይፈልጋል። በመሆኑም የዚህ ዓመቱም ዘገባ ብዙ የመፍትሄ ሃሣቦችን የጠቀለለ ነው። ፍላስቤክ እንደሚሉት ይሁንና ምክሩ አብዛኛውን ጊዜ አለመሰማቱ ላይ ነው ችግሩ!

“መደመጡ እንዲህ በቀላሉ የሚሆን ነገር አይደለም። ፖለቲካ ፖለቲካ ነው። ጀርመን ውስጥ የዩንክታድ ምክር የሚሰማው በጥቂቱ ነው። ግን ቻይና፣ ሕንድና ብራዚል ውስጥ ብዙ ተደማጭነት አለን። ስለዚህም ድምጻችንን በማሰማት ይበልጥ ተደማጭነት እንደምናገኝ ተሥፋ እናደርጋለን”

በአጠቃላይ ዓለምአቀፉ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ አመጣጡን ለመተንበይ ያልተቻለውን ያህል የወቅቱ የማገገም አዝማሚያ ጽናት ይኑረው አይኑረው እንዲህ ብሎ መናገሩም የሚያዳግት ነው። በመሆኑም የሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታትም ምናልባት የቀውሱ ጥላ እንደጋረዳቸው ሊቀጥሉ ይችላሉ። እርግጥ ቡድን-ሃያ መንግሥታት ዘላቂ መፍትሄ ከፈለጉ ዓለምአቀፉን የኤኮኖሚ ስርዓት ታዳጊ አገሮችን ጭምር በሚጠቅም መንገድ ለመጠገን የሚያበቃ ወሣኝ ዕርምጃ ማድረጋቸው ግድ ነው የሚሆነው።

MM/DW/UNCTAD