ታዳሽ የኃይል ምንጭ ከ «ፕላስቲክ» | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 27.03.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ታዳሽ የኃይል ምንጭ ከ «ፕላስቲክ»

የተፈጥሮ አካባቢ ብክለት፤ የአየር ንብረት ለውጥ ክሥተት፤ የወቅቶች ጊዜአቸውን ጠብቀው አለማባት፣ የጎርፍ ማጥለቅለቅ፣ የከባድ በረዶ ፤ የኃይለኛ ሐሩር፣ የባህር ማዕበልና የመሳሰለው ፍርርቅ፤ የበረሃ መስፋፋት፤ የምድር ግለት እየጨመረ መሄድ

የተፈጥሮ አካባቢ ብክለት፤ የአየር ንብረት ለውጥ ክሥተት፤ የወቅቶች ጊዜአቸውን ጠብቀው አለማባት፣ የጎርፍ ማጥለቅለቅ፣ የከባድ በረዶ ፤ የኃይለኛ ሐሩር፣ የባህር ማዕበልና የመሳሰለው ፍርርቅ፤ የበረሃ መስፋፋት፤ የምድር ግለት እየጨመረ መሄድ፤ በአቶም ኃይል የኤሌክትሪክ ማመንጫ አውታሮች ለአደጋ ተጋላጭነት ፣ በየጊዜው የምንሰማውና እየታዘብንም የምናልፈው ጉዳይ ከሆነ ከራርሟል።
የሆነው ሆኖ ፤ በኢንዱስትሪ በበለጸጉትና በሥነ-ቴክኒክ በገፉት ፤ እንዲሁም በአንዳንድ አዳጊ አገሮች፤ ፕላኔታችንን የሚታደግ ታዳሽ የኃይል ምንጭ ይበልጥ ሊስፋፋ እንደሚገባ በመገናኛ ብዙኀን በሰፊው መነሣት መጣሉ ተዘወትሮ ነው የሚሰማው።
ለምሳሌ ያህል ባለፈው ኅዳር 17-29 ፤ 2005 ዓ ም፤ ዶሃ ፣ ቐጠር ውስጥ፣ የተባበሩት መንግሥታት፣ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ነክ ጉባዔ ቢካሄድም፤ የአየር ንብረት በካዮች የተባሉት፣ ዩናይትድ እስቴትስና ቻይና፤የኪዮቶ ቀጣይ የሆነውን ስምምነት እንዲቀበሉት የቀረበውን ጥያቄ ለሟሟላት ዝግጁ ሆነው እንዳልተገኙ በጊዜው የተገለጠ ጉዳይ ነው። ያም ሆኖ፤ በቀሪዎቹ ብዙኀን ዘንድ ተስፋን ማጫሩ አልቀረም።


በቅርቡ፣ በርሊን ፤ ጀርመን ውስጥ፣ የተባበሩት መንግሥታት ፣ «የአረንጓዴ አየር ንብረት ግምጃ ቤት » አዳዲሶቹ የቦርድ አባላት ስብሰባ ባደረጉበት ወቅት፤ ለተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ የሚታገሉና በጥሞና የሚከታተሉ ፣ ከጀርመንና ከቀሪው የዓለም ክፍል የተውጣጡ 75 ቡድኖች፤ ሲቭሉ ማኅበረሰብ በስፋት የትግሉ ተሳታፊ እንዳይሆን ገደብ በሚያስቀምጡ የቦርዱ ደንቦች ላይ ቅሬታቸውንም ሆነ ንዴታቸውን ከማንጸባረቅ ወደ ኋላ አላሉም። በተባበሩት መንግሥታት ፣ የአየር ንብረት ጉዳይ መዋቅራዊ ስምምነት(UNFCCC) የበላይ ተቆጣጣሪነት፤ እ ጎ አ በ 2010 የተቋቋመው ይኸው «የአረንጓዴ አየር ንብረት ግምጃ ቤት» ፣ ወደፊት፤ አዳጊ አገሮች፤ የአየር ንብረት መዛባትን ለመካላከል ይቻላቸው ዘንድ ፣ በያመቱ 100 ቢሊዮን ዶላር ያህል እርዳታ እንዲቀርብላቸው ለማድረግ ይሆናል የሚታገለው። ዋና ጽ/ቤቱ በዋሽንግተን ፤ ዩናይትድ እስቴትስ የሚገኘው የምድራችን ወዳጆች የተሰኘው ለተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ የሚታገለው ድርጅት እንደሚለው፤ የሲቭሉ ማኅበረሰብ ፤ ጠቃሚ ተባባሪ ኃይል በመሆን፣ የተባበሩት መንግሥታት ፣ «የአረንጓዴ አየር ንብረት ግምጃ ቤት »በ 21 ኛው ክፍለ ዘመን፤ በሳይንስና ፍትኅ ላይ ተመሥርቶ ተግባሩን እንዲቀጥል ለማብቃት ሰፊ እገዛ ለማድረግ ባልተሳነውም ነበር።
የታዳሽ የኃይል ምንጭን በተመለከተ፣ በማደግ ላይ ያሉ አገሮችም ሆኑ ከእነርሱ አንድ እመርታ ያሳዩ ሃገራት በሥነ ቴክኒክ ዝውውርም ሆነ ራሳቸው የሥነ ታክኒክ ምርምርን በማጠናከር በአረንጓዴ የኃይል ምንጭ፤ Green Electricity (Green Power)የህዝባቸውን የኑሮ ዕድገት ለማስገኘት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ ። በዚህ ረገድ አመርቂ ውጤት ያስመዘገበች፤ 192 ሚሊዮን ኑዋሪዎች ያሏት ግዙፋ የላቲን አሜሪካ ሀገር ብራዚል ናት። የብራዚል ሳይንቲስቶች በዚህ ረገድ ያስመዘገቡት ውጤት፣

የታዳሽ ኃይል ምንጭን ይበልጥ እንዲስፋፋ አስተዋጽዖ ሳያደርግ እንደማይቀር ይታመናል። ሳይንቲስቶቹ ፣ የፀሐይን ኃይል በማጥመድ ኤልክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የተጠቀሙት በተለመደው በ«ሲሊከን» ሳይሆን በልዩ ስስ ፕላስቲክ ነው። ይህን ልዩና በቀላል ወጪ ጠቀሜታ የሚሰጥ ፕላስቲክ የሠሩት ፤ በደቡብ ምሥራቅ ብራዚል በሚናስ ጌሬስ ክፍለ ሀገር በሚገኘው የምርምር ተቋም የሚሠሩ ጠበብት ናቸው። ብራዚላውያኑ ጠበብት የሠሩትን ከተፈጥሮ ቁስ አካል የተገኘውን ስስ ፕላስቲክ ለመሥራት በዩናይትድ እስቴትስና በአውሮፓ ለብዙ ዓመታት ምርምሩ ሲካሄድ እንደነበረም ተወስቷል። ይህን «ሶላር ፕላስቲክ» የሚል ሥያሜ የሰጡትን አዲስ ግኝት አስመልክተውም ብራዚላውያኑ ሳይንቲስቶች በሰጡት መግለጫ ላይ ፤ ከፀሐይ፣ በአዲስ መልክ ታዳሽም ሆነ «ንፁህ» የኃይል ምንጭ ማግኘት መቻሉ መለስተኛም ቢሆን እንደ አብዮት የሚቆጠር ነው ማለታቸው ተጠቅሷል።
የንግድ አስተዳደር ፕሮፌሰር አንድሬ ፔሬይራ ካርቫዮ እንዳሉት ፣ «ብራዚል ፣ ከዩናይትድ እስቴትስ, ጃፓንና ጀርመን ጋር ስትወዳደር ጨቅላ ናት፣ የአረንጓዴ ሥነ ቴክኒክን ምርምር በተመለከተ ግን፣ በፋጣኝ መራመድ ብቻ ሳይሆን መሮጥ የምትችልበት አቅም አላት። »
የታዳሽ ኃይል ምንጭን አስፈላጊነት በተመለከተ ከአውሮፓው ሃገራት ህዝብ መካከል፤ ላቅ ያለ ድጋፍ በመስጠት ከሚገኙት መካከል ጀርመናውያን ይገኙበታል። በተለይ በጃፓን ፉኩሺማ ላይ የአቶም ኃይል ማመንጫ አውታር፣ በውቅያኖስ ማዕበል ሳቢያ አደጋ ከደረሰበትና ፈንድቶ በአካባቢው አደገኛ ብክለት ካደረሰ ወዲህ፤ ጀርመናውያን ፣ ወደ ታዳሽ የኃይል ምንጭ እንዲዞር አጥብቀው ነው ምኞታቸውንም ፍላጎታቸውንም ያንፀባረቁት። በመሆኑም አረንጓዴ የኃይል ምንጭ በሚሰኘው ለመጠቀም፣ በራሳቸው ተነሳሽነት የተመዘገቡ ጥቂቶች አይደሉም። ለምን ሲባሉም እንዲህ ምላሽ የሰጡ አሉ።
* « በአረንጓዴ የኃይል ምንጭ ነው የምጠቀመው። ለምን ቢሉ? ዘለቄታ ያለው የኃይል ምንጭ ነክ የኤኮኖሚ መርኅ እንዲኖር በመሻቴና በአመዛኙም ዋጋው ረከስ ያለ በመሆኑ ነው።
* ለአረንጓዴ የኃይል ምንጭ ግምት መስጠቱ ተገቢ ሆኖ ስለተሰማኝና ተፈጥሮ እንዲጠበቅ ስለምፈልግ ነው።


* ምክንያቱ ፣ በእርግጠኝነት የተሻለ ስሜት እንዲያድርብኝ፤ ከውጭ ፣ በአጠቃላይ፣ ለተፈጥሮ አካባቢ ይበልጥ ይሠራ ዘንድ የበኩሌን ድርሻ ለመወጣት ነው።
* በአሁኑ ጊዜ ዋጋው ይበልጥ ስለሚያማልል
* አላውቅም፤ ሲነገርም ይህ ይበልጥ ጤናማ ነው የሚመስለኝ።
*የተፈጥሮ አካባቢ፤ ብዙ ገንዘብ ስላለኝ፤ እስቲ ለታዳሽ የኃይል ምን ጭ አንድ ነገር ላድርግ ብዬ ነው።
* አረንጓዴ የኃይል ምንጭ፤ ለራስ ልጆች ለተፈጥሮ አካባቢም ግልጽ ነው ይበጃል ብዬ ነው።
* መለስ ብለው በፉኩሺማ የደረሰውን ልብ ካሉ፣ በእርግጥ ፊትን ወደ አረንጓዴ የኃይል ምንጭ መመለስ ተገቢ ነው።»
ከኖርዌይ፤ ባጠቃላይ ከእስካንዲኔቪያ አገሮች፤ ኦስትሪያና እስዊትስዘርላንድ ቀጥሎ ጀርመንም ውስጥ ብዙዎች የአገሪቱ ዜጎች፤ ለተፈጥሮ ጠንቅ ያልሆነ ታዳሽ የኃይል ምንጭ እንዲኖራቸው ነው የሚፈልጉት። በኖርድ ራይን ቬስትፋለን ፌደራል ክፍለ ሀገር፤ የሸማቾችን ጥቅምና መብት ይዞታ የሚመለከተው ማዕከል ፤ በተለይ የኃይል ምንጭ ጉዳዮች ተመልካች ዑዶ ዚቨርዲንግ እንዲህ ይላሉ።
«ጀርመን ውስጥ፤ በመሠረቱ፤ ለኃይል ምንጭ ለውጥ፤ ቀጣይነት ላለው አገልግሎት በማሰብ ፣ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት፣ ወደ አረንጓዴ የኃይል ምንጭ ለመዞር የሚሹ ዜጎች ቁጥር ብዙ ነው። እንደሚመስለኝ የዚህ አዝማሚያ ሥረ-መሠረት፣ የጀርመን የተፈጥሮ አካባቢ ጥብቃ ነክ ንቅናቄ፣ እንዲሁም ባለፉት ዓመታት የተካሄደው አጠቃላዩ የአቶም ኃይል ምንጭን የሚመለከተው ውይይት ነው።ዋናው መለኪያም እርሱ ነው የሚል እምነት አለኝ።»


ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic