ታዋቂዉ የፑቲን ተቀናቃኝ ታሰሩ | ዓለም | DW | 27.03.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ታዋቂዉ የፑቲን ተቀናቃኝ ታሰሩ

የፕሬዚዳንት ፑቲን ተፎካካሪና የክሬምሊን ቤተ-መንግሥት ታዋቂ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ አሌክሴይ ናቫልኒ ሞስኮ ላይ የተደረገዉን ከፍተኛ የተቃዉሞ ሰልፍ ተከትሎ ታሰሩ። ናቫልኒ የ 15 ቀናት እስራት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።

በሩስያ አንድ የሀገሪቱ ፍርድ ቤት ትናንት በመዲናይቱ ሞስኮ ፀረ ሙስና ተቃውሞ ሰልፍ ያካሄዱትን የተቃዋሚ ቡድን መሪ አሌክሴይ ናቫልኒ በ15 ቀን እስራት እንዲቀጡ እና 20,000 ሩብል ወይም 350 ዩኤስ ዶላር እንዲከፍሉ በየነ። የፍርድ ቤቱ ዳኛ አሌስያ ኦርክሆቫ  እጎአ በ2018 ዓም በሚደረገው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በፕሬዚደንት ቭላዲሚር ፑቲን አንፃር ለመፎካከሩ ያቀዱት ናቫልኒ ፈቃድ ሳያገኙ ከሰባት እስከ ስምንት ሺህ ሰው ተሳትፎበታል የተባለውን የትናንቱን ተቃውሞ በማዘጋጀታቸው ጥፋተኛ ብለዋቸዋል። ናቫልኒ ብይኑ ከተሰጠ በኋላ ፀረ ሙስና ትግላቸው ትክክለኛ መሆኑን ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።
«የትናንቱ ተቃውሞ በሩስያ በሙስና አንፃር የሚታገል እጩ መርሃግብርን የሚደግፉ ብዙ መራጮች መኖራቸውን ያሳየ ይመስለኛል። እነዚህ መራጮች ፖለቲካዊ ውክልና ማግኘት ይፈልጋሉ። እና እኔ የእነዚህ ሰዎች ተወካይ ለመሆን እፈልጋለሁ፣ ለዚህም ነው ለሀገሪቱ ከፍተኛ ስልጣን የመፎካከር መብት አለኝ ብዬ የማስበው። »
እጎአ ከ2011 ዓም ወዲህ በሞስኮ በተካሄደው ትልቁ ፀረ ሙስና ተቃውሞ ወቅት ከናቫልኒ ጋር ትናንት ወደ አንድ ሺህ የሚገመቱ ተቃዋሚዎችም ታስረዋል። ዩኤስ አሜሪካ እና የአውሮጳ ኅብረት እስራቱ ፀረ ዴሞክራሲ ነው በሚል ሩስያ እስረኞቹን እንድትፈታ ቢጠይቁም፣ ሩስያ ጥያቄውን ውድቅ አድርጋዋለች።

አርያም ተክሌ

አዜብ ታደሰ