ታንዛንያ እና ከጀርመን ካሳ የመጠየቅ እቅዷ | አፍሪቃ | DW | 11.02.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ታንዛንያ እና ከጀርመን ካሳ የመጠየቅ እቅዷ

ታንዛንያ የቀድሞዋ ቅኝ ገዢ ጀርመን በዚያን ጊዜ ለፈፀመችው በደል በይፋ ይቅርታ እንድትጠይቅ እና ካሳ እንድትከፍል ትፈልጋለች። ጀርመን እጎአ ከ1905 እስከ 1907 ዓም በቀድሞዋ የጀርመን ምሥራቅ አፍሪቃ ፣ በዛሬዋ ታንዛንያ የተካሄደውን የማጂ ማጂ ዓመፅ በኃይል መደምሰሷ የሚታወስ ነው። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:08

ታንዛንያ ለቅኝ አገዛዙ በደል ከጀርመን ካሳ ታገኝ ይሆን?

እርግጥ፣ የታንዛንያ መንግሥት እስካሁን ይህን በተመለከተ ይፋ ጥያቄ አላቀረበም። ይሁን እንጂ፣ የታንዛንያ መከላከያ ሚንስትር ሁሴን ምዌይኒ የሃገራቸው የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በዚሁ ጉዳይ በተቻለ ፍጥነት ከጀርመን መንግሥት ጋር እንደሚወያይ ተስፋ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። የታንዛንያ ምክር ቤት ከሶስት ቀናት በፊት ፣ ባለፈው ረቡዕ የካቲት ስምንት፣ 2017 ዓም በጀርመን ቅን አገዛዝ ዘመን የተፈፀመው በደል ሰለባ ለሆኑ ለብዙ ግለሰቦች ቤተሰቦች ካሳ ሊከፈላቸው ይገባል በሚል ያነሳውን ጥያቄ መንግሥት የመከታተል እና የመጠየቅ ግዴታ እንዳለበት ምዌይኒ  ከዶይቸ ቬለ ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ እምነታቸውን ገልጸዋል።

የቀድሞ የጀርመን ቅኝ ግዛቶች


« ካሳ እንዲከፈል እፈልጋለሁ። ታንዛንያ ኬንያ እና ናሚቢያን የመሳሰሉ ሌሎች አፍሪቃውያት ሃገራት  በቅኝ አገዛዝ ዘመን ለተፈፀመባቸው በደል ከቀድሞዎቹ ቅኝ ገዢ መንግሥታት በይፋ ካሳ እንዲከፈላቸው የጠየቁበትን ድርጊት በአርአያነት ትከተላለች። በዚሁ የካሳ ጉዳይ ላይ ከጀርመን መንግሥት ጋር መደራደር እንደምንችል እናምናለን። »
በቀድሞዋ የጀርመን ምሥራቅ አፍሪቃ ፣ በዛሬዋ ታንዛንያ ከ1905 እስከ 1907 ዓም በተካሄደው የማጂ ማጂ ዓመፅ 10,000 ሰዎች እንደተገደሉ እና እንደተሰቃዩ የታንዛንያ መከላከያ ሚንስትር ምዌኒ አስረድተዋል።
የታንዛንያ መንግሥት ከጀርመን መንግሥት ካሳ ለመጠየቅ ማሰላሰል የያዘበት ርምጃው በብዙ የሃገሪቱ ዜጎች ዘንድ ትልቅ ድጋፍ አግኝቷል። ሌሎች ሃገራት ለደረሰባቸው የጦር ወንጀል ካሳ እየተከፈሉ፣ ታንዛንያ ዝም ልትል እንደማይገባ ነው ያመለከቱት። ለምሳሌ በዶይቸ ቤለ የኪስዋሂሊ ክፍል የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አስተያየት ከሰጡት  መካከል የፌስቡክ ተጠቃሚዎች  የካማ አካባቢ ነዋሪ ኢኖሰንት ዮና ኢሳያ በቅኝ አገዛዙ ዘመን የጀርመን ጦር በታንዛውያን ላይ ላደረሰው ስቃይ እና መከራ የጀርመን መንግሥት ካሳ የመክፈል ግዴታ አለባት ሲል፣ ሌላው የባጋሞዮ ነዋሪ ሼቻምቦ ጀራልድ ካሳ ለመጠየቅ የተያዘው እቅድ ጠቃሚ እንዳልሆነ ነው የሚናገረው፣ እንደ ጀራልድ አስተሳሰብ ፣ ታንዛንያ ኢንዱስትሪያዊ ልማቷን ለማሳደግ የሚችሉ ጀርመንን የመሳሰሉ ኢንዱስትሪ ሃገራት ርዳታ ያስፈልጋታል፣ በዚሁ ረገድም ጀርመን እስካሁን ብዙ እንዳደረገች ነው ያመለከተው።  

ጀርመን በአሁኑ ጊዜ ከቀድሞ ቅኝ ግዛቶቿ ጋር የቅርብ ግንኙነት ፈጥራለች። የጀርመን ፕሬዚደንት ዮአኺም ጋውክ ታንዛንያን እጎአ በ2015 ዓም መጎብኘታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ሁለቱ ሃገራት ጥሩ የሚባል የኤኮኖሚ ግንኙነት አላቸው። ይሁን እንጂ፣ የበጀርመን የቅኝ አገዛዝ ዘመን የተፈፀሙ በደሎች ጥለውት ያለፉ ጠባሳ ዛሬም በጋራ ግንኙነታቸው  ላይ አሉታዊ ነቁጣ መጣሉ አልቀረም።  በጀርመን መዲና በርሊን ቤተ መዘክሮች ውስጥ ከቀድሞ የጀርመን ምሥራቅ አፍሪቃ የመጡ በመቶ የሚቆጠሩ አንገታቸዉ የተቀላ አፍሪቃውያን የራስ ቅሎች መኖራቸውን አንድ  «አአርዴ» በመባል የሚታወቀው የሃገሪቱ መንግሥት ቴሌቪዥን ድርጅት ጋዜጠኛ ባለፈው ህዳር ወር ማጋለጡ ይታወሳል። ብዙዎቹ ከአሁኗ ርዋንዳ ሲሆኑ፣ 60 ዎቹ ከአሁኗ ታንዛንያ እንደሆኑ ይገመታል። 
በቅኝ አገዛዝ ዘመን ለተፈፀሙ በደሎች ኃላፊነት በመውሰዱ ጉዳይ ላይ በጀርመን ህብረተሰብ ውስጥ ካለፉት ዓመታት ወዲህ ውይይት መጀመሩ አበረታቺ መሆኑን በፌዴራዊው ምክር ቤት ቡንድስታክ የግራ ፓርቲ እንደራሴ ኒየማ ሞቫሳት ገልጸዋል።
« ጀርመን በናሚቢያ ተወላጆች በተለይ በሔሬሮ እና ናማ ጎሳ ተወላጆች  ላይ ጭፍጨፋ መፈፀሙን አምና የተቀበለችበት እና ካሳ የመክፈሉ ጥያቄም የተነሳበት ድርጊት ተመሳሳይ ጥያቄ ያለውን የታንዛንያን መንግሥት በዚሁ እቅዱ እንዲቀጥልበት አበረታቶዋል። በታንዛንያ የሰለባዎቹ ቁጥር ከናሚቢያ ይበልጣል። የታሪክ ምሁራን እንደሚገምቱት፣ ቅኝ ገዢው የጀርመን ጦር እጎአ በ1905 እና በ1907 ዓም መካከል በአንፃሩ በደቡብ ታንዛንያ የተነሳውን የማጂ ማጂ ዓመፅ በኃይል ርምጃ በደመሰሰበት ጊዜ እስከ 300,000 የታንዛንያ ተወላጆች ነበር የተገደሉት።»
በዚሁ ጊዜ ግዙፍ የእርሻ ማሳዎች በመቃጠላቸው በአስር ሺዎች የሚገመቱም በረሀብ ተሰቃይተዋል። በቀድሞ ደቡብ ምዕራባዊ አፍሪቃ፣ በአሁኗ ናሚቢያ ውስጥ የጀርመን ቅኝ ገዢ ጦር እጎአ ከ1904 እስከ 1908 ዓም ድረስ  አገዛዙን አንቀበልም ባሉ በሔሬሮ እና ናማ ጎሳ ተወላጆች  ላይ ባካሄደው ጭፍጨፋ ከሰባ ሺሕ በላይ የሐሬሮ ተወላጆችን ሕይወት አጥፍቷል።

 
ጀርመን በቅኝ አገዛዙ ዘመን ለተፈፀመ በደል ኃላፊነት የመውሰድ ኃላፊነት አለባት የለባትም የሚለው ጥያቄ እስከቅርብ ጊዜ በፊት ድረስ ንዑሱን ትኩረት ብቻ ያገኘ ጉዳይ እንደነበር ነው በፌዴራዊው ምክር ቤት ቡንድስታክ የግራ ፓርቲ እንደራሴ ኒየማ ሞቫሳት የሚያስታውሱት። የጀርመን የቅኝ አገዛዝ ወንጀሎችን እና በደሎችን የሚያስታውስ አንድም መታሰቢያ እንደሌለ እና በጀርመናውያን ትምህርት ቤቶችም ተማሪዎች ስለጀርመን የቅኝ አገዛዝ ታሪክ ተማሪዎች በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እንደማይደረግ ሞሳቪት አክለው አስረድተዋል። 
የጀርመን መንግሥት በናሚቢያ የሃገሩ ጦር የፈፀመውን በደል እንደ የዘር ፍጅት /ጎሳ ጭፍጨፋ የተቀበለው ባለፈው ዓመት ነበር። ይህም ከ100 ዓመት በላይ ክርክር በኋላ እዚህ መደረሱ አዎንታዊ ቢሆንም፣ ለናሚቢያውያን ርምጃው በቂ ሆኖ አልተገኘም። የሄሬሮ እና የናማ ባህላዊ መሪዎች ለተፈፀመባቸው በደል የጀርመን መንግሥት በተባጭ ካሳ እንዲከፍላቸው በመጠየቅ  ከጥቂት ጊዜ በፊት በዩኤስ አሜሪካ ካሳ በመጠየቅ ክስ መስርተዋል።   
« በዚያም ሆነ በዚህ ጀርመን ለቅኝ አገዛዝ ሰለባ  ቤተሰቦች ካሳ የመክፈል ሞራላዊ እና ታሪካዊ ግዴታ አለባት። ግዴታዊ ሕጋዊ ነው አይደለም ይህን የታሪክ ምሁራን መወሰን አለባቸው። ይሁንና፣ ጀርመን ይህንን አሳሳቢ ጉዳይ እንደ ዋዛ እንዳታልፍ ሞራላዊ ኃላፊነትዋ ያስገድዳታል። »
የኬንያ እና የናሚቢያን ምሳሌ ለሚመለከት ታንዛንያ ካሳ ለመጠየቅ የያዘችው እቅድ ደህና እድል ሊኖረው ይችላል ብሎ ሊያስብ ይችላል። እንደሚታወሰው፣  ብሪታንያ በየቅኝ አገዛዝ ዘመን  በኬንያ በ1950ኛዎቹ የማው ማው ዓመፅን በደመሰሰችበት ርምጃዋ ለሞቱት ሰለባ ቤተሰቦች 19,9 ሚልዮን ፓውንድ ካሳ ለመክፈል ወስናለች፣ ጀርመንም የናሚቢያን እንደ ጎሳ ጭፍጨፋ ከመቀበሏ ሌላ፣ መንግሥት ባለፈው ጥር ለናሚቢያ የሔሬሮ እና የናማ ጭፍጨፋ ሰለባ ቤተሰቦች ካሳ ሊከፍል እንደሚችል መጠቆሙን አንዳንዶች ገልጸዋል።ጀርመን  የካሳውን ጉዳይ ፣ ማለትም፣ የሚከፈላቸዉ ወገኖች ማንነት፣ የክፍያዉ አፈፃፀምን የመሳሰሉ ጥያቄዎችን በተመለከተ ከናሚቢያ መንግሥት ጋር በመደራደር ላይ ይገኛል።  

አርያም ተክሌ/ማርቲና ሽቪኮቭስኪ

ልደት አበበ
 

Audios and videos on the topic