ታንዛኒያ ኢትዮጵያዉያን እስረኞችን ልትለቅ ነዉ | ኢትዮጵያ | DW | 08.02.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ታንዛኒያ ኢትዮጵያዉያን እስረኞችን ልትለቅ ነዉ

የታንዛንያ  መንግስት ወደ 2ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞችን ለመፍታት መወሰኑን ታንዛኒያ ዳሬሰላም የሚገኜዉ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ገለፀ።በሌላ በኩልም እዚያው ታንዛኒያ በቅርቡ 14 ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ይጓዙበት በነበረው ተሽከርካሪ ውስጥ በአየር እጦት ታፍነው መሞታቸዉን ኢምባሲዉ ገልጿል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:50

የሚለቀቁት እስረኞች ወደ ሁለት ሺሕ ይጠጋሉ

 

ታንዛኒያ በህገ ወጥ መንገድ  ወደ ደቡብ አፍሪቃ ለመሄድ የሚፈልጉ ኢትዮጵያዉያን እንደመሸጋገሪያ የሚጠቀሙባት ሀገር ነች።ከዚህም ጋር ተያይዞ የሀገሪቱን ድንበር ያለህጋዊ ፈቃድ ለማቋረጥ ሲሞክሩ  በሀገሪቱ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር የሚዉሉና በየስርቤቶቹ የሚንገላቱ ኢትዮጵያዉያን በርካቶች መሆናቸዉ ይነገራል። ይህንን በመገንዘብ ይመስላል በቅርቡ ስራዉን የጀመረዉና ዳሬሰላም የሚገኜዉ የኢትዮጵያ ኢምባሲ የመጀመሪያ ስራዉ ያደረገዉ ይህንኑ የኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ጉዳይ መሆኑን በታንዛኒያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዮናስ ዮሴፍ ለDW የገለፁት። 
በዚህም  ዜጎችን ማዕከል ያደረገ የመንግስት የዲፕሎማሲ አቅጣጫን በመከተል ወደ ሁለት ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያዉያን እስረኞችን ከሀገሪቱ መንግስት ጋር በተደረገ ተከታታይ ዉይይት  እንዲፈቱ መወሰኑን አምባሳደሩ አመልክተዋል።


ኢትዮጵያዉያኑ በታንዛኒያ እስር ቤቶች  እስከ ሁለት ዓመት የታሰሩና በአብዛኛዉ ወጣቶች መሆናቸዉን የኢምባሲዉ ዓባላት በእስር ቤቶቹ ባደረጉት ጉብኝት ለማረጋገጥ መቻሉንም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ኢምባሲ በትናንትናዉ ዕለት ከሀገሪቱ ዉጭ ጉዳይ ሚንስትር ጋር ባካሄደዉ ዉይይትም የእነዚሁ ኢትዮጵያዉያኑ እስረኞች ጉዳይ ዋና መነጋገሪያ ሆኖ እንደነበር አምባሳደሩ ገልፀዋል። ኢትዮጵያዉያኑ በቅርቡ ይፈታሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን አፈፃጸሙን በተመለከተም በቀጣይ ከታንዛኒያ  ከመንግስት ጋር ዉይይት እንደሚደረግ አስረድተዋል።


እንደ አምባሳደር ዮናስ ዮሴፍ በሚቀጥለዉ ሳምንትም 300 በላይ ኢትዮጵያዉያንን ከዓለም ዓቀፉ የስደት ድርጅት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ መንግስት ወጭ ከታንዛኒያ ወደ ሀገራቸዉ ይመለሳሉ።
በሌላ በኩልም በታንዛኒያ  በቅርቡ 14 ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ይጓዙበት በነበረው ተሽከርካሪ ውስጥ በአየር እጦት ታፍነው መሞታቸዉንና ከነዚህ ዉስጥም የ4ቱ አስከሬን ወደ  ኢትዮጵያ መላኩን አምባሳደሩ ገልፀዋል።
ለዕስራትና ለሞት የሚዳረጉት ኢትዮጵያዉያኑ ስደተኞች  ወደ ታንዛኒያ የሚመጡት በተሳሳተ መረጃ ለደላላ በርካታ ገንዘብ ከፍለዉ  በመሆኑ ህገ ወጥ ስደትን በተመለከተ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ በሀገር ቤት በሰፊዉ ሊሰራ እንደሚገባ አምባሳደሩ አሳስበዋል።

ፀሐይ ጫኔ

ሂሩት መለሰ

 

Audios and videos on the topic