ታኅሣሥ 11 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ  | ስፖርት | DW | 20.12.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

ታኅሣሥ 11 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ 

በርካታ ጨዋታዎች በተሰረዙበት የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የሳምንቱ መጨረሻ ግጥሚያዎች ማንቸስተር ሲቲ  እና አርሰናል ተጋጣሚዎቻቸው ላይ አራት አራት ግቦችን ከመረብ አሳርፈዋል። በትናንቱ ጨዋታ 3 ተጨማሪ ነጥቦችን መሰብሰብ የቻለው ማንቸስተር ሲቲ መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:21

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በርካታ ጨዋታዎች በተሰረዙበት የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የሳምንቱ መጨረሻ ግጥሚያዎች ማንቸስተር ሲቲ  እና አርሰናል ተጋጣሚዎቻቸው ላይ አራት አራት ግቦችን ከመረብ አሳርፈዋል። በትናንቱ ጨዋታ 3 ተጨማሪ ነጥቦችን መሰብሰብ የቻለው ማንቸስተር ሲቲ መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው። ከእረፍት መልስ አንድ ተጨዋቹ በቀይ ከሜዳ የተሰናበተበት ሊቨርፑል በብርቱ ፍልሚያ እና ተጨማሪ እድል ነጥብ ተጋርቶ መውጣት ችሏል። ከመሪው ጋር ያለው ነጥብ ግን ከአንድ ወደ 3 ከፍ ብሏል። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ባየር ሙይንሽን መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው። 

ወደ እንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እና ቡንደስሊጋ ውጤቶች ከማለፋችን አስቀድሞ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሳምንቱ መጨረሻ ስላገኟቸው ድሎች የምንለው ይኖረናል። ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ተጨዋቾች በሚሳተፉበት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አቋምን እንቃኛለን። በበርካታ ውድድሮች አብሮ የተጓዘ ጋዜጠኛንም አነጋግረናል።

አትሌቲክስ

በቅድሚያም አትሌቲክስ። በሳምንቱ መጨረሻ በዓለም ዙሪያ በተከናወኑ የአትሌቲክስ ፉክክሮች ኢትዮጵያውያን እንደተለመደው ድል ቀንቷቸዋል። ጣሊያን ውስጥ በተከናወነው የሲታዴላ ሲታ ሙራታ ግማሽ ማራቶን የሴቶች ፉክክር አዲስዓለም በላይ 1:12:07 በመሮጥ 1ኛ ደረጃን አግኝታለች።  ስፔን ውስጥ በተደረገው የኢንትርናሲኦናል ዲ ቬንታ ዲ ባኖስ አገር አቋራጭ 10.575ሜትር ውድድር ደግሞ 32:37 የሮጠው ንብረት መላክ በወንዶች ፉክክር 2ኛ ወጥቷል። በተመሳሳይ የሴቶች 7975ሜትር ፉክክር ልቅና አምባው በ29:53 2ኛ ደረጃን ይዛለች። በታይዋን የታይፒ ማራቶን ውድድር በወንዶችደመቀ ካሰው በ2:11:41በመሮጥ  1ኛ፤ እንዲሁም መሰረት አራጋው በ2:14:59 2ኛ ደረጃን ይዘው በድል አጠናቀዋል። በሴቶች ደግሞ አለምፀሃይ አሰፋ 2:30:44 በመሮጥ 1ኛ ሆና አሸንፋለች። በዚሁ ውድድር ገላኔ ቡልቡላ በ2:38:55 7ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። ጃፓን በተደረገ የሳንዮ ሴቶች ግማሽ ማራቶን ውድድር፤ ዘይቱና ሁሴን በ1:09:31 1ኛ ደረጃ ደስታ ቡርቃ በ1:09:31 2ኛ ደረጃን ይዘው ድል ማስመዝገባቸውን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

Symbolbild Startlinie Startschuss

እግር ኳስ

ኮስታሪካ በምታዘጋጀው ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ሴቶች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ግጥሚያ ለመግባት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መንገዱን እያመቻቸ ነው። ዐርብ ዕለት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተደረገው የማጣርያ የመልስ ግጥሚያ ቦትስዋናን 5-1 (በድምር 8-2) በማሸነፍ ወደ ቀጣይ ዙር ያለፈው የኢትዮጵያ ቡድን በቀጣይ ዙር ታንዛንያን ይገጥማል።  ኢትዮጵያ ወደ ተከታዩ ዙር ማለፏን ተከትሎ በ4ኛው ዙር ከታንዛንያን ጋር ትጫወታለች። ለመሆኑ ብሔራዊ ቡድኑ አቋሙ ምን ይመስላል? የናሁ ቲቪ የስፖርት ክፍል ታላፊ ጋዜጠኛ  አሸናፊ ዘለሌ ከቡድኑ ጋር በተለያዩ ሃገራት ተጉዞ ቡድኑን በቅርበት ተከታትሏል።

ፕሬሚየር ሊግ

ትናንት ማንቸስተር ሲቲ ኒውካስል ዩናይትድን 4 ለ0 ሲያሸንፍ አርሰናል ተጋጣሚው ሊድስ ዩናይትድን 4 ለ1 ድል አድርጓል። ቸልሲ ከዎልቭስ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይቷል። ብርቱ ፉክክር እና በርካታ የመከኑ የግብ ዕድሎች በታየበት የትናንቱ ግጥሚያ ሊቨርፑል ከቶትንሀም ጋር ሁለት እኩል ተለያይቶ ነጥብ ተጋርቷል። ሐሪ ኬን እና ሶን ሆይንግ-ሚን ለቶትንሀም ብርቱ ሆነው ታይተዋል። ሐሪ ኬን 13ኛው ደቂቃ ላይ ነበር የመጀመሪያዋን ግብ ለቶትንሀም ያስቆጠረው። ሊቨርፑል በ35ኛው ደቂቃ ላይ አቻ የምታደርገዋን ግብ አግኝቷል።  ዲዬጎ ጆታ በጭንቅላት ገጭቶ ከመረብ ያሳረፋው ግብ ድንቅ ነበር። ከሜዳው ውጪ የተጋጠመው ሊቨርፑል በ69ኛው ደቂቃ ላይ በአንድሪው ሮበርትሰን ግብ ሁለት ለአንድ መምራትም ችሎ ነበር።

77ኛው ደቂቃ ላይ ግን ይኸው አንድሪው ሮበርትሰን በሠራው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ዳኛው ቀይ ካርድ የሰጡት የቪዲዮ ረዳት ምስሉን ደጋግመው ከተመለከቱ በኋላ ነው። ሮበርትሰን በእርግጥም ከኳስ ጋር የተጋጣሚውን ሁለት እግሮች ተንሸራቶ ለመጨርገድ ያደረገው ሙከራ ቀይ የሚያሰጠው ነበር።

ሆኖም ሐሪ ኬን ቀደም ሲል ሮበርትሰን ላይ ተመሳሳይ ጥፋት በሠራበት ወቅት ለምን ዳኛው በቪዲዮ ረዳት ምስል ታግዘው ጥፋቱን ዐላዩም ሲሉ የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ንዴታቸውን ገልጠዋል። በዚህም የተነሳ በዳኛው ቢጫ ካርድ ተሰጥቷቸዋል። አሰልጣኙ ከመበሳጨት ይልቅ ግን ሁለት መሳፎቻቸውን አጋጥመው ስላቅ በተሞላበት ሁኔታ ለምስጋና ጎንበስ ብለዋል። በእርግጥም በቀይ ከሜዳ የተሰናበተው ሮበርትሰን ላይ የቶትንሀሙ ኬን ጥፋት ሠርቶበት ነበር። በወቅቱ ግን ዳኛው ጨዋታው እንዲቀጥል ነው ያደረጉት። ምናልባት የቪዲዮ ረዳት ምስል ቢመለከቱ ኖሮ ኬንም ከሜዳ በቀይ ሊሰናበት ይችል ነበር። ያም በመሆኑ የዬርገን ክሎፕ ቁጣ እና ንዴት ተገቢ ነበር ማለት ይቻላል። 

በዕለቱ የሊቨርፑል ግብ ጠባቂ አሊሰን ቤከር የመጀመሪያው ግብ ከተቆጠረበት በኋላ 30ኛው ደቂቃ ላይ ከዴል ዓሊ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተው ኳሷን በድንቅ ኹኔታ በማጨናገፍ ሊቨርፑልን 2 ለ0 ከመመራት አትርፎ ነበር።  37ኛው ደቂቃ ላይ ዲዬጎ ጆታ የቶትንሀም ፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ኳሷን እየገፋ ወደ ግቡ ሲቀርብ ከኋላ በኤመርሰን ሮያል ተገፍትሮ ቢወድቅም ዳኛው ፍጹም ቅጣት ምት ሳይሰጡ ቀርተዋል። የቪዲዮ ረዳት ምስሉንም አልተመለከቱም። እንግዳው ቡድን ሊቨርፑል በቶትንሀም ጫና ቢፈጠርበትም 43ኛው ደቂቃ ላይ አሌክሳንደር አርኖልድ ድንቅ ሙከራ አድርጎ ነበር ግብ ባይሳካለትም። ከእረፍት መልስ 2 ለ1 ተጋጣሚውን ሲመራ የነበረው ሊቨርፑል በግብ ጠባቂው አሊሰን ቤከር ስኅተት ግብ ተቆጥሮበታል። ኳሷን ለማጨናገፍ ቀደም ብሎ ከግብ ክልሉ የወጣው ግብ ጠባቂ ኳሷን በእግሩ እመታለሁ ብሎ በመሳቱ ሶን ሆይንግ-ሚን ተረጋግቶ ከመረብ አሳርፏታል። በሁለቱም በኩል በርካታ ቢጫ ካርዶች ታይተዋል። ሁለቱም አሰልጣኞች ተጨዋቾችን ቢቀይሩም ውጤቱ ግን ሊቀየር አልቻለም።

በዚህም መሠረት የፕሬሚየር ሊጉን ማንቸስተር ሲቲ በ44 ነጥብ ይመራል። ሊቨርፑል በ41 ይከተላል። ከዎልቭስ ጋር ያለምንም ግብ የተለያየው ቸልሲ 38 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቅዳሜ ዕለት ሊድስን 4 ለ1 ያሸነፈው አርሰናል 32 ነጥብ ይዞ በአራተኛ ደረጃ ይከተላል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ዌስትሀም ዩናይትድ በ28 ነጥብ 5ኛ ሲሆን፤ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ማንቸስተር ናይትድ 27 ነጥብ ይዞ  6ኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል። ሦስት ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ቶትንሀም በበኩሉ በ26 ነጥቡ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በርንሌይ 11፤ ኒውካስል እና ኖርዊች 10 ነጥብ ይዘው ከ18ኛ እስከ 20ኛ ደረጃ ከታች ተደርድረዋል። በርንሌይ 3፤ ኖርዊች አንድ ተስተካካይ ጨዋታዎች ይቀራቸዋል። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በኮሮና የተነሳ አምስት ጨዋታዎች ለሌላ ጊዜ ተላልፈዋል።  

ቡንደስ ሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ መሪው ባየር ሙይንሽን ቮልፍስቡርግን ዐርብ ዕለት 4 ለ0 ድል አድርጎ ነጥቡን 43 አድርሷል። ለባየር ሙይንሽን ግቦቹን ያስቆጠሩት፦ ቶማስ ሙይለር፤ ዳዮት ኡፓሜካኖ፤ ሌሮይ ሳኔ እና ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ናቸው።

በሔርታ ቤርሊን ቅዳሜ ዕለት የ3 ለ2 ሽንፈት የገጠመው ቦሩሲያ ዶርትሙንድ በ34 ነጥብ በደረጃ ሠንጠረዡ ሁለተኛ ሆኖ ባየርን ሙይንሽንን ይከተላል። ፍራይቡርግ 29 ነጥብ ሰብስቦ ሦስተኛ ነው። ባየርን ሌቨርኩሰን እና ሆፈንሀይም 28 ነጥብ አላቸው በግብ ክፍያ ተለያይተው 4ኛ እና 5ኛ ደረጃ ይዘዋል። ሽቱትጋርት፤ አርሜኒያ ቢሌፌልድ እና ግሮይተር ፍዩርትስ 17፤ 16 እና 5 ነጥብ ብቻ ይዘው ከ16ኛ እስከ 18ኛ ያለውን የቡንደስሊጋው የመጨረሻ ደረጃ ይዘዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic